Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለመንግሥት 76 ሚሊዮን ዶላር ሊያበድር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳዊት እንደሻው

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ከከፈተ ከሁለት ዓመት በኋላ ትልቅ ነው የተባለለትን የ76 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ለመፈራረም፣ ኃላፊዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ይልካል፡፡

ከወር በፊት በኢትዮጵያ መንግሥትና በባንኩ መካከል የተደረገው ይኼ የብድር ስምምነት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንሲንግ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሚያደርገው እገዛ ይውላል፡፡

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፒም ቫን በሌኮም፣ እንዲሁም ሌሎች ኃላፊዎች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህም መሠረት የባንኩ ኃላፊዎች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር አድርገውት ከነበረው ስምምነት የሚቀጥልና ተመሳሳይ የሆነ ስምምነት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ድረስ የሚቀጥለው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማገዝ ፕሮጀክት 276 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚያስወጣ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የዓለም ባንክ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቷል፡፡

በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የሚሰጠው ብድር፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የሊዝ ፋይናንሲንግ ሥራ እንደሚያግዝ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የልማት ባንክ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለማቃለል ያግዛል፤›› ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በልማት ባንክ በኩል የሚደረገው እገዛ በሁለት መስኮቶች የሚወጣ ሲሆን፣ አንደኛው በቀጥታ በባንክ እንደ ሊዝ ፋይናንሲንግ ሲሰጥ ሌላው ደግሞ እንደ መሥሪያ ካፒታል ልማት ባንክ ለመረጣቸው 12 ባንኮችና ዘጠኝ ማይክሮ ፋይናንሶች ይሰጣል፡፡

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ለኃይል፣ ለኮሙዩኒኬሽንና ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 800 ሺሕ የሚጠጉ አነስተኛና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ ይገመታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች