- በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይ ምስለ ቅርፁ እንዲቆም ይደረጋል ተብሏል
በታዋቂው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌይ ስም የተሰየመውና በአዲስ አበባ ከተማ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ የሚገኘው አደባባይ ፈረሰ፡፡ ለቦብ ማርሌይ ምስለ ቅርፅ ማቆሚያና በስሙ ለሚጠራ አደባባይ ተለዋጭ ቦታ እንደተሰጠ ታውቋል፡፡
ለአዲስ አበባ መንገዶች የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ምክንያት ሆነው ከሚጠቀሱ አደባባዮች መካከል አንዱ የሆነው የቦቦ ማርሌይ አደባባይ የፈረሰው ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በፈረሰው አደባባይ ምትክ መንገዱን በትራፊክ መብራቶች ለማስተናገድ የሚያስችል ግንባታ ጀምሯል፡፡
በባለሥልጣኑ ውሳኔ መሠረት ከሚፈርሱት አደባባዮች አንዱ መሆኑ ቀድሞውኑ የታወቀው የቦብ አደባባይ እስካሁን ሳይፈርስ የቆየው የአቀንቃኙን ምስለ ቅርፅ ማሳረፊያ ተተኪ ቦታ ለማግኘት ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡ ይሁንና ለምስለ ቅርፁ ማኖሪያ የሚሆን ቦታ የከተማው አስተዳደር በማዘጋጀቱ፣ ምስለ ቅርፁ ከነበረበት ቦታ ተነስቶ አደባባዩን በማፍረስ የአስፓልት ኮንክሪት ግንባታ ሥራ መካሔድ ጀምሯል፡፡
ለምስለ ቅርፁ ማዛወሪያና በቦብ ስም የሚጠራ ተለዋጭ ቦታ ለማግኘት በተደረገው ሙከራ ስድስት አማራጭ ቦታዎች ቀርበው በመጨረሻው፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚገኝበት እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያለ ቦታ ተመርጧል፡፡ በዚህ ቦታ አዲስ አደባባይ በመገንባት ምስለ ቅርፁ እንዲያርፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ምስለ ቅርፁን የማስቀመጡ ሥራ በልዩ ሥርዓት የቦብ ማርሌ ቤተሰቦች ወዳጆች በሚገኙበት በክብር እንደሚፈጸም ምስለ ቅርፁን አሠርተው በኢምፔረያል አካባቢ ካኖሩት ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ለከተማው የትራፊክ መጨናነቅ መንስዔ ነበሩ ካላቸው አደባባዮች ውስጥ እስካሁን ስድስተኛውን አፍርሷል፡፡
በተለይ በቀለበት መንገዱ ጋር የተያያዙ አደባባዮች መፍረስ እንደሚኖርባቸው በማመን እስካሁን የጀሞ አደባባይ፣ 18 ማዞሪያ፣ የቦሌ ሚካኤል፣ ለቡ መብራት ኃይልና የጃክሮስ አደባባዮች ፈርሰው ለተሽከርካሪዎች ምቹ ይሆናል በተባለ መንገድ ተገንብተው የትራፊክ መብራት እንዲተከልላቸው ተደርጓል፡፡ የጃክሮስ አደባባይ የፈረሰው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡
ባለፈው ቅዳሜ የፈረሰው የቦብ አደባባይም የአስፓልት ሥራው በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናቅቆ በአራት አቅጣጫ የሚተላለፈውን የትራፊክ ፍሰት በመብራት ለማስተናገድ በሚያስችለው ደረጃ እየተገነባ ነው፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አደባባዮችን በማፍረስ ለትራፊክ ምቹ ይሆናል ባለው መንገድ እየሠራ ያለው ሥራ በጊዜያዊነትም ቢሆን የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ በማስተንፈስ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደ ገብርኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት ከስድስቱ አደባባዮች ሌላ ቀሪ አራት አደባባዮች በአዲሱ በጀት ዓመት ይፈርሳሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል የሳሪስ አቦና የጀርመን አደባባዮች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለሥልጣኑ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ናቸው ከተባሉት አደባባዮች ሌላ የተጎዱ መንገዶች ጥገናም በማካሄድና ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት አደባባዮችን በማፍረስና መልሶ በመብራት እንዲስተናገድ የማድረጉ ሥራና በከተማዋ ውስጥ ላካሄዳቸው የመንገድ ጥገናዎች እስካሁን ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 130 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው መንገድ ጠግኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለመጠገን ታቅዶ የነበረው 90 ኪሎ ሜትር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አደባባዮችን በማጥፋት በመብራት የማስተናገዱ ዘላቂ ይሆናል ተብሎ ስለማይታመን አደባባዮቹ በነበሩባቸው ቦታዎች ላይ ተላላፊ መንገዶችን ወደመገንባት ይገባል፡፡ ተላላፊ መንገዶች ያስፈልጋቸዋል ለተባሉ አደባባይ የነበረባቸው መንገዶች ላይ ለሚገነቡት ተላላፊ መንገዶች የሚሆን ዲዛይን እየተሠራ ሲሆን የሚካኤል አደባባይ አልቋል፡፡ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ግንባታቸው ይጀመራል ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥም ቀዳሚው ይኸው የሚካኤል አደባባይ ነው፡፡