[ክቡር ሚኒስትር ከአንድ ባለጉዳይ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተነጋገሩ ነው]
- ለምን ነበር የመጣኸው ወዳጄ?
- አሳሳቢ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስቲ ንገረኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎን ለማግኘት እኮ አንድ ዓመት ነው የፈጀብኝ፡፡
- ለምን እባክህ?
- ማን አስቀርቦ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን ያህል?
- እርስዎን ከማግኘት ኤቨረስት ተራራ መውጣት ይቀላል፡፡
- ኧረ አታጋን እባክህ?
- ባጋንን ኖሮ ዓመት ሙሉ እለፋ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- እሺ ለምን ፈለግከኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ለአገር የሚጠቅም ነገር ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ይፈልጉ ነበር፡፡
- ታዲያ ማን ከለከላቸው?
- ማን ያስቀርባቸው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት እባክህ?
- ደላሎች ጣልቃ እየገቡ አስቸገሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ደላላ ነው የምትለው?
- እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ እያሉ የሚያስቸግሩ ናቸዋ፡፡
- ስለምንድነው የምታወራው?
- የውጭ ኢንቨስተሮች በመከራ ስናመጣ ማስተናገድ አልተቻለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- አንዱ ወገን ለኮሚሽን እየተሯሯጠ ጉቦ ይቀባበላል፡፡
- ሌላውስ?
- ሌላው ደግሞ ድርሻውን ካላገኘ እንቅፋት ይሆናል፡፡
- እሺ?
- አገር በሕጉ መሠረት ማስተናገድ ሲገባት ቢሮክራሲው አላሠራ ይላል፡፡
- ለዚህ ነው የፈለግከኝ?
- ሌላም አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- ኤሌክትሪክ እየጠፋ ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡
- እሺ?
- በዚህ ላይ ለኢንቨስትመንት የማይመች ተግባር ይፈጸማል፡፡
- ለምሳሌ?
- ኢንቨስተሮችን ማበሳጨት አንዱ ችግር ነው፡፡
- አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል እኮ?
- የት ነው የሚቀርበው ክቡር ሚኒስትር?
- ቅሬታ የሚሰማ አካል ዘንድ፡፡
- ችግር ሲፈጠር የሚያዳምጥ የለም፡፡
- ቀጥል፡፡
- ኢንቨስተሮች እየተማረሩ ነው ሲባል ግድ የማይሰጣቸው ሞልተዋል፡፡
- ለምን ይሆን?
- ወይ አለማወቅ ወይ ንቀት እየበዛ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ምን ላድርግ ታዲያ?
- ኃላፊነትዎን ይወጡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት አድርጌ እባክህ?
- ስብሰባችሁ ላይ ተነጋገሩበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ የምትለውን እንዴት ላምን እችላለሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ዓለም አቀፍ ሚዲያው እያናፈሰው እኮ ነው፡፡
- ምኑን?
- የታዋቂውን አፍሪካዊ ኢንቨስተር ኩርፊያ ነዋ?
- ማነው እሱ?
- አሊኮ ዳንጎቴ፡፡
- ምናለ እባክህ?
- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቴን አቆማለሁ ብሏል፡፡
- አትቀልድ በለው፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ኢንቨስተር ቀልድ እንደማያውቅ አያውቁም እንዴ?
- ምንድነው የሚያውቀው ታዲያ?
- መወሰን!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተው እየተነጋገሩ ነው]
- የሰሞኑን ወሬ ለምን አልነገርከኝም?
- የቱን?
- የቢሊየነሩን የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት ጉዳይ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አልሰሙም እንዴ?
- አንተ ካልነገርከኝ እንዴት እሰማለሁ?
- ሰውየው አምርሯል አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛ በገዛ ሀብታችን ማዘዝ አንችልም ማለት ነው?
- እንችላለን ክቡር ሚኒስትር፣ ግን. . .
- ግን ምን?
- ዙሩን አከረርነው መሰል?
- የምኑን ዙር?
- ኢንቨስተር እሽሩሩ ይፈልጋል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን የት ነው የተማርከው?
- አገሮች ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆን አለባቸው ይባል የለ እንዴ?
- እኛ ምን አጠፋን ታዲያ?
- ሥራቸው እንቅፋት ሲያጋጥመው መደገፍ አቅቶናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛ መቼ እንቢ አልን?
- እንቢ ብላችኋል ተባልን እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ማን ነው ያለን እባክህ?
- የውጭ ሚዲያ ላይ እንደዚያ ነው የተባለው ክቡር ሚኒስትር?
- አንዳንዴ ቆፍጠን ማለት አለብን፡፡
- በእኛ ጥፋት ኢንቨስተሮች ሲሸሹ ሌሎች አገሮች ይፈነድቃሉ፡፡
- ምን ለመሆን?
- ኢንቨስተሮቹን እያግባቡ ጠራርገው ይወስዱብናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛም አንድ ነገር ማድረግ አለብን፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- የጥፋት ኃይሎችን ማጋለጥ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር?
- አቤት?
- ከዚህ በፊት ሌላ ነገር ቢቀድም ይሻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ይቅደም?
- የተበላሸውን ማስተካከል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው የተበላሸው አንተ?
- የአገሪቱ ስም ጎደፈ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተብሎ?
- ለኢንቨስትመንት የማትመች፡፡
- ማን ነው ያለው?
- መቼም እኔ እንዳልሆንኩ ያውቃሉ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ተበሳጭተው ጸሐፊያቸውን አስጠሯት]
- የታለ ያ የማስተባበሪያ ዳይሬክተር ተብዬው?
- የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የት ሄደ?
- ፈቃድ ሞልቶ እረፍት ወጥቷል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ካለበት በአስቸኳይ አስጠሪው፡፡
- አገር ውስጥ የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- አሜሪካ ሄዷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሊሠራ ነው የሄደው?
- ሚስቱ እዚያ ልትወልድ ነው መሰል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱም ለዚህ በቃ?
- አይ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- እሱ እኮ ንጉሥ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት እባክሽ?
- ወዳጀ ብዙ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማለት?
- በዚህ በኩል የአገር ውስጥ ባለሀብቶች. . .
- ምን?
- በዚያ በኩል የውጭ ኢንቨስተሮች. . .
- ምንድነው የምትይው?
- ይወዱታል ማለቴ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱ ምን ስለሆነ?
- አሪፍ ጉዳይ ገዳይ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ደግሞ ምን ማለት ነው?
- ጉዳያቸውን ያስፈጽምላቸዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱ ተላላኪ የሆነው ከያዘው ኃላፊነት በልጦበት ነው?
- እንደ ጉድ ብር ያፍስበታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ተደርጎ እባክሽ?
- ስማርት ስለሆነ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሀብት በሀብት ሆኗል እያልሽኝ ነው?
- ቢጠሩት የማይሰማ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ሊሆን ቻለ?
- ሁሉንም ነገር ተቆጣጠረው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ሁሉ ሲደረግ አንቺ የት ነበርሽ?
- እዚችው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት አልነገርሽኝም?
- የእሱ ምላስ ጥሬ እየቆላ እኔን ማን ሰምቶኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ከአሜሪካ መቼ ነው የሚመለሰው?
- አሜሪካ የሄደ ሰው ስለመመለሱ ምን ማረጋገጫ አለ?
- ማለት?
- አይመጡም ያልናቸው ከች ይላሉ፡፡
- ይመጣሉ ያልናቸውስ?
- መግለጫ ሲሰጡ ይሰማሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን መግለጫ?
- ፀሐዩ መንግሥታችንን እያወገዙ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ልማታዊ መንግሥታችንን ምን ብለው ያወግዛሉ?
- አገሪቱን ገሃነም አደረጋት እያሉ ነዋ!
[ክቡር ሚኒስትር ለምሣ ቤት ሲደርሱ ባለቤታቸው እየጠበቋቸው ነበር]
- ዛሬ አሪፍ ምሣ አለ ማለት ነው፡፡
- ሌላ ጊዜስ?
- አንቺ ከሌለሽ እኮ አይጣፍጠኝም፡፡
- እባክህ አትፎግረኝ፡፡
- ፉገራ ባውቅ መጫወቻ እሆን ነበር?
- ልክ ነህ የተከበርከው ሚኒስትር፡፡
- ለምን እንዲህ አልሽ?
- አንተ በሌላ ነገር ሰው ስታደርቅ ትውላለህ. . .
- እሺ?
- ሌሎች በአንተ ከለላ የራሳቸውን ኢምፓየር ይገነባሉ፡፡
- ለምን እንዲህ አልሽ?
- የማላውቅ መሰለህ?
- ምኑን?
- አንተ ነጋ ጠባ ቴሌቪዥን ላይ ልማት. . . ልማት. . . ትላለህ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
- የምለውማ የሌሎቹን ጥፋት ለመሸፈን ትሯሯጣለህ ነው፡፡
- ለምሳሌ?
- ኢንቨስተሮች ተከፍተዋል ሲባል አንተ ታስተባብላለህ፡፡
- እሺ እባክሽ?
- አንተ እንደ ቋንጣ የደረቀ ወሬ ስታወራ ሌላው. . .
- ሌላው ምን?
- ሌላውማ በቪላ ላይ ቪላ. . .
- ምን?
- በቢዝነስ ላይ ቢዝነስ. . .
- እንዴ?
- በብር ላይ ብር ይከምራል፡፡
- ያለ መረጃ አታውሪ እባክሽ?
- በማስረጃም አስደግፍልሃለሁ፡፡
- ምኑን?
- የሀብት ተራራ ስለሠሩት ነዋ፡፡
- ይኼንን ወሬ ከየት ነው የምትለቃቅሚው?
- ዓይንህን ከፈት ብታደርግ ታየው ነበር፡፡
- ዓይኔ ተጨፍኗል ማለት ነው?
- ተጨፈነ ከማለት ይልቅ. . .
- እህ?
- ተደፍኗል ቢባል ይሻላል፡፡
- አልገባኝም?
- እስኪ የበታቾችህንና ዙሪያህ ያሉትን እያቸው፡፡
- ምን ሆኑ?
- ሠሩት፡፡
- ምኑን ነው የሠሩት?
- ሲስተሙን በሚመቻቸው መንገድ ተጠቀሙበት፡፡
- እንዴት አድርገው?
- እየፐወዙት ነዋ፡፡
- ኧረ እባክሽ አልገባኝም?
- ይቀጠርልሃል፡፡
- ምንድነው የሚቀጠርልኝ?
- አስተርጓሚ!