የሼፍ ገነት አጎናፍር ‹‹ሚልስ ባይ ገነት›› የተሰኘ ሬስቶራንት አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ይገኛል፡፡ በተለምዶ ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› በሚል በሚጠራው አካባቢ ላለፉት 17 ዓመታት ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገሮችም ተወላጆች መዳረሻ ሆኗል ሬስቶራንቱ፡፡ ሼፍ ገነት በዋነኛነት የሚታወቁት ክሽን ባለው የዶሮ ወጣቸው ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሎስ አንጀለስ ታይምስ ስለ ሬስቶራንታቸው መጣጥፍ አስነብቧል፡፡
የሬስቶራንቱ ግድግዳ በተለያዩ የሥነ ጥበብ ውጤቶች የተሽቆጠቆጠ ሲሆን፣ መመገቢያ ጠረጴዛዎቹና ወንበሮቹ ዘወትር ለማዕድ በሚጋብዝ መንገድ ይደረደራሉ፡፡ በሬስቶራንቱ በርካታ ዓይነት ምግቦች የሚሰናዱ ሲሆን፣ ብዙዎች ወደ ሥፍራው የሚያቀኑት ግን ዕውቁን ዶሮ ወጥ ለመመገብ ነው፡፡
‹‹ዘለግ ላለ ሰዓት ተቁላልቶ የሚሠራው፣ በቅመም ያበደ ዶሮ ወጥ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው፤›› ሲሉ ሼፏ ይገልጻሉ፡፡ ለሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደተናገሩት፣ ለዓመታት ተወዳጅ የሆነው ዶሮ ወጣቸውን በብቸኛ የልጅ ልጃቸው ስም ‹‹ሪያ›› ብለው የምግብ ዝርዝሩ ላይ አስፍረውታል፡፡
ሆኖም ብዙዎችን የሚያስገርመው ሼፍ ገነት የሚሠሩትን ዶሮ ወጥ ፈጽሞ አለመመገባቸው ነው፡፡ ‹‹ለረዥም ዓመታት አትክልት ተመጋቢ ሆኛለሁ፤›› ይላሉ፡፡ የዶሮ ወጣቸውን ጣዕም የሚለኩት ከተመጋቢዎች በሚሰጣቸው አስተያየት እንጂ ቀምሰው አይደለም፡፡
ከአንድ ልጃቸውና የልጅ ልጃቸው ጋር ለዓመታት ለመኖር ስለሚመኙ አትክልት ተመጋቢ በመሆንና መጠጥ በማቆም ጤነኛ ሕይወት እየመሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሼፍ ገነት ሎስ አንጀለስ ውስጥ ካሉ ምርጥ ሼፎች መካከል አንዷ ተብለው ተሰይመዋል፡፡
ሼፏ የተወለዱት አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው ሲሠሩ ከተዋወቁት ባለቤታቸው ጋር ስዊድን መኖር ጀመሩ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ከተለያዩ በኋላም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከልጃቸው ጋር እየኖሩ ነው፡፡
የ64 ዓመቷ ገነት፣ ሼፍ እሆናለሁ ብለው አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እናቴን ያሳደጓት ሴት ባለሙያ ነበሩ፡፡ ምግብ መሥራት የተማርኩትም ከእሳቸው ነው፤›› ይላሉ፡፡ ልጃቸው ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ሎስ አንጀለስ ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥረው ሲሠሩ ነበር የዛሬው ማንነታቸው በድንገት የተፈጠረው፡፡
በአንድ መሰናዶ ላይ ምግብ እንዲያቀርቡ ተጠርተው እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ምግብ መሥራት ይጀምራሉ፡፡ ምግቡን የቀመሱ ሁሉ ስለወደዱት በድጋሚ እንዲሠሩላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ወቅት ምግብ ማብሰልን እንደ ሙያ የመያዝ ሐሳቡ ብልጭ አለላቸው፡፡ ‹‹ሙያ የሚፈተሽበት›› ተብሎ የሚታወቀው ዶሮ ወጥን በዋነኛነት መሥራቱንም ተያያዙት፡፡
ዛሬ ላይ በዶሮ ወጣቸው ታዋቂ የሆኑት ሼፍ ገነት፣ በሎስ አንጀለስ ምግብ አፍቃሪዎች ተወዳጅ ናቸው፡፡ ምግባቸውም ስለማይጠገብ ሬስቶራንቱን በርካቶች እንደሚያዘወትሩ ሎስ አንጀለስ ታይምስ አስነብቧል፡፡