Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለተፈጠረው ችግር ተወቃሹ መንግሥት ነው!

መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት በጀት መመደብ አልቻልኩም ብሏል፡፡ ይህ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰማ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የአሥር ወራት ሪፖርት ሲቀርብ እንደተሰማው፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በመንግሥት ፋይናንስ ማስቀጠል ትልቅ ጫና ስለፈጠረ ሌሎች አማራጮች ይታያሉ ተብሏል፡፡ መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 750 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ቢያቅድም፣ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በበጀት ስለማይደገፍ ለማስፈጸም እንደማይችል ይፋ ተደርጓል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በተመለከተ በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ዓምድ በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳቦች ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ሰሚ ባለመገኘቱ ግን አሁን እንደ ድንገተኛ ደራሽ ውኃ አስደንጋጭ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በ1996 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አዝጋሚ ጉዞ በማድረግ፣ 140 ሺሕ ያህል ቤቶች ተሠርተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ የዚያን ጊዜዎቹ ተመዝጋቢዎች በዚህ ዓመት መጨረሻ ተገንብተው የሚጠናቀቁ 30 ሺሕ ቤቶችን እንደሚከፋፈሉ ይጠበቃል፡፡ ከ13 ዓመታት አሰልቺ ጥበቃ በኋላ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ፖሊሲ ከማውጣትና ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ በግሉ ዘርፍ ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ሲማስን በመክረሙ፣ እጅግ አንገብጋቢ መሠረታዊ ፍላጎት የሚባለውን የቤት ችግር ሊፈታ አልቻለም፡፡ ይህ የሚያሳየው የፖሊሲ ውድቀትን ነው፡፡

በ2005 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቤት ፈላጊ የከተማ ነዋሪዎችን በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 መርሐ ግብሮች በመመዝገብና ንግድ ባንክ እንዲቆጥቡ በማድረግ ግንባታ ቢጀመርም፣ በተለይ በ40/60 አንድም ቤት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ የቤቶቹን ሙሉ ክፍያ ከፈጸሙ ጀምሮ በየወሩ ያለማቋረጥ የሚቆጥቡ ዜጎች በመንግሥት በመተማመን ግዴታቸውን እየተወጡ ቢሆንም፣ መንግሥት ያለ ሥራው የገባበትን ፕሮጀክት ማስፈጸም ባለመቻሉ ብቻ ተስፋ ቆራጭነት ሰፍኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 131 ሺሕ ቤቶች እየተገነቡ ቢሆንም፣ የበጀት እጥረት ተብሎ ግንባታቸው ለተወሰነ ጊዜ ቆሞ ነበር፡፡ ኮንትራክተሮችና ግብዓት አቅራቢዎችም ሥራ ፈተው ነበር፡፡ ነገር ግን ቦንድ በማስያዝ 15 ቢሊዮን ብር በመገኘቱ 170 ሺሕ ያህል ቤቶችን ለመገንባት እንዲውል ተደርጓል የተባለው ከወራት በፊት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ያለው መንግሥት የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር እኔ ነኝ የምፈታው በማለቱ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ከአገር ውስጥና ከውጭ በመስኩ ልምድ ያዳበሩ ኩባንያዎችን በጨረታ አወዳድሮ ከባንኮች ጋር በሚደረግ ትስስር፣ ቤቶቹ እንዲገነቡ የፖሊሲ ማዕቀፍ ቢኖረው ኖሮ ትርምስ አይፈጠርም ነበር፡፡

ገና ከመነሻው ከመንግሥት የሚገኝ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደማይኖር፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚያግዝ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ልምድ እንደሌለ፣ የአመራሮችም ሆነ የሠራተኞች የማስፈጸም አቅም አናሳነት፣ የሥነ ምግባር ችግሮችና የመሳሰሉት ጥያቄ ተነስቶባቸው ነበር፡፡ አሁን ለቤቶቹ ግንባታ ማካሄጃ ፋይናንስ አይኖርም ሲባል በተጓዳኝ እነዚህ ችግሮች ተዘርዝረዋል፡፡ ከመነሻው ፖሊሲው በሚገባ ካለመቀረፁም በላይ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች አልታዩም፡፡ በዕቅዱ መሠረት የቤቶች ግንባታ ይካሄዳል ቢባልም፣ ለነዋሪዎች በሚፈለገው መጠን ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ከ13 ዓመታት በኋላም በሺዎች የሚቆጠሩ ተመዝጋቢዎች አሁንም በምሬት ውስጥ ሆነው እየጠበቁ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ያለመታከት እየቆጠቡ ያሉትም መቼ ቤት እንደሚደርሳቸው መረጃው የላቸውም፡፡ ከስንት ጊዜ አንዴ ቤቶች ተገንብተው ሲጠናቀቁና ዕጣ ሲወጣ ከሚደረግ ሸብ ረብ ሌላ የቤቶቹ ግንባታ የማጠናቀቂያና የማስረከቢያ ጊዜ ሲያጥር አይታይም፡፡ ጭራሽ አሁን ደግሞ መንግሥት ገንዘብ ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለመኖሩ ሳቢያ ዜጎች በጉጉት ስለሚጠብቋቸው ቤቶቻቸው የተብራራ ማብራሪያ የሚሰጣቸው የለም፡፡

መንግሥት አሁን አማራጮችን እየዳሰስኩ ነው እያለ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መሬት በማቅረብ የማኅበራት ቤቶች ግንባታ ማስፋፋት ዋነኛው ዓላማ ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ቤት ፈላጊዎችን ከግንባታ ተቋራጮች ጋር በማጣመር የቤት ፍላጎት ጥያቄ እንዲመለስ ዕቅድ መያዙ ተሰምቷል፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ መሠረታዊ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ችግር ማስታገስ የሚቻለው ደግሞ በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ተግባራዊ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች የቤት ያለህ በሚሉበት በዚህ ጊዜ፣ የተለመደው አዙሪት ውስጥ ገብቶ ከመዳከር በአፍሪካም ሆነ በሌላ አኅጉር ምርጥ የሚባሉ ልምዶችን በባለሙያዎች አስጠንቶ ሳይንሳዊ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች አማራጫቸውን ይዘው ሲቀርቡ በዚያው መንገድ ማስተናገድ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ደግሞ በሞርጌጅ አሠራር ባንኮችን በማሳተፍ ከኩባንያዎች ጋር ማቆራኘት ይቻላል፡፡ ወይም በጥናቱ መሠረት የተሻለ አማራጭ ማግኘትም ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም 28 ያህል የውጭ ኩባንያዎች በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ ግብሮች ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡ ታዲያ አማራጮችን መፈተሽ ይሻላል? ወይስ በስህተት ላይ ሌላ ስህተት መድገም?

በደርግ ዘመን መሬት እየተመሩ የራሳቸውን ጎጆ የቀለሱ፣ በአነስተኛ ወለድ በሚገኝ ብድር በማኅበራት እየተደራጁ ቤቶቻቸውን የሠሩ ዜጎች በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ብዙ ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ቆይቶም ቢሆን በማኅበራት ተደራጅተው ቤቶቻቸውን የገነቡ አሉ፡፡ በኋላ ግን ከመሬት ድልድል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሙስና በመስፈኑና በከተማው ውስጥ የመሬት ጥበት በማጋጠሙ ወደ ሌላ መፍትሔ ተገባ፡፡ ይህም መንግሥት መሬት እያቀረበና በጀት እየያዘ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ነው፡፡ ነገር ግን ያለፉት 13 ዓመታት ጉዞ ሲቃኝ የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ በመጠኑ ዕፎይታ ለመፍጠር ቢሞከርም፣ አሁንም ችግሩ እግር ተወርች ይዟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ቢመድብም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 16 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ቢያደርግም፣ ተመዝጋቢዎች በየወሩ ከሚቆጥቡትና ከሙሉ ክፍያ ቢሊዮን ብሮች ተገኙ ቢባልም ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣሙም፡፡ አሁን በይፋ እንደተነገረው ደግሞ የገንዘብ እጥረት መንግሥትን ሊያስቆመው ነው፡፡ ወትሮም በማስፈጸም አቅም ማነስ ምክንያት ጥራት ትልቁ ችግር የሆነበት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በዕጣ የደረሳቸው ዜጎችን አቅም የሚፈታተን ተጨማሪ ወጪ አስወጥቷቸዋል፡፡ መንግሥት ድንገት ከዓመታት በፊት ዘው ብሎ የገባበት ፕሮጀክት አሁን ችግሩ ቁልጭ ብሎ ታይቷል፡፡

ችግርን ከመሠረቱ ማወቅ የመፍትሔ ግማሽ አካል ነው እንደሚባለው፣ ምንም እንኳ በጣም የዘገየ ቢሆንም መላ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ደመነፍሳዊ አካሄድ ሳይሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ መቅረብ አለበት፡፡ በመስኩ የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ዜጎች በማሳተፍ ይህንን ትልቅ አገራዊ ችግር መፍታት ተገቢ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የተረመጡ ልምዶችን በማምጣትና በመስኩ የዳበረ ልምድ ያላቸው አስተማማኝ ኩባንያዎች በመጋበዝ ችግሩን መቅረፍ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት አዋጭ የሆነ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመቅረፅ በተጨማሪ አመቺ ምኅዳር በመፍጠር ሚናውን መጫወት አለበት፡፡ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣትም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ መሆኑ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚበረታታውና የተሻለ ተጠቃሚነት ማግኘት የሚችለው በቤቶች ግንባታ ጭምር ስለሆነ ዕድሉን መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መንግሥት ከቤቶች ግንባታ ራሱን ሲያወጣ ጥናት የጎደላቸው አሠራሮችን ያስወግድ፡፡ በጋራ መኖረያ ቤቶች ግንባታ ለተፈጠረው ችግር ተወቃሹ መንግሥት ራሱ መሆኑን ይመን!

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...