ሰላም! ሰላም! አገር ለካ ቢሊየነሮችን አፍርታለች? ምቀኛ ደስ አይበለው እንጂ ወገን በባለፀጋነት ሲጠራ እንዴት ደስ አይል? ‘በሬው በሬ ሆኗል የሚሸጠው ከብት፣ አሁን የት ይገኛል የላመ አካላት’ ሲሉ ሰምቼ ውዷ ማንጠግቦሽ ዘልዝላ እንድትጠብሰው ሥጋ ይዤ ገባሁ። ማን ከማን ያንሳል? ዓላማዬ ከጥብሱ በኋላ እሷን እቅፍ ለማድረግ ነበር። ‹‹እነገርሃለሁ ስል?›› አለች ሥጋውን እንደ ባላንጣ እያየች። ‹‹ምኑን?›› ስላት፣ ‹‹የፍየል ሥጋ ጥሩ ነው ሲሉ ሰምቼ፤›› ስትለኝ ያው የፈረደበት አሥርና አምስት ዋና ዋና በፍየል ሥጋ ላይ የተገኙ የጥናት ውጤቶች በሬዲዮ ሰምታ መስሎኝ፣ ‹‹ምን ተባለ ደግሞ?›› አልኳት። ‹‹ምቀኛን ይከላከላል አሉኝ፤›› ብላኝ አረፈችዋ። አሁን ይኼ የሚያሳየው በምግብ ዋስትና ራስን መቻልን ነው? ወይስ ሥጋ ለሥጋ መዘላዘል? ‘ወይ ጥጋብ’ አለ ያገር ሰው ሳይጠግብ? በሽታ እንዲሁም በአምሮት ጠግበን መሰለኝ እኛም ይኼው ሥጋን ‘ኤክስሬይ’ ማሽን አደረግነው። ቀናውን ከምቀኛው የሚለይ። ግርም አይልም? ታዲያ እኔ አንበርብር ምንተስኖት ሲፈጥረኝ ቆቅ አይደለሁ? ከማን ጋር መዋል ብትጀምር ነው እንዲህ ያለ ነገር ማመን የጀመረችው ብዬ መከታተል ጀመርኩ። ባያት ባያት ምንም አዲስ ነገር የለም። የድስት እጣቢ ወይም የጠረገችውን ቆሻሻ ለመድፋት ካልሆነ ከቤት አትወጣም። ሲጨንቀኝ የባሻዬን ልጅ አማክረኝ አልኩት። እሱ ደግሞ በእኔ ያሾፋል።
‹‹አይ አንበርብር ዘመኑ እኮ የብልጦች ነው። ቫይበሯን፣ ፌስቡኩን፣ ምናምን አትፈትሽም? በህዕቡ እየተደራጀህ ወዳጅ ለማፍራት እኮ ዛሬ ዛሬ እንደ ቀድሞው ዘመን መኳተን ቀርቷል። ‘ሰርችን’ መጫን ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፤›› እያለኝ አንጀቱ እስኪፈርስ ሳቀብኝ። እሱ ሲስቅ ብሎ ብሎ ይኼ ፌስቡክ ምናምን የሚሉት ነገር እኔም ቤት ገባ እያልኩ ቅስሜ ተሰብሯል። ይኼን በተነጋገርን በነጋታው በጊዜ ወደ ቤት ስገባ ማን ይቀበለኛል የቱርክ ፊልም። ‘ባለፈው የፍየል ሥጋ ጥሩ ነው አላልሽኝም ነበር? ለካ የዶሮ ነው። መቼ አጣሁት ምቀኛዬ አንቺ ነሽ’ ብላ ዋናዋ ገጸ ባህሪ ከተቀናቃኟ ስትጣላ ዓይን ለዓይን ግጥም። ‘እኔስ መቼ አጣሁት ጠላቴን’ ብዬ፣ ‹‹እዚህ ቤት ግን ዜና መስማት አይቻልም?›› አልኩና ጣቢያ ቅይር። ለካ ገዢው ጣቢያ ለዘመናት ብቻውን ዓይናችንንም ቀልባችንንም ተቆጣጥሮት የኖረው ወዶ አይደለም አልኩኝ ቢቸግረኝ። የባሳ አለ አገርህን አትልቀቅ አሉ ስደተኞች!
ስደተኛ ስል የዚህ የሳዑዲ የምሕረት አዋጅ የሚሉት ነገር ያልበጠበጠውን አትጠይቁኝ። ሰሞኑን ሦስት አራት ቤቶች አሻሽጫለሁ ብላችሁ አታምኑኝ። ወላጆች ተመላሽ ልጆቻችን ሲመጡ የሰውም የመንግሥትም ፊት እንዳይጠብሳቸው እያሉ በመከራ ለመጦሪያ ተሠርቶ የተከራየላቸውን ቤት እያስለቀቁ እየሸጡ ነው። ማለት ‘ካልኩሌሽኑ’ ግን አልገባኝም። ‹‹ቤትን ያህል ነገር መሸጥ ጥሩ ነው?›› ብላቸው አንድ ሁለቱ እንዳንተ ዓይነት ደላላ አይተንም አናውቅ ካሉኝ በኋላ፣ ‹‹ቤት ባዶውን ምን ይሠራል? ቀለብ አለ፣ መውጣት አለ፣ መግባት አለ ባዶ እጃቸውን ቢመጡ ግድግዳውን አይግጡት። ቤት ሠርታ ነበር ግን መሶብ የላትም ሲባሉ ቆመን ልናይና ልንሰማ? አናደርገውም፤›› አሉኝ አንዲት እናት በቁጣ።
‘ከባለቤቱ ያወቀ ብዬ’ ዝም አልኩ። የአንደኛው ደንበኛዬ ቤት በእጥፍ ዋጋ ተከራየ። የሁለቱ ጆሮውን ተባለ። ከሁለቱ አንደኛው ጣጣ ፈንጣጣው ከማለቁ አስቀድሞ ገዢ፣ እኔና ሻጭ መኖሪያ ቤት ቡና ልንጠጣ በዚያውም ሻጭ ዶሴውን ለማጠናቀር ወደ ቤታቸው አመራን። ከመጣችሁ አይቀር ተብሎ ምሳ ቀረበ። ቡና ተፈላ። የሰዓቱ ዜና ተሰማና በመሀል ለእነዚህ ምስኪን የሰው አገር ሰዎች የአገራችሁ ግቡ ጥሪ፣ በተቀረፁበት ካሜራ ጥራት ሳቢያ ይሁን በኑሮ መመቻቸት እንጃ ዳያስፖራ የመሳሰሉ አርቲስቶች ተቆጣጠሩት። ‹‹ልክ በድሎት በምርጫ አማርጠው የተሰደዱ ይመስል…›› ብለው ልጃቸው ለፍታ የገዛችላቸውን ኮንዶሚኒየም ቤት የሚሸጡት አባትና እናት አቀርቅረው ቀሩ። ይኼኔ ነው ‘የቀበሮ ባህታዊ በጎች መሀል ገብቶ ይሰግዳል’ ነው ምንትስ ብለው ባሻዬ ዘወትር የሚተርቱት ተረት ትዝ ያለኝ!
እናም ነገሩ ከንክኖኝ ዋለ። የከነከነኝ የኅብረተሰብን ንቃታ ህሊና የሚያዘቅጡ፣ የኅብረተሰብ የቁጠባ ባህል እንዳይጎለብት የሚገዳደሩ መልዕክቶችና ማስታወቂያዎች በሚተላለፍበት መስኮት እንዴት መኖር እንዳለበት ግራ ገብቶት፣ ስደትን ብቸኛ አማራጭ ያደረገ ወዝአደር ሲከተከት ማየቴ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ይኼኛው አዋጅ ጠበቅ ተደረገ? ብዬ ነበር። ያው ማንን እጠይቃለሁ አጠገቤ ያለው አንድ ምሁር ነው። ምሁር አያሳጣችሁ ብያለሁ እግረ መንገዴን። የባሻዬ ልጅ ሰምቶኝ ሲያበቃ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ!›› ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። አተነፋፈሱ ከበሻዬ እሱ የሚቀድም ነበር የሚመስለው። ለነገሩ ማን ከማን እንደሚቀድም የሚያውቀው እሱ አምላክ ብቻ ነው። ይኼን አንቀበል ብለን አይመስላችሁም ለመቀዳደም ስንሽቀዳደም ስንቱ አገር ከኋላችን እየተነሳ የቀደመን። ብቻ የበሻዬ ልጅ እንደምንም ታሽቶ ሲያበቃ፣ ‹‹የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለን ማለፍ ነው፤›› አለኝ። ‹‹ምን አደረጉ እነሱ?›› አልኩ የሳዑዲ ተመላሾችን ያለ መስሎኝ። ‹‹ማን እነሱን አለህ? የእኛዎቹን ነው እንጂ?›› ብሎ ተቆጣኝ።
ማንጠግቦሽ ይኼን የቱርክና የኮሎምቢያ ፊልም እየከሰከሰች ስንቱን ወሬ አስመልጣኛለች አልኩ ያመለጠኝ ሁነት ያለ መስሎኝ። ‹‹ደግሞ ምን አጥፍተን ይሆን?›› ስለው፣ ‹‹ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ታስታውሳለህ? የተናገሩትን ታስታውሳለህ? ሲናገሩ ያጨበጨብንላቸውን አስታውስ። ዛሬ ደግሞ እኛ በእነሱ ሜዳ ዓለም እያየን እየፀለይን ነው፤›› ሲለኝ ግራ ገብቶኝ፣ ‹‹ምንድነው የምትቀባጥረው?›› አልኩት ጤነኝነቱን ተጠራጥሬ። ‹‹አንተ መቀባጠር በለው እኔ ደግሞ መጠርጠር እለዋለሁ። በፖለቲካው ዓለም ምንም ነገር በአጋጣሚ እንዲያው ደርሶ አይሆንም። ምናልባት ጓደኛ አመራረጣችን፣ ከአመራረጣችንም አስተቃቀፋችን፣ ከአስተቃፋችንም አገባበዛችን፣ አዘፋፈናችን ወይም አፀላለያችን አይተው ፊት ያጠቆሩብን ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፤›› ብሎኝ ጥሎኝ ሄደ። ሳይሉኝ በገዛ እጄ እስኪ ዓሳ ጎርጉሬ ዘንዶ ላውጣ!
እናላችሁ ስለዚህ ገንዘብን በውጭ ምንዛሪ ስለማሸሽ ነገር ሰሞኑን ብዙ ስሰማ ነበር። ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር የምንሸጋገረው እንግዲህ በዚህ አያያዛችን መሆኑ ነው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ግን በቃ ሁሉም ሰው የሚያስበው አንድ ዓይነት ነገር ነው ማለት ነው?›› አለኝ በቀደም የባሻዬ ልጅ ነገሩን አንስቼለት። እንዴት ስለው፣ ‹‹ሠርተህ ሠርተህ ሲጠራቀምልህ ለምንድነው ከትልቅ ቤት፣ ከቅንጡ አውቶሞቢልና ከውስኪ ቤት ሌላ ማሰብ የማይቻለው?›› ሲለኝ ነገር አታምጣ ብዬ እንዳልሰማ ሆንኩበት። ነገር ፈርቼ እንጂ በውስጤ የሚብላላው መዓት ነው። በተለይ ስለእኛ የምናወራቸውንና የምናደርጋቸውን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነገሮች ሳይ ሳቄም እንባዬም እኩል ይመጣል። ለምሳሌ ብዬ ላስቆጥራችሁ።
ለምሳሌ ‘አገር አገር…’ እያሉ ለመጮህና ለመተማማት አንደኞች ነን ዘወር ተደርገን ስንታይ፡፡ ተውት ሌላውን ለአካባቢያችን ፅዳት መጠበቅ ግድ የማይሰጠን ሆነን እንገኛለን። ‘እከሌ ሀብታም ነው ግን አይሰጥም። አቤት ተሸክሞት ሊሞት ነው? ወይስ መቃብር ቤት ሲወርድ ሊንተራሰው ነው?’ እያልን ባላሀብቱን ሁሉ ስናማ ላየን ከእኛ በላይ መፅዋችና የተቸገረ የሚረዳ ያለ አይመስልም። ነገር ግን እንዲያ ከምንለው ውስጥ እንዳቅሚቲ የምናከራያት ቤት ያለችን ሰዎች የተከራይ ለቅሶና ብሶት ምንም ሳይሰማን በወር በወር ኪራይ የምንጨምር ሆነን እንገኛለን። እንዲያው እሱን ትታችሁት የቤት ውስጥ ሠራተኞቻችንን በትህትና፣ በወንድምና በእህትነት ስሜት የምንንከባከባቸውስ ስንቶቻችን ነን? ታዲያ ዛሬ ብርን በውጭ ምንዛሪ እየተኩ ሀብት ከአገር ያሸሻሉ ብሎ የሚያማን ምን የማያውቀን ነው!
በሉ እንሰነባበት። ነግሬያችሁ እንደሆነ ትዝ አይለኝም ብቻ ጥላቻ ሥር ሲሰድ ከባህር ዛፍ ሥር የሚበልጥ አይመስለኝም ነበር። መሰንበት ደጉ ይኼው ያረጋግጥልን ይዟል። ‹‹አንበርብር ምንም ቢሆን ዕድሜን አትጥላው። ነገህ ውስጥ ነው የትላንት ንስሐህ ሕይወት የሚኖረው፤›› የሚሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ባሻዬ ከእኔ በላይ በሥልጣን፣ በፍትሕ፣ በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም የተሠራውን ሁሉ ቆመው ታዝበዋል። ሸፍጥ፣ ቂም በቀል፣ ምቀኝነትና አድርባይነት በባሻዬ የሕይወት ምዕራፎች ብዙ ጠባሳ አበጅተዋል። እሳቸው ታዲያ የሆኑትን ሁሉ ሆነው ያዩትን ሁሉ ዓይተው፣ ዛሬያቸውን ሳይፀየፉ ሌላው ጭምር ለነገ እንዲጓጓ ሲሰብኩ ሳይ ይገርመኛል።
አዘውትረው፣ ‹‹በጥላቻ ፍሬ አታፈራም!›› ሲሉኝ ማንዴላን ይመስሉኛል። (ነፍሳቸውን ይማርና ለካ ማንዴላም አርፈዋል? እንኳን ያረፉትን የቆሙትን የሚያስረሳን ዘመን አትሉኝም) ‘ሰው በቀን ውስጥ ቢያንስ ለሰላሳ ሰከንድ ዕብድ ወይም ጅል ይሆናል’ እንዲሉ ጠቢባን (ይኼን ይኼን እንኳ ራሳችሁ አጣሩ) በቀን ውስጥ ለተወሰነች ጊዜ ስጃጃል ወይም ሳብድ፣ ‘ምነው ባሻዬ ኪኒን በሆኑና በፍፁም ጥላቻና ጨለምተኝነት የተዘፈቁ ሰዎች ውጠዋቸው በዳኑ’ እላለሁ። የሚታየውና የሚሰማው ያስብላላ። ለማንኛውም ከጭፍን ጥላቻና ከጨለምተኛ አመለካከት ይሰውራችሁ ብያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ከላይ ጀመር አድርጌ የተውኳት ጉዳይ ማሳረጊያ ብትሆነንስ? እንግዲህ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ይኼ የዓለም ሀብታሞችን በዝርዝር የሚያስተዋውቀን ‘ፎርብስ’ አምስቱን የእኛ ሰዎች ጀባ አለን አሉ፡፡ ባለ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ባለሀብቶች ብሎአቸው ነው አሉ፡፡ እንግዲህ በእኛ ብር ሲመታ ቢሊየነሮች አይደሉ? የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የእነ እንትናም አለ ገና…›› ሲለኝ በእርግጥም ቢሊየነሮቻችን አምስት ብቻ እንዳልሆኑ ትዝ አለኝ፡፡ ‹‹የእኔ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው…›› ከሚሉት ጀምሮ፣ አንገታቸውን የደፉ ሁሉ ቀና ቀና ይበሉ እንጂ? ያለበለዚያ ፈረንሣዊው ፈላስፋ ባልዛክ፣ ‹‹ከእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ አንድ ወንጀል አለ፤›› እንዳለው ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል የሚለውን ሐሳብ ብዙዎች እያብላሉት እንደሆነ፣ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው (ያሁነያ)፡፡ እኔ ደግሞ ዲታ ነን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ ብያለሁ፡፡ ወጣ ወጣ በሉ የምን መደበቅ ነው? መልካም ሰንበት!