Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየመሠረተ ልማቱን ያህል ተመጣጣኝ ስፖርተኛ የማፍራት ጥያቄ

የመሠረተ ልማቱን ያህል ተመጣጣኝ ስፖርተኛ የማፍራት ጥያቄ

ቀን:

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ከተሞች ለወጣት ስፖርተኞች መገኛ በመሆን አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል ማዘውተሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በተለያዩ ስያሜዎች የሚታወቁ ለበርካታ ወጣት አትሌቶች መገኛ የሆኑ የሰፈር ሜዳዎች ከዘርፉ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ለሌላቸው መሠረተ ልማቶች ተሸንሽነው አልቀዋል፡፡ የክልል ከተሞችም የዚህ ተመሳሳይ እጣ እየገጠማቸው ይገኛል፡፡

 

በዚህ የተነሳ ለእግር ኳስ፣ ለሩጫና ለሌሎችም ስፖርቶች ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ የነበራቸው ታዳጊ ወጣቶች በመድረኩ ታሪክ ጠቃሽ እየሆኑ ከዚያ ሲያልፍም ለተለያዩ ሱሶች ተጠቂ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንዲሰፋም ምክንያት ሆኗል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ በአትሌቲክሱም ሆነ በእግር ኳሱ እንዲሁም በሌሎችም ስፖርቶች የሚመዘገበው ውጤትና ፍላጎቱ መጣጣም እየቻለ አይደለም፡፡

የሩቁ ቀርቶ ከሰሞኑ ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና አቻው የደረሰበት ሽንፈት በሁሉም አቅጣጫ መነጋገሪያ እንደሆነ ይገኛል፡፡ በዋናነትም የስፖርት ማዘውተሪያዎች እጥረትና የዘፈቀደ ሥራ ውጤት ተደርጎም እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡

መንግሥት የስፖርት መሠረተ ልማት አውታሮችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በተለይ ትልልቅ የውድድር ማከናወኛ ዘመናዊ ስታዲየሞች ግንባታ በዋናነት ትኩረት እየተሰጠው መሆኑ ይወሳል፡፡ በሁሉም ክልሎች በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ ስታዲየሞች እየተገነቡ መገኘታቸው ተገቢነቱ ባያጠያይቅም፣ በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያዎች በዛው ልክ እንዲስፋፋ አለመደረጉ ግን ትዝብትን እያጫረ መጥቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስታዲየሞቹ ለትልልቅ ውድድሮች ማካሄጃ እንጂ ለዕለታዊ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የማይሆኑ በመሆናቸው ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት ስለመሆኑም በብዙዎች ይነሳል፡፡

ከእነዚህ ግዙፍ ስታዲየሞች ግንባታ በተጓዳኝ የአገሪቱ ስፖርት ቀድሞ በውጤታማነቱ ከሚጠቀሰው አትሌቲክስ ጀምሮ የሁሉም ስፖርቶች ውጤት እንደ ካሮት ሥር ወደ ታች እየወረደ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያ በውስን የአትሌቲክስ ውድድሮች በኦሊምፒክ የምታስመዘግባቸው ሜዳሊያዎች ቁጥር መመልከት እንደሚቻል የሚናገሩ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ አሁን አሁን በብቸኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ከሽንፈት ማግስት ሁሌም የመፍትሔው አካል ሊሆን እንደማይችል የሚታመነው ምሬትና የቁጭት አስተያየት ብቻ ሆኗል፡፡ ይኼው ለዓመታት በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም ዋንጫ ሲንፀባረቅ ቆይቷል፡፡ አሁንም ከወዲሁ ወደ መፍትሔው ለመሄድ የሚያመላክተውን ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን መቀመርና ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ ቁጭቱና ዋይታው መቀጠሉ አይቀርም፡፡

በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጣው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አዲሱ አመራር ለቶኪዮ ኦሊምፒክና ለሌሎችም ዓለም አቀፍ ውድድሮች፣ አገሪቱ በስፖርቱ ያላትን የተፎካካሪነት አቅም ማጎልበት ትችል ዘንድ ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ያማከለ የአራት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ ከዕቅዶቹ መካከልም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በስፖርቱ መሠረተ ልማትና በተለይም ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ሊያደርጉት ስለሚገባው ቅድመ ዝግጅት የተመለከተው ይገኝበታል፡፡

እስከአሁንም በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋ አስተዳዳርና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልሎች ግምገማዊ የመስክ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ይኼው በሌሎችም ክልሎች ቀጣይነት እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን፣ ባለፈው ሳምንት በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ያለውን ስፖርታዊ ክንዋኔ ምን እንደሚመስል ተመልክቷል፡፡ በፕሮግራሙ የታደመው የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል እንደታዘበው ከሆነ ክልሎቹ በአብዛኛው በግዙፉ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ላይ ተጠምደዋል፡፡

የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መዲና የሐረር ከተማም 1.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዛ የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት ለመሆን ግማሽ መንገድ ላይ ደርሳለች፡፡ የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀምዛ መሀመድ እንደተናገሩት፣ ስታዲየሙ በስፖርቱም ሆነ በስፖርት ቱሪዝሙ ዘርፍ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ጤናማና አምራች ዜጎችን ከማፍራት አኳያም የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ስታዲየሙ 24 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ከመሆኑም በላይ በወንበር 60 ሺሕ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውና ግንባታው በሦስት ምዕራፍ ይጠናቀቃልም ተብሏል፡፡ ከስታዲየሙ ጎን ለጎን 250 የመኝታ ክፍሎች ያለው ዘመናዊ ሆቴልና በውስጡ 16 የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ስፋት ያላቸው የቢዝነስ ማዕከሎችና ሌሎችንም መሠረተ ልማት አሟልቶ እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉብኝቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የሐረሪ ክልል ለ2020 ኦሊምፒክ ሊያደርግ በሚገባው ዝግጅትና ለዚያ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚጠበቅበትን ቅድመ ሁኔታ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከወዲሁ ለመምከር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡ በማያያዝም አገሪቱ በኦሊምፒክም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በአሁኑ ወቅት በሐረር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የክልል ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ባልነበሩበት ወቅቶችና ዓመታት የነበረው ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ መፍትሔው ደግሞ የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ለሌሎችም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች ተወዳዳሪ ለመሆን ቀድሞ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ሲቻል እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ 

መንግሥትና ሕዝባዊ አደረጃጀቱ በስፖርቱ ዘርፍ ከመቼውም በተሻለ እጅና ጓንት በመሆን መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው፣ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን አስተያየት አጠናክረዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሀምዛ በበኩላቸው፣ ማሳሰቢያው የሐረሪ ክልል ማኅበረሰብና ወጣቱ ያለውን እምቅ ችሎታና ሀብት በመለያየት ጥቅም ላይ የሚያውልበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ገልጸው፣ በዚሁ አግባብ ክልሉም በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ መንግሥታዊ አካሉ እነዚህን የመሰሉ ተደጋጋሚ የጉብኝት ፕሮግራሞች ቀጣይነት እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል፡፡

  • ከመወዳደሪያ ይልቅ ለማዘውተሪያ ትኩረት የሰጠው የድሬዳዋ አስተዳደር

በዘጠኝ ቀበሌዎች የተከፋፈለው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሌሎች ክልሎች እየተከናወነ እንዳለው የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት የመሆን ፍላጎት እንደነበረው ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ለጊዜውም ቢሆን ከመወዳደሪያ ስታዲየም ግንባታ ይልቅ ለነባሩ ስታዲየምና በትልቁ ለማዘውተሪያ ስፍራዎች ቅድሚያ መስጠቱን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡ ከንቲባው አቶ ኢብራሂም ኡስማን ሚኒስትር ዴኤታውን ያካተተው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ልዑካን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ለጊዜውም ቢሆን የዘመናዊ ስታዲየሙን ግንባታ በመግታት ነባሩን ስታዲየሙ በማካተት ለማዘውተሪያዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ምክንያቱን አስመልክቶ ከንቲባው እንዳብራሩት፣ ለስፖርቱ ዕድገት ከታች እስከ ላይ ከማዘውተሪያ እስከ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ቅብብሎሹን የጠበቀ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል በትልቅ ደረጃ ለውድድር የሚያስፈልገው ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ጉዳይ ጊዜውን ጠብቆ እውን የመሆኑ ነገር ባያከራክርም፣ ከስር ለዚያ የሚመጥን አቅምም ጥራትም ያለው ስፖርተኛ ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም በትልቅ ደረጃ ለምጠብቀው ውድድር ከስታዲየም ይልቅ ማዘውተሪያዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ያምናሉ፡፡

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ገንብቶ ለዚያ የሚመጥን ተወዳዳሪ ከሌለ ዞሮ ዞሮ ስታዲየሙ ከኮንስርት ዝግጅት ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረውም አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደዚህ የመሰሉ ግንባታዎች ሲከናወኑ የመሠረተ ልማቱን ያህል ተመጣጣኝ ስፖርተኛ የማፍራት ጥያቄም ሊታሰብበት እንደሚገባ የሚያምኑ አሉ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ከድር ጅሃር በበኩላቸው፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ለታዳጊ ወጣቶችና ለስፖርቱ በሰጠው ትኩረት በተለይም በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቶች ከሚገኙ ማዘውተሪያዎች ውጪ የባለቤትነት ማረጋገጫ ያላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ  ማዘውተሪያዎችች ወደ 14 ከፍ እንዲሉ መደረጉን ጭምር ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንድ ቀበሌ በአማካይ ከአንድ በላይ የማዘውተሪያ ባለቤት እንዲሆን መደረጉም ተነግሯል፡፡ አንዳንዶቹን ማዘውተሪያዎች ሪፖርተር ተዟዙሮ እንደተመለከተው ከሆነ፣ ሜዳዎቹ ሙሉ በሙሉ በታዳጊ ወጣቶች የተያዙና ተራ በሚጠብቁ አዘውታሪዎች የተሞሉ ነበሩ፡፡

የ2020 ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩን ስፖርታዊ ክንዋኔ ምን እንደሚመስል ግምገማዊ ጉብኝት ያደረገው ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው፣ ድሬዳዋ በ1990ዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ይፋ የሆነውን የስፖርት ፖሊሲ ሰዎች በሚኖሩበት፣ በሚሠሩበትና በሚማሩበት ሁሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያረጋገጠውን ድንጋጌ እውን ማድረጉን ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ በተጓዳኝም የሦስት ዓመት ዕድሜ ለቀረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የድሬዳዋ አስተዳደር ከወዲሁ ሊያደርግ ያሰበውን ዝግጅት አስመልክቶ፣ ፕሬዚዳንቱ አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ለከተማው ካቢኔ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካለው ውስን በጀት ለስፖርቱና ለመሠረተ ልማቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ከመሆኑም በላይ ቀደምቱንና ነባሩን ስታዲየም ከ167 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የማሻሻያ ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባውና የካቢኔ አባላቱ ተናግረዋል፡፡ ከስታዲየሙ ጎን ለጎንም ለድሬዳዋ ከተማው ስፖርት የገቢ ማጠናከሪያ እንዲውል ደረጃቸውን የጠበቁ የሆቴልና ተያያዥ ግንባታ በዙሪያው እያከናወነ ይገኛል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ምን እያደረገ ነው ለሚለው ጥያቄ ከንቲባው፣ በኅብረተሰቡ በዋናነት የሚዘወተሩ እንደ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስና ዋና የመሳሰሉ ስፖርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ተገቢው እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዋናነትም ለስፖርቱ ማነቆ ተብለው በተለይም ከአሠራርና ከአደረጃጀት ጋር የተያያዙ የተሐድሶና የማጥራት ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ከ17 በላይ ፕሮጀክቶች በሁለቱም ፆታዎች ምልመላና ዝግጅት ተደርጎ የምዘና ውድድሮች እየተደረጉ እንደሚገኝም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ለቡድኑ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...