Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሽብርተኝነት እየተፈተነች ያለችው ታላቋ ብሪታኒያ

በሽብርተኝነት እየተፈተነች ያለችው ታላቋ ብሪታኒያ

ቀን:

ታላቋ ብሪታኒያ እ.ኤ.አ. ከ2000 በፊት ሽብርን አስተናግዳ ብታውቅም፣ ዘንድሮ እየገጠማት ያለውና በተለይ ከእስልምና አክራሪነትና እስልምናን ከመፍራት የሚመነጨው ግን ለዜጎች፣ በተለይም በመዲናዋ ለሚገኙት ሎንዶነርስ ሥጋት፣ ለአገሪቷ ደኅንነት ክፍልም ፈተና ሆኗል፡፡

ታላቋ ብሪታኒያ ከ20 ዓመታት በፊት ከሰሜን አየርላንድ ግጭት ጋር ተያይዞ በአይሪሽ ሪፐብሊካን ታጣቂዎች ጥቃት ይፈጸምባት የነበረ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ የነበረው ገጽታ ተቀይሯል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ በዓረቦችና በእስራኤል ግጭት ምክንያት ከመካከለኛው ምሥራቅ አቆጥቁጠዋል በሚባሉ የሽብር ቡድኖች ሰለባ ሆና የምታወቅ ቢሆንም፣ ሁኔታዎች የከረሩትና ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች መታየት የጀመሩት ከ21ኛው ክፍለ ዘመን (2000) በኋላ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1971 እስከ 2001 ባሉት ዓመታት በሽብር ጥቃት 430 ሲሞቱ፣ ከእነዚህ 125 ከሰሜን አየርላንድ ግጭት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1988 ከፍራንክፈርት ለንደንንና ኒውዮርክን አልፎ ወደ ዲትሮይት ይበር የነበረው ፓን አም የበረራ ቁጥር 103 ውስጡ በቦምብ ጋይቶ ስኮትላንድ ሎከርቢ በመኖሪያ ሥፍራ ላይ በመከስከሱ፣ መሬት የነበሩ፣ 16 የአውሮፕላኑ ሠራተኞችና 234 መንገደኞች ሞተዋል፡፡ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ከስኮትላንድ ያርድ ጋር በመተባበር ባደረገው ምርመራም፣ የሎከርቢው ፍንዳታ ከተከሰተ ከሦስት ዓመታት በኋላ በሁለት የሊቢያ ዜጎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ሟቹ የወቅቱ የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ሁለቱን ሰዎች ለፍርድ አሳልፈው መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2001 የሊቢያ የደኅንነት ባለሙያ አብደልባሴት አል ሜግራሂ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የዕድሜ ልክ እስራት ቢፈረድበትም፣ እ.ኤ.አ. በ2009 ባጋጠመው የፕሮስቴት ካንሰር የስኮትላንድ መንግሥት ከእስር ለቆት በ2012 ሕይወቱ አልፏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሎከርቢው ፍንዳታ እ.ኤ.አ. በ1988 መከሰቱ ሽብር በዓለም ሊስፋፋ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ሲሆን፣ ኃያላኑ አገሮችም ሽብርን ለመከላከል በአገሮች ጉዳይ ጦር ሲሰብቁና ጣልቃ ሲገቡ ኖረዋል፡፡ በአገሮች ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግንባር ቀደሞቹ አሜሪካና እንግሊዝ ከደረሱባቸው የሽብር ጥቃቶች የመከቷቸው እንደሚያይሉ ቢናገሩም፣ ባልታሰበ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው የሽብር ጥቃት ዜጎቻቸውን እያጡ ነው፡፡ የሽብር ጥቃቱም በዓለም በርካታ አገሮችን የነካና ሥጋት ላይ የጣለም ነው፡፡

ታላቋ ብሪታኒያም እ.ኤ.አ. 2017 ከገባ ከመጋቢት አጋማሽ ወዲህ ብቻ አራት የሽብር ጥቃቶችን አስተናግዳለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ባለፈው ሰኞ የተነገረው አንዱ ነው፡፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት፣ እሑድ ለሰኞ አጥቢያ በለንደን ሙስሊሞች ካፈጠሩ በኋላ በመስጊድ የሚያከናውኑትን ፀሎት ጨርሰው እየወጡ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ የተከራየውን መኪና በእግረኞች መንገድ ላይ በመንዳት አንድ ቀድሞ ታሞ በመንገድ ላይ የመጀመሪያ ዕርዳታ በማግኘት ላይ የነበረን ሲገድል፣ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠማቸውም አሉ፡፡ በለንደን ሰቨን ሲስተርስ ጎዳና በሚገኘው የሙስሊም መረዳጃ ቤትና ፊንስቤሪ ፓርክ መስጊድ አካባቢ የሽብር ጥቃቱን በሙስሊሞች ላይ ያደረሰው የ47 ዓመቱ የዌልስ ካርዲፍ ነዋሪ ዳረን ኦስቦርን ነው፡፡

የካርዲፍ ማዕከላዊ ግዛት ፓርላማ አባል ጆ ስቴቨንስ፣ ስለ ሚስተር ኦስቦርን ብዙም የሚታወቅ መረጃ አለመኖሩን የተናገሩ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡ ቤተሰቦቹን ያነጋገረው ቢቢሲ በበኩሉ እናቱ፣ እህቱና የአጎቱ ልጅ በሁኔታው እንደተደናገጡ አስፍሯል፡፡ ቤተሰቦቹ በሰጡት መግለጫም ‹‹ተደናግጠናል፡፡ የሚታመን አይደለም፡፡ የምናውቀው ባህሪም አይደለም›› ሲሉ ድርጊቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋለው ኦስቦርን፣ ‹‹ሙስሊሞችን መግደል እፈልጋለሁ፤›› እያለ በተደጋጋሚ ይናገር እንደነበር ቢቢሲ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ያሰፈረ ሲሆን፣ ይህ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ መንታ አመለካከት ፈጥሯል፡፡ አንዳንዶች የየቀን ሥራቸውን ለመሥራት አስጊ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን፣ ‹‹ፍርኃት ውስጥ እየኖርን ነው›› በማለት ሲገልጹ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት በማውገዝና ከጎናቸው በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ሥፍራ አበባ ያስቀመጡም አሉ፡፡

ጥቃቱን በፈጸመው ግለሰብ ላይ ምዕመኑ ጥቃት ለማድረስ ሲረባረብ የነበረ ቢሆንም፣ በኢማም መሐመድ መሐሙድ ግሳፄ ሊተርፍ ችሏል፡፡ ኢማሙ በቅርቡ በለንደን ብሪጅ ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት በማስታወስም፣ ይኼኛውም ተመሳሳይነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኅብረተሰቡ አንድነት አልተበተነም፡፡ ያለንን አንድነት አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ አንድ ላይ መሆን አለብን፤›› ሲሉም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በችግር ጊዜ አንድ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው አክለዋል፡፡

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጥቃቱን አድርሷል ተብሎ ጥርጣሬ በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ዓላማ ያደረገው፣ የዕለት ተዕለት ኑሮዋቸውን ለመምራት የሚሠሩ ንፁኃን ዜጎች ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሽብርተኝነት ተደባብሶ እንደማይቀርም አክለዋል፡፡

የለንደኑ ከንቲባ ሳዲቅ ካን በጥቃቱ ዙሪያ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የሽብር ጥቃቱን ‹‹በሎንደነርስ (የለንደን ነዋሪዎች) ንፁኃን ላይ በረመዳን ሆን ተብሎ የተፈጸመ፤›› ብለውታል፡፡ በለንደን ብሪጅ፣ በማንቸስተርና በዌስት ሚኒስትር ላይ እንደተፈጸመው ሁሉ፣ ይህም በአንድ ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመና በብሪታናውያን የሠለጠነ አብሮ የመኖር ብሂል ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ከመጋቢት ወዲህ በብሪታኒያ ከተፈጸሙት ጥቃቶች በዌስት ሚኒስትር ብሪጅ የተፈጸመውም ይገኝበታል፡፡ የ52 ዓመቱ እንግሊዛዊ ካሊድ ማሱድ በዌስት ሚኒስትር ብሪጅ ላይ መኪናውን በማሽከርከር በፓርላማ አካባቢ የነበረ ፖሊስን በስለት ወግቶ መግደሉ፣ በኋላም ራሱ መገደሉ ይታወሳል፡፡ በዚህ የሽብር ድርጊት ማሱድን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ፣ 49 ተጎድተዋል፡፡ የሽብር ጥቃቱም ከእስልምና አክራሪነት የመነጨ ነው ተብሏል፡፡

በግንቦት ወር ደግሞ የማንቸስተር አሬና ግራንዴ ኮንሰርት እንደተጠናቀቀ ሕዝብ በተሰበሰበበት በአጥፍቶ ጠፊ በተፈጸመ የቦምብ በጥቃት 22 ሰዎች ሲሞቱ፣ 120 ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሰኔ መግቢያ በለንደን ብሪጅ ላይ መኪና በፍጥነት በማሽከርከርና ሰዎች በተሰበሰቡበት በማጋጨት፣ በኋላም ከመኪናው የአጥፍቶ ጠፊ የሚመስል ቀበቶ የታጠቁ ሦስት ሰዎች ወጥተው በአቅራቢያው በሚገኝ ሱፐር ማርኬት ገብተው ሰዎችን በስለት በመውጋት ስምንት ገድለው በ48 ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እነሱም ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡

ከሦስት ቀናት በፊት በተከሰተው የሽብር ጥቃት የተመዘገበው አንድ ሞት በመኪና ከመግጨት ጋር ይሁን ቀድሞ ከነበረ ችግር ባይለይም፣ በመኪና ሰዎችን እየገጩ መግደል ወይም መጉዳት አዲስ የሽብር ጥቃት ዘዴ ሆኗል፡፡ የቡድኑን ዓላማ ተከትለው ጥቃት ለሚፈጽሙ ኃላፊነቱን የሚወስደው አይኤስም በብሪታኒያ በተከታታይ ለደረሱት ሦስት ጥቃቶች ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

በብሪታኒያ እስልምናን ከማክረርና ከመፍራት ጋር በተያያዘ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ አራት የሽብር ጥቃቶች በመፈጸማቸውና በለንደን ባለ 24 ፎቅ የግሬንፌል ሕንፃ በእሳት ጋይቶ 79 በመሞታቸው፣ ነዋሪዎች ብሶታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ብዙዎችን በቅኝ ግዛት በመያዟ፣ አሁን ድረስም በየደሴቱ በምታስተዳድራቸው ስፍራዎች በትልቅነቷ የምትታወቀው ‹‹በብሪታንያ ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም የተባለላት›› ታላቋ ብሪታኒያ፣ አሁን ደግሞ በሽብር እየተፈተነች ነው፡፡

የለንደን ከንቲባ ቢሮ እንደገለጸው፣ በሰኔ መግቢያ ላይ በለንደን ብሪጅ ከደረሰው የሽብር ጥቃት በኋላ በነበረው የመጀመሪያ ሳምንት 36፣ በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ 120 እስልምናን ከመፍራት ጋር የተያያዙ ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ የጥላቻ ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱን ያመለክታል ብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...