Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱ በድንበር ጉዳይና በፖለቲካ እስረኞች ዙሪያ እንደማይደራደር ግልጽ አደረገ

ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱ በድንበር ጉዳይና በፖለቲካ እስረኞች ዙሪያ እንደማይደራደር ግልጽ አደረገ

ቀን:

  • ቃል የተገባው የድብልቅ የምርጫ ሥርዓት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል፣ በድንበርና በፖለቲካ እስረኞች ጉዳዮች ለድርድር እንደማይቀመጥ አቋሙን ግልጽ አደረገ፡፡

ገዥው ፓርቲ አገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ለማውጣት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለድርድር መጥራቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች 13 ረቂቅ የመደራደሪያ አጀንዳዎችን አቅርበዋል፡፡

የቀረቡትን ረቂቅ አጀንዳዎች ለማፅደቅ ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደ የፓርቲዎች ውይይት ነው ኢሕአዴግ አቋሙን ግልጽ ያደረገው፡፡

በዚህም መሠረት የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀጾች እንዲሻሻሉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበውን የመደራደሪያ አጀንዳ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ  የሚሻሻለው በድርድር ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እንደሆነ፣  የኢሕአዴግ ተወካይና ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ግልጽ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድንበርን በተመለከተ የቀረበውን የመደራደሪያ አጀንዳ ኢሕአዴግ እንደማይቀበል አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ በዚህ የድርድር አጀንዳ ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሊነሱ የታሰቡ ርዕሶች የኢትዮጵያን የባህር በር የማስመለስ ጉዳይ፣ በጎንደር መተማ በኩል ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጠ ተብሎ ስለሚወራው መሬትና በቀይ ባህር አካባቢ የዓረብ አገሮች ወታደራዊ መስፋፋት ጉዳይ ላይ ለመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው በሰጡት ምላሽ ድርድር ማለት ሰጥቶ የመቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ኢሕአዴግ በዚህ አጀንዳ ላይ ልደራደር ቢል እንኳ ተቃዋሚዎች የባህር ወደብ ከየት አምጥተው ሊሰጡት ነው? ኢሕአዴግስ ወደብ ከየት አምጥቶ ሊሰጣቸው ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የድንበር ጉዳይ በፓርቲዎች ድርድር ሳይሆን በሁለት ሉዓላዊ አገሮች መካከል ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ በመመሥረት የሚፈጸም በመሆኑ፣ ለመንግሥት የሚተው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ እንደማይደራደር አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በራሳቸው አባላት ላይ ደረሰ የሚሉትን አፈናና እስር በመጥቀስ ለመሞገት ቢሞክሩም፣ ወንጀል ሳይሠራ የታሰረ ወይም ፖለቲከኛ ስለሆነ ወይም ፖለቲካ ስለጻፈ የታሰረ ጋዜጠኛ አለመኖሩን አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ መግባባትና ብሔራዊ እርቅ ተብሎ የቀረበውን አጀንዳ በተመለከተ ኢሕአዴግ ግልጽ ባደረገው አቋሙ መሠረት፣ ብሔራዊ ዕርቅ የሚለው ሐረግ እንዲሰረዝ ብሏል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ከማንም ጋር ፀብ ላይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በከፋቸው ዘመን እንኳን  ፀብ ውስጥ ገብተው አያውቁም፤›› የሚል ምክንያት የሰጠው ገዥው ፓርቲ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደማይደራደር ግልጽ አድርጓል፡፡

ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተም ሕገ መንግሥቱን ማክበር፣ በሰላማዊ ትግልና በሕግ የመገዛትና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የመሳሰሉትን የማያካትት ከሆነ እንደማይደራደር፣ ይህም ቢሆን ከሥልጣን በመለስ ብቻ መሆን እንዳለበት አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በተመለከተ ሰላማዊ ያልሆነ የትግል አማራጭን ያልተከሉ ፓርቲዎች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመጡ በሚል አጀንዳ ዙሪያም እንደማይደራደር ግልጽ አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት ኢሕአዴግ ለመደራደር ዝግጁ የሆነባቸው አጀንዳዎች የምርጫ ሕጎችን ማሻሻል፣ ሌሎች ሕጎችን ማሻሻል (የፀረ ሽብር ሕጉን፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅን፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ)፣ የፍትሕ አካላትን አደረጃጀት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ፣ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ ለመደራደር ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ውጪ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጉዳዮች ላይ አፈጻጸምን የሚመለከቱ በመሆናቸው፣ ድርድር ሳይሆን ውይይት ሊያደርግባቸው ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ግጭት አዘል ተቃውሞ ከተረጋጋ በኋላ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ቃል ከገባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ የምርጫ ሥርዓቱን ከአብላጫ ድምፅ ወደ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት እንደሚለውጥ ገልጾ ነበር፡፡ ይህንንም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር በማድረግ እንደሚፈጽመው ቃል ገብቶ ነበር፡፡

ይህንን ዕውን ለማድረግ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54(2) መሻሻል ያለበት ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ዙሪያ እንደማይደራደር በመግለጹ ቃል የገባው ተመጣጣኝ ውክልና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ እየተነገረ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...