Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ንፁህ ውኃ ለማቅረብ ፕሮጀክት ነደፈ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ንፁህ ውኃ ለማቅረብ ፕሮጀክት ነደፈ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዙሪያው ለሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ የሚያስችል አዲስ ዕቅድ አፀደቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት አስተዳደሩ 660 ሚሊዮን ብር በጀት ይዞ ወደ ግንባታ እየገባ ነው፡፡

በመጀመሪያ ዙር ውኃ የሚቀርብላቸው የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ገላን፣ በኬ፣ ድሬ፣ ሰንዳፋና በረህ ናቸው፡፡ እነዚህን ከተሞች ውኃ የሚያጠጡ ሰባት ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ ተገልጿል፡፡

በሁለተኛው ዙር ደግሞ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ሆለታ፣ ለገጣፎና ለገዳዲ ናቸው፡፡ እነዚህን ከተሞች ውኃ የሚያጠጡ አሥር ጥልቅ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ በዕቅድ ተይዟል፡፡

በሦስተኛው ዙር ደግሞ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማን ንፁህ ውኃ አቅርቦት ያሻሽላል ተብሎ የሚጠበቀው የገርቢ ግድብ ግንባታ ለሱሉልታና ለአካባቢው ንፁህ ውኃ ያጠጣል ተብሎ ታቅዷል፡፡

አቶ አወቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ በጀትና በራሱ አቅም ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች እንዲገነባና ከገላን ከተማ በስተቀር ሌሎቹ የከተማ አስተዳደሮች የውኃ መስመር ዝርጋታዎችን በራሳቸው አቅም እንዲያካሂዱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ሰሞኑን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ በወቅቱ እንደገለጹት አስተዳደሩ ይህንን ፕሮጀክት በራሱ ወጪ እንደሚያካሂድ፣ ሥራውን የበለጠ ለማስፋፋት ደግሞ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ውይይት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋናዎቹ የውኃ ምንጮች የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ናቸው፡፡ በተለይም በግድብ በኩል ለገዳዲ፣ ድሬና ገፈርሳ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በቅርቡ ገርቢ፣ ወደፊት ደግሞ ሲቢሉ አዲስ አበባን ውኃ ያጠጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ የመጠጥ ውኃ የግድብ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

ከግድብ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ የተካሄደባቸው፣ ወደፊትም የሚካሄድባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ አካባቢዎች አዲስ አበባን ውኃ ቢያጠጡም እነሱ ግን በውኃ እጥረት ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው አግባብ አለመሆኑ በተለያዩ መድረኮች ሲነሳ ቆይቷል፡፡

በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቅሬታ በመነሳት በ2006 ዓ.ም. በዙሪያው ለሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ውኃ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ቢጀምርም ብዙም እንዳልገፋበት ተገልጿል፡፡

አቶ አወቀ እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት በተሻለ ደረጃ ፕሮጀክቱን ለማካሄድ ታቅዷል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዙሪያው ለሚገኘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውኃ ለማቅረብ ቢወስንም፣ በከተማው ውስጥ የውኃ እጥረት እየተባባሰ ነው፡፡ በተለይ የሰሜንና የሰሜን ምሥራቅ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ውኃ በሳምንት አንዴ እንኳ በቅጡ እያገኙ አለመሆኑን እየገለጹ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ለችግሩ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥንና የተወሰኑ ጉድጓዶች ረዥም ጊዜ ማገልገላቸውን ለውኃ እጥረት እንደ ምክንያት እያቀረበ ይገኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...