Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኬኬ ድርጅት ባለቤት አራጣን በሚመለከት በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጨረሻ የመከላከያ ምስክራቸውን አሰሙ

የኬኬ ድርጅት ባለቤት አራጣን በሚመለከት በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጨረሻ የመከላከያ ምስክራቸውን አሰሙ

ቀን:

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ውስጥ ተካተው አራጣ በማበደር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የመጨረሻ የመከላከያ ምስክራቸውን አሰሙ፡፡

አቶ ከተማ በከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸው ክስ፣ ለአቶ ዮሐንስ ጌታነህ ድርጅቶች ማለትም ጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ለጌታነህ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የአራጣ ብድር መስጠታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ እሳቸው አራጣ አለማበደራቸውንና የዱቤ ሽያጭ በውክልና መስጠታቸውን የሚያስረዱላቸው ሁለት የመከላከያ ምስክሮች እንዳላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤት አቅርበው ነበር፡፡ ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ሁለቱም የመከላከያ ምስክሮች በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ በመሆኑም አንደኛው የመከላከያ ምስክር ብቻ እንዲሰሙላቸው ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡

የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ መሆናቸውን የገለጹት የመከላከያ ምስክሩ አቶ አያሌው አዲሱ ሰነዶችን እያዩ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በሟች አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ባለቤትነት የሚታወቁት ጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ጌታነህ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ መጋቢት 29 ቀን 1997 ዓ.ም. እና መስከረም 24 ቀን 2000 ዓ.ም. ከኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የንግድ ውክልና ውሎችን ፈጽመዋል፡፡

የውክልና ውሎቹን የፈጸሙት የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚያመርታቸውን ምርቶችና የንግድ ዕቃዎች በዱቤ ሽያጭ ለመውሰድ ነው፡፡ የምርቶቹ ብቸኛ ወኪል ሆነው ከወሰዱ በኋላ፣ ለሌሎች የንግድ ተቋማት የሚያከፋፍሉ በመሆናቸው 482,104,941 ብር የሚያወጡ ምርቶችን በዱቤ ሽያጭ እንደወሰዱ አስረድተዋል፡፡ የአቶ ዮሐንስ ድርጅቶችም የወሰዱትን የዱቤ ሽያጭ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቼኮች ከፍለው ሒሳብ ያወራረዱ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ለዱቤ ሽያጩ ክፍያ የተፈጸመባቸውን በድምሩ 70,083,347 ብር የያዙ 33 ቼኮችን የአራጣ ብድር የተፈጸመባቸው አስመስሎ ክስ መመሥረቱን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከአቶ ዮሐንስ ሁለት ድርጅቶች መከፈል ከነበረበት ዕዳ ሳይከፈል ተንጠልጥሎ የነበረውን አሥር ሚሊዮን ብር አቶ ከተማ በኩባንያቸው ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ካላቸው የዲቪደንድ ድርሻ ላይ እንዲከፈል በማድረጋቸው፣ ለዕዳው ማወራረጃ ገቢ መደረጉን ምስክሩ ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ባቀረባቸው 33 ቼኮች ላይ በድምሩ ከ70,083,347 ብር ውስጥ፣ አሥር ሚሊዮን ብር ኩባንያው ከሽያጭ ያገኘው መሆኑንና በውስጥና በውጭ ኦዲተሮች ተረጋግጦ ለመንግሥት ግብር መከፈሉንም ምስክሩ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የአራጣ ክፍያ ተፈጽሞባቸዋል በማለት ለክሱ ማስረጃነት ካቀረባቸው ቼኮች መካከል 30 ሚሊዮን ብር የታዘዘባቸው ቼኮች ለባንክ ቀርበው ክፍያ እንዳልተፈጸመባቸው ባንኩ በጽሑፍ ማረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡ የሟች አቶ ዮሐንስ ንብረት የተባሉት ሁለቱ ድርጅቶች፣ የኩባንያው ብቸኛ ወኪል በመሆናቸው በሚያከናውኑት ሽያጭ መጠን ሁለት ፐርሰንት ኮሚሽን ሲከፈላቸው እንደነበረም ምስክሩ አስረድተዋል፡፡

ምስክሩ በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤቱ መስቀለኛና የማጣሪያ ጥያቄዎች የቀረበላቸው ቢሆንም፣ ከላይ ያብራሩትን የምስክርነት ቃል ደግመው በማብራራት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ከተማ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ላይ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ለማሰማት ለሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የኬኬ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ በፎርብስ መጽሔት በዓመት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አላቸው ተብለው ይፋ ከተደረጉ አምስት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መካከል አንዱ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...