Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የታወቅንበትን እንግዳ አቀባበል በሆቴል አገልግሎት ላይ ብናውለው ትልቅ ለውጥ ይመጣል››

አቶ አንዱዓለም ታደሰ፣ የሆቴል አስተዳደር ባለሙያ

ሆቴሎችን፣ ሪዞርቶችንና ሬስቶራንቶች በማደራጀት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አንዱዓለም ታደሰ የተወለዱት በያቤሎ ከተማ ሲሆን፣ ዕድገታቸውና ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሐዋሳ ከተማ ነው፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለምረቃ የበቁበት የሆቴል አስተዳደር (ማኔጅመንት) ትምህርት መከታተላቸው ባደጉባትና በተማሩባት ሐዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች በሙያቸው ለመሥራት አስችሏቸዋል፡፡ በሥራቸው ዙሪያ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሆቴል ማደራጀት ሥራ ጋር እንዴት ተገናኙ?

አቶ አንዱዓለም፡- ሐዋሳን አውቃታለሁ፤ ከ15 ዓመት በፊት ገና ምንም ያልነበራት ከተማ ነበረች፡፡ ብዙም ሆቴል ስላልነበራትም ሰዎች ተዝናንተው ወደ ሻሸመኔ አደራቸውን ይመለሱ ነበር፡፡ ገና ግንባታ ላይ ነበረች፡፡ ወደዚህ ሥራ የገባሁት ፈልጌው አልነበረም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ራቅ ብዬ መማር ነበር የምፈልገው፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ማንኛውም ተማሪ በአካባቢው ባለ ዩኒቨርሲቲ ይማር የሚል ሕግ በመውጣቱ እሱን ተቀብዬ ስገባ በህልሜም በውኔም የሌለ ከመረጥኩት የትምህርት ዓይነት ውጪ ሆቴል ማኔጅመንት እንደደረሰኝ በጋዜጣ ተመለከትኩ፡፡ ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ ትምህርቴን በመቀጠል ለዩኒቨርሲቲውም ሁለተኛ ባች ሆኜ ተመረቅሁ፡፡ ትምህርቱ ለዩኒቨርሲቲውም ለእኔም በዚህ ሥራ ላይ ለተሰማሩም አዲስ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ቀጥታ ወደ ማናጀርነት ነው የገባሁት፡፡ ከተማዋም ትልልቅ ሆቴሎች እየተገነቡባት እንዲሁም አገልግሎት መስጠት የጀመሩም ነበሩባት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሌዊ ሪዞርት ሐዋሳ ፒያሳ ያለውን ማናጀር በመሆን ነው ሥራዬን የጀመርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴል ማደራጀት ማለት ምን ማለት ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ሆቴል ማደራጀት ማለት ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ባለሙያ በሆቴሉ ባለቤት አቅም ልክ፣ ይህን ያህል ሰው የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ፣ ይህን ያህል የመኝታ ክፍሎች ወዘተ… ብሎ ዲዛይን ይሠራል፡፡ በተሠሩት ላይ ደግሞ አደራጁ አዳራሹ ከመኝታ ክፍሉ፣ ኪችኑ ከመመገቢያ አዳራሹ እንዲሁም ሌሎችም የሆቴሉ ክፍሎች እንዴት እርስ በርስ ተቆላልፈውና ተመጋግበው ይሠራሉ የሚለውን ዲዛይን ይሠራል፡፡ ከዛ ግንባታው ካለቀ በኋላ ደግሞ ሰዎችን ያሠለጥናል፣ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ ለማኔጅመንት የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ሲስተም መዘርጋት፣ ያንን ለማይችሉ ደግሞ በማንዋል እንዲሠሩ ማዘጋጀት፣ በጥቂቱ ሲሆኑ በአጠቃላይ ሕንፃው ላይ ነፍስ በመዝራት ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል እንዲሆን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስንት ሆቴል አደራጅተዋል?

አቶ አንዱዓለም፡- ሥራውን የጀመርኩት ፒያሳ በሚገኘው ሌዊ ሪዞርት ነው፡፡ ከዛም ሐይቁ ዳር ሪዞርት ሲገነባ ያንን በማደራጀትና በማናጀርነት እየሠራሁ ኃይሌ ሪዞርት መጣ፡፡ ከኃይሌ ጋር መሥራት ደግሞ ዕድሉ ስለገጠመኝ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ የሱንም ለሁለት ዓመት በማደራጀትና በማናጀርነት ከሠራሁ በኋላ ራሴን ሳየው የማደራጀቱን ሥራ አሁን ባለኝ አቅም ሙሉ በሙሉ መሥራት እንደምችል በማመኔ የራሴን ቢሮ በመክፈት የማደራጀቱን ሥራ በስፋት ጀመርኩ፡፡ የቢዝነስ ፈጠራ በውስጤ እንዳል ያላሰብኩት ትምህርት አውጥቶልኛል፡፡ ከሆቴሉ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲ ስማር የተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኜ ለትምህርት ቤቱ የሚቀርበው እንጀራ ከየመደብሩ የሚገዛው በከፍተኛ ወጪ ነበር፡፡ ግዢውን በከተማ የሚኖሩ ደካማ እናቶች 200 የሚሆኑ በማደራጀት ከጤፍ ግዢ ጀምሮ እንጀራ አቅርቦት ድረስ ለዩኒቨርሲቲው እንዲያቀርቡ አደረግኩ፡፡ ለእነዚህ እናቶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ዛሬ ለሆቴሎች ጭምር አቅርቦት ማድረግ ችለዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ የቢዝነስ ፈጣራዎችንም በከተማ ላሉ ነዋሪዎች ሠርቻለሁ፡፡ ከአደራጀኋቸው በርካታ ሆቴሎች ለምሳሌ ጎንደር ላንድ ሆቴል፣ ሐዋሳ ኃይሌ ሪዞርት፣ ሌዊ፣ ሴንትራል ኬርድ ይገኙበታል፡፡ አሁን በማናጀርነት እየሠራሁ ያለሁበት ባለ አምስት ኮከብ የሆነው ሮሪ ሆቴል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉ ሆቴል ገንቢዎች ወደእናንተ የመምጣት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አንዱዓለም፡- የሆቴል ኢንዱስትሪውና ባለሙያ በአገራችን የቅርብ ጊዜ ዕድገት ነው ያላቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ሥራ ከጀመርኩበት ከአሥር ዓመታት በፊት በባለሙያ እየተመሩ ይሠሩ የነበሩት ታላላቅ ሆቴሎች የነበሩትን ያህል የሆቴል ልምድ በሌላቸው በኮንስትራክሽን ባለሙያ ብቻ ተመርተው ወደ ሥራ የገቡም አሉበት፡፡ ከነችግሩ የተገነባው ሆቴል ደግሞ ባለቤቱ ለወደደው ሰው ነበር እንዲያስተዳድር የሚሰጠው፡፡ ይህ ደግሞ ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ የዕድሜውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኢንተርናሽናል ሆቴሎች መምጣት በዛው ልክ ዩኒቨርሲቲዎችም ለኢንዱስትሪው የሚሆን ባለሙያን ማፍራት በመጀመራቸው ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ከትክክለኛ የሆቴል ባለሙያ ጋር መመካከር፣ አስተያየት መጠየቅ፣ አምኖ መቀበል ይታያል፡፡ ስለዚህ ከኮንስትራክሽን ባለሙያ ወደ ሆቴል ባለሙያ እየተቀየረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት የኤሌክትሪክ ዝርጋታ የውኃ መስመር እንዲሁም የአንድ ሆቴል ግንባታ ምን መምሰል እንዳለበት ጥቂት ስለሚማር ቢያንስ ፕላኑን በማጥናት መስተካከል ያለበትን አስተያየት መስጠት ይችላል፡፡ እንግዲህ ለአሁኑ ጊዜ ባለሙያና ባለሀብት በጥምረት የሠሩት ማሳያ ይሆናል ብዬ የማስበው ሮሪ ሆቴልን ነው፡፡ ከሐሳቡ ጀምሮ አሁን እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በርካታ የሆቴል አማካሪዎችን በመቅጠር፣ አስተያየት በመጠየቅ የአገሪቱን የአምስት ኮከብ ደረጃን ባከበረ መልኩ ተገንብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴሎች በብዛት እየተገነቡ ቢሆንም የአገልግሎት (ሰርቪስ) አሰጣጣቸው ግን ገና እንደሆነ ይነገራል፤ ችግሩ ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ያው አሁንም ኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ ነው፡፡ ትንሽ ግን መሻሻሎች ይታዩበታል እላለሁ፡፡ ቢያንስ አሁን ባሉ ትምህርት ቤት ከራስ ንጽሕና አጠባበቅ ጀምሮ የእንግዳ አቀባበል መስተንግዶው ትምህርቱ ይሰጣል፡፡ በዚህም ባለሙያው ቢሆን ለውጥ ሲያመጣ ይታያል፡፡ ግን ይኼ የእነሱ ችግር ብቻ አይደለም እንደ አገርም መታየት ያለበት ነው ደረጃውን የሰጣቸው አካል ቁጥጥር ካላደረገ መመለሳቸው አይቀርም፡፡ በቁጥጥሩ ወቅትም ጉድለት የታየባቸውን ቅጣት በመጣል ቀሪውም ተስተካክሎ ይሠራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሌላው ምናልባት በየዓመቱ ማን ምን ዓይነት ደረጃ እንዳገኘና እንዳለው ለኅብረተሰቡ ማስተዋወቅ ተጠቃሚው ከየትም ቢመጣ ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ ሆቴሉም ደረጃውን እንደጠበቀ ሊሠራ ያስችለዋል፡፡ የታወቅንበትን እንግዳ አቀባበል በሆቴል ላይ ብናውለው ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በሆቴል ማደራጀት ወይም ማናጀርነትህ እንደ ትልቅ ችግር የሚነሳው ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ዋነኛ ችግሩን መመለስ ነው፡፡ የሆቴል ሥራ ደግሞ ወጥነት ይፈልጋል፡፡ በየትኛውም አገልግሎት የሚዋወቅ ከሆነ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በሚገባው መልኩ አደራጅተህ ስትሄድ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነሱ በሚመቻቸው መልኩ መልሰውት ታገኘዋለህ፡፡ ማናጀር ስትሆንም እንደዚህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደፊት ሆቴሎች ሲገነቡ ምን መደረግ አለባቸው ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡- ዘመኑ የውድድር ነው፡፡ ትላልቅ ስም ያላቸው ሆቴሎች እየመጡ ነው፡፡ ውድድሩ የሚሆነው ልምድ ባለውና በሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ሆቴል መሥራት የሚያስብ ሰው ከመሬት መረጣ ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም እንኳን ከባለሙያ መለየት የለበትም፡፡ ምክንያቱም ቢዝነሱ ዛሬ ተሽጦ የሚመለስ አይደለም፡፡ ቀስ እያለ የጥራት ስሙን መጠበቅ ይገባዋል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...