የአፍሪካ መዲና በመባል በምትታወቀው አዲስ አበባ እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪ ብዛት ማስተናገድ እንዲቻልና የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡
ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በጌት ፋም ሆቴል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ስትራቴጂካዊ ፕላን ለፓርኪንግ ልማትና አስተዳደር›› በሚል ርዕስ የትራንስፖርት ፕሮግራሞ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከባለሀብቶች ጋር ባደረገው ውይይት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገትን የሚመጥኑ ዘመናዊ የፓርኪንግ ሥፍራዎች ሊገነቡ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ እንደተናገሩት፣ በመዲናዋ እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር ለማስተናገድና የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ፣ እንዲሁም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከመንገድ ውጪ የሚገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች መኖር ወሳኝ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሥር የሚገኙ ተቋማት የተለያዩ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችን በተመረጡ የከተማዋ ክፍሎች በመገንባት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን፣ በቀጣይ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚለሙ 60 ቦታዎች መለየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የፓርኪንግ አገልግሎት ዘርፍ መንግሥት ብቻውን አልምቶ አይዘልቀውም፡፡ በመንግሥት ብቻ ተይዞ ቀልጣፋ ሊሆን አይችልም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባለሀብቶች በዘመናዊ ፓርኪንግ ልማት ዘርፍ ለማሳተፍ ፍላጎታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት በዘመናዊ ፓርኪንግ ልማት ዘርፍ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚፈልግ የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን፣ በተለይ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችን ማስተዳደር ሙሉ በሙሉ በግሉ ዘርፍ የማካሄድ ፍላጎት እንዳለ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ትንሳዔ ወልደ ገብርኤል፣ በአዲስ አበባ 426,000 ያህል ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ገልጸው እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ ብዛት ፍላጎት ሊያረካ የሚችል የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅርቦት አለመኖር የከተማዋ አንገብጋቢ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከመንገድ ውጪ የተገነቡ የመኪና ማቆሚያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር የመንገድ ዳር ማቆሚያ እንዲበራከት ማድረጉን አቶ ትንሳዔ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከመንገድ ውጪ የተገነቡ የመኪና ማቆሚያዎች ባለመኖራቸው አሽከርካሪዎች በመንገድ ዳር ለማቆም ይገደዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት መንገዶች ይጠባሉ፡፡ በሙሉ አቅማቸው የትራፊክ ፍሰቱን ማስተናገድ አይችሉም፡፡ ይህም የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ፣ የትራፊክ አደጋዎች መጨመር፣ የአየር ብክለት መጨመርና ሌሎች ተያያዝ ችግሮች ያመጣል፤›› ብለዋል፡፡
ለዚህም መፍትሔው የመንገድ ዳር ፓርኪንጎች በማስወገድ ከመንገድ ውጪ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በመገንባት መንገዶችን በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥር እየሰደደ የመጣውን ችግር ለመፍታት መስተዳድሩ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ማስተር ፕላን ውስጥ 60 ቦታዎች ለዘመናዊ ፓርኪንግ መመረጣቸውን፣ መስተዳድሩ በራሱ ገንዘብ ጥናት በማካሄድ የፓርኪንግ ቦታዎች መገንባት መጀመሩን ገልጸው፣ ከግል ባለሀብቱ ጋር በጥምረት ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከመንገድ ውጪ የሚገነቡት የመኪና ማቆሚያዎች የመሬት ላይ፣ ከመሬት በታችና ከመሬት በላይ የሚገነቡ ሕንፃዎች ናቸው፡፡ በመሬት ላይ የሚገነቡት የመኪና ማቆሚያዎች የተለመዱ ሲሆኑ ከመሬት በታችና በላይ የተለያየ ቁጥር ያላቸው ወለሎች የያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች የሚያቆሙ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡ ሌላው በአነስተኛ ቦታ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች መያዝ የሚችሉ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ የሆኑ ስማርት ፓርኪንግ በተመረጡ የከተማዋ ክፍሎች እንደሚገነቡ ተነግሯል፡፡
ሁለት የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያዎች ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሲሆኑ፣ ሁለት ደግሞ በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ አራት የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያ ግንባታ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ፣ ሦስት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሕንፃዎች እንደሚገነቡና ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጀርባና ቦሌ ቢር ጋርደን አካባቢ ከመሬት በታች የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡
በመገናኛ ዘፍመሽ ሞል አንድ ስማርት ፓርኪንግ በቅርቡ የተመረቀ ሲሆን፣ ሁለት ተጨማሪ ስማርት ፓርኪንጎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ አራተኛውን ስማርት ፓርኪንግ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመገናኛና ወሎ ሠፈር የመሬት ላይ ፓርኪንግ የተገነባ ሲሆን በሾላ፣ አዲስ ከተማና ቸርችል ጎዳና የፓርኪንግ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መንግሥት በፓርኪንግ ልማት ዘርፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት የማልማት ፅኑ ፍላጎት አለው፡፡ ‹‹ባለሀብቱን ለማሳተፍ የታሰበው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው መንግሥት በራሱ ወጪ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በመገንባት በጨረታ ለግሉ ዘርፍ ይሰጣል፡፡ አስፈላጊውን ክፍያ በመፈጸም የማስተዳደሩን ሥራ ሙሉ በሙሉ የግል ባለሀብቶች ይሠራሉ፡፡ ሁለተኛው አማራጭ መንግሥት የተመረጡ ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎች ለግሉ ዘርፍ በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ ይሰጣል፡፡ ባለሀብቱ ዘመናዊ ፓርኪንግ (ሕንፃ ወይም ስማርት ፓርኪንግ) ገንብቶ፣ ለረዥም ጊዜ (30 እስከ 50 ዓመታት) ያስተዳድራል ከዚያም ለመንግሥት ያስተላልፋል፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በፓርኪንግ ልማት ዘርፍ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት ሊሠሩ የሚችሉበትን ስትራቴጂካዊ ፕላን ለማዘጋጀት የሚያስችል ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስጠና ሲሆን፣ የጥናቱ ውጤት በውይይቱ ወቅት ቀርቧል፡፡
አሁን ባለው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የፓርኪንግ ሕንፃ ግንባታ ብቻውን አዋጪ (አትራፊ) ላይሆን ስለሚችል፣ ተጓዳኝ የንግድ ሥራዎች አብረውት ቢካሄዱ መልካም እንደሚሆን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ የፓርኪንግ ልማት ዘርፍ እንደ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቶት የብድር አቅርቦትና የኢንቨስትመንት ማበረታታቻዎች እንዲደረግለት በጥናቱ ምክረ ሐሳብ ውስጥ ተካቷል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች መንግሥትና የግሉ ዘርፍ እንዴት አብረው መሥራት እንደሚችሉ የሚገልጽ ግልጽ የሆነ መመርያና ደንብ እንዲዘጋጅ፣ ዘርፉ አትራፊ እንዲሆን፣ የማስታወቂያ ቢል ቦርድ፣ ፀጉር ቤት፣ ሲኒማ ቤት፣ የተሽከርካሪ ቀላል ጥገና፣ ጎሚስታና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡
ወንዞች በኮንክሪት ተሸፍነው ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውሉበት ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ በቅርቡ የተመረቀውን ስማርት ፓርኪንግ ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ጠብቆ የማቆየት ብቃት ችግር እንደሚኖር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቱ መዋዕለ ንዋዩን አፍስሶ ዘመናዊ ፓርኪንግ እስከገነባ ድረስ ንብረቱን እስከ መጨረሻው በባለቤትነት ሊያስተዳድር እንደሚገባ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
ከተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፣ ዶ/ር ሰለሞን የፓርኪንግ አገልግሎት ባለሀብቱ በሰፊው እንዲሳተፍ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፣ ባለቤትነቱ ግን በመንግሥት መያዝ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
‹‹የፓርኪንግ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በግል ይዞታ ሥር ከዋሉ የዋጋ ተመን የማውጣት መብትም የባለሀብቱ ስለሚሆን፣ የትራንስፖርት ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ የሚለው ዓላማ ይጠፋል ማለት ነው፡፡ ባለሀብቱ የሚያወጣው ዋጋ ከፍተኛ ሲሆንና ሰፊው ማኅበረሰብ ሊጠቀምበት የማይችል ከሆነ የፓርኪንግ ዕጦትና የትራፊክ መጨናነቅ ችግሮችን አይፈታም፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ባለሀብቱ በመንግሥት የተገነቡ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችን በኮንትራት ወስዶ ማስተዳደር፣ የራሱን ፓርኪንግ ገንብቶ ለረዥም ጊዜ አስተዳድሮ ለመንግሥት የሚያስተላልፍበት አሠራር እንደሚዘረጋ ተገልጿል፡፡
በቀጣይ የፓርኪንግ ልማት ዘርፍ ለባለሀብቱ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራና መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ የሚሠሩበት የፓርኪንግ ልማት ዘርፍ ፖሊሲ ተቀርፆ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ በግሉ ዘርፍ የተነሱት ሐሳቦች በረቂቅ ፖሊሲ ውስጥ በግብዓትነት እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ በክፍያ የሚሠሩ 120 የመንገድ ዳር ፓርኪንጎች በጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በተደራጁ ወጣቶች እንደሚተዳደሩ ታውቋል፡፡