Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምክንያት የማያልቅበት ደካማ አፈጻጸም

የንግድ ሚኒስቴር የዚህን ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት በሚያቀርብበት ወቅት ትኩረቴን በመሳብ እንድከታተለው ከሚገፋፉኝ ጉዳዮች አንዱ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ክንውን የተመለከተው ክፍል ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ለዓመታት ሲቀርቡ ከነበሩት ሪፖርቶች ምንም ለውጥ የማያሳይ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱም ሊሆን ይችላል ትኩረቴን የሳበው፡፡

የዘንድሮው የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ለፓርላማው በቀረበ ቁጥር ‹‹የወጪ ንግድ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት አልተከናወነም፤›› የሚለው አገላለጽ ሳይጠቀስ የቀረበበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ መቼ ይሆን የውጪ ንግድና አደገ፣ ተመነደገ የሚባለው? ይናፍቃል፡፡ የታሰበውን ያህል ማስገኘት አልቻለም ከሚለው ገለጻ በተጓዳኝ፣ ለዘርፉ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን የሚቀርበው ምክንያትም በየዓመቱ አንድ ዓይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዓለም ገበያ መቀዛቀዝ፣ በቂ ምርት አለማምረት፣ የተመረተውም ለገበያ አለመቅረቡ፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መቀነሱ ወዘተ. የሚሉት ምክንያቶች ዛሬም ሳይፎርሹ ቀጥለዋል፡፡ እነዚህን ምክንያቶች ያላካተተ ሪፖርት መቅረብ አቁሟል፡፡

ይህ የሚያሳየው እስከ ዛሬ የነበረውን ክፍተታችን እንደ ትምህርት ወስደን ያለማሻሻላችን ነው፡፡ የተደጋገመ ምክንያት ደግሞ ከአሰልቺነቱ በላይ እውነትነቱ ያጠራጥራል፡፡

ሁለት አሠርት ዓመታት ተመሳሳይ ምክንያት ይዞ መቅረብ ምን ያህል ተዓማኒነት ይኖረዋል፡፡ አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች መንደር ለመቀላቀል ከሚያስችሉ ውጥኖች መካከል አንዱ የወጪ ንግዱ ማደግ ነው፡፡ ይህ ማለትም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት ማብዛት ማለት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አገሪቷ አላት የሚባለውን አቅም በመገንዘብ፣ ተደምሮና ተቀንሶ የተጣለው የወጪ ንግድ የገቢ ዕቅድ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ሆነ ሁለተኛው ጊዜ በወረቀት የተቀመጠውን በተግባር ለማሳካት አልተቻለም፡፡

ከዘርፉ ይገኛል የተባለው ውጤት ለማሳካት በየመድረኩ የተደረጉ ፉካራዎች በፉከራ ቀርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በ2008 ዓ.ም. እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ይገኝበታል የተባለው የውጪ ንግድ ዘርፍ፣ በዚያው ዓመት በ11 ወራት ውስጥ ያሳካው የዕቅዱን 59 በመቶው ብቻ ነው፡፡

ይህ አፈጻጸም እንዳለ ሆኖ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጨረሻ ላይ 14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢወጠንም ከአካሔዱ እንደሚታየው ይህንን ዕቅድ ማሳካት እንደተዓምር የሚቆጠር ከባድ ነገር ነው፡፡ እርግጥ ነው ዘርፉ ብዙ ችግር ያለበት ቢሆንም፣ በምክንያትነት በሪፖርት የሚቀርበው ነገር ሲታይ ግን ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በብርቱ አለመሠራቱን የሚያመላክት ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የተገባው ቃል አለመተግበሩን በደንብ የሚያሳብቅ ሲሆን፣ ችግሩ በዘርፉ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚያስጠይቃቸው ሊሆንም ይገባዋል፡፡ ስለዚህ አሁንም የውጪ ንግድ በምክንያት የተበተበ ሆኖ እንዳይዘልቅ ትርጉም ያለው ዐርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ ከዚህ ዘርፍ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ግማሹን እንኳን ማሳካት ሳይቻል ሲቀር ብዙ ተብሎ ነበር፡፡ በዕቅዱና በክንውኑ መካከል ያለውን ልዩነት ከግምት በማስገባት ለምን አልተሳካልንም የሚለው ነጥብ እየተነሳ ብዙ ምክክር ተደርጎበት ነበር፡፡ ምክንያት ስለመሆናቸው የተጠቀሱ ጉዳዮችም ተለይተው ነበር፡፡ ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በማስወገድ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ማሻሻል ይቻላል ተባለ፡፡ ለለውጥ ብዙ ተስፋ ቢደረግም ውጤት ግን አልታየም፡፡ ከመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን በላይ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም በሁለተኛው የዕቅድ ዘመም የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ዓመታት የተገኘው ገቢ ከመጀመሪያውም የዕቅድ መዘንም ያነሰ ሆነ፡፡

በሰሞኑ የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከሚቀርቡት የተለየብኝ ነገር ቢኖር ስለኮንትሮባንድ የተነገረው ነው፡፡ ኮንትሮባንድ አገር እያጠፋ መሀምጣቱ እውነት ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች እየታየም ነው፡፡ በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አካላም በርካቶች ናቸው፡፡ ለአገር ተቆርቋሪ መሳዮችም በማበርበሩ ውስጥ እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ ሚኒስቴሩም ይህንን አስታውቋል፡፡ የአገራችን ገበያዎች በኮንትሮባንድ በሚገቡ ምርቶች እየተሞሉ በሕጋዊ መንገድ የሚገባው ንግድን እየበረዙ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በየዓመቱ በቁጥጥር ሥር ከሚያውላቸው ባሻገር፣ በሽሽግ መግባታቸውም እየታወቀ እንዳልታዩ የሚታለፉ የኮንትሮባንድ ምርቶች ተዋንያን ላይ የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡

ኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ብቻም ሳይሆን፣ ለወጪ ንግድ የሚቀርቡ ምርቶችንም ይነካካል፡፡ የቀድን ከብቶች ያለ ችግር በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ሲወጡ እየታየ የሚደረገው ቁጥጥር ደካማ መሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ገንዘብ እንድታጣ የሚያደርግ ነው፡፡

ስለዚህ የወጪ ንግድ አፈጻም ማነስም ሆነ የኮንትሮባንድ ንግድ መባባስ ዘርፉን በቅርብ ተከታትሎ መፍትሔ ካለመውሰድ ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳያል፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራውም ቢሆን በተለይ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የላላ መሆኑን ሊያሳይ ይችላልና ‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም፤›› እንደሚባለው የወጪን ንግዱን ደካማ ታሪክ ለመለወጥም ሆነ ኮንትሮባንድን ለመከላከል ወኔ የታጠቀ ሥራ ይሠራ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት