Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጃፓን ኩባንያ 30 የሚደርሱ ኩባንያዎች የሚገቡበትን ልዩ የማምረቻ ዞን ለመገንባት ስምምነት ፈረመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቶሞኒየስ የተባለው የጃፓን ኩባንያ በቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት እየተገነባ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ31 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍና ከ20 እስከ 30 ለሚገመቱ የጃፓን አምራቾች የሚውል ልዩ የማምረቻ ዞን ለመገንባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ኩንባያው ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በ186 ሔክታር መሬት ላይ እየተገነባ በሚገኘው የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገቡ የጃፓን ኩባንያዎችን የሚጠቀሙባቸውን የማምረቻ ሼዶች በራሱ ዲዛይንና በራሱ ወጪ እንደሚገነባ ይፋ አድርጓል፡፡

የቶሞኒየስ ኩባንያ ዳይሬክተር ሒሮሺ ኦትሱቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው እስከ 30 የሚደርሱ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና በተዛማጅ ምርቶች የሚሰማሩ ኩባንያዎች እንደሚመጡ በማሰብ የመግባቢያ ስምምነቱን በመፈረም ግንባታ ለማካሔድ ታቅዷል፡፡ የቶሞኒየስ እህት ኩባንያ የሆነው የካምቦዲያው ፕኖም ፔን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦሌ ለሚ ሁለት የጃፓን ልዩ ዞን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሒሮሺ ኡይማትሱ እንደተናገሩት፣ ኩባንያው የመሬት ሊዝ ስምምነቶችን ከመንግሥት ጋር ከተፈራረመና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ካጠናቀቀ በኋላ በመጪው ዓመት ወደ ግንባታ የመግባት ዕቅድ ይዟል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሒደት እንዲሁም እየተስፋፋ የመጣውን የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ከካምቦዲያና ከታይላንድ ጋር በማነፃፀር ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ ከዛሬ አሥር ዓመታት በፊት ካምቦዲያ ውስጥ ይታይ የነበረው ዓይነት ነው ያሉት ኡይማትሱ፣ ከ30 ዓመታት በፊትም ታይላድ በተመሳሳይ የለውጥ ሒደት ውስጥ ለማለፍ ዛሬ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ዓይነት እንቅስቃሴ ስታደርግ መቆየቷን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምቹ ካሏቸው ነገሮች መካከል የሕዝብ ብዛቱ አንደኛው ጥሩ አጋጣሚ ሲሆን ይህም ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያን በመፍጠር አገሪቱን ለአምራቾች ተመራጭ እንድትሆን ያደርጋታል ማለታቸው አንዱ ሲሆን፣ በቀላሉ መሠልጠን የሚችሉና ለፋብሪካ ሥራ ቀልጣፋ የሆኑ በርካታ ወጣቶች የሚገኙባት አገር መሆኗ፣ ለሠራተኞች የሚከፈለው ዝቅተኛ የክፍያ መጠን፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠየቀው ዝቅተኛ የአገልግሎት ታሪፍ ከተጠቀሱት አገሮችም ይልቅ ኢትዮጵያን ተመራጭ እንደሚያደርጋት ይናገራሉ፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ የሚታየው የሕግ አተገባበር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የአገልግሎት መቆራረጥ በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፣ ወዘተ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውጭ ኢንቨስተሮች ሲነሱ ከሚደመጡ የቢሮክራሲ ችግሮች መደብ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ቪዛና የሥራ ፈቃድ በቀላሉ የማግኘት ጉዳይ በርካቶችን ሲያሳስባቸው እንደመቆየቱ መጠን መንግሥት እልባት ማበጀቱን ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመዘርጋት ሁሉም መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቶቻቸውን ለአምራቾች እንዲያቀርቡ በመደረጉ የተንዛዛ አሠራር ችግር እንደማይፈጠር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ አስታውቀዋል፡፡

የጃፓን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በርካታ ድርድሮች ሲካሔዱ መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ ፍፁም፣ በአሁኑ ወቅት የቶሞኒየስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቅ እመርታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ እንደ ጃፓን ያሉ በአደጉ አገሮችን ለማስተናገድ ገና ብዙ ይቀረዋል ብለው ያምናሉ ያሉት አቶ ፍፁም ይህ አመለካከታቸው እየተቀየረ በመምጣቱ ቁጥራቸው እየተበራከቱ የሚመጡ ኢንቨስተሮች እንደሚጠበቁም ጠቅሰዋል፡፡

በአቶ ፍፁም አነጋገር የሚስማሙት ኡይማትሱ፣ አሁንም ድረስ ጃፓናውያን ለአፍሪካ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ በርካቶች አፍሪካን የሚያዩበት ዓይን በዱር እንስሳት የተሞላ፣ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉት ሥፍራ እንደሆነና በድርቅና በረሃብ ቸነፈሮች ዘወትር የሚጠቃ አኅጉር እንደሆነ ማሰባቸው ዛሬም ድረስ ያልተቀረፈ እንደሆነ በመጥቀስ እንዲህ ያለው አመለካከት ቀስ በቀስ እየተለወጠ ሲመጣ የጃፓን ኩባንያዎች በብዛት ሊመጡ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በሌላ በኩል በጃፓን መንግሥት በሚደረግ የቴክኒክ ድጋፍ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክር መድረክ ሲካሔድ ቆይቷል፡፡ በዚህ መድረክ የሚነሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች አወጣጥና አተገባበር፣ በተግባር ሒደት የታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦችም እየተነሱ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምክረ ሐሳቦች ሲቀርቡበት የቆየ መድረክ ነው፡፡

በዚህ መድረክ የሚሳተፉ የጃፓን ምሁራን አሁንም በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ያብራራሉ፡፡ መንግሥት በቅርቡ ኢንተርኔት መዝጋቱ፣ ሕጎችን በየጊዜው መለዋወጡ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁና ማራዘሙ፣ የፖለቲካ ቀውስ መከሰቱ ለአገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት በተለይም እንደ ጃፓን ካሉ አገሮች ለሚመጣ ኢንቨስትመንት ጥቁር ጥላ እንደሚያጠላበት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምሁራን ገልጸዋል፡፡ 

ይህም ሆኖ ከስምምነቱ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁትን እነ ሚትሱቢሺ፣ ቶሺባ ኮርፖሬሽን፣ ማሩቤኒ የተባሉትን ጨምሮ 20 የጃፓን ኩባንያዎችን የወከሉ የንግድ ልዑካን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡

በአንፃሩ ሰሞኑን በተከታታይ ይፋ የተደረጉ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርቶች አገሪቱን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሰላል ላይ ተንጠላጥለው ከሚገኙ አገሮች ተርታ በቁንጮነት ከማስቀመጥ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ካስመዘገቡ አምስት ዋና ዋና አገሮች አንዷ መሆኗን፣ ከቬትናም በመቀጠልም በዓለም ሁለተኛዋ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚገኙባት አገር ለመሆን እንደበቃችም በሪፖርቶቻቸው አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች