ሰዒድ ኑሩ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች
ማኅበር የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ
የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድ ሰኔ 8 ቀን 1999 ዓ.ም. የአገሪቱን የ2000 ዓ.ም. በጀት በሚሊኒየም ክብረ በዓል ዋዜማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ነበር፡፡ አቶ ሱፊያን ባቀረቡት የበጀት ሰነድ 43.9 ቢሊዮን ብር እንዲፀድቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ወቅት በጀቱ ግዙፍ ነው ተብሎ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ በጀት ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ጉድለት ነበረው፡፡ ከአሥር ዓመታት ቆይታ በኋላ የወቅቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የ2010 ዓ.ም. በጀት፣ ክብረ ወሰን የሰበረ የበጀት ረቂቅ አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሰነድ እንደተመለከተው፣ ለቀጣዩ በጀት ዓመት 320.8 ቢሊዮን ብር እንዲፈቀድ የጠየቁ ሲሆን፣ ይህ ግዙፍ በጀት የ53.9 ቢሊዮን ብር ጉድለት አሳይቷል፡፡ የበጀቱን ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው ለክልሎች በድጎማ የሚሰጠው በጀት፣ የካፒታል በጀት፣ የመደበኛ በጀትና የድህነት ቅነሳ በጀት ነው፡፡ በወቅታዊው የበጀት ቀመር ጉዳይ ውድነህ ዘነበ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ሰዒድ ኑሩን (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የዛሬ አሥር ዓመት በኢትዮጵያ ሚሊንየም ክብረ በዓል ዋዜማ የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 43.9 ቢሊዮን ብር በጀት እንዲያፀድቅላቸው ሲያቀርቡ፣ በጀቱ እጅግ ከፍተኛ ነው ተብሎ ነበር፡፡ ከአሥር ዓመት በኋላ የአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) 320.8 ቢሊዮን ብር ሲያቀርቡ በድጋሚ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው ተብሎ ነበር፡፡ በሁለቱ በጀቶች መካከል ያለው የመግዛት አቅም ምን ይመስላል? አንድነትና ልዩነታቸውስ?
ዶ/ር ሰዒድ፡- ሁለት ነገሮችን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ የመጀመሪያው ኢኮኖሚው በምን ያህል ፍጥነት እያደገ ነው የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው የዋጋ ግሽበቱ ነው፡፡ የምትመድበው በጀት የመግዛት አቅሙ ምን ያህል ነው? ምን ያህል የማስፈጸም አቅም አለው? አንደኛው ኢኮኖሚው በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በ10 እና በ11 በመቶ እያደገ ነው፡፡ በዚያው ልክ የሚሰበሰበው የታክስ ገቢ ይጨምራል፡፡ አሥር ዓመት ቀላል አይደለም፡፡ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ሁኔታ ትልቁ ምክንያት የዛሬ አሥር ዓመት ምናልባት በአሥር ብር እንገዛቸው የነበሩ ዕቃዎች ዛሬ አንድ መቶ ብር ገብተዋል፡፡ ምናልባት ወደ አሥር እጥፍ ማለት ነው ዕድገቱ፡፡ በተለይ በዚያን ጊዜ አካባቢ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ነበር፡፡ ትልቅ መሟሟቅ ነበር፡፡ በአብዛኛው መንግሥት የሚመራው የመሠረተ ልማት ግንባታ ነበር፡፡ ምንም መሠረተ ልማት ለሌላት አገር ኮብልስቶን፣ ኮንስትራክሽን፣ የመንገድ ሥራ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ፣ የቤቶች ልማት በሙሉ ትልልቅ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ ይህን ስታደርግ ወጪ ይጨምራል፡፡ እነዚህ ግንባታዎች ለምርት ያላቸው አስተዋጽኦ ዘግይቶ ነው የሚታየው፡፡ እንደምታስታውሰው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ነበር፡፡ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ዋጋ በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡ ካሰላነው በጊዜ ዋጋ መሆን አለበት፡፡
የዛሬውን በጀት በሚሊኒየም ከነበረው ዋጋ ጋር ብታሰላው ትልቅ አይደልም፡፡ የሚሊኒየሙ በጀት 43,947,669,337 ብር ነበር፡፡ የአሁኑ በጀት 320.8 ቢሊዮን ብር ነወ፡፡ አሁን የተያዘው 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት በ2000 ዓ.ም. በነበረው ዋጋ 110 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው በዋጋ ንረት የመጣ ነው፡፡ በአማካይ ዋጋ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ በዚያ ወቅት በመቶ ብር ትገዛ የነበረው ዕቃ አሁን ሦስት መቶ ብር ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ከመፈጸም አንፃር፣ ሥራ ከመሥራት አንፃር የምታየው የገበያ ዋጋን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ መነሻችን ይኼ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. በሚሊኒየም ወቅት 43.9 ቢሊዮን ብር በጀት ሲቀርብ ጉድ ተብሏል፡፡ አሁን 320.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል አሁን ይኼም ትልቅ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በ650 በመቶ ዕድገት አለው፣ ነገር ግን በትክክለኛ ዋጋ ብታሰላው 155 በመቶ ብቻ ነው ሥራ የመፈጸም አቅሙ፡፡ ሌላው የተቀረው የዋጋ ንረት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዘንድሮው በጀት ከ2009 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ምን ገጽታ አለው?
ዶ/ር ሰዒድ፡- የ2010 ዓ.ም. በጀት ከ2009 ዓ.ም. በጀት ጋር ሲነፃፀር 17 በመቶ ያህል ዕድገት አሳይቷል፡፡ የ2009 በጀት ከ2008 በጀት ጋር ሲነፃፀር ዕድገቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ ስምንት በመቶ ቢሆን፣ እስከ ዛሬም ስምንት በመቶ ስለነበር የተጣራ የስምንት በመቶ ዕድገት ይኖራል፡፡ በሁለት ከፍለን እንየው፡፡ ባለፈው ዓመት ተጨማሪ በጀት ነበር፡፡ መሀል ላይ ተጨምሯል፡፡ አሁን የምናወዳድረው በጀትን ከበጀት ጋር ነው፡፡ በጊዜው ዋጋ የይስሙላ ዋጋ (ኖሚናል) 17 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ የዋጋ ጭማሪም ስለሚኖር በጀቱ በመፈጸም አቅሙ የዋጋ ንረት ይደግማል ብለን ብናስብና ስምንት በመቶ ይሆናል ብንል፣ ዕድገቱ ስምንት በመቶ ይሆናል፡፡ መንግሥት ያቀዳቸውን ዕቅዶች ከማስፈጸም አንፃር ዕድገት አለ፡፡ ገንዘቡ ዕድገት አለው፡፡ ከመፈጸም አቅም አንፃር በስምንት በመቶ አድጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ለ2010 ዓ.ም. የቀረበው በጀት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የበጀት ጉድለት አለበት፡፡ ይህንን የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ የውጭ ብድርና ዕርዳታ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ በመምጣቱ ከዋጋ ንረት አንፃር ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እንዴት ይታያል?
ዶ/ር ሰዒድ፡- የበጀት ጉድለቱ 53.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህን ስናወዳድር ሁለት ነገሮችን ማየት ይኖርብናል፡፡ አንደኛ ጉድለቱ በ2010 ዓ.ም. በሚኖረው ዋጋ ብታስበው የስምንት በመቶ ወይም የአሥር በመቶ የዋጋ ልዩነት ስለሚኖር ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ ሁለተኛው ማየት ያለብን ከኢኮኖሚው አንፃር ሲታይ ይህ የዋጋ ጉድለት ምን ያህል ነው? ይህንን የበጀት ጉድለት የሚሸከም የኢኮኖሚ ዕድገት አለን ወይ? ባለፈው ዓመት በበጀት ተይዞ የነበረው የበጀት ክፍተት ወይም ጉድለት በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በዕቅድ ተይዞ የነበረው ሁለት በመቶ ነው፡፡ ይኼ ዕቅድ ተተግብሯል ወይ የሚለውን የምናየው ይሆናል፡፡ በ2006 ዓ.ም. የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 1.8 በመቶ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ 2.9 በመቶ ነበር፡፡ አሁን ያለው የበጀት ጉድለት የፈለገውን ያህል ትልቅ ይምሰል እንጂ ከጂዲፒው ጋር ማየት ያስፈልጋል፡፡ መለኪያችን እሱ ነው፡፡
በ2010 ዓ.ም. በጀት ላይ በጊዜው ዋጋ 19 በመቶ ሊያድግ ይችላል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተቀመጠው ጂዲፒ 11 በመቶ ያድጋል ቢባል፣ እዚህ ላይ የዋጋ ንረቱን ስምንት በመቶ ስትደምርበት 19 በመቶ የጂዲፒ ዕድገት ይኖራል፡፡ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ ሲሰላ በ19 በመቶ ዕድገት ይኖራል፡፡ እንደዚህ ከሆነ የአሪቱ ኢኮኖሚ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን 53.9 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ስታሰላው 3.5 በመቶ ያህል ነው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተያዘው አንፃር ሲትይ ትንሽ ሞቅ ብሏል፡፡ የ0.5 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ይኼ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ኢኮኖሚው ከዚህም በላይ ሊያድግ ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ጉድለቱን የምንሸፍንበት መንገድ ነው፡፡ በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን ስንችል ትልቅ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ክፍተቱን በሁለት ከፍለን እንየው፡፡ አንዱ በዋጋ ንረት ሁለተኛው አጠቃላይ ያሰብናቸውን ዕቅዶች ከማሳካት አንፃር እንየው፡፡ እንግዲህ ክፍተቱን ለመሙላት ገንዘብ ማተም ሊሆን ይችላል፡፡ ቦንድ መሸጥ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህ በምንሸፍንበት ጊዜ ከዋጋ ንረት በተጨማሪ ሌላ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡
የዋጋ ንረትን ለመቋቋም አንድ መውጪያ አለን፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማ ከሆነ ንረቱን የማረጋጋት ድርሻው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ከባድ የሚሆነው ግን ጂቲፒ የሚያስበው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በተለይም ወደ ማኑፋክቸሪንግ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋል፡፡ ግብርና በተፈጥሮው ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን አይፈልግም፣ ቢበዛ ማዳበሪያ ይፈልጋል፣ ግብርና ያለማዳበሪያ ሊሠራም ይችላል፡፡ ምን ማለት ነው? ግብርና ብዙ ካፒታል ሳይሆን ብዙ ሠራተኛ የሚፈልግ ነው፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለመግባት ሲታሰብ ግን ለሚኖሩት ግብዓቶች ካፒታልና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋሉ፡፡ ጥሬ ዕቃ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ስለሌሉን ከውጭ ነው የምናስገባው፡፡ ጥሬ ዕቃ ከማስመጣት ገና አልተላቀቅንም፡፡ ቆርቆሮ እንኳ ለማምረት የምንጨምረው እሴት ቆርቆሮ ማጠፍ በሆነበት መሠረታዊ ግብዓቱን ከውጭ ማስገባት ይጠይቃል፡፡ ጥጥ እንኳ ከውጭ እናስገባለን፡፡ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ እየተረባረብን ባለንበት ወቅት ጥጥ ከውጭ ይገባል፡፡ የጥጥ ምርት ስለሌለ ማለት ነው፡፡ ቢኖርም ዘለቄታዊ አይደለም ይቆራረጣል፡፡ ሁሉንም በአገር ውስጥ ማምረት እስክንጀምር ከውጭ ማስገባታችንን እንቀጥላለን፡፡ ከውጭ የምናስገባው ደግሞ በብር አይደለም፣ በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ በሚሆንበት ጊዜ የቱንም ያህል ገቢ በአገር ውስጥ ብታሰባስብም እነዚህን ግብዓቶች በብር ልታስገባ አትችልም፣ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ የሚገኙባቸው የታወቁ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ከኤክስፖርት፣ ከውጭ በዕርዳታና በብድር፣ በውጭ የሚኖሩ ሰዎች የሚልኩት ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በእጃችን ላይ ያለው ኤክስፖርት ነው፡፡ ኤክስፖርት ደግሞ ያለው አፈጻጸም ደካማ ነው፡፡ የውጭ ዕርዳታ እየቀነሰ ነው፡፡ ለምግብ ዕርዳታ እንኳ እየቀነሰ ነው፡፡ ብድር አስቸጋሪ ነው፡፡ የውጭ ብድር የሚመሠረተው በኤክስፖርት አፈጻጸም ጥንካሬ ነው፡፡ የአበዳሪዎች ዋነኛው ጥያቄ መክፈል ይችላሉ ወይ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የበጀት ጉድለት ባይኖር እንኳ በጀቱ በአገር ውስጥ ቢሸፈን እንኳ፣ ይኼን 320.8 ቢሊዮን ብር እዚሁ ብንሸፍን በብር አሁን ባለንበት ሁኔታ ትራንስፎርሜሽኑ ያቀደቸውን ከማሳካት አንፃር የውጭ ምንዛሪ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ ትርጉም ባለውና ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ ጎላ ባለ ደረጃ በውጭ ምንዛሪ መገኘት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በ2010 በጀት ዓመት ከአገር ውስጥ 221 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ይሰበሰባል የተባለው ሁሉ ካለመሰብሰቡ አንፃር የሚሰካ ይመስልዎታል?
ዶ/ር ሰዒድ፡- ማሳካት ይቻላል፡፡ ምናልባት ካለፈው ዓመት ዕቅድ ጋር ሲወዳደር ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ዕቅዱን ማሳካት ይቻላል፡፡ በ2009 ዓ.ም. መንግሥት በአብዛኛው በሌሎች ሥራዎች በተለይም በፖለቲካ ተጠምዶ ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች መንግሥት ሠራም አልሠራም የሰዎች አስተሳሰብ ለወጥ ይላል፡፡ አንዳንዴም ማባበል ይኖራል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ሥራዎች መወጠር ሲኖር ያልታዩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ገና አልተነካም፡፡ ወደፊት እንደ ኢኮኖሚው ይወሰናል፡፡ ጥያቄው እንዲያውም ኢኮኖሚው ያመነጫል ሳይሆን፣ መሰብሰብ ያለበት ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም ነው ቁም ነገሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 45 ቢሊዮን ብር ያህል ከውጭ በሚገኝ ገንዘብ ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ አገሪቱ ብዙ ብድር ያለበት እንደመሆኑ ተፅዕኖ አይፈጥርም?
ዶ/ር ሰዒድ፡- አንፃራዊ ነው፡፡ አሁን ባለው ብድር ላይ ባናበዛ ጥሩ ነው፡፡ አሁን ያለውን የኤክስፖርት አፈጻጸም ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለውን የዕርዳታና የብድር አሰጣጥ አዝማሚያ ብዙም ተስፋ ባናደርግበት መልካም ነው፡፡ አንድ ነገር ግን ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው፣ ለኤክስፖርት ነው፡፡ ኤክስፖርቱ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በዋጋ ቀንሷል? አዎ ቀንሷል፡፡ ዓለም አቀፍ አንድምታ አለው፡፡ ይህን የምናካክሰው በምንድነው? የምንልከውን ምርት መጠን በመጨመር ነው፡፡ ጥራቱን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ለኤክስፖርት ታስበው የነበሩ ፕሮጀክቶችን የሞት ሽረት ትግል አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሌላኛው ሬሚታንስ ነው፡፡ በይፋ የገባ ሬሚታንስ ይፋ ባልሆነ መንገድ ይወጣል፡፡ እዚህ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ዋናው ከውጭ የምናስገባውን እዚህ ማምረት መቻል ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በሰፊው ያሻሽላሉ የተባሉ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች ይጠናቀቃሉ ከተባለበት ጊዜ እጅግ የዘገዩ አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ስኳርና ከስኳር ተረፈ ምርት ይገኛል የተባለው ኢታኖል፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ በወቅቱ መድረስ ባለመቻላቸው ኢኮኖሚውን መደገፍ አልቻሉምና ተፅዕኖው እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ሰዒድ፡- እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ትልቅ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ፡፡ አርበኛ መሆን ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዳቸው የሚያማልሉ ዕቅዶች አገርን የሚያሳድጉ፣ ከልመና የመውጣት ልዕልና የማጎናፀፍ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱን አላውቅም የሙስናውን ነገርና ሌላ ሌላውን ተወውና አንደኛ ስናቅድ ለዕድገት ከመጓጓታችን የተነሳ በአገር ውስጥ አቅም መሥራት ፈልገን ይሆናል፡፡ አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡ ግብርና የእኛ ባህል ነው፡፡ እንጀራ መጋገርና ወጥ መሥራት እንችላለን፡፡ ከቴክኖሎጂና ከብረት ጋር መታገል የእኛ ባህል አይደለም፡፡ በአንድ ሌሊት ሊመጣ አይችልም፡፡ ጥርስህን ልትነቅልበት ይገባል፡፡ እኛ ምንም በማናውቀው ነገር ሌሎች ባህል ባደረጉት ሥራ ላይ ስንገባ አርበኝነት አንግበን ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመማር ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ቴክኖሎጂውን እስክንማር ድረስ ጊዜው ስለማይጠብቀን ኮንትራት ሰጥተን ልናሠራ ይገባል፡፡ ይኼ ሲሆን ከፕሮጀክቱ እዚህና እዚያ የሚቆነጠር ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ስህተት የሠራን ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ቢሆንም የዚያኑ ያህል የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት አውታሮች እየተዋጡ ነው የሚል ሐሳብ ይደመጣል፡፡ ከዚህ አንፃር የሕዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚው ጋር ያለው አንድምታ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ሰዒድ፡- ሕዝብን ምንም አታደርገውም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ መሠረቱም ሰፊ ነው፡፡ ምንም አታደርገውም፡፡ ምንም ከማታደርጋቸው ነገሮች አንዱ የሕዝብ ቁጥር ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው የምታቅደው ዕድገት ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥራችን ለእኔ መባረክ ነው፡፡ ጥሩ ጎኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ ጎኑ ችግር አለው፡፡ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለደካማ አገር ችግር ነው፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዛ የምንለው አቅማችን ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡ ሰፊ አገርና ሰፊ ሀብት ይዘን የሕዝብ ቁጥራችን ጥንካሬ ሊሆነን ይገባል፡፡