Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የዲጄ ሙያ እንዲያድግ በትምህርት መታገዝ አለበት››

‹‹የዲጄ ሙያ እንዲያድግ በትምህርት መታገዝ አለበት››

ቀን:

አሮን ከበደ፣ የኢትዮጵያ ዲጄዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

      የኢትዮጵያ ዲጄዎች ማኅበር ባለሙያዎችን ይዞ መሥራት የጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ፍቃድ አግኝቶ በይፋ ሥራ የጀመረው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ማኅበሩ ሙያተኞቹ በትምህርት የተደገፈ ሥራ እንዲያከናውኑ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በሙዚቃው ዘርፍ የሚጫወቱትን ሚና ከማሳደግ አኳያም ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የማድረግ ዓላማ አንግቧል፡፡ 2,000 አባላት ያሉት ማኅበሩ፣ ይፋዊ ፈቃድ ካገኘ በኋላ በዘርፉ ስለሚኖረው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ዲጄዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዲጄ አሮን ከበደን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ፍቃድ አግኝቶ በይፋ ሥራ ከመጀመሩ በፊት እንቅስቃሴ ታደርጉ ነበር፡፡ ፍቃድ ማግኘታችሁ እንቅስቃሴያችሁን ተቀባይ ከማድረግና በዘርፉ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠር አንፃር ምን ለውጥ ያመጣል?

አሮን፡- ብዙ ጥቅም አለው፡፡ በግል ሆነንና በማኅበር ሆነን እያንዳንዱን በር ስናንኳኳ የምናገኘው ምላሽ ይለያያል፡፡ ማኅበሩ ፍቃድ እስኪያገኝ ሦስት ዓመት ወስዶብናል፡፡ እዚህ አገር ሙያውን የያዝነው በልምድ እንጂ በትምህርት አይደለም፡፡ ፍቃዱን የተከለከልነውም ለዚህ ነበር፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር ተጠይቆ ፈቃዱ በብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጠን ተደረገ፡፡ ሙዚቀኞች፣ ዲጄዎች  ዘፈናችንን ሳይከፍሉ ያጫውታሉ፣ ወንጀለኛ ናቸው ብለውን ነበር፡፡ እንደ ማኅበር ሆነን ምላሽ ብንሰጥም ፍቃዱን አለማግኘታችን ክፍተት ፈጥሮ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ ዲጄዎች በልምድ ብቻ እንደመሥራታቸው፣ ዲጄነት በትምህርት የታገዘ እንዲሆን ማኅበሩ ምን እያደረገ ነው?      

አሮን፡- ትምህርት ቤት ለማቋቋም ፍቃደኛ የሆነ ባለሀብት ትምህርት ቤት እንዲከፍትና ሥርዓተ ትምህርት እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ አንድ ዲጄ ችሎታውን አሳድጎ ሳውንድ ኢንጂነር ወይም ፕሮዲውሰር ሊሆን ይችላል፡፡ ሙያው እንዲያድግ ግን በትምህርት መታገዝ አለበት፡፡ ሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት ደረጃም ያስፈልገዋል፡፡ እኛ ያዘጋጀነው ሰነድ አለ፡፡ ባህልና ቱሪዝምም ከኛ ባለሙያ ወስዶ የሚያዘጋጀው ሰነድ አለ፡፡ ቲጂ ራስታ የሚባል ፈረንሣይ ተምሮ፣ ሰርተፍኬት አግኝቶ፣ ትምህር ቤት ለመክፈት አስፈላጊ መሣሪያዎችን ያሟላ ባለሙያ አለ፡፡ ትምህርት ቤቱ እንዳይከፈት የተጓተተው በሥርዓተ ትምህርት አለመኖር ምክንያት ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ዲጄ ፒንክና ሌሎችም ከውጪ ተምረው ከመጡ ዲጄዎች ጋር እንተጋገዛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት የሙያተኞችን መብት በማስጠበቅ ረገድ የሠራቸውን ብትገልጽልን?

አሮን፡- የዛሬ አሥር ዓመት የወጣው ሕግ የአንድን ድምፃዊ አልበም ገዝቶ ማዳመጥ እንጂ ሕዝብ በተሰበሰበበት ማጫወት አይቻልም ይላል፡፡ ለማጫወት የከዋኙ ፍቃድ መገኘት አለበት፡፡ ሕጉ ክፍተት ስላለው ዲጄዎች ሙዚቃ ማጫወት አይችሉም የሚል ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበሩት አመራሮች ጋር በጉዳዩ ዘሪያ ተነጋግረናል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እስከ 200 ሲዲ፣ ቢሮ፣ ስፒከርና ሚክሰር ያለው ሰው መስፈርት ስለሚያሟላ ሙዚቃ እንዲያጫውት ፍቃድ እንዲሰጠው በተስማማንበት ወቅት ነው ይህ የተነሳው፡፡ መስፈርቱን ለማሟላት ግን አብዛኛው ዲጄ አቅም የለውም፡፡ ዲጄው ሠርግ ብቻ የሚሠራ ከሆነ ይህን ማሟላት ስለማይችል ወደ ሕጋዊነት መምጣት አይችልም ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ስናነጋግራቸው የራሳችንን መስፈርት አውጥተን እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል፡፡ የሮያሊቲ ክፍያ ሲፀድቅም ፓርላማ ሄደን አስተያየታችንን ሰጥተናል፡፡ በርካቶች ማኅበራችን እንዳለ ስለሚያወቁ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበርን ጨምሮ ብዙዎች እንደ ማኅበር ያነጋግሩናል፡፡ ዓውደ ጥናቶች አዘጋጅተን ነበር፡፡ እንደ ዴቪዶ ካሉ ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርገናል፡፡ ከውጪ የመጡ ዲጄዎችም ሥልጠና ሰጥተውናል፡፡ የክለብ ባለቤቶች ከዲጄዎች ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች አሉ፡፡ የክለብ ባለቤቶች ዲጄዎቹ አይታዘዙንም ይላሉ፡፡ ባለቤቱ ሙያውን ሳያከብር ዲጄዎቹን ለማዘዝ ይፈልጋል፡፡ ሙዚቃ ማጫወት ለሙያተኛው መተው አለበት፡፡ ዲጄው የክለቡን ስሜት እያየ ሙዚቃ ያጫውታል እንጂ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ለማስደስት አይሠራም፡፡ አንዳንድ የክለብ ባለቤቶች ዲጄዎችን ሦስት ቀን አሠርተው ሊያባርሯቸው ይችላሉ፡፡ የሙከራ ጊዜ አለመሰጠቱ ልክ ካለመሆኑ በላይ የባለሙያውን ሞራል ይነካል፡፡ ዲጄው የሚከፈለውም አነስተኛ ገንዘብ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች እንደ ማኅበር እንፈታለን፡፡

ሪፖርተር፡- በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት በተቀመጡት መስፈርቶች የአንድን ዲጄ ሙያዊ ብቃት በዕውን መመዘን ይቻላል?

አሮን፡- መስፈርቱ ሲወጣ የራሳቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡ ዲጄዎቹ ወደ ሕጋዊ አሠራር መምጣት ስላለባቸው የተቀመጠ መስፈርት ነው፡፡ በመስፈርቱ መሠረት ገንዘብ ያለው ሁሉ ተነስቶ 200 ሲዲ ገዝቶ፣ ቢሮ ተከራይቶና ስፒከር ገዝቶ ዲጄ ነኝ ሊል ይችላል፡፡ ይኼ ግን በሙያው ሕግ ዲጄ አያደርገውም፡፡ አንድ ዲጄ የኮምፒውተር ዕውቀቱና ምን ያህል ክለብ ውስጥ እንደሠራ መፈተሽ አለበት፡፡ ዲጄ ማለት የሙዚቃ ላይብረሪ ስለሆነ የሙዚቃ ዕውቀቱ መታየት አለበት፡፡ ሬጌ፣ ኦልድ ስኩል፣ ፈንክና ብዙ የሙዚቃ ስልቶች አሉና እነዚህን ማወቅ አለበት፡፡ የ70 ዓመት አዛውንትና በሃያዎቹ ዕድሜ ክልል ያለውንም ማስደስት መቻል አለበት፡፡ እውነተኛ ዲጄ ማለት እንደዚህ ዓይነቱ ነው፡፡ ሙያው ገንዘብ ስለሚያስገኝ ብቻ ያለዕውቀት የገቡ ሰዎች አሉ፡፡ በልምድም ቢሆን አገሪቱ ውስጥ ያሉት ዲጄዎች ጥሩ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ዲጄ ከሚያጫውተው ሙዚቃ ጋር የመስተካከል ነገር አለ፡፡ ዲጄነት አሁን ሳይንስ ሆኗል፡፡ ዓለም ላይ ዲጄዎች በአንድ ሰዓት ውስጥ በተወሰኑ ሰከንዶች ሙዚቃ እየቀያየሩ በማጫወት ተዓምር ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ከልምድ ይልቅ በትምህርት መታገዝ ወሳኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ዲጄዎች ባሻገር በሌሎች ከተሞች ያሉ ዲጄዎችንም ያማከለ ነው?

አሮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 5,000 የሚሆኑ ዲጄዎች አሉ፡፡ በክልል ከተሞችም ዲጄዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ትግራይ፣ መቐለ ብቻ ከመቶ በላይ ዲጄዎች አሉ፡፡ በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል ዲጄዎች ጋር ዱከም ላይ ስብሰባ ይኖረናል፡፡ ሁሉም ዲጄዎች ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ የተወሰኑ ዲጄዎች የብቃት ማረጋገጫ አውጥተው በጎን በኩል ምንም ማስረጃ የሌላቸውም እየሠሩ ነው የሚል እሮሮ ይሰማል፡፡ ለዚህ መፍትሔ የሚሆነው ሁሉንም ዲጄ ወደ አንድ መድረክ ማምጣት ነው፡፡ ‹‹ሠርግዎን በዲጄ›› አዲስ አበባ ተጀምሮ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይና ሌሎችም አካባቢዎች ተለምዷል፡፡ በአንድ ወቅት የሠርግ ዲጄዎች ሕገወጥ ስለሆኑ ማቆም አለባቸው ተብሎ በአዕምራዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ዕርምጃ ሊወሰድ ሲል አዲስ አበባ ያሉ ዲጄዎች አስቁመዋል፡፡ አዲስ አበባ ያሉት ዲጄዎች ከሌሎች ከተሞች ዲጄዎች ጋር ተሳስረው ያመጡት ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሌሎች አገሮች ዲጄዎች በሙዚቃው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በፌስቲቫሎችና በኮንሰርቶች እንዲሁም በኅብረተሰቡና በሙዚቀኞች ዘንድ ዲጄዎች ያላቸው ቦታ አነስተኛ መሆኑ በሙያው ያሳደረውን ተዕፅኖ ብትገልጽልን?

አሮን፡- የማኅበረሰቡ አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑ እንዳለ ሆኖ እኛም ግንዛቤው እንዲፈጠር አልሠራንም፡፡ ዲጄነት ሲዲ እየቀያየሩ ሙዚቃ መክፈት አይደል እንዴ? የሚል አለ፡፡ ከወጣት ሙዚቀኞች ጋር ጥሩ ግንኙነት ቢኖረንም ከቀሩት ጋር እንደ ባላንጣ እንተያያለን፡፡ ኮንሰርት ሲዘጋጅ የዲጄው ስም ሳይጻፍ ዲጄ ብቻ ይባላል፡፡ ዲጄ የሚገባው ባንድ እንዲያርፍ እንጂ የመዝናኛው አካል እንደሆነ አይወሰድም፡፡ ይህንን ማስተካከል የምንችለው እኛው ዲጄዎች ነን፡፡ ቀስ በቀስ የግንዛቤ ለውጥ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ሠርግ በዲጄ የተለመደውም ግንዛቤው ስለተፈጠረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ማዕቀፉስ ሥራችሁን ይደግፋል?

አሮን፡- እኛን የሚደግፍ ሕግ የለም፡፡ ሪሚክስ ስናደርግ ዘፈኑን አበላሻችሁ እንባላለን እንጂ አካፔላ የሚሰጠን፣ ሪሚክስ አድርጉልኝ የሚለን ዘፋኝ የለም፡፡ ሌላ አገር ለምሳሌ በሬጌ ሙዚቃ ለዲጄው ሪድም ይሰጠዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉት ዲጄዎች ናቸው፡፡ እዚህም ዲጄዎች እንደ አንድ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካል መታየት አለባቸው፡፡ ዲጄዎች አሁን 70 በመቶ የውጪ 30 በመቶ የአገር ውስጥ ሙዚቃ ክለብ ውስጥ ያጫውታሉ፡፡ 30 በመቶ የውጪ አድርጎ የአገር ውስጥ ሙዚቃ እንዲጎላ ማድረግ ይችላል፡፡ በኮምፒውተር ሳይንስ ጎበዝ የሆኑ አሪፍ ሪሚክስ መሥራት የሚችሉ ብዙ ዲጄዎች ቢኖሩም ሕጉ ላይ ክፍተት ስላለ በፍራቻ እየሠሩ አይደለም፡፡ ከዋኙ መፍቀድ አለበት የሚለው ሕግ ለኛ ሥራ አመቺ አይደለም፡፡ በግብዓት በኩልም ዲጄዎች ዕቃ ሲያስገቡ እጥፍ ይቀረጣሉ፡፡ ዲጄዎች ዘመናዊ መሣሪያ በትንሽ ዋጋ የመግዛት አቅም ቢኖራቸውም አገር ውስጥ ለማስገባት ቀረጡ ስለሚከብዳቸው እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም አይችሉም፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች ደግሞ በሙዚቃ ኮንሰርትና ሌሎችም መርሐ ግብሮች ሲሠሩ ትልቅ ልዩነት የሚያመጡ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቀኞች ዲጄዎች ሙዚቃ የሚያጫውቱት ያለፈቃድ መሆኑን ሲወነጅሉ የእናንተ ምላሽ ምንድነው?

አሮን፡- ችግሩ የተፈጠረው ሕጉ ክፍተት ስላለው እንጂ ሕገወጥ ዲጄ የለም፡፡ አንዳንድ ዘፋኝ አልበም ሲያወጣ ወደ እኛ ይዞት ይመጣል፡፡ ከዓመታት በፊት ስለ ዲጄዎች ሚና ግንዛቤ ቢፈጠር ኖሮ ሕጋዊ እንባል ነበር፡፡ ስለዚህ ዘፋኙ አልበሙን ሲሰጠን ካስፈለገ አስፈርመነው ሙዚቃውን እናጫውታለን፡፡ የኢትዮጵያ ዲጄ ማኅበር ዘፈኔን ያጫውትልኝ ብሎ ከፈረመ ሕገወጥ አንሆንም፡፡ ዲጄ፤ ሙዚቃ ከድምፃዊ ወደ ሕዝቡ ጆሮ የሚደርስበት ትንራስፖርት ነው፡፡ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ክለብ ውስጥም ዲጄ ስላለ ሕገወጥ ሊባል አይችልም፡፡ ሠርግ በባንድ መሥራት ሲቀንስ ጥቅማቸው የተነካ ሰዎች ቢወነጅሉንም፣ ወጣቶቹ እንደ ጆኒ ራጋና ሔኖክ መሐሪ ያሉት ድምፃውያን   ስለዲጄዎች ጥሩ ግንዛቤም አላቸው፡፡  ስለ ዲጄም ዘፍነዋል፡፡ ሪሚክስ ሲደረግ ማስፈቀድ የግድ ስለሆነ ይህንን ጥሶ አልበም ያወጣ ዲጄ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በሮያሊቲ ክፍያ ጉዳይ የዲጄዎችን ድምፅ በማሰማት ረገድ የነበራችሁ ተሳትፎ ምን ነበር?

አሮን፡- ሮያሊቲ ክፍያን ለመደገፍ ነው ወደ ፓርላማ የሄድነው፡፡ የትኛውም ዲጄ ወደ ፕሮዲውሰርነትና ሳውንድ ኢንጂነርነት ስለሚሄድ የሮያሊቲ ክፍያ ሲከበር ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ለሙዚቃውም ዕድገት ያግዛል፡፡ ዲጄዎች ክለብ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ ቢያጫውቱ ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ ናይጄሪያዎች በሙዚቃው ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉት የራሳቸውን ሙዚቃ በማጫወት ነው፡፡ እኛም የራሳችንን ሙዚቃ አጫውተን፣ ሮያሊቲ ሲከፈል ለኛም ለሙዚቀኛውም ይጠቅማል፡፡ ዲጄ ሮያሊቲ የማይከፍልበት አግባብ ክለብ ውስጥ የክለብ ባለቤት ስለሚከፍል፣ ኮንሰርት ላይ ደግሞ አዘጋጁ ስለሚከፍል ነው፡፡ ሬዲዮ ላይ  ዲጄው ተባባሪ አዘጋጅ ሆኖ ውል ካለው ሮያሊቲ ሊከፍል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ዓመታት የነበረው የዲጄዎች ጉዞ ሲቃኝ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ተገቢውን ቦታ አግኝተዋል?

አሮን፡- የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገባንን ቦታ አላገኘንም፡፡ እኔ ከዛሬ አሥራ ምናምን ዓመት በፊት ስሠራ አንድ ወይም ሁለት አማርኛ ሙዚቃ እናጫውት ነበር፡፡ አሁን ብዙ አማርኛ ዘፈን እያጫወትን ዘርፉም እያደረገ ነው፡፡ ሆኖም ዲጄው የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን መደገፍ እንደሚችል ታውቆ መታገዝ አለብን፡፡ ትናንት የከሰሱን ሙዚቀኞች ዛሬ ሙዚቃቸውን እንድናጫውት አልበማቸውን መስጠታቸው ጥሩ ጅማሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ የሙያ ማኅበራት በየመስካቸው ሙያተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቢቋቋሙም ተጠናክረው የሚቀጥሉት ጥቂቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዲጄዎች ማኅበር በዘርፉ ዘለቄታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ጥንካሬ አለው ብለህ ታምናለህ? በቅርብ ርቀት የያዛችኋቸው ዕቅዶችስ ምንድናቸው?

አሮን፡- የዲጄዎች ሽልማት ለማዘጋጀት አስበናል፡፡ ዲጄዎች ተሰባስበው የትኛው ዲጄ ምን ዓይነት ሙዚቃ እንዳጫወተ፣ ድምፁ ምን ያህል የጠራ እንደሆነና በሌላም መስፈርት መዝነው ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ዲጄዎችን የሚያበረታታ ሲሆን፣ የማኅበራችንን ጽሕፈት ቤት አንድ ግቢ ውስጥ አድርገን ዲጄዎች እንዲጠቀሙበት እንፈልጋለን፡፡ ዲጄዎች መዚቃ ዳውንሎድ የምናደርግበት፣ እርስ በርስ ያለንን የሙዚቃ ክምችት የምንለዋወጥበት፣ ሙዚቀኞች አልበማቸውን የሚሰጡበት ቦታ እንዲኖረን እያሰብን ነው፡፡ ትልልቅ ዲጄዎች ልምድ የሚያካፍሉበትና አዳዲስ ዲጄዎች የሚወጡበትም ይሆናል፡፡ ሙያው እንዲከበር ጠንክረን እንሠራለን፡፡ የሙያ ማኅበራት ድክመት የሚመጣው አመራሩን የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሲያራምዱት ነው፡፡ እኛ የተወሰነ ሠርተን አዲስ ጉልበት ላላቸው ወጣቶች እናስረክባለን፡፡ የኛ ሙያ የሚመለከታቸው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በራቸውን ክፍት ቢያደርጉልን መልካም ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...