- መንግሥት እስከ ጂቡቲ ለማጓጓዝ ጥረት እያደረግኩ ነው ብሏል
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ከወራት በፊት ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰነድ አልባ ዜጎችን ለማስወጣት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ተገደው ሊወጡ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡ ይህም መንግሥትን እንዳሳሰበው ተገልጿል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ዜጎችን ለማስወጣት ተቀምጦ የነበረው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ስምንት ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ብቻ ከ400,000 በላይ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስከ ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ 82,343 ኢትጵያውያን ብቻ የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ 30 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ታውቋል፡፡
አቶ መለስ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ዜጎችን የመመለሱ ሒደት በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የነበረ ቢሆንም፣ መውጣት ከሚገባቸው ሰነድ አልባ ዜጎችና ከቀሩት ቀናት አንፃር ሲታይ ወደ አጣዳፊ ሁኔታ እየተገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግሥት ዜጎችን ያለ እንግልት የመመለስ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት አለበት›› ያሉት አቶ መለስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየቀኑ ከ1,400 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ይህንን አዋጅ ካወጀ ማግስት ጀምሮ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሳዑዲ መንግሥት ያወጣውን የዕፎይታ ጊዜ አዋጅና አንድምታ በተመለከተ በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎች መረጃ እንዲኖራቸው የማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሀብት የማሰባሰብ፣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ተመላሾች በሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተፈለገውን ያህል ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዳልተመለሱ በተደጋጋሚ ጊዜ እየተነገረ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የመውጫ ቪዛ የሚጠይቁና የተሰጣቸው ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ቢሆንም ትልቁ ፈተና ከፊት ያለው ጉዳይ እንደሆነ አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡
ሰነድ አልባ ዜጎች ለሁለት ወራት ያህል በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገዩም በቀሪ ቀናት ለመምጣት ወደ ሪያድ፣ ጂዳ፣ ዳማምና ሌሎች ሩቅ ከተሞች ሳይቀር እየተመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ለምዝገባ ወደ ኤምባሲዎች እየመጡ መሆኑን አቶ መለስ ቢናገሩም፣ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የተወሰኑ ቀናት ሲቀሩ በኤምባሲ መጨናነቅ እየተፈጠረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት ሲባልም የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ለዚህ ሲባልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ የትኬት ቢሮዎችን እንደከፈተና የክፍያ ዋጋውንም ዝቅ እንዳደረገ ተገልጿል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ሰነድ አልባ ዜጎችን ለማቋቋም ሲባልም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሳዑዲ ተመላሾች በሚቋቋሙበት ሒደት ላይ መንግሥት ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መለስ፣ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶችና የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ይዘዋቸው የሚመጡ ዕቃዎችን በተመለከተ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በመነጋገር አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለአብነት ያህልም 21 ኢንች ቴሌቪዥን ለማስገባት የጠየቁ ተመላሾች ከዚህም ከፍ ያለ መጠን ያለው ዕቃ ይዘው በሚመጡበት ጉዳይ ላይ የተለየ አሠራር መዘጋጀቱን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ከተመላሾች ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ መስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ 700 ያህል ሰዎች ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እነዚህ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች የተዘጋጁበት ዋነኛ ምክንያትም የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ በግድ ወደ አገር የሚገቡ የአካል ጉዳተኞችና ሕፃናት ሊኖሩ ስለሚችሉ እነሱን ለመንከባከብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሰነድ አልባ ዜጎችም በክልሎች እየተመዘገቡና ወደ ፊትም ድጋፍ በሚሰጣችው ላይ ከክልል መንግሥት ጋር እየተወያዩ መሆኑን አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ያህል ትግራይ ክልል እስካሁን ወደ አገር ቤት ከገቡት ሰነድ አልባ ዜጎች መካከል 500 ያህል ተመላሾች ሪፖርት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን 134፣ በቡታጅራ አካባቢ ደግሞ 166 ወጣቶች ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የገቡ ዜጎችም በየክልሎቻቸው እየሄዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ መንግሥት የአውሮፕላን በረራዎች ምልልስ ከመጨመር በላይ፣ ተመላሾችን እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በመርከብ ለማድረስ ጥረት ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓርብ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ ከቀሩት ውስን ቀናት አንፃር ዜጎች በፍጥነት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መርከብ ሌላው አማራጭ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንድ መርከብ ስድስት ሺሕ ያህል ሰዎችን ማጓጓዝ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡