Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሕዝብ ቆጠራ ለሚውሉ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዥ የ317.5 ሚሊዮን ብር ስምምነት ከሁዋዌ ኩባንያ ጋር ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ለሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሚያገለግሉ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዥ፣ ከቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ ጋር የ317.5 ሚሊዮን ብር ስምምነት አደረገ፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሁዋዌ በጨረታ ከሚገዙት 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 126 ሺሕ ፓወር ባንኮች፣ ከእያንዳንዳቸው ግማሹን ያቀርባል፡፡

ሁዋዌ ኩባንያ 90 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 63 ሺሕ ፓወር ባንኮችን ያቀርባል፡፡ ስምምነቱ የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባና የሁዋዌ ኩባንያ ተወካዮች በተገኙበት ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ተፈርሟል፡፡

ከሳምንት በፊት የታብሌቶቹና የፓወር ባንኮቹ 665 ሚሊዮን ብር ኮንትራት ለሁዋዌና ሌኖቮ ለተባለ ሌላ የቻይና ኩባንያ የጨረታ አሸናፊነቱ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

ለስድስት ወራት ሲካሄድ የነበረው ጨረታ ሲያወዛግብ የቆየ ቢሆንም፣ በዋናነት የአገር ውስጥ አምራቾች የጨረታውን አወጣጥና ሒደት ሲወቅሱ ነበር፡፡ ጨረታው የአገር ውስጥ የሞባይልና የታብሌት ኮምፒዩተር አምራቾችን ያገለለ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በዚህ ጨረታ አሥራ ስምንት ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ተጋብዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከተጋበዙት ውስጥም በቀድሞ ስሙ ቴክኖ ሞባይል ተብሎ የሚጠራው የአገር ውስጥ ኩባንያ ከውጭ ተፎካካሪዎች ጋር ተሳትፎ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ኩባንያ የቴክኒክ ግምገማውን ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ በመጨረሻው የጨረታ ፉክክር ሌኖቮና ሁዋዌ ወደ ፋይናንስ ዙር እንዲያልፉ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ሲል በነበረ ተመሳሳይ የቴክኒክ ግምገማ ውጤት ሁዋዌና ባክ ዩኤስኤ የተባለ ኩባንያ አልፈው ነበር፡፡

ነገር ግን ለመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በቀረበ ቅሬታ ባክ ዩኤስኤ ኩባንያ የቴክኒክ ግምገማውን እንዳያልፍ ተደርጎ፣ ከዚያ በፊት ግምገማውን ወድቆ የነበረው ሌኖቮ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡

ከዚህም ሒደት በኋላ ሁዋዌና ሌኖቮ ለአንድ ታብሌት 141.7 ዶላር፣ እንዲሁም ለአንድ ፓወር ባንክ 15 ዶላር ዋጋ ለማቅረብ የተስማሙ ሲሆን፣ ዕቃዎቹን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለማድረስ ደግሞ እያንዳንዳቸው ለታብሌት 15.75 ብር፣ እንዲሁም ለፓወር ባንክ 14.63 ብር ዋጋ አቅርበዋል፡፡

ይኼም በመጨረሻ በአገልግሎቱ ተቀባይነትን አግኝቶ ኩባንያዎቹ አሸናፊ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ዕቃዎቹን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ አቅርበው እንዲጨርሱ ይጠበቃል ሲሉ አቶ ይገዙ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለፍጥነት ሲባልም ዕቃዎቹን ከሥር ከሥር እንዲያቀርቡ ይደረጋል በማለት አስረድተዋል፡፡ የሕዝብና የቤት ቆጠራው በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ቆጠራ መንግሥት ሦስት ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡

665 ሚሊዮን ብር ለሚወጣበት ለዚህ ኮንትራት አቅራቢዎቹ ዕቃዎቹን ከቀረጥና ታክስ ነፃ የሚያስገቡ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ራሱ ለመንግሥት ይከፍላል ተብሏል፡፡ ሁለተኛው አሸናፊ ድርጅት ሌኖቮ በቅርቡ ስምምነት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች