Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዳዲስ ኃላፊዎች ተሾሙ

ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዳዲስ ኃላፊዎች ተሾሙ

ቀን:

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ33.144 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ሦስት ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ተሾሙለት፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተሰየሙት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ አርብ ሰኔ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ኮርፖሬሽኑ ከመመሥረቱ በፊት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በነበረበት ወቅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ የቆዩትን አቶ ሀብታሙ ሲሳይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋል፡፡ አቶ ዓለማየሁ ከአቶ ሀብታሙ በተጨማሪ፣ ኮርፖሬሽኑ ያሉትን ሦስት ዘርፎች ለሚመሩ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ብርሃኑ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ብርሃን ዜና፣ የቤቶች አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋለም ኩመሌ ተሹመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በነበረበት ወቅት የሥራ ሒደቶች አስተባባሪና ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ የቆዩት አቶ ሙደር ሰማንና የዋና የሥራ ሒደት መሪና አስተባባሪ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ዓለም ሰገድ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተብሎ የተቋቋመው የቀድሞው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ያስተዳድር የነበረ ነው፡፡ ይዞታዎቹ በልማት ምክንያት እየፈረሱ፣ መሬቱም ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው በመሰጠታቸው ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከ17 ሺሕ ያልበለጡ ቤቶች ብቻ በሥሩ ይገኛሉ፡፡   

ከ26 ዓመታት በፊት ከግንባታ ውጪ ተድርጎ እስካሁን የቆየውና አሁን ኮርፖሬሽን የተባለው ተቋም፣ ያሉትን ቤቶች በአግባቡ እያስተዳደረ አለመሆኑ ሲያስወቅሰው ቆይቷል፡፡

ታኅሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አነሳሽነት በተካሄደ የኦዲት ግኝት ስብሰባ ላይ፣ ኤጀንሲው ቤት ለመከራየት ውል በገቡና በየዓመቱ ውላቸውን በማያድሱ ደንበኞች ላይ ቅጣት የማይጥል መሆኑ፣ ቤት በነፃ እንዲሰጣቸው ከሚፈቀድላቸው ደንበኞች ጋር አጠቃቀሙን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውል የማይፈራረም መሆኑ፣ በሥሩ ከሚተዳደሩ ቤቶች ውስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው ቤቶች እንዳሉና ካርታ ካላቸው ቤቶች ማኅደር ውስጥም ቅጃቸው ያልተያያዘ ቤቶች የሚገኙ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኤጀንሲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት የውል ግዴታቸውን ባለማክበርም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከተከራዮች ሳይሰበሰብ የቆየ ውዝፍ የቤቶች ኪራይ 98,943,642.56 ብር ያልታሰበ መሆኑንም በኦዲት ግኝት መረጋገጡ ተመልክቷል፡፡

ኤጀንሲው በአዲሱ አደረጃጀቱ እነዚህን ችግሮች የመፍታትና አዳዲስ ግንባታዎች የማካሄድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኮርፖሬሽኑን ባቋቋመበት ደንብ እንደተገለጸው፣ ኮርፖሬሽኑ 33,144,772,136 ብር የተፈቀደ ካፒታልና 11,048,257,378 ብር በጥሬና በዓይነት በተከፈለ ካፒታል ተመሥርቷል፡፡

አዲሶቹ የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት ኮርፖሬሽኑ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ለተፈጠረው የመኖሪያ ቤት እጥረት አስተዋጽኦ በሚኖረው ደረጃ ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በመካከለኛው ክፍል የሚገኙ ይዞታዎችን በማፍረስ አፓርታማዎችን ገንብቶ ለነዋሪዎች በኪራይ እንደሚያቀርብ፣ ለመንግሥት ተሿሚዎችም እንዲሁ መኖሪያ ቤቶችን እንደሚገነባና በመንግሥት ውሳኔ ለሽያጭ የሚያቀርባቸው ቤቶች እንደሚኖሩም ታውቋል፡፡

ይህንን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግም አቶ ዓለማየሁ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት 22ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ የተወሰነውን ውሳኔ በማስታወስ፣ የአዲስ አበባ ከተማና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በኮርፖሬሽኑ ሥር ያሉ ይዞታዎችን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንዳይሰጡ አሳስበዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...