የዶራሌህ ሁለገብ ወደብ ግንባታ መጠናቀቁ ይፋ በተደረገ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ታጁራ የተሰኘውና በአብዛኛው የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያገልገል የሚጠበቀው ወደብ ሥራ መጀመሩን የጂቡቲ መንግሥት አስታወቀ፡፡
በ30 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለው የታጁራ ወደብ በ90 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገባ ሲሆን፣ በአብዛኛው የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ከማስተናገድ በተጨማሪ የገቢ ዕቃዎችንም እንደሚያካትት የጂቡቲ ባለሥልጣናት ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደቡን ሥራ ባስጀመሩበት ሥነ ሥርዓት ወቅት አስታውቀዋል፡፡ የጂቡቲ ወደቦች አስተዳደርና ነፃ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡባካር ኦማር ሐዲ እንዳስታወቁት፣ የታጁራ ወደብ 35 በመቶ የኢትዮጵያ የገቢ ዕቃዎችን ያስተናግዳል፡፡
ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምር እንደነበር የሚጠበቀው የታጁራ ወደብ፣ ከኢትዮጵያ የሚጓጓዘውን 2,000 ቶን በቀን፣ ወይም አራት ሚሊዮን ቶን በዓመት የፖታሽ ማዕድን የማስተናገድ አቅም አለው ተብሏል፡፡ የፖታሽ ማዕድን በአብዛኛው በትግራይና በአፋር ክልሎች የሚገኝ ነው፡፡ ሁለቱ ክልሎች ለጂቡቲ ካለቸው ቅርበት አኳያ የታጁራ ወደብ ለፖታሽ ማዕድን ማስተናገጃነት እንዲውል መደረጉ፣ ከተዘረጋው የባቡር ትራንስፖርት አኳያም የፖታሽን የወጪ ንግድ ወጪን በመቀነስ አዋጭ እንደሚያደርገው ከኢትዮጵያ በኩል ይገለጻል፡፡
ከታጁራ ባሻገር የጂቡቲ መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት ያስጀመረው የዶራሌ ሁለገብ ወደብ፣ በ590 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይፋ የተደረገው ከሦስት ሳምንት በፊት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የዶራሌ ሁለገብ ወደብን፣ እንዲሁም የታጁራ ወደብን ጨምሮ የጂቡቲ መንግሥት አራት ወደቦችን እየገነባ ነው፡፡ የዶራሌ ወደብ በጠቅላላው 690 ሔክታር መሬት የሚያካልል ሰፊ ይዞታ አለው፡፡
የጂቡቲ በጂቡቲ መንግሥት የ76.5 በመቶ ድርሻ እንዲሁም ቻይና መርቻንት ሆልዲንግስ በተባለውና ግንባታውን ባከናወነው ኩባንያ የ23.5 በመቶ ድርሻ የተገነባው የዶራሌ ወደብ፣ 57 ሔክታር የሚሸፍን ጠቅላላ የጭነት ቦታ አለው፡፡ ትልልቅ ብትን ጭነቶች የሚስተናገዱበት 20 ሔክታር የሚሸፍን ስፋት ያለው ተርሚናል፣ እንዲሁም 23 ሔክታር የሚሸፍን የኮንቴይነር ማስተናገጃ፣ 15 ሔክታር የተሽከርካሪ ጭነቶች (ሮሮ) መጫኛና ማውረጃ ቦታን ጨምሮ 35 ሺሕ ካሬ ሜትር የማከማቻ መጋዘንና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎችን አካቷል፡፡ ይህ ወደብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ የበቃው ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ሲያስተናግድ የቆየው የጂቡቲ ወደብ እያደገ በመጣው ከፍተኛ ጭነት ሳቢያ እየተጣበበ በመምጣቱ፣ አዳዲስ ወደቦችን ለመገንባት መነሳቱን የጁቡቲ መንግሥት ይፋ ካደረገ ከአራት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ገንዘብ ሊያገኝ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በወደቦቹ ግንባታ መጓተት መከሰቱን ማስታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
በየዓመቱ በጂቡቲ ወደብ የሚስተናገዱና ትራንዚት የሚያደርጉ መርከቦች ቁጥር በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የሚገልጸው የጂቡቲ መንግሥት ከእስያ፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ አገሮች የሚመላለሱ ከ30 ሺሕ በላይ መርከቦችን በማስተናገድ የ20 በመቶ ጭማሪ የሚታይበት ከ5.7 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት በየዓመቱ በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የዶራሌ ወደብን የገነባው የቻይናው መርቻንት ሆልዲንግስ ኩባንያ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በሽርክና መሥራት የጀመረው ከአራት ዓመታት በፊት ነው፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነውን የንግድ መርከብ ድርጅትን የ40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ጥያቄ አቅርቦ ድርድር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከታጁራ ወደብ በተጨማሪ በተያዘው ወር የጨው ምርት ማስተናገጃው የጎውበት ወደብ ግንባታ ተጠናቆ እንደሚመረቅ ይጠበቃል፡፡ ከሁለቱ ወደቦች በተጨማሪ የቁም ከብቶች የሚስተናገዱበት የዳመርጆግ ወደብ ግንባታ ተጠናቆ ለሥራ መዘጋጀቱን የጂቡቲ መንግሥት አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳ የጂቡቲ መንግሥት ተጨማሪ አራት ወደቦችን በማዘጋጀት በአብዛኛው የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ዕቃዎች በቅልጥፍና ለማስተናገድ ያለውን ፍላጎት በተግባር እያሳየ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች አገሮች የሚገኙ አማራጭ ወደቦችን ማፈላለጉን አልገታም፡፡ በቅርቡ ይፋ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፣ በሶማሌላንድ በሚገኘው የበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ በመግዛት በወደቡ የባለቤትነት ብቻም ሳይሆን የተጠቃሚነት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሱዳን በሚገኘው ፖርት ሱዳን ወደብም ከፍተኛ የማዳበሪያ ጭነቶችን ማስገባት ከጀመረ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
ከ900 ሺሕ ያነሰ ሕዝብ ያላት ጂቡቲ ለወደቦች፣ ለባቡር፣ ለመንገድ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይልና ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ጋር ለምትገናኝባቸው መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ በጠቅላላው 14 ቢሊዮን ዶላር ያህል በጀት መመደቧ ሲታወቅ፣ በአብዛኛው ከቻይና መንግሥት በምታገኘው ፋይናንስ እንደሚሸፈኑ ይታወቃል፡፡