Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ባንክ ዕርምጃ የጋምቤላ ኢንቨስተሮችን አስቆጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ 110 የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ታማሚ ብድር ጎራ (Non-performing Loan) ማስገባቱ ተቃውሞ ቀሰቀሰ፡፡

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ መንግሥት ይኼንን ችግር አጢኖ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለሀብቶች የያዟቸውን ፕሮጀክቶች ወደ ታማሚ ብድር ጎራ በማስገባት በሐራጅ እንዲሸጡ እስከ ማመቻቸት መድረሱ ተገቢነት የለውም፡፡ ይህ ኃላፊነት ከሚሰማው የመንግሥት ተቋም የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፤›› በማለት ማኅበሩ ወቅሷል፡፡

‹‹የባንኩ አመራሮች ችግሮቹን በመገንዘብ ፕሮጀክቶችን ወደ ታማሚ ጎራ ከማስገባታቸው በፊት አስቸኳይ የማስተካከያ ውሳኔ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፣ እስካሁን ድረስ ትርጉም ያለው መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ብድር ከወሰዱ 194 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መካከል፣ 110 ፕሮጀክቶች በታማሚ ብድር ጎራ ገብተው ይገኛሉ፤›› በማለት ያብራራው የማኅበሩ ደብዳቤ፣ ‹‹ይህንን ሁኔታ በፅኑ እንቃወማለን፡፡ መንግሥት ባለበት አገር እንዲህ ዓይነት ተግባር መፈጸም እንደሌለበትም እናምናለን፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

አባላቱን ወክሎ ተቃውሞውን ያቀረበው የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ የጋምቤላ እርሻ ኢንቨስተሮች ብድር ከወሰዱ ሁለት ዓመት ያህል እንዳስቆጠሩ፣ በችግር ውስጥ ሆነው በመሥራት በመንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው ብድሮቻቸውን እየመለሱ ውጤታማ ሥራ እንደሚያከናውኑ ይጠበቅ ነበር ብሏል፡፡

‹‹ሆኖም ባለሀብቶቹ ብድር ከወሰዱ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳይደረግላቸው፣ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ከግንዛቤ ሳይገቡ በመንግሥት መመርያ የተፈቀደ የዕፎይታ ጊዜ ተከልክለው፣ የተሰጣቸውን መሬት በወጉ አጥንተውና አልምተው ሳይጨርሱ ባንኩ ወደ ታማሚ ብድር ጎራ ሊያስገባቸው መሯሯጡ አግባብ አይደለም፤›› ሲል ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሠራር ምክንያትና በአጠቃላይ በክልሉ ካሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም ብሏል፡፡

በተለይ ስምንት ዋና ዋና ችግሮች ጎልተው መውጣታቸውን ማኅበሩ ገልጾ፣ ከእነሱ ውስጥም የባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ የማያሠራና ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑ፣ በእርሻ ኢንቨስትመንት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የዕፎይታ ጊዜ የሚፈቀድ ቢሆንም ባንኩ ግን ይህን መከልከሉ፣ መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ የግብዓት አቅርቦት አለመስጠቱ፣ በክልሉ በየጊዜው የፀጥታ መደፍረስ የሚያጋጥም መሆኑ፣ ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ተፈጥሮ የነበረው የመሬት መደራረብ ለመፍታት ረዥም ጊዜ መወሰዱ፣ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ በቂ ምርት አለመገኘቱ፣ በክልሉ የተፈጠረውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያካሄደው ጥናት አንድ ዓመት በመውሰዱና በዚህ ጊዜ የእርሻ ሥራ በመቆሙ፣ የተረጋጋ የአገር የውጭ ገበያ ለኪሳራ መዳረጉ በኢንቨስተሮች ላይ ችግር መፍጠሩን ማኅበሩ ጠቅሶ፣ ባንኩ ግን እነዚህን መጠነ ሰፊ ችግሮች ከግንዛቤ ሳያስገባ ዕርምጃ መውሰዱ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ ባንኩ እነዚህን ችግሮች በድጋሚ እንዲፈትሽና የማሻሻያ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ ማሻሻያ ተብለው ከቀረቡ ስድስት ጉዳዮች መካከል የብድር የመመለሻ የጊዜ ገደብ እንዲራዘም፣ እስካሁን በጥቃቅን ምክንያቶች የተራዘሙ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ለተያዘባቸው ፕሮጀክቶች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ እንዲሰጥ፣ ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲፈቀድ፣ በኢንቨስትመንት መመርያ የተቀመጠው የዕፎይታ ጊዜ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በየጊዜው እየተዳከሙ የሚገኙ ታማሚ የብድር ጎራ እየገቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው ችግር ተፈቶ በዚህ ክረምት ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዲደረግ፣ መንግሥት ችግሩን በመረዳት የዘር ጊዜ ሳያልፍ መፍትሔ እንዲሰጥ በአፅንኦት ጠይቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች