Friday, February 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከቃላት ድርደራ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ተግባር ትበልጣለች!

 ንድፈ ሐሳብ አንድን ጉዳይ ከሥር መሠረቱ በመተንተን ለሚፈለገው ዓላማ ቅርፅ ለማስያዝ የሚያግዝ የዕውቀት ዘርፍ ሲሆን፣ ተግባር ደግሞ ያንን የተጠና ጉዳይ የተሟላ ይዘት እንዲኖረው የሚረዳ ነው፡፡ ለዚህም ነው ንድፈ ሐሳብ በተግባር ካልታገዘ ቁስ አካላዊ ኃይል መሆን አይችልም የሚባለው፡፡ ከዚህ ወጣ በማለት በነባራዊው ዓለም ውስጥ በተለይ በአገር ግንባታ ጉዳይ ላይ ከተግባር ይልቅ የቃላት ድርደራ ሲበዛ ውጤት አይገኝም፡፡ የሚነገረውና የሚደረገው ካልተናኙ ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ ቅራኔ እያደገና እየከከረ ሲሄድ ሥር ይይዝና የማይታረቅ ይሆናል፡፡ ልዩነትን ከመቀበል ይልቅ ወደ መደፍጠጥ እሳቤ ይገባና የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመነዝረው ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት፣ እንዲሁም በፖለቲከኞችና በሕዝብ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ፈሩን እየሳተ ያለው ቃልና ተግባር አልገናኝ እያሉ ነው፡፡ በቅርቡ በአገሪቱ የደረሰው አደጋ ዋነኛ መስንዔ በሕዝብና በመንግሥት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡ በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የሕዝብ እምነት በማጣታቸው የዳር  ተመልካች ነበሩ፡፡ ጭራሽ የሕዝቡ ጥያቄ በሌሎች ወገኖች ተጠልፎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ልዩ ገጽታ ተጎናፅፎም ነበር፡፡ ቃልና ተግባር መገናኘት ሲያቅታቸው ውጤቱ እንዲህ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት አገሪቱን እንደ መምራቱ የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ስለሚመለከቱት፣ ‹ጥልቅ ተሃድሶ› ውስጥ መግባቱ አይዘነጋም፡፡ ኢሕአዴግ የገባበት ‹ጥልቅ ተሃድሶ› በመጀመሪያ ራሱን ለማዳንና የሚመራውን ሥርዓት ለመታደግ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ አመራሩንና አባላቱን በተዋረድ አሳትፎበታል፡፡ በዚህ ተሃድሶ አማካይነትም የሕዝቡን ጥያቄዎች በየደረጃው ለመፍታት፣ ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የማይመጥንና ፍጥነት የጎደለው አዝጋሚ ለውጥ ለማምጣት መሞከር እንደማያዋጣው ተናግሯል፡፡ የሕዝብ ትዕግሥት አንድ ቦታ ላይ እንደሚያበቃም መገንዘቡን አስረድቷል፡፡ በመልካም ቃላትና በማራኪ ዲስኩሮች የሕዝቡን ልቦና ማግኘት እንደማይቻልና ከብዙ ሺሕ ቃላት ድርደራ አንዲት ተግባር ሕዝቡን ድምዳሜ ላይ እንደምታደርስ መተማመን መፈጠሩን አሳውቋል፡፡ ይህ በንድፈ ሐሳብ የተገለጸ በመሆኑ፣ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት የሚናገረውን በተግባር ማሳየት መቻል አለበት፡፡ ችግሮችን በግልጽ አውቆ ስህተቶችን ማረም ያስከብራል እንጂ አያስነቅፍም፡፡ አሁን ትልቁ ችግር ቃልና ተግባር እንዴት ይገናኙ የሚለው ነው፡፡

እንደሚታወቀው የዚህ ዘመን ትውልድ አጥብቆ ጠያቂ እየሆነ ነው፡፡ መብቱንም ለማስከበር አማራጭ የሚለውን ነገር ለመውሰድ እንደማይመለስ አሳይቷል፡፡ የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት አገሪቱ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሱባቸው አገር ለመሆን በመቻሏ እንደሚኮሩ በአደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ የሚያንቀላፋ ሳይሆን በጣም ንቁ ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው ፍላጎት ከዕድገት ጋር የተያያዘና የበለጠ ለውጥና ተጠያቂነትን የሚሻ መሆኑን፣ በዓላማቸው መሠረትም ተኝቶ የማያስተኛ ትውልድ መፈጠሩ የሥራቸው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ አስተያየት በቀና መንፈስ ወደ ተግባር ተተርጉሞ ማየት ደስ ይላል፡፡ እያስቸገረ ያለው ግን ይህ አስተሳሰብ በገዥው ፓርቲ አባላት ዘንድ ከላይ እስከ ታች ድረስ የመስረፁ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብ በግልጽ የሚታዘባቸውና ‹ድንቄም ተሃድሶ› የሚባልባቸው ችግሮች አሁንም በብዛት አሉ፡፡ በተለይ በስመ ኢሕአዴግነት በሚፈጸሙ አሳዛኝ ተግባራት ሳቢያ ሕዝቡ እነዚህ ሰዎች ካለፈው አልተማሩም ለካ እያለም ነው፡፡ የሕዝብ ጥርጣሬ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ የሚከተለው ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ኢሕአዴግ መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆኖ ችግሮቹን ለማወቅና ዕርምጃ ለመውሰድ መነሳቱን ያሳወቀበት ‹ጥልቅ ተሃድሶ› አንድ ቦታ ላይ የሚቆም ሳይሆን፣ በስፋትና በጥልቀት ተገብቶበት ብዙ የሚሠራበት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜ ለማይሰጡ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ምላሽ መስጠት መቼም ቢሆን የሚታለፍ አይደለም፡፡ በአመራር ደረጃም ሆነ በታችኛው እርከን ያሉ የራሱን ሰዎች ሸንቆጥ ማድረግ ካልቻለ ግን ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ ሕዝብ ከቃላት ድርደራ ይልቅ ተግባርን ያስቀድማልና፡፡

ገዥው ፓርቲ ተሃድሶ ውስጥ ከገባ በኋላ መጠኑና ዓይነቱ ይለዋወጥ እንጂ የተወሰዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች ግን ሕዝብን እያረኩ ነው? ወይስ ፋይዳ የላቸውም? ድርጅቱንና ሥርዓቱን ከመታደግ በዘለለ ለአገር ዘለቄታዊ ህልውና ያላቸው ምላሽ ምን ይመስላል? አገሪቱ ያንን የመሰለ አውዳሚ አደጋ ውስጥ ላለመመለሷ ምን ማስተማመኛ አለ? በአጠቃላይ ቃል በተገባው መሠረት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን አዲስ ምዕራፍ ይጀመራል? ወይስ ጥያቄ ያስነሳው    የአውራ ፓርቲ አስተሳሰብ ተጠናክሮ ይቀጥላል? ኢሕአዴግ ባለፉት አሥራዎቹ ዓመታት በአገሪቱ የታየውን የኢኮኖሚ መነቃቃት በማስታከክ አዳዲስ የሕዝብ ፍላጎቶች  መፈጠራቸውን በአዎንታዊ ጎን ያየዋል፡፡ ነገር ግን ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ባልተናነሰ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች በጣም መጨመራቸው አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ በፖለቲካው መስክ የሚታየው የኋልዮሽ ጉዞ የአገሪቱን ገጽታ በጣም እያበላሸው ከመሆኑም በላይ፣ በሕገ መንግሥቱ ሳይቀር ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ባለመከበራቸው ብቻ ሕዝቡን ወደ አመፅ ገፍተውታል፡፡ በገዥው ፓርቲም ሆነ በመንግሥት ውስጥ የተፈጠረው ብልሽት አገርን የሚንድ ሥጋት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ በሕግ የተፈቀዱ መብቶች እየተጣሱ አገር የቅራኔዎች መሻኮቻ ሆናለች፡፡

ሕዝብ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መተዳደር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ የግለሰቦችና የቡድኖች ፍላጎት ብቻ ሲከበር ሕዝብና መንግሥት ይለያያሉ፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንድ-ሦስተኛ ክፍል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውንና አገሪቱ ፈርማ የተቀበለቻቸውን መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶች በውስጡ አጭቋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት በተግባር ሥራ ላይ ቢውል ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ዜጎች የሚመስላቸውን አመለካከት በነፃነት ያራምዳሉ፡፡ መደራጀት ፈተና አይሆንም፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ የፖለቲካ ሥራ ዳር ድንበር ይኖራቸዋል፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ይሆናሉ፡፡ ተጠያቂነታቸውም እንደዚሁ፡፡ ማናለብኝነትና እንዳሻው መሆን ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ መብትና ግዴታ መሳ ለመሳ ሆነው ይከናወናሉ፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ በሥልጣን መባለግ በሕግ ያስጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት በሚባል መሥፈርት ዜጎች አይመዘኑም፡፡ ፍትሕ ይሰፍናል፡፡ የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር ማሰሪያ ይሆናል፡፡ ይህ በጎ ምኞት ዕውን የሚሆነው ግን ቃልና ተግባር ሥራ ላይ ሲውሉ ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ያገባናል የሚሉ ዜጎችም ሆኑ የተለያዩ አካላት ልብ ሊሉት የሚያስፈልገው ከአገር በላይ ምንም አለመኖሩን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ በማፈንገጥ ሕዝቡን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከትና በመሳሰሉት በመከፋፈል አገሪቱን ለማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች ይበቃችኋል መባል አለባቸው፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ወገኖች ራሳቸውን ለሥልጡን ፖለቲካ በማዘጋጀት ለውይይትና ለድርድር ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲም የሕዝብ ውክልና ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያገለለና ለትዝብት የሚዳርግ አጉል ውይይትና ድርድር ውስጥ ከመግባት መታቀብ አለበት፡፡ በሕዝብ ዘንድ እዚህ ግባ የማይባሉና ትኩረት የሌላቸውን ብቻ ሰብስቦ የተለመደው አዙሪት ውስጥ መዳከር ፋይዳ የለውም፡፡ እዚህ ላይ መወሳት ያለበት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ደረጃ የማውጣትና የመፈረጅ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከሕዝብ ትዝብትና ጥላቻ ለመዳን ከእውነት ጋር መጋፈጥ አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡ በደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትግል የረባ ነገር አይገኝም፡፡ ራሳቸውን ከድርድር የሚያሸሹ ኃይሎችም ካለፈው ስህተታቸው ተምረውና ጠንክረው መቅረብ ሲገባቸው፣ ያረጁና ያፈጁ አተካራዎችን ተገን እያደረጉ መሸሽ የለባቸውም፡፡ ሕዝብ አማራጭ ይፈልጋል እያሉ ራስን ከአማራጭነት ማሸሽ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አደገኛ አማራጭ ውስጥ ገብተው የሚዳክሩ ደግሞ አደብ ገዝተው ወደ ሥልጡን መንገድ ቢመለሱ የተሻለ ነው፡፡ የያዙት ጎዳና መድረሻው አዘቀት እንጂ ለሕዝብ ፋይዳ የለውም፡፡ ጉም የመዝገን ያህል ቅዠት ውስጥ ሆነው በከሰረ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ማደናገር ለጊዜው ነው እንጂ ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ የሚያወሩት በዓይን አልታይ ሲል ውጤቱ ኪሳራ ይሆናል፡፡ እየሆነም ያለው ይኼው ነው፡፡ ለማጠቃለል ቃልና ተግባር የማይገናኙበት የፖለቲካ ጉዞ ለአገር አይበጅም፡፡ ይህ ዘመናዊ ትውልድም አይታለልም፡፡ በደመነፍስ መጓዝ ዘመን አልፎበታልና፡፡ ለዚህም ነው ከቃላት ድርደራ ይልቅ አንዲት ሰናፍጭ የምታህል ተግባር ትበልጣለች የሚባለው!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...

ቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

በንጉሥ ወዳጅነው  በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ትናንትም ቢሆን የተመረጡም ሆኑ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...