[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተነጋገሩ ነው]
- አንተ ምን ሆነሃል?
- ትንሽ ተበሳጭቼ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ፊትህን ጥለኸዋል እኮ?
- አዋረዱን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማነው የሚያዋርደን?
- የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አደረጉ?
- አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- መሸነፋችንን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መሸነፍ ይገርማል እንዴ?
- ኧረ ይኼ ይብሳል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- አምስት ለባዶ እኮ ነው የረፈረፈን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን?
- የጋና ብሔራዊ ቡድን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጨዋታው የት ነበር?
- እዚያው ጋና ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከልማታዊ መንግሥታችን ጋር ግንኙነታቸው እንዳይበላሽ ብለው ነው በአምስት ብቻ የማሩን ገባህ?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ለነገሩ ጋና እኮ ወደፊት ለዓለም ዋንጫ ያሠጋል ይባልለታል፡፡
- ቢሆንስ ክቡር ሚኒስትር?
- በአምስት ጎሎች ብቻ የማሩን ለወዳጅነታችን ሲሉ ነው አልኩህ፡፡
- ከዚህ በላይ ምን ይምጣ ክቡር ሚኒስትር?
- ደርዘን ቢከቱብን ምን ትሆን ነበር?
- ጨርቄን ጥዬ አብድ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳንም በትንሹ ገላገለህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር?
- አቤት?
- ይኼ የእግር ኳሳችን ጉዳይ ምን ይሻለዋል?
- ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገዋል፡፡
- እንዴት ተደርጎ ክቡር ሚኒስትር?
- በመጀመሪያ ይጠረነፋል፡፡
- ብሔራዊ ቡድኑ?
- አዎ፡፡
- ከዚያስ?
- ተጨዋቾቹ አንድ ለአምስት ይደራጃሉ፡፡
- ከዚያስ ክቡር ሚኒስትር?
- ከዚያማ ሥልጠናው በልማታዊ አስተሳሰብ ይካሄዳል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፊፋ ይኼንን አይፈቅድም እኮ?
- ፊፋ ምን አገባው?
- የእግር ኳሱ የበላይ አስተዳዳሪ እሱ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላ ዘዴ እንጠቀማለን፡፡
- ምን ዓይነት ዘዴ?
- ከውስጥ የሚሠራው ከደጅ እንዳይታይ አድርገን ነዋ፡፡
- ይኼ ምን ማለት ይሆን ክቡር ሚኒስትር?
- እግር ኳሱን ልማታዊ አቅጣጫ ማስያዝ ይባላል፡፡
- ኧረ ይኼ አያዋጣም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ የጎል ጎተራ ሆነህ ትቀጥላለህ?
- እርስዎ እንዲህ ነው የሚያስቡት ክቡር ሚኒስትር?
- አማካሪው አንተ ምን የተሻለ ሐሳብ አለህ?
- ከላይ እስከ ታች እንደገና ብናደራጀው ይሻላል እላለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ይዘህ እባክህ?
- ክለቦቹንና ፌዴሬሽኑን ይዘን ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጨለምተኛ ሆነሃል ማለት ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አምስት ጎሎች ተቆጠሩብን ብለህ እያለቃቀስክ አልነበረም?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በልማታዊ አቅጣጫ የማይፈታ ችግር የለም፡፡
- እንዴት አድርገን ክቡር ሚኒስትር?
- ያለ የሌለ የሰው ኃይላችንን ይዘን በመሠለፍ ነዋ፡፡
- ማለት ክቡር ሚኒስትር?
- ጋናዎች 11 አይደሉ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛ ደግሞ 33 ሆነን እንገባለን፡፡
- ያለ ሕጉ ክቡር ሚኒስትር?
- ካስፈለገ ሕጉን ልማታዊ እናደርገዋለን፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ እንደወጣ ጸሐፊያቸው ገባች]
- ፈለግሽኝ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- አንድ ችግር ገጥሞኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የ40/60 ቤቶች ዕጣ ሊወጣ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
- እና?
- ዕጣው ውስጥ እንድገባ እንዲያደርጉኝ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንቺ የሠራሽው ቤት አለሽ አይደል?
- 40/60 ተመዝግቤያለሁ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በሕጉ መሠረት ባንኩ አያስተናግድሽም ገባሽ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- በአንዲት ብጫቂ መመርያ ችግር ውስጥ ልግባ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ቤት እያለሽ እንዴት ተመዘገብሽ?
- ቤቱ በባሌ ስም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አየሽ የአንቺም ማለት እኮ ነው፡፡
- እኔና ባሌ ግን. . .
- ግን ምን?
- ለጊዜው ተለያይተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለ40/60 ቤት ብለሽ ትዳርሽን ታፈርሻለሽ?
- እንደሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነው ታዲያ?
- ቤቱ ሲገኝ እንደገና አንድ ላይ እንሆናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን አንድ ላይ አይደላችሁም እንዴ?
- አንድ ላይ ነን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነው ታዲያ ተፋታን የምትይኝ?
- አልጋ ለይተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- ለልጆቹ ብለን ነው አንድ ጣሪያ ውስጥ ያለነው ብለን አስወርተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማታ ማታ ግን. . .
- ማታ ማታማ ተቃቅፈን ነው የምንተኛው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሲነጋስ?
- እንዴት አደራችሁ እየተባባልን ከተለያዩ ክፍሎች እንወጣለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ደግሞ ከየት የመጣ ፋሽን ነው?
- የአገሩ ባለሀብትና ባለሥልጣን እንዲህ አይደል እንዴ የሚኖረው ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን ይኼ ኑሮ ይባላል?
- ዓላማ ካለ አሪፍ ይሆናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ግን ኪራይ ሰብሳቢ ኑሮ ብየዋለሁ፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ፀረ ልማት ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ አንድ ስብሰባ እየወሰዳቸው ነው]
- እነዚህን የመሳሰሉ ሕንፃዎች ማን ነው የገነባው እባክህ?
- ክቡር ሚኒስትር የ40/60 ቤቶች ናቸው፡፡
- እንዲህ ያምራሉ እንዴ?
- ደስ ይላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መቼ ነው ዕጣቸው የሚወጣው?
- አልታወቀም ተብሏል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዕጣ የሚያገኟቸው ሰዎች በልማታችን ደስተኛ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡
- ምን ዋጋ አለው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ማለትህ ነው?
- በመጀመሪያው ዙር እኮ በጣም ትንሽ ቤቶች ናቸው የሚወጡት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ያህል ተመዝጋቢዎች አሉ?
- ከ160 ሺሕ በላይ ናቸው አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በትዕግሥት መጠበቅ አለባቸው፡፡
- አራት ዓመት ጠበቁ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ ይቆጥባሉ?
- 16 ሺሕ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ከፍለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እነዚህ ልማታዊ ናቸው እባክህ?
- አራት ዓመት ገንዘባችንን ብንሠራበት ኖሮ ቢያንስ ሁለት ቤቶች ይገዛልን ነበር እያሉ እያዘኑ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሌሎቹስ?
- ሌሎቹም በየወሩ ከኑሮ ጋር እየታገሉ ይቆጥባሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትዕግሥት ካለ ሁሉም ይደረስበታል፡፡
- በዚህ አዝጋሚ ሁኔታ ትዕግሥት የሚባለው ቃል ከመዝገበ ቃል ሳይጠፋ አይቀርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- የቤት ተመዝጋቢዎችን እሮሮ በቀጥታ ቢሰሙት ያልኩት ይገባዎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን እሮሮ ነው የምታወራው?
- ሰው የኪራይ ኑሮ አንገፍግፎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከታገሡ የተመኙት ይደርሳል አልኩህ፡፡
- አሁን ግን ችግሩ ከመጠን በላይ ሆኗል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በልማት ዘመን የምን ችግር ነው የምታወራው?
- ከ160 ሺሕ በላይ ቤት ፈላጊዎች በስንት ዓመት የሚደርሳቸው ይመስልዎታል?
- እኛ እኮ ደርግን ለመጣል የታገልነው ለ17 ዓመታት ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ያንንና ይኼንን ምን አገናኛቸው?
- በአንድ ሌሊት እንዲሁ የሚገኝ ነገር የለማ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአንድ ሌሊት ሚሊየነር የሚሆኑ በዝተው የለ እንዴ?
- በዚህ ዘመን ግን በልማታዊ አቅጣጫ ከተመራህ በግማሽ ሰዓትም ይሳካል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እውነትዎን ነው?
- ስዋሽ ታውቀኛለህ?
- አሁን ገና አሳቁኝ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤት ሲደርሱ ባለቤታቸው እየጠበቋችው ነበር]
- እንዴት አመሸሽ ውዴ?
- አለሁልህ፡፡
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- ስልኬ ሲጮህ ነው የዋለው፡፡
- በደህና ነው?
- ምን ደኅንነት አለ ብለህ ነው?
- ምነው?
- ሁሉም እየደወለ አማልጂኝ ይላል፡፡
- ከማን ጋር?
- ከአንተ ጋር ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምን ምክንያት?
- በፈረደበት 40/60 ነዋ፡፡
- ምን ለመሆን?
- ዕጣው ውስጥ ለመካተት፡፡
- የቤቱ ጉዳይ እኔን አይመለከትም፡፡
- ማንን ነው የሚመለከተው ታዲያ?
- ባንኩን ነዋ፡፡
- እንደምንም ብለህ ለሦስቱ እንኳ ተሟሟትላቸው እባክህ?
- አይመለከተኝም አልኩሽ፡፡
- እንደምንም ብዬ እንደማግባባህ ቃል ገብቼላቸው ነበር፡፡
- ፀረ ልማት ቃል ከአፍሽ ባይወጣ ጥሩ ነበር፡፡
- ለምን እባክህ?
- ከአቅም በላይ ነው፡፡
- ይህችም ውለታ ሆና ከአቅም በላይ ሆነች?
- ስላልገባሽ ነው፡፡
- ምኑ ነው የማይገባኝ?
- 40/60 ቤቶች ላይ ዓይኖች በዝተዋል፡፡
- ለምን?
- ቤቶቹን አይተሻቸዋል?
- አውቃቸዋለሁ ይኼን ያህል ናቸው፡፡
- መንግሥት ቤት ባይሰጠኝ ኖሮ እኔም ዕጣ ውስጥ ብገባ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
- ምን አልክ የተከበርከው ሚኒስትር?
- እነዚህ ቤቶች እኮ ውብ ናቸው፡፡
- አንተ ሰው ያምሃል እንዴ?
- ምነው?
- ሰው መዋኛ ያለው ግዙፍ ዘመናዊ ቪላ ይመኛል አንተ ግን. . .
- እኔ ምን?
- ተወው የእኔ ዕድል ነው፡፡
- የአንቺ ዕድል ምን ሆነ ደግሞ?
- ዕድሌማ እንደ ቢዝነስ ሰው ሳይሆን. . .
- ምን?
- እንደ ደረቅ ካድሬ ከሚያስብ ጋር አቆራኝቶኝ ነዋ፡፡
- ይኼን ፀረ ልማት አስተሳሰብሽን ተይ ብያለሁ፡፡
- አንተም እኝኝኝ አትበልብኝ፡፡
- አንቺም እንደ ፀረ ሰላም ኃይሎች አትሁኝብኝ፡፡
- እንዴት እባክህ?
- ሰላሜን ነሳሽዋ?
- ትልቅ ነገር እንደ መመኘት. . .
- እና?
- ዝም ብለህ አነስተኛና ጥቃቅን ትወዳለህ፡፡
- አነስተኛና ጥቃቅን እኮ የልማታችን አጋር ነው፡፡
- አንተ ሰውዬ?
- አቤት?
- እንዲህ ዓይነቱን የሰቸለ አባባልህን ሌላ ቦታ ተጠቀም፡፡
- ለምን?
- ስሰማው ያቅረኛል፡፡
- አንቺ ጤና የለሽም እንዴ?
- አንተን በሽተኛውን ልጠይቅህ እንጂ?
- እኔ በሽተኛ?
- ታዲያስ?
- እንዴት እባክሽ?
- ጓደኞችህ የትና የት ተተኩሰዋል. . .
- እኔስ?
- አንተማ ገና ከመሬት አልተነሳህም፡፡
- እስቲ ይህንን አባባል ተርጉሚልኝ?
- ተቸክለሃል!