Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በመንግሥት ፋይናንስ ማስቀጠል አዳጋች መሆኑ ይፋ ተደረገ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በመንግሥት ፋይናንስ ማስቀጠል አዳጋች መሆኑ ይፋ ተደረገ

ቀን:

  • ለቤት ፈላጊዎች መሬት ማቅረብ በአማራጭነት ተጠቁሟል

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በመንግሥት ፋይናንስ ማስቀጠል ትልቅ ጫና በመንግሥት ላይ በመፍጠሩ፣ ሌሎች አማራጮች እየተዳሰሱ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በመንግሥት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ቤቶች ቀደም ሲል በርካታ ቤቶች በመጀመራቸውና ሥራው ግዙፍ በመሆኑ ለቤት ልማቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 750 ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ በበጀት ያልተደገፈ በመሆኑ ዕቅዱን ለማስፈጸም ትልቅ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የበጀት ችግሩን መፍታት እንዳልተቻለና በ2009 በጀት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፈቀደው የቤት ልማት ፋይናንስ በመዘግየቱ፣ ሥራ ተቋራጮችና ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሥራ በማቆም ተበትነው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በስተመጨረሻ የአዲስ አበባ አስተዳደር ቦንድ በማስያዝ 15 ቢሊዮን ብር ማግኘት የቻለ መሆኑን፣ ይህም ከ170 ሺሕ በላይ ቤቶች ግንባታ ማስፈጸሚያ እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በቦንድ ከተፈቀደው 15 ቢሊዮን ብር ውስጥ 8.6 ቢሊዮን ብር በመለቀቁ ሥራውን ማስቀጠል መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም የተጀመሩ 1,292 ቤቶች ግንባታቸውን ተጠናቆ ከንግድ ባንክ ጋር የቤት ርክክብ መደረጉንና በሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት ዕጣ በማውጣት፣ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎቹ እንዲተላለፉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡    

እንዲሁም የ20,932 ቤቶች ግንባታ አፈጻጸም ወደ 69 በመቶ መድረሱን፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጀመሩ 17,005 ቤቶች ግንባታ በአማካይ 35.4 በመቶ መድረሱን ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡

የ20/80 ቤቶች አፈጻጻምን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ በ2006 ዓ.ም. የተጀመሩና በሁለት ፓኬጆች የተካተቱ 52,651 ቤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በፓኬጅ አንድ የተያዙት 26,480 ቤቶች ሲሆኑ አፈጻጸማቸው በአማካይ 65.52 በመቶ እንደደረሰ፣ በሁለተኛው ፓኬጅ የተካተቱ 26,171 ቤቶች አፈጻጸም ደግሞ በአማካይ 48.3 በመቶ እንደደረሰ ጠቁመዋል፡፡

በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጀመሩ 41,421 ቤቶች አፈጻጸም ደግሞ 33.91 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በመንግሥት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ቤቶች ቀደም ሲል በርካታ ቤቶች በመጀመራቸው፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የበጀት ጫና መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መስጠታቸውንና በካይዘን አሠራሮችን ከላይ እስከ ታች ድጋፍ ሥርዓት ተፈጥሮ እየተሠራ ቢሆንም፣ ለቤት ልማት የሚያስፈልገው ፋይናንስ በወቅቱ አለማግኘት፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ዘመናዊ አለመሆን፣ የማስፈጸም አቅም ችግር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እክል ፈጥረዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተያዙትን 750 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት ከፍተኛ ፋይናንስ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የአገሪቱ የልማት ፍላጎቶች በርካታ በመሆናቸው ሌላ አማራጭ መፈለግ አለስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹በመሆኑም መሬት አዘጋጅቶ በማቅረብ የማኅበራት ቤቶች ግንባታን ማስፋፋት ዋነኛው አማራጭ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቤት ፈላጊዎችን ከግንባታ ተቋራጮች ጋር በማጣመር የቤት ፍላጎት እንዲመለስ የማድረግ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ መንገድ ቤት ፈላጊው ዘንድ ያለውን አቅም አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሰጠው አስተያየት የፋይናንስ ችግሮችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በፍጥነት ተነጋግሮ መፍታት ያስፈልጋል ብሏል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...