እነሆ መንገድ። እንደ ሾተላይ ልጅ አለቀለት ሲባል በጠፋው ተስፋ ልክ ተስፋ እያገረሸው፣ ሊቀበር ባለበት መሬት ሕይወት ዘርቶ አዲስ ወኔና ጉልበት ይጓዛል። እግር ውሎ ይግባና። የመንገዱና የመንገደኛው አመል እንደሆነ ለወሬ አልመች ብሏል። ያውም የወሬ ‹ታለንት› እኩል በተካፈለባት ምድር። ‹‹ወሬ ጠፋ ትለኛለህ?›› ሲል የምሰማው ወያላውን ነው። የዛሬ ወያላችን ሾፌራችንን በዕድሜ ይበልጠዋል። ክንዱ ሳይበቃው ገጹ በፈርጣማ ክፍልፋይ ጡንቻው ተከፋፍሎ ወጣት ባይመስል፣ አንዴ አይደለም ሁለት ጊዜ ወልዶ ያደርሰዋል ይባልለታል። ብላቴናው ሾፌራችን የታላቁን ወያላ ስላቅ እያጣጣመ፣ ‹‹የወሬ እናት ሞተች አሉ። ለጊዜው የልማት እናት አንደኛ ተጠርጣሪ ተብላ ተይዛለች አሉ፡፡ ወሬን ተራራ፣ ተራራ አልኩኝ . . . ኢቢሲ አይደብቀውም አሉ፤›› ይለዋል። ‹‹ተው እንጂ!›› ወያላው ያዳንቃል። ተሳፋሪው አንድ በአንድ ወደ ታክሲያችን እየዘመተ መቀመጫውን እየያዘ ነው። የወያላውና የሾፌሩ ነገረ ሥራ ተሳፋሪውን በድራማ እያማለለ የሚሸቅል እንጂ፣ የግላቸውን ፍሬፈርስኪ የያዙ አይመስሉም። ወያላው ቀጥሏል።
‹‹እና ‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች› ስለጉዳዩ ምን ገለጹ ተባለ?›› ያሽሟጥጣል ወያላው። ብላቴናው ተረበኛ ዘዋሪ ተቀብሎ፣ ‹‹ዌል እንግዲህ ብዙ ብለዋል። ለምሳሌ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠቀሰ የመዲናችን ነዋሪ እንደገለጸው የወሬን እናት የልማት እናት ‹መርደር› ማድረጓ በእውነቱ ‹ሪል› ከሆነ ለአገሪቱ ‹ፊውቸር› ጥቅሙ የጎላ ይሆናል ብሏል። ሌላዋ እንዲሁ ስሟም መልኳም እንዲጠቀስ ያልፈለገች ወጣት ደግሞ በእውነቱ ‹ፌር› አይመስለኝም። ማንም ገደለ ማንም ሞተ ወሬን ያህል ‹ሂውጅ የሶሳይቲ› ቤንዚን እንዲህ አቅሎ ማየት የኋላ የኋላ ሂውጅ ኮስት ያስከፍላል ብላለች…›› ሲል ገሚሱ ግራ ተጋብቶ ገሚሱ እየተዝናና ሲያዳምጠው ቆየ። ድንገት ወያላው፣ ‹‹ከሁሉ ከሁሉ እኔን የገረመኝ ቋንቋችን ራሱ ስደተኛ በሆነበት ዘመን ስደትን አውጋዡ ነው…›› ብሎ በሩን ከረቸመውና ወደ ተሳፋሪው መለስ ብሎ፣ ‹‹ሲሪየስሊ!›› አለ ሸራፋ ጥርሱን እያስቃኘ። አቤት የዘመኑ ወሬና አወራሩ። ማማሩ ወይስ መምረሩ!
ጉዟችን ተጀምሯል። ጭቅጭቁም አብሮ ጀምሯል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየሙ ተሳፋሪዎች ናቸው። አንደኛው “ምን ያጋፋሃል? ድንበርህን ብትጠብቅ ይሻልሃል፤” ማለት። “ማን ያሰመረው ድንበር ነው? ወንበር እኮ ነው፤” ብሎ ያ ማባባስ። “ምንድነው ሽብሩ?” ብሎ ጎልማሳው ወያላ መገላገል ያዘ። “አታየውም እንዴ እግሩን እላዬ ላይ ሰቅሎ?” ይደነፋል ከሳሽ። “ወንበሩ ሰፊ ነው፣ ደግሞ እግሩን አልጫነብህም፤” ብሎ ወያላው አይቶ ፈረደ። “ለምን ይታከከኛል?” ከሳሽ ነገር ነገር አለው። “ታክሲ ውስጥ ነው እኮ ያለኸው ወንድም? የግልህ ሊሞዚን አደረግከው?” ተከሳሽ እያባሰው ሄደ። “በቃ ወደ ግዛቴ አትምጣ ማለት አትምጣ ነው፤” ከሳሽ ደረቅ ቢጤ ይመስላል። “ፌዴራሊዝም ታክሲ ተሳፍሯል እንዴ?” ትላለች ባለሻሿ። ሸሪፎ፣ “ተይው ሰዓቱ ደርሶ ነው እንዲህ የሚሆነው፤” እያላ ያዛጋል።
“ሲከር ይበጠሳል ተስማሙ እስኪ…” ብለው አንድ አዛውንት መሸምገል ያዙ። ‹ፈርስት’ እሱ ሥርዓት ይያዝ፤” አለ ከሳሽ። “አዛውንቱ ‘ፈርስት’ የሚባል አማርኛ የለም። በቅድሚያ አትልም?” ብለው እንደለመዱት ሲጦፉ፣ “አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ እስካልሆነ ድረስ ‹I don’t care›…›› ብሎ ጮኸባቸው። እሳቸው እንዳቀረቀሩ ቀሩ። ወዲያው መውረጃው ደርሶ ‹‹ወራጅ!›› ሲል አዛውንቱ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው፣ “በላ ወንበርህን ይዘህ ውረድ፤” አሉት ድንበር ድንበር ሲል የቆየውን። ይኼኔ አመዱ ቡን። አዛውንቱም፣ “ጊዜና ታክሲ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር አንድ ቀን ፈልገን ሳይሆን ሳንፈልግ ከተሳፈርንበት የምቾት ኮርቻ ላይ ማስወረዳቸው ነው። ስንሞት ሁሉ ቀሪ ነው። ስንኖር ግን ከተጋራናነው መሬቱ፣ ሳሩ ቅጠሉ፣ እንስሳቱ ሁሉ ለእኛ ነው። እስኪ እንቻቻል? በድንበር፣ በክልል፣ በቀዬ ተቀያይመን ስለኖርን ባስከበርነው ይዞታ አፈር አንቀበር። መሬቱስ ችሎናል ምናለበት እኛ ብንቻቻል?” ሲሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ስቆባቸው ወረደ። አውቆ አበዱ ባሰን እኮ ዘንድሮ!
በአንድ ሁከተኛ የተነሳውን ግብግብ ለማስረሳት የተሳፈሪውን ቀልብ ለመሳብ ይመስላል ሾፌሩ ሬዲዮ ከፍቶ የሰዓቱን ዜናዎች ያስደምጠናል። “አይ አንተ ፈጣሪ ሩሲያን ከተረሳችበት አስታውሰህ እንዲህ በየአርዕስተ ዜናው ስሟን ያስናኘኸህ አምላክ፣ እባክህ እኛንም አስታውሰን እባክህ?” ይላል ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ እጆቹን ዘርግቶ። ይኼን ጊዜ አጠገቡ የተቀመጠው ወጣት፣ “ደስ አይልም?” ብሎ ፀሎቱን አቋረጠው። “ምኑ?” ሲለው፣ “ለጉልቤም ጉልቤ ሲያዝበት ደስ አይልም?” አለው። ጎልማሳው፣ “ደስ ይል ነበር። ግን ጉልቤ ሲበዛ ደግሞ ጥሩ አይደለም። በዚያ ያ ጎረምሳ ሚሳይል ያስወነጭፋል። በዚህ አክራሪ ነኝ ባይ አረመኔ በየአገሩ ሰው ያርዳል። ማን ለማን ነው የታዘዘው እስኪ?” ብሎ መልሶ ሲጠይቀው፣ “ዋናው ላይ ነዋ። ምሥራቅ ለምዕራብ መታዘዝ መናዘዝ ጀመረ። አሜሪካ እንዲህ አድርጋ፣ አሜሪካ እንዲህ ቆንጥጣ፣ አሜሪካ እንዲህ ስቃ፣ አሜሪካን ትን ብሏት… ከሚል ዜና ዕድሜ ይስጣቸውና እነ ፑቲን፣ እነ ኪም ጆንግ ኡን ጆግ ስሙም ልቡም አይያዝልኝም፣ ብቻ ገላግለውናል። እሱ ያለ ቀን ደግሞ እኛም…” ብሎ ሳይጨርሰው፣ “በል በል ወንድም። እኛ ከዚህ በላይ ማዕቀብ የሚችል ትከሻ የለንም። እንኳን አዲስ ለሚጣል ማዕቀብ ኑሮንም አልቻልነው…” ብሎ ጎልማሳው አቋረጠው።
“እስኪ ስላቁን ተውትና አንዴ ዜና እንስማበት?” ሲል ከኋላ መቀመጫ፣ “ሰው በዜና ብቻ አይኖርም በስላቅና ሽሙጥ ጭምር እንጂ ብለህ ጥቅስ ለጥፍማ፤” ይላል ጎልማሳው። “አንዳንዶቻችሁ የምታስወነጭፉት ሚሳይል የት ላይ እንደሚያርፍ እያስተዋላችሁ፤” ብሎ ወያላው ማስጠንቀቂያ ቢጤ ሲወረውር መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ተኮራኩረው የሳቁ እስኪመስል ድረስ በሳቅ አሽካክተው፣ “ፀረ ሚሳይል መግዛት ነዋ። ደግሞ ለዚህም ተበደሩና ግማሹን ቆርጣችሁ ኑሯችሁን አደላድሉበት አሏችሁ። ግን ሰሞኑን እንዴት ነው? ከቁጥሩ ነው ከጆሯችን? ተበጀተ ሲባል የምትሰሙት የሚሊዮን ብዛትና ዓላማው እየተመጣጠነላችሁ ነው?” ትላለች። “ማንን ነው? ይኼ ጆሮዬ እኮ እንቢ አለ በቃ፤” ብለው አዛውንቱ ከጎናቸው ያለውን ቢጠይቁት፣ “እንኳን ቀረብዎ፣ እንኳንም አልሰሙ፤” ብሏቸው ሲያበቃ፣ “ምነው ጆሮ እንደሚያከራክር ሁሉ ሆድም የሚያንገራግር ሆኖ ቢፈጠር?” አለን ወደ እኛ ዞሮ። ወይ ታክሲና አፍ!
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወያላው ሒሳቡን ተቀብሎ መልሳችንን አድሎ ከጎኑ ክሩን ከሚያስደግፍባት መቀመጫ ላይ ለሚተዋወቃት ቆንጆ ሰፋ ያለ ቦታ መርቶ፣ “እንዴት ነሽ እባክሽ?” ይላታል። “እባክህ ጋብዘኝ፤” ትለዋች ደኅንነቱን ትታ። “አንቺ በቃ ካለ ጋብዘኝ አታውቂም?” ይላታል። “አንተስ ሰላም በጠፋበት በዚህ ጊዜ አሥር ጊዜ እንደ ጀማሪ አፍቃሪ ደህና ነሽ ደህና ነሽ አይሰለችህም?” አለችው። “እንኳን አሥር መቼ ሁለት ጊዜ ጠየቅኩሽ?” ሲላት፣ “ትናንት ተገናኝተን ጠይቀኸኝ መልሼልሃለሁ። አለቀ! ወር ሳይሞላህ እንዳትጠይቀኝ፤” ብላ ተቆናጠረችበት። “ጉድ ነው እንደ ቤት ኪራይ ክፍያ ጤና ይስጥልኝም ወር በገባ ሆነ ደግሞ?” ብሎ አጠገቧ ተጨናንቆ የተቀመጠ ወጣት አሽሟጠጠ። “አዎ። በኪራይ ኖረን በመዋጮ እየተቀበርን እስኪ አሁን በየቀኑ ጤና ይስጥልኝ ስንባባል አያቅርም?” አለችው መለስ ብላ። “አይምሰልሽ አቦ ደሃ ከጤናው በቀር ሀብት የለው፤” ወያላው ስብከት ጀመረ። “እኔስ ገንዘብ ቢሰጠኝ ነበር የምመርጠው። ጤና በኪራይ ቤት በቀን አንዴ እየተበላ በራሱ ካንሰር በለው፤” ብሎ መሀል ረድፍ የተሰየመ ኮልታፋ ጨዋታውን አፋፋመው።
“ኧረ ተመስገን ነው እናቴ። ይኼንንስ ማን አየብን?” ብለው አጠገቡ የተቀመጡ አዛውንት ሲናገሩ፣ “ድሮስ ማን ያይብናል እማማ? ነው ወይስ ጉዳይ ለማስፈጸም የኩላሊት ጉቦ ስጡን መባል ተጀመረ?” አላቸው። “ኩላሊት? እኮ ይኼ እዚህ ከሙሃይቴ ከፍ ብሎ የምነካው ጎኔ ሥር ያለውን ማለትህ ነው?” አዛውንቷ የምራቸውን ደነገጡ። “እህ ሌላ አለ?” አላቸው ግራ ገብቶት ግራ አገባባቸው። “ሞልቶ! የበግ አለ። የበሬ አለ። የፍየል አለ…” ሲሉ ፈገግ አስባሉን። ይኼን ጊዜ ኮልታፋው፣ “አይ እማማ። እሱማ ድሮ በደጉ ጊዜ ቀረ። አሁን ማን ይሙት የበግ ኩላሊት እንደ ልባችንና እንደለመድነው፣ እንዳሻን የምናገኝ ቢሆን ኖሮ የገዛ ኩላሊታችንን እየበላን እንጨርሰው ነበር?” ሲላቸው እስኪያስነጥሳቸው ከት ብለው ሳቁ። “ቆይ ግን ኩላሊት በመብላት ኩላሊት ይጠገናል እንዴ? ግራ አጋባን እኮ ሰውዬው!” ስትል ደግሞ አንዷ፣ “ኤችአይቪ እንደ አዲስ አገርሽቶ ወገኖቻችንን በዝምታ እየጨረሰ እናንተ ስንት ምልክትና ድምፅ ያለውን ኩላሊት ታነሳላችሁ?” አለ ጎልማሳው። “ይደንቃል እንዴ ይኼ? ሲከፋን ሆነ ስንደሰት በዓል ሲሆን ሐዘን፣ የፈንጠዝያ የስካር፣ የዳንኪራና የድሪያ ልፈፋ በተቆጣጠራት አገር ኤችአይቪ አይደለም ማንሰራራት ጠቅልሎ እንደ ሞኝ ጉርሻ ቢውጠን ይገርማል?” ብላ ወጣቷ ደነፋች። መልስ የመለሰላት አልነበረም። ወያላው መጨረሻ ብሏል። በካቻምናው ሕመም ዘንድሮ ልንሞት? እግዚኦ! መልካም ጉዞ!