Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለዕርዳታ ፈላጊዎች መድረስ ካቃተው መቶ በመቶ እኛ እንሸፍናለን››

አቶ ምትኩ ካሳ፣ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር

አቶ ምትኩ ካሳ ለ30 ዓመታት በተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሠርተዋል፡፡ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ዞን ባሉ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ፣ በተለይ ከፕላንና ኢኮኖሚ ጋር በተያያዙ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕላን ቀጣና ጽሕፈት ቤት፣ የቦረና ፕላን ኮሚቴ፣ የጌዴኦ ዞን የፕላንና ኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤቶች ከሠሩባቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚያም በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ሥር በሚገኘው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ መምርያ ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተመድበው የሠሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ነው፡፡ ከዚህ ኃላፊነታቸው በኋላ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ይርጋለም ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ምትኩ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሳይንስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ኔዘርላንድስ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዳዊት ታዬ በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ድርቅ የዕለት ዕርዳታ ፈላጊዎች ከሚሰጥ ዕርዳታ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለውን እንቅቃሴ፣ እንዲሁም በቅርቡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሰኔ ወር በኋላ የምሰጠው ዕርዳታ የለኝም በማለት በይፋ ከማሳወቁ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ብዥታ ላይ አቶ ምትኩን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት ኮሚሽን ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ከዕርዳታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለያዩ ስያሜዎች ከ40 ዓመታት በላይ የቆየም ነው፡፡ በቀድሞና በአሁኑ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? አመሠራረቱና ተልዕኮውን ይግለጹልኝ?

አቶ ምትኩ፡- የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት የሚባለው መዋቅር ከ1966 ዓ.ም. ድርቅ በኋላ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመ ነው፡፡ ለማቋቋምም ምክንያት የሆነውም በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል የደረሰው የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ተብሎ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መልኩን እየቀያየረ በመምጣት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚል ስያሜም ነበረው፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ከምግብ ዋስትና ቢሮ ጋር በማዋሀድ የአደጋ መከላከል ዝግጅትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሆኖ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተዋቅሮ በሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራ ተቋም ሆኖም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ኃላፊነትን ለመወሰን በወጣው አዋጅና ኮሚሽኑን ለማቋቋም በወጣው ደንብ መሠረት፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚል መጠሪያ ተሰጠው፡፡ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ስንል በአደጋ ሥራ አመራር ሥር ያሉትን ሁሉንም ዘርፎች ያካተተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹን?

አቶ ምትኩ፡- መከላከል፣ ማቅለል፣ ዝግጁነት፣ ምላሽ መስጠት፣ ማገገምና መልሶ ማቋቋም የሚሉትን ስድስት የሥራ ክፍፍሎች የያዘ ነው፡፡ እነዚህን የሥራ ዘርፎች ይዞ ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ ከነበረው አሠራር በተለየ እንዲሠራ የተደረገ ነው፡፡ በዚህም ከቀድሞ አሠራሩ በተለየ እንዲዋቀር የተደረገ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የነበረውን አሠራር ስንወስድ ገጠርና ድርቅ ተኮር ነበር፡፡ በአጠቃላይ ገጠር ላይ ርብርብ የሚያደርግና ብሎም ከአደጋዎች መካከል ድርቅን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አንዱ ልዩነት ይህ ነው፡፡ አሁን ከአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት አንፃርና ከአየር ንብረት ለውጥ ስንነሳ የአደጋዎች በዓይነት መከሰት ነገሩን እንድናጤን አድርጎናል፡፡ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር አያይዘን ስናይ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ የጎርፍ አደጋና የደን ቃጠሎ ሰፍቷል፡፡ ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞም የከተሞች እሳት ቃጠሎ ይኖራል፡፡ ወደፊት ከባቡር መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል አደጋ ሊኖር ይችላል፡፡ በከተሞች ከሕንፃ መስፋፋት ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሕንፃ መደርመስና ቃጠሎ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ አደጋ ድርቅ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ እየሆነ መጥቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ኮሚሽኑ በድርቅ ላይ በመሥራት ይሠሩ የነበረውን በሌሎች አደጋዎችም አጠቃሎ የሚሠራ ሆኗል ማለት ነው?

አቶ ምትኩ፡- አንዱ እሱ ነው፡፡ ሁለተኛ አደጋዎች በሰፋ ቁጥር የአንድ መሥሪያ ቤት ብቻ ኃላፊነት አይሆንም፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት አደጋዎችን ብንወስድ ቅርብ የሆነው መሥሪያ ቤት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የበሽታው ወረርሽኝ ቢኖር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡ ከአደጋዎች ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቶች ቢፈርሱና የውኃ መጥለቅለቅ ቢደርስ፣ ለትምህርት ቤቶች ቅርብ የሆነው ትምህርት ሚኒቴር ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ ሌሎቹም መሥሪያ ቤቶች ከእነሱ ኃላፊነት ጋር የተያዙ ሥራዎች አሉዋቸው፡፡  በዚህ መነሻ የአደጋዎችን ባህሪ በተከተለ አግባብ እያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ ሌላው እንደ ልዩነት የሚወሰደው ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር አደጋው ከደረሰ በኋላ ነው ምላሽ ለመስጠት የምንሯሯጠው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት የመከላከል ሥራ ይከናወናል፡፡ ለምሳሌ ድርቅን ብንወስድ ድርቅ ከእርጥበት እጥረት ነው የሚመጣው፡፡ ድርቅን ለመከላከል አንዱ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ የውኃ ጥበቃ ነው፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጎለብት በማድረግ መስኖን በመጠቀም ሰብል ማምረት ይቻላል መስኖን በመጠቀም ሰብል ማምረት ብንችል ድርቁን ትርጉም ባለው መንገድ ይቀንሰዋል፡፡ በአርብቶ አደሮች አካባቢም የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ መስኖን በመጠቀም የእንስሳት መኖ እናለማለን፡፡ ይህም ድርቅ በሚኖርበት ጊዜ በመስኖ የለማውን መኖ በማቅረብ ድርቁን መቋቋም ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ በተጨባጭ ተግባራዊ እየተደረገ ነው?

አቶ ምትኩ፡- አዎ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የት?

አቶ ምትኩ፡- በሶማሌና በአፋር ክልሎች ሠርተናል፡፡ 1,400 ሔክታር መሬት በመስኖ መኖ እየለማ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጎርፍ አደጋ መከላከልን የሚመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ ድሬዳዋ ከተማን ብንወስድ ባለፈው ዓመትም ጎርፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአሥር ዓመት በፊት ደርሶ እንደነበረው ዓይነት ጉዳት አላደረሰም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ቀድሞ በተሠራው ሥራ ነው፡፡ ጎርፍ ተንደርድሮ ወደ ድሬዳዋ ከተማ እንዳይመጣ ተደርጓል፡፡ ይህ የመከላከል ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ምላሽ የመስጠት ብቻ ሳይሆን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ዝግጁነትን ብትወሰድ ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ 643 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት አለ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ምግብ ነክ ያልሆነ ክምችትም አለ፡፡ ይህም አደጋዎች ቢከሰቱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ምላሽ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ሥጋት አመራር የተሸጋገረ ጭምር መሆኑን ነው፡፡ ሌላው መሠረታዊ ለውጥ ያለው ከዓለም አቀፍ መድረኮች ጋር የማጣጣም ሥራ ነው፡፡

ሌላው እስካሁን ያልተተገበረውና ወደፊት የምንተገብረው አሠራር አለ፡፡ ከሕገ መንግሥታችን አንፃር የሚታይ ነው፡፡ በፊት የነበረው ፖሊሲ የወጣው በ1986 ዓ.ም. ነው፡፡ ሕገ መንግሥታችን የፀደቀው ደግሞ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ነው፡፡ ስለዚህ ቀደም ብሎ የነበረው አደጋ የመከላከል ፖሊሲ (1986) የወጣው ሕገ መንግሥቱን አያውቀውም ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ፌዴራል አወቃቀር ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ አለ፡፡ የኢኮኖሚ መብቶች የሚያስጠብቅበት ከፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን አጋርነት በመውሰድ፣ የክልሉ ችግር በሆኑባቸው ዘርፎች ላይ የሚሠራበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ እሱን ተከትሎ የአደጋ ሥጋት አመራር ሥራ ይህ መደረጉ ክልሎች ከመከላከል ጀምሮ የምላሽ ሥራ እንዲያከናውኑ ያስችላል፡፡ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲሠሩም ያደርጋል፡፡ ስለዚህ አደጋ ወደፊት ሲኖር ምላሽ መስጠት የሚጀመረው ከወረዳው ነው፡፡ ራሱ ነው ምላሽ የሚሰጠው፡፡ ለምሳሌ ጎርፍ ቢከሰት ወደ ፌዴራል አይመጣም፣ ራሱ ነው ምላሽ የሚሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- አቅም ይኖራቸዋል?

አቶ ምትኩ፡- አዎ፡፡ ለዚህ ተብሎ ሀብት ይያዛል፡፡ ከወረዳው አቅም በላይ ከሆነ ዞን፣ ከዞኑ በላይ ከሆነ ክልል፣ ከክልል አቅም በላይ ከሆነ ክልል ለክልል ይሠራበታል፡፡ ከክልሎች በላይ ከሆነ ፌዴራል ይገባበታል፡፡ ፌዴራል በክልል ደረጃ የማይሸፈኑ ሥራዎችን ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ እሳት ማጥፊያ ሔሊኮፕተሮች፣ አውሮፕላኖችና ትልልቅ ማሽኖች ቢኖሩ በፌዴራል ደረጃ ይያዛሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን በክልል ደረጃ መያዙ አስፈላጊ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከገለጻዎ መረዳት እንደቻልኩት ኮሚሽኑ ጥቅል የአደጋ መከላከል ሥራዎች ኃላፊነት አለበት፡፡ የጎርፍ፣ የእሳት፣ የድርቅና ሌላም አደጋዎች ላይ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ  ሰሞኑን ለንደን በአንድ ሕንፃ ላይ የደረሰውን ዓይነት የእሳት አደጋ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ በሕንፃ ላይ ቢደርስ፣ ቃጠሎውን ለመከላከል የሚያስችሉ መሣሪያዎች ታጥቃችኋል?

አቶ ምትኩ፡- ይህንን ነገር በሁለት መንገድ ልናይ እንችላለን፡፡ አንደኛ በተለይ በከተሞች እሳት አደጋ ላይ በጣም መሥራት ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣንን ብንወስድ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ያለው አቅምና አሁን ያለው አቅም አንድ አይደለም፡፡ አሁን አቅሙ ጨምሯል፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እዚህ ፊት ለፊታችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ45 በላይ ፎቅ ያለው ሕንፃ እየገነባ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለን የእሳት አደጋ መከላከል አቅም 45ኛ ፎቅ ላይ እሳት ቢነሳ ማጥፋት ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከትራንስፖርት ዘርፍ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አደጋ ቢከሰት ምን መደረግ አለበት? የሚለውም መታየት አለበት፡፡ ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ መታሰብ ያለባቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ፡፡ በተለይ ከፍሳሽ ማስወገጃዎች  ሲስተማችን ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት ራሱ ትልቅ ችግር ያለበት ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከ85 በመቶ በላይ ሕዝባችን ገጠር በመኖሩ ለእሱ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከተሞች እያደጉ ነው፡፡ የገጠር ድርሻ እየቀነሰ የከተማ ድርሻ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ይህ ከሆነ ለገጠር የሰጠነውን ዓይነት ትኩረት ለከተሞችም ሊሰጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ከተሞቻችን ለአደጋ አይበገሬ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የዓለም ባንክ በአንዳንድ ከተሞች ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ አሥራ አንድ ከተሞች ላይ ባነጣጠረው በዚህ ጥናት የትኞቹ ከተሞች ናቸው ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑት፣ የትኞቹ ናቸው ለመሬት መንሸራተትና ተመሳሳይ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑት ብሎ በደንብ ለይቷል፡፡ ክልሎች በዚህ ዕቅድ ልክ ያቅዳሉ፡፡ የሰው ኃይል፣ የማቴሪያል ሀብትና የፋይናንስ ሀብታቸውን በዚያው ልክ እንዲያሳድጉ ተደርጎ አደጋን በአግባቡ መመከት የሚችሉበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ግን ገና እያደገ ያለ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመሥሪያ ቤታችሁ ስም ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው አገልግሎታችሁ ከድርቅና ከዕርዳታ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው፡፡ በየዓመቱ የዕለት ዕርዳታ እየተጠየቀ ዜጎች ዕርዳታ ሲሰጣቸው ይታያል፡፡ በየዓመቱ ድርቅ አለ እየተባለ ይለመናል፡፡ ዓምና ነበር፣ ዘንድሮም ተከሰተ፡፡ አሁንም ዕርዳታ እየተጠየቀ ነው፡፡ ድርቅ ተከሰተ እየተባለ ዕርዳታ እየተለመነ ነው፡፡ ይኼ መቼ ይቆማል?

አቶ ምትኩ፡- በመሠረቱ እኔ ድርቅ ይቆማል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ድርቅ ይኖራል፡፡ ግን ሁሌም ዕርዳታ ይጠየቃል?

አቶ ምትኩ፡- መጀመርያ ድርቁ የማይቆምበትን ነገር ላስረዳ፡፡ የኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የግብርና ሥነ ምኅዳር ብዝኃነት፣ የአግሮ ኢኮሎጂካል ዳይቨርሲቲና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡን ስናይ በአገራችን ያለውን የዝናብ ሁኔታ በሚወስኑ ሁለት ውቅያኖሶች ማለትም ሰላማዊ ውቅያኖስና ህንድ ውቅያኖስ ተፅዕኖ ሥር ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ትሮፒካል ፓስፊክ ኦሽን ለአምስት ተከታታይ ወራት ከ0.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሞቆ ሲቆይ ኤልኒኖ ይኖራል፡፡ ኤልኒኖ ካለ ደግሞ ድርቅ አለ ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኤልኒኖ ሲቀንስ ላኒና ይኖራል፡፡ ላኒና ሲኖር ደግሞ ጎርፍ አለ፡፡ ስለዚህ ጎርፍና ድርቅ ከዚህ ይመነጫል፡፡ ወደ ህንድ ውቅያኖስ ስንመጣ ሰሜናዊና ምሥራቃዊ ክፍሉ ሲሞቅና ምዕራባዊ ክፍሉ ሲቀዘቅዝ ኔጌቲቭ ኢንዲያን ኦሽን ‹ዲያፓል› የሚባል ነገር አለ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የአገራችን ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ በድርቅ ይጠቃል፡፡ አሁን የምናየውን በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን ድርቅ ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ እውነታ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጡን እያባባሰው መጥቷል፡፡ ድሮ በረዥም ዓመታት (ከ10 እስከ 12 ዓመታት) ይታይ የነበረው በሁለትና በሦስት ዓመታት እንዲከሰት እያደረገ ነው፡፡ ይህ በመኖሩ ኢትዮጵያችንን ካለችበት የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የትም መውሰድ አንችልም፡፡ ይህ ስላለ እኛ ማድረግ የሚገባን የድርቅን ዑደት መስበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ምትኩ፡- የድርቅን ዑደት ለመስበር የውኃ ልማት ላይ ማተኮር ነው፡፡ እርጥበት እቀባ ላይ መሥራት ነው፡፡ ለዚህም አነስተኛና ከፍተኛ የመስኖ፣ የደን ልማት ላይ መሠራት አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ የግብርና ሥርዓታችንን ዘመናዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የግብርና ምርታማነትን መጨመር ያሻል፡፡ በዓመት ሁለት ሦስት ጊዜ ማምረትን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ገዥው የመስኖ ልማት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግራችንን ማፋጠን ነው፡፡ ይህም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምንመጣበትን ፍጥነት መጨመር የምንችል ከሆነ፣ ድርቅ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ትርጉም ባለው መልክ መቋቋም እንችላለን እንጂ ዕርዳታ በራሱ የሕመም ማስታገሻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዕርዳታ የሕመም ማስታገሻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ፈውስ እያመጣም፡፡ ይህ ከሆነ በተደጋጋሚ ድርቅ ተከሰተ ተብሎ በየዓመቱ ዕርዳታ እየተጠየቀ ነው፡፡ መንግሥትም ከራሱ በጀት ይመድባል፡፡ ይህ ድግግሞሽ ደግሞ ቀጥሏል፡፡ ዓምና 10.2 ሚሊዮን ተረጂዎች ነበሩ፡፡ ይህ አለፈ ተባለ፡፡ እንደገና ዘንድሮ መጣ፡፡ ዘንድሮም ዕርዳታ ይሰጠን እየተባለ እየተጠየቀ ነው፡፡ መቼ ነው በራስ አቅም እንዲህ ያለውን አደጋ መቋቋም የሚጀመረው?

አቶ ምትኩ፡- ይህንን ነገር ጀምረናል፡፡ ድርቁ እንዴት መሰለህ? አዝማሚያውን ላሳይህ፡፡ የ2007/08 የምርት ዘመን የመኸር ግምገማ አድርገን ያገኘነው አኃዝ 2.9 ሚሊዮን ተረጂዎች ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. የበልግ ዝናብ በመዛባቱ ምክንያት ነሐሴ 2007 ዓ.ም. ላይ ቁጥሩ ወደ 4.5 ሚሊዮን አደገ፡፡ ኤልኒኖ ደግሞ መጣ፡፡ ነሐሴ ላይ 4.5 ሚሊዮን የነበረው በመስከረም 2008 ዓ.ም. የመጀመርያ ሳምንት ወደ 7.4 ሚሊዮን አደገ፡፡ በመስከረም ሦስተኛ ሳምንት ላይ ደግሞ ወደ 7.7 ሚሊዮን ጨመረ፡፡ በጥቅምት ደግሞ 8.2 ሚሊዮን ሆነ፡፡ በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ደግሞ 10.2 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጊዜ እኛ ቁጥሮቹን እየተከታተልን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ እያቀረብን ነው፡፡ ታስታውስ እንደሆነ በዚያን ጊዜ ለጋሾች አልሰጡንም ነበር፡፡ ምንም አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሁለት ሥራዎችን ነው ያከናወነው፡፡ አዝማሚያውን ስናይ የሚያዋጣ አልነበረም፡፡ ከሐምሌ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ 1.9 ቢሊዮን ብር ለእርጥበት እቀባ ሥራ ነው የሰጠነው፡፡ ማረጋገጥም ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል ብትሄዱ ከዚህ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ በርካታ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡ በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ የተሠራ ሥራ አለ፡፡ ለምሳሌ ቆቦ ላይ የያሉ መስኖ ተቋማት የኃይል አቅርቦት ያገኙት በዚህ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እኛ እየሠራን ያለነው በተጓዳኝ ነው፡፡ የድርቅ አደጋውን መቋቋም የሚያስችሉን የልማት ሥራ አንዱ ሲሆን፣ ጎን ለጎን ደግሞ የምላሽ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ይህም ማለት የምንችለውን ያህል ለድርቅ ተጋላጭ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ቁጥርን መቀነስ ነው፡፡ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑትን ቀነስን ማለት ደግሞ በፌዴራል ሳይሆን በክልል አቅም መቋቋም የምንችለው የተረጂ ቁጥር እንዲኖር ማድረግ ቻልን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ግን 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለድርቅ ተጋልጠዋል፡፡ ለእነሱ ዕርዳታ እየተጠየቀ ነው፡፡

አቶ ምትኩ፡- እሱንም ቢሆን በአብዛኛው እየሸፈነ ያለው መንግሥት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ እየተሰማ ካለው መረጃ አንፃር ግን ዘንድሮ ላሉ ተረጂዎች እየተሰጠ ያለው ዕርዳታ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ለተረጂዎች የሚሰጥ ነገር የለም እየተባለ ነው እኮ?

አቶ ምትኩ፡- ይህንን ነገር ግልጽ ላድርግልህ፡፡ አዎ 7.8 ሚሊዮን ተረጂዎች አሉ፡፡ ለተረጂዎቹ ዕርዳታ የሚሰጡት ኦፕሬተሮች ሦስት ናቸው፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፣ ሁለተኛው በካቶሊክ ሪሊፍስ ሳይቲ ኮንሰርቲየም ሥር ያሉ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ነው፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት እየረዱዋቸው ያሉትን ተረጂዎች ስንወስድ በመንግሥት እየተረዱ ያሉት 4.7 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የካቶሊኩ ኮንሰርቲየም  ደግሞ 1.4 ሚሊዮን ተረጂዎችን የሚሸፍን ነው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ለሚሆኑት ነው ዕርዳታ የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ አቅርቦቱ ላይ መስተጓጎል የሚኖረው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚሸፍነው  ላይ ነው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደግሞ ረጂ አይደለም፡፡ አስፈጻሚ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከረጂዎች ያገኘው ሀብት አሁን አልቆበታል፡፡ ከሰኔ ወር በኋላ የሚሰጠው የለም፡፡ ይህ ስለሆነ ድርጅቱ የሚሰጠው ስለሌለው መጮህ አለበት፡፡ ይህ ጩኸት ነው እንግዲህ ሰሞኑን የሞቀው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ1.7 ሚሊዮን ተረጂዎች የምሰጠው ዕርዳታ ሊያልቅብኝ ነው ብሎ መጮህ ሲገባው ለ7.8 ሚሊዮን ብሎ ነው የጮኸው፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም ምግብ ድርጅት አጯጯሁ አጠቃላዩን በመጥቀስ ነው ከተባለ በሥሩ ግን 1.7 ሚሊዮን ተረጂዎች አሉ፡፡ እነዚህ ተረጂዎችስ ምን ሊሆኑ ነው ታዲያ? የምሰጠው የለንም ካለ እሱ ዕርዳታ ሲቀርብላቸው የነበሩ ዜጎች አደጋ ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡

አቶ ምትኩ፡- እኛ ለምንሸፍናቸው ተረጂዎች በመንግሥት በኩል እጥረት የለብንም፡፡ ሁለት አማራጮች አሉ፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጩኸት ሰምተው ረጂዎች ከሰጡት ጥሩ ነው፡፡ ካልሰጡት ግን እሱ ሲረዳቸው የነበሩትን ተረጂዎች እኛ ጠቅልለን እንይዛለን፡፡ 4.7 ሚሊዮኑ ላይ 1.7 ሚሊዮን ጨምረን መንግሥት ለ6.4 ሚሊዮን ተረጂዎች ይደርሳል ማለት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለዚህ የሚሆን አቅም አለው?

አቶ ምትኩ፡- አዎ አለን፡፡ የእህል መጠባበቂያ ክምችት ላይ አለን፡፡ ሁለተኛ እየገባ ያለ እህል አለ፡፡ ዓምና በሦስት ዙር ነው የገዛነው፡፡ መጀመርያ 222 ሺሕ ቀጥሎ፣ 405 ሺሕ፣ ከዚያ 499,576 በአጠቃላይ ወደ 1.12 ሚሊዮን ኩንታል እህል ገዝተናል፡፡ ወደ አምስት መርከቦች የሚሆን የሚገባ እህል አለ፡፡ 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ይሆናል፡፡ ስለዚህ አቅሙ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዕርዳታ አሰጣጡ ጋር የአልሚ ምግብ እጥረት አለ ተብሏል? ይህ ክፍተት ችግር እያስከተለ ነው?

አቶ ምትኩ፡- በአልሚ ምግብ አቅርቦት ላይ ሁለት ነገሮች ነው እየሠራን ያለነው፡፡ አንደኛ ከአሥር የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎቻችን መካከል ሰባቱ እየሠሩ ናቸው፡፡ ዓምና ማዕድንና ቫይታሚን ከውጭ ነው የገባው፡፡ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ መድቦ አስገብቶ ከሽያጫቸው የተቀነሰ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ ነው የሠራነው፡፡ 117 ሚሊዮን ብር መድበን ከዚህ ውስጥ ወደ 74 ሚሊዮን ብር ወደ ውጭ ምንዛሪ ቀይረንላቸው ማዕድንና ቫይታሚን የገባ አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰባት ኢንዱስትሪዎች ያመርታሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- እጥረት የለም እያሉኝ ነው?

አቶ ምትኩ፡- እጥረቱ አልታየም፡፡ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በዘንድሮ የምርት ወቅት የድርቅ አደጋው የሚሸፍነው የአገሪቱ አካባቢ የት የት ነው? የጉዳቱ መጠንስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ምትኩ፡- ከቆዳቱ ስፋቱ ስንነሳ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ባለው ድርቅ ግን በደቡብ የነበረው ድርቅ ከሌላው አካባቢ ያነሰ ነበር፡፡ ዘንድሮ ጎልቶ ለምን ታየ?

አቶ ምትኩ፡- አዎ ትንሽ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ቅድም ከአደጋ ነፃ አይደለንም ያልኩህ፡፡ ኤልኒኖ ሲከሰት ደጋና ወይና ደጋው ክፍል ነው፡፡ በጣም ያጠቃውን አሁን ጥሩ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ የሚዲያ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች አካላት ወደ ሶማሌ ክልል ስትሄዱ ያያችሁት ሽኒሌ፣ ዋርዴና ጎዴ አልዳችሁም? ያኔ ዋርዴና ጎዴ ጥሩ ነበሩ፡፡ ዓምና የተጎዳው ሽኒሌ ነበር፡፡ ኤልኒኖ ጉዳት አድርሶበት ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ግን የተጎዳው የሶማሌ ደቡብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል ሊጎዳ የቻለው ደግሞ የህንድ ውቅያኖስ ተፅዕኖ ነው፡፡ ለዚህ ነው አንላቀቅም የምልህ፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቦታ እየቀያየረ ነው?

አቶ ምትኩ፡- አዎ እየተቀያየረ ስለሚመጣ አንላቀቅም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ስለማንላቀቅ የልማት ነገሮች ላይ መተኮር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ዓምና ድርቅ በነበረባቸው ቦታዎች ዘንድሮ የለም? የተለወጠ ነገር አለ?

አቶ ምትኩ፡- ለምሳሌ የአማራና የትግራይ ክልል ዓምና በጣም ተጎድተው ነበር፡፡ አሁን ብትሄድ ድርቅ አታይም፡፡

ሪፖርተር፡- ዓምና ቆቦና በአንዳንድ የአማራና የትግራይ አካባቢዎች ድርቅ ያጠቃቸውን ቦታዎች ተመልክቻለሁ፡፡ ድርቁ ከፍቶ ነበር፡፡ አሁን እነዚህ አካባቢዎች ድርቅ የለም? ምን የተለወጠ ነገር አለ?

አቶ ምትኩ፡- አሁን ቆቦ ብትሄድ ዓምና ካየኸው ጋር ብታነፃፅረው ተለውጧል፡፡ ደቡብ ትግራይ አላማጣና ሞሆኒ የመሳሰሉትን ብታይ ትልቅ ለውጥ አለ፡፡ አሁን የበልግ ዝናብ አግኝተዋል፡፡ ዓምና የበልግ ዝናብ ችግር ነበር፡፡ የክረምት ዝናብም ችግር ነበር፡፡ ይህ የኤልኒኖ ተፅዕኖ ነው፡፡ ተፅዕኖኖው ያልነካው ክፍል የለም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎችን በአካል ተገኝተን መታዘብ እንደቻልነው ድርቅ አለባቸው የተባሉ አካባቢዎች የሚከሰተው የውኃ እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ከምግብ የበለጠ የከፋው ይህ ችግር ብዙ ቦታ ታይቷል፡፡ ውኃ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ከመሆኑ አንፃር እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን አድርጋችኋል? ለምሳሌ በሶማሌ አካባቢ ያለው እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡

አቶ ምትኩ፡- የውኃ እጥረቱን ችግር በሁለት መንገድ እየፈታን ነው፡፡ እንደ ትልቅ ማሳያ የምንወስደው በሶማሌ ክልል የተሠራውን ነው፡፡ በክልሉ በርካታ የጎርፍ መቀልበሻ ስትራክቸሮች ተሠርተዋል፡፡ በብዙ ቦታዎች ተሠርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የት?

አቶ ምትኩ፡- ለምሳሌ ከጅግጅጋ ተነስተህ ወደ ጎዴ ስትሄድ ደገሃቡርና ቀብረ ደሃርን ይዘህ ወደ ታች ስንሄድ በርካታ ውኃ መያዣ ስትራክቸሮች ተሠርተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር አንድ ቦታ በተሠራው ጉድጓድ 150 ኪሎ ሜትር ድረስ በመዘርጋት ኅብረተሰቡ ውኃ እንዲያገኝ ነው የተደረገው፡፡ ቀብሪ በያ ላይ የጎለበተው ውኃ እስከ ሽላቦ ድረስ በውስጥ ውኃ እያገኘ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሶማሌ ክልል 150 የውኃ ማጓጓዣ ቦቴዎች አስገብቷል፡፡ የውኃ ጉድጓዶችን በማስፋፋቱ ምክንያት ንፁህ ውኃ እየተቀዳ በቦቴዎቹ እየተመላሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዕርዳታ ዕደላ ጋር በተያያዘ የታዘብነው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ አሁንም ስለመቆሙ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአንዳንድ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች አመራሮች ሳቢያ ዕርዳታውን በአግባቡ ያለማደል ችግር ታይቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለተረጂዎቹ ከሚሰጠው እህል ላይ እየቀነሱ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ሙስና ነበር፡፡ በግልጽ ለመናገር የዕርዳታ እህል ይሰረቃል፡፡ ከተረጂዎች አንደበት ሰምተን እንደነበረው ዕርዳታ ለመስጠት ጉቦ ይጠየቅም ነበር፡፡ ከአምስት ኪሎ በቆሎ ላይ አዳዩ አንድ ሁለት ኪሎውን ወስዶ ቀሪውን ይሰጥ ነበር፡፡ የዕለት ምግቡን ለማግኘት የሚጣጣር ተረጂ ሊደርሰው ከሚገባው እህል ላይ እንዲህ ያለ ውንብድና ሲሠራ ነበር፡፡ ይህ በግልጽ ያየነው ስለሆነ፣ እንዲህ ያለ ያልተገባ ድርጊት የፈጸሙት ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ወሰዳችሁ? ተጨባጭ የሆነውን ማለት ነው፡፡ አሁን ይህ ድርጊት ላለመፈጸሙ ምን ማረጋገጫ ይኖራል?

አቶ ምትኩ፡- ያልከው ትክክል ነው፡፡ ታይቷል፡፡ የሚያጋጥምም ነው፡፡ ከአካባቢ አካባቢ ይለያል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ጉዳይ ያሳሰርናቸው የወረዳ አስተዳዳሪዎች አሉ፡፡ በምዕራብ ሐረርጌና በደቡብ ክልል የታሰሩ አሉ፡፡ የተጠየቁም አሉ፡፡ ስለዚህ ክትትል ያስፈልጋል፡፡ ክትትል የምለው ለምሳሌ የሚዲያ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ሄደዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሄደዋል፡፡ እነዚህ የሄዱት ሁሉ ግብረ መልስ ሰጥተውናል፡፡

በዚያ ግብረ መልስ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚመራው የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ብሔራዊ ኮሚቴ (ኮሚሽኑ ጸሐፊ የሆነበት) እና ሁሉንም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚመለከት ብሔራዊ ምክር ቤት አለ፡፡ በዚህ ተገምግሞ ችግሩ የታየባቸው ቦታዎች ላሉ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች በአድራሻቸው ተገልጿል፡፡ ችግሮቹ የታዩባቸውን ቦታዎች በአብነቶች ጭምር ግንኙነት ተደርጎ ክልሎች ዕርምጃ ወስደዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከስርቆትም ባሻገር ሌሎች ተግባራት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በማዳበሪያ ሒሳብ ማስከፈል፣ ለጄሪካን ክፈሉ ማለት እነዚህ ሁሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተለቅመው ወጥተው ግንኙነት ተደርጓል፡፡ ትልቁ ነገር እንዲህ ያለውን ነገር መዋጋት ያለበት ኅብረተሰቡ ነው፡፡ በዕርዳታ መስጫ ጣቢያ ላይ አሁን ኮሚቴ አለ፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ከአረጋውያን፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች ቀበሌ ከሚሠሩ የጤናና የግብርና ባለሙያዎች ጭምር ያካተተ ኮሚቴ ነው፡፡ የዕርዳታ ክፍፍሉን ይከታተላሉ፡፡ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችም እንዲገመግሙ እየተደረገ ነው፡፡ ዕርዳታ የኪራይ መሰብሰቢያ ምንጭ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆን የለበትም፡፡ አንዱ ትኩረት ሰጥተን እየሠራንበት ያለ ነገር ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ፌዴራል ላይ ሆነን አይደለም የምንቆጣጠረው፡፡ ከስፋቱ አንፃር ማለት ነው፡፡ 1,900 የዕርዳታ ማሠራጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ አሁን እያንዳንዱ አካልና ከፌዴራል ጀምሮ ክልሎችም ተመሳሳይ ኮሚቴ አላቸው፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴ እንዳለ ሁሉ ዞንና ወረዳ ላይ አሉ፡፡ ቀበሌ ላይ ያለውን እየገመገሙ መፍታት አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ ኅብረተሰቡ ኪራይ ሰብሳቢነትን በፅናት መዋጋት አለበት፡፡ ለአንድ ተረጂ 15 ኪሎ ነው የሚሰጠው፡፡ 15 ኪሎ ሊሰጠኝ ይገባል ብሎ ብሎ መከራከር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ድርቅ ሲከሰት የተረጂዎች ቁጥር ይደበቃል ይባላል፡፡ እርግጥ ነው?

አቶ ምትኩ፡- የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ 7.8 ሚሊዮን ተረጂዎች አሉ ተብሎ ይፋ አድርገናል፡፡ አሁን የጨመረ ነገር የለም፡፡ ችግሩ 7.8 ሚሊዮን የዕለት ደራሽ የሚቀርብለት ኢትዮጵያዊ ከሰኔ በኋላ የሚላስ የሚቀመስ የለውም መባሉ ነው፡፡ ውሸት ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት ለ4.7 ሚሊዮን ተረጂዎች ሲያሠራጭ ነበር፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚሰጠው ዕርዳታ ካላገኘ እሱ ሲደርስ የነበረውን ደርቦ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ በአጭሩ እኛ እንሸፍናለን፡፡ ከፍ አድርጌ ልንገርህ? የልማት በጀታችንንም ቢሆን አጥፈን ለሕዝቡ እንደርሳለን፡፡ ከዚህ ውጪ የ1966 እና የ1977 ዓ.ም. ዓይነት ነገር አይመጣም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንድነው? ሰው ሸብረክ የሚባል ይመስለዋል፡፡ ዜጋን ማቆየት አለብን፡፡ የፈለገውን የልማት ሥራ ብታከናውን እኮ ሰውየው ሲኖር ነው ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ አስፈላጊውን ሁሉ አድርገን ዜጎችን እንታደጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ መንግሥትም ሆነ እንደ ዜጋ የብዙዎች ምኞት ከዕርዳታ መላቀቅ ነው፡፡ እየተረዱ መኖርን ማንም አይሻም፡፡ ስለዚህ በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት ለሚከሰት አደጋ የሌሎች ዕርዳታ ሳይፈለግ አንድ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት እንኳን በመቆየት ዕርዳታ የማይለመንበት ጊዜ መቼ ይመጣል ብለው ያስባሉ?

አቶ ምትኩ፡- ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ዕርዳታን መቶ በመቶ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብትወስድ ወደ 42 ሚሊዮን ዜጎቻቸው የምግብ ዕርዳታ ይቀርብላቸዋል፡፡ እነሱ የበሰለ ምግብ ይወስዳሉ፡፡ እኛ ደግሞ ስንዴ እንወስዳለን፡፡ ከድህነት የማውጣት ማኅበራዊ ፖሊሲ አለ፡፡ እሱ የደሃ ደሃ የሚባለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ነው፡፡ አቅመ ደካማ የሆኑት ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ የሙያ ክህሎት እንዲያገኙ ታደርጋለህ፡፡ ሁለተኛው ቀጥታ ከተረጂነት የሚያወጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት ታደርጋለህ፡፡ ለምሳሌ ወደ አርብቶ አደሩ አካባቢ ስንሄድ ውኃን መሠረት ያደረገ በመንደር የመሰባሰብ ፕሮግራም ይደረጋል፡፡ በመንደር አሰባሰብ በተሻለ የኢንቨስትመንት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡

 ሪፖርተር፡- አንድ ጥያቄ ደግሜ ላነሳ ነው፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለዕርዳታ ከሚያቀርበው ማጣት ጋር ተያይዞ በተረጂዎች ላይ ምንም ጉዳት እንደማይደርስ ሊያረጋግጡልን ይችላሉ? የዓለም የምግብ ፕሮግራም ይደግፋቸው የነበሩ ተረጂዎች ያለ ችግር ማስተናገድ ትችላላችሁ? እርግጠኛ ነዎት?

አቶ ምትኩ፡- የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለዕርዳታ ፈላጊዎች መድረስ ካቃተው መቶ በመቶ እኛ እንሸፍናለን፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...