Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሳይጠየቁ መቅረት እንዲህ ይንገሥ!!

ሳይጠየቁ መቅረት እንዲህ ይንገሥ!!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የኢንተርኔት ግንኙነትን መዝጋት የቢሻኝ ውሳኔ ነው ወይ? ሌላው ሌላው የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት ጉዳይ ቢቀር መንግሥት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው የሚለውን፣ የሚያስቀድመውን ልማቱን፣ ኢንቨስትመንቱን አይጎዳውም ወይ? ብሎ መጠየቁ በዚህ ረገድ የሰፈነውን ኃላፊነት የጎደለውንና ሳይጠየቁ መቅረትን እንደ ባህል ያፀደቀውን አሠራር ያነሳል፣ ያወሳል፣ ያስታውሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኢንተርኔት ግንኙነትን እንደ ቤት አምፖል መቆጣጠር፣ ብልጭ ድርግም ብዙ ጊዜም ድርግም ማድረግ፣ በማብሪያና ማጥፊያው እንዳሻው ማዘዝ የሚገርም አስተዳደጋችን፣ የአሠራር ባህላችን፣ ጠያቂ የሌለበትና ሳይጠየቁ መቅረት የለማበት አሠራራችን አንዱ መገለጫ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ውኃ ቀለብ ነው፡፡ ውኃ ሕይወት፣ ኃይል፣ ኢነርጂ መብራትም ነው፡፡ በዓባይና ጣና አገር የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሰጪው ድርጅት ደንበኞች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ዛሬም ኩራዝ ከነጭሱ አልቀረም፡፡ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁሉም አልተዳረሰም፡፡ ‹ዮኒቨርሳል አክሰስ› አልሆነም፡፡ የኤሌክትሪክ ቢል የወር ባለ ዕዳው ደንበኛ ድርግም ብሎ በመጥፋቱ የሚታወቅ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየኮሪደሩ፣ በየመተላፊያው መንገድ በሚጮህና በሚጤስ ጀኔሬተር የሚታገዝና የተተካ አማራጭ የግድ እንዲኖረው የተገደደ ሕዝብ ነው፡፡ ሻማ፣ ፋኖስ፣ ባትሪ ‹‹ሶላር›› ኩራዝ፣ ወዘተ ቆጣሪ በተገጠመለት የአዲስ አበባ ቤት ሁሉ የቤት ቁሳቁስ ሆነዋል፡፡ ቡሆና የቡሀቃ ይዞ ከአንዱ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል የጨለማ ወረዳ ወደ ሌላው ተረኛ የብርሃን ወረዳ መፍለስ፣ የአዲስ አበባ ሳይቀር ኑሮ ሆኗል፡፡

ጉዳቱም፣ አደጋውም ባለቤትና ቆጣሪ ያጣ በየቤቱና በየዘርፉ የሆድ ውስጥ ሙሾ ሆኖ የተቀበረ አንድ ብሶት ነው፡፡ የየዳቦ ቤቱ፣ የየፀጉር ቤቱ፣ የየወፍጮ ቤቱ እንባ የትኛውም እግዜር ደጅ የማይደርስ የሙሽራ ለቅሶ ሆኗል፡፡ በዚህ መካከል የምንሰማቸው ያልተለመዱ፣ ያልተጠበቁ፣ ነገር ግን የዚህ ችግር ቀጥተኛ ጣጣዎች ለምሳሌ የሆቴል ቤት ጀኔሬተር ጭስ የአልቤርጎ ተከራዮችን አፍኖ ገደለ መባሉ የአንድ ሰሞን ጉድ ሆነው ያልፋሉ፡፡

ለምሳሌ ያነሳነው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ብልጭ ድርግም ማለት የኢትዮጵያ ቤተሰቦች የጓዳ ጎድጓዳ ጣጣ ብቻ አይደለም፡፡ የአገሪቷ የውኃና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ‹‹የሚያለቅሱበት›› ቢያንስ ቢያንስ የሚያሳብቡበት ምክንያት ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መስጠት ሥራ ላይ እንቅፋት አጋጠመኝ ብሎ አደባባይ ወጥቶ መልስ የሚሰጠውን፣ ሪፖርት የሚያቀርበውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅትም በሕግ መሠረት የሚያነጋግረው፣ የሚያስተዳድረው፣ የሚቆጣጠረው፣ ልኩንም የሚነግረው የሥልጣን አካል አመራርና ባለሥልጣን በእጅጉ ይጎድለናል፡፡

ለየትኛውም ፖለቲካ ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት መገንባት አልሳካልን ብሎ እንጂ፣ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌን በልጦ እንዲገኝ የሚያደርግ ፍጥርጥር አጥተን እንጂ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪነትን ሥራ ለመንግሥት ብቻ የተከለለ፣ ለግል የተከለከለ ማድረጋችን ብቻ ለዚህ ሁሉ የዘፈቀደና የቢሻኝ ‹‹የእንዳሻህ አድርገው›› አሠራር ባላደረገን ነበር፡፡

እውነት ነው ኢትዮ ቴሌኮም ብቸኛ የሆን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ነው፡፡ ለዚያውም በሕግ፡፡ የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕግ ይህንን ይደነግጋል፡፡ ይህንን የሚደነግገው ሕግ ራሱ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ‹ፊልድ› ያስፈልጋል ይላል፡፡ ማንኛውም ሰው ያኔ ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ አሁን ደግሞ ኤጀንሲውን ከተካው ሥልጣን አካል የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖረው፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት አይችልም በማለት ይደግጋል፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት በ1989 ዓ.ም. የወጣውና በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1939 ዓ.ም.፣ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋሙትን የቴሌኮሙዩኒኬሽን የሕግ ማዕቀፎች ሽሮ በአዲስ የተካው ሕግ ዋና መነሻና መንደርደሪያ በሕጉ መግቢያ ላይ የተገለጹት ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡

አንደኛው መነሻ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለአገሪቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን መንደርደሪያ ያደርጋል፡፡ ሌላው በዚህ አገር ውስጥና በዚህ ዘርፍ ታይቶም፣ ታልሞም፣ ስለመኖሩም ጭምር የማይታወቀውን ለውጥ በሕግ ያመጣው ነው፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ይበልጥ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ የቁጥጥር ተግባር የሚያከናውነው አካል አገልግሎቱን ከሚሰጠው ድርጅት ለይቶ ማደራጀትና ቁጥጥሩ የሚካሄድበትን ሁኔታ መደንገግ አስፈላጊነት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ፣ በኢትዮጵያ የቴኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ውስጥ ተጣብቆ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ የኖረው የቁጥጥርና አገልግሎት የመስጠት ተግባር ተለያየ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን (የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም) እና ኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ (አሁን የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት የወሰደው ሥራ) በሕግ ተለያዩ፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕጉ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የመስጠት ሥራ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ደነገገ፡፡ የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወይም ራሱን ተክቶ የሚቋቋመው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ‹‹ብቸኛ የሆነው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት፤›› ነው ቢልም፣ ይህ ድርጅት ራሱ ባለፈቃድ ድርጅት እንደሆነ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት ወሰነ፡፡ በተለይም ከሚያዝያ 19 ቀን 1991 ዓ.ም. ጀምሮ በፀናው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ደንብ የመሸጋገሪያ ድንጋጌ መሠረት፣ ‹‹የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመሥጠት ላይ የሚገኘው ድርጅት ይህ ደንብ በሥራ ላይ ከሚውልበት ቀን ጀምሮ በ12 ወራት ውስጥ በዚህ ደንብ መሠረት የሚሰጡ አስፈላጊዎቹ ፈቃዶች ማውጣት አለበት፤›› በማለት ደነገገ፡፡

በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ፈቃድ ማውጣት ያለበት፣ በፈቃድ የሚሠራ፣ ፈቃድ ለማውጣትና ፈቃዱን በሕግ በተወሰነው ጊዜ ለማሳደስ ደግሞ የፈቃድ ሁኔታዎቸን ማሟላት ያለበት ድርጅት ነው፡፡ ከፈቃድ ተራ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ደግሞ የገዛ ራሱ የማሟያና የመጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤት መሆን ነው፡፡

ይህን ጉዳይ በዝርዝር ያነሳሁበት ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መደርገም፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመስጠት ተራ የዘወትር ሥራዬ ላይ ፈተና ሆነብኝ ማለት ‹የእናቴ ቀሚስ እያደናቀፈኝ› ከማለት የማይለይ መሆኑን ለማሳየት ብቻ አይደለም፡፡ በሕግ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት ከተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የተለየ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ይህ ሁሉ የተመሰቃቀለና ጠያቂም ተጠያቂም የሌለበት ጨለማ የወረሰው አሠራርና ህልውና ሆኗል፡፡ የቁጥጥር ተግባሩን አገልግሎቱን ከሚሰጠው የመንግሥት የልማት  ድርጅት መለየት አስፈላጊ ነው ተብሎ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ሆኖ የተቋቋመው፣ አገልግሎት ሰጪውም የመንግሥት ልማት ድርጅት ሆኖ የተመሠረተው ከ1989 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡ የኤጀንሲው የቁጥጥር ተግባር ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሕግ የተዛወረው በ2003 ዓ.ም. ነው (አዋጅ ቁጥር 691)፡፡

በመጀመርያዎቹ የኤጀንሲው የሥልጣን ዘመን ገና የአዲስ ጎጆ ወጪው የኤጀንሲው የቁጥጥርና የሕግ ሥልጣንና ተግባር በግዙፉ ኮርፖሬሽን ታሪክና የአሠራር ባህል ፊት ከመጤፍ ባለመቆጠሩ፣ በዚህ ላይ የአገልግሎት ሰጪው ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ የሥልጣን ዳር ድንበር በልማት ድርቶች የመልካም አስተዳደር ሕግ ከተወሰነው ይልቅ፣ በቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት በተመደቡት ባለሥልጣናት ሌላ ቁመናና አቋም ልክ ይበልጥ ክብደትና ዋጋ ስላለው ኤጀንሲው ‹‹መጫወቻ›› እና የውሸት የውሸት እንደሆነ ዘለቀ፡፡ እንደሆነ ሕልውናው በሕግ ከመከናወኑ በፊት ተፈጸመ፡፡ የአገሪቱ የስልክ ቁጥሮች አሰጣጥ ፕላን የሥልጣን ባለቤትነትና ባለመብትነት የማን እንደሆነ በተግባር እስኪጠፋ ድረስ አገልግሎት ሰጪው ድርጅት ‹‹ባትጋሩኝ›› ብሎ ሁሉንምና ያፈቀደውን ወሮ እስኪያዝ ድረስ የተበለሻሸው፣ ዛሬም ከ20 ዓመታት በኋላ ተቆጣጣሪውን ከአገልግሎት ሰጪው ለይቶ መግዛት ማቋቋም ባለመቻሉ ነው፡፡ ከሕግ በላይ መሆንን የሚከላከል ፍጥርጥር ስለሌለ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ዝንባሌን በልጦ የፀና ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት በመጥፋቱ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለየትኛውም ቡድን ፖለቲካ ሳይወግን በሕግና በሕግ ብቻ የሚመራና እሱኑ የሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ ያለመግባታችን ሰፊ ችግር አካል ነው፡፡

ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም ዕድሜ አለው፡፡ የእዚህን አገልግሎት አሰጣጥ የረዥም ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ ሽሮ በ1989 ዓ.ም. በአዲስ የተካው የአገራችን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕግ፣ ከሁሉም በላይ የመንደርደሪያ ዓላማ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለአገሪቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው የሚል ነው፡፡ ለዚህም ነው ጽሑፌን ስጀምር መንግሥት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ግንኙነት ማገድን የመሰለ ዕርምጃ የቢሻኝ ውሳኔ የሚገዛው ጉዳይ ሲያደርግ፣ ሌላው ቢቀር ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ነው የሚለው የሚያስቀድመውን ልማቱን፣ ኢንቨስትመንቱን አይጎዳውም ወይ ብዬ የተነሳሁት፡፡ ከዚህም የተነሳ የማይዘነጋውን ሊዘነጋም የማይገባው የዚህን ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብትና የመሠረታዊ ነፃነት ገጽታ ለጊዜው አቆይተን የልማቱን ነገር ብቻ እናንሳ፡፡

ልማት የአገሪቱ ዋናና አውራ አጀንዳ ነው፡፡ በመንግሥት ፖሊሲና በየዕለቱ እንደሚነገረው ሁሉም ነገር ወደዚህ ‹‹ጦር ግንባር›› የዞረ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይና ግንኙነት ፖሊሲ ራሱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በማካሄድ የአገሪቱን የውጭ ንግድና ቱሪዝም ማስፋፋት፣ የውጭ ኢንቨስተሮቸን በመለየትና በመሳብ ላይ ያተኩራል፡፡ በአገር ውስጥ የመልማት በውጭ ኢንቨስትመንት ያለመዘነጋት ጉዳይ ደግሞ በመሠረተ ልማት፣ ማለትም በኃይል ምንጭ፣ በመንገድ፣ በውኃ፣ በስልክና በኢንተርኔት ዝርጋታ በሰው ኃይል ልማት፣ በመንግሥታዊ አያያዝና እንክብካቤ የመወዳደር ትግል ያለበት ግዳጅ ነው፡፡ ኤምባሲዎቻችን የኢንቨስትመንትና የንግድ አምባሳደሮች የማድረግ ሥራችን የሚሰምረው፣ በከፍተኛ ሹማምንትም ሆነ በአገርና በመንግሥት መሪዎች ደረጃ ነጋ ጠባ የሚደረገው የሥራ ጉበኝት ከተራ መንከውከውና የ‹‹ሰው እጅ›› ከማየት የወጣ ጥረት የሚሆነው፣ በዚህ ረገድ የተዋጣለት ስንሆን ነው፡፡ የተወዳዳሪነት ብልጫ ሲጤን ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ ዘመነ ግሎባላይዜሽን ነው፡፡

ኢሕአዴግ ራሱ እንደሚለውና በጽሑፍ እንዳሰፈረው ዘመኑ ግሎባላይዜሽን፣ እንዲሁም የመረጃ ዘመን ነው፡፡ እግጅ በጣም ብዙ መረጃ በሴኮንዶች በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ማንቀሳቀስ መቻል ወይም አለመቻል፣ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ተወዳድሮ ለማሸነፍ መቻል ወይም አለመቻል ነው፡፡ ኩባንያዎች የዋጋ፣ የመጠን፣ የዓይነት መረጃ በፍጥነት መቀያየር መቻል አለባቸው፡፡ ገንዘብ በሴኮንዶች ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ መተላለፍ አለበት፡፡ ምርቶች፣ ዲዛይኖችና አገልግሎቶች በዚህ ፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ባለንበት ዘመን በአሜሪካ ፍርድ ቤት ጉዳይ ይዘው የሚከራከሩ ጠበቆች አብኛውን የክርክሩን ዝግጅት ሥራ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አማካይነት ህንድ አገር ለሚገኙ ብቃቱ ያላቸው ግን ቀላል ወጪ ለሚጠይቁ ጠበቆች እየሰጡ ነው የሚያሠሩት፡፡ በጣም ብዙ አገልግሎቶች (የፋይናንስ፣ የኢንሹራንስ፣ የዲዛይን ሥራ፣ ወዘተ) በዚህ መንገድ ነው የሚከናወነው (ኢሕአዴግ የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂና አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጋቢት 1999 ዓ.ም.)፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ሆኖ የማሰማራት መብት የተፈቀደው ለመንግሥት ብቻ መሆኑ፣ ለግሉ መስክ በተለይም ለውጭው ባለሀብት መከልከሉ ይህንን እውነት ማናጋት የለበትም፡፡ ልማትም ሆነ የውጭ ካፒታልን የመሳብ ኢንቨስትመንትና ኢንቨስተሮችን የማስተናገድ ጉዳይ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች አገሮች ጋር መወዳደር፣ ዋስትና ሰጥቶና ብልጫ አምጥቶ የተሻለ ሳቢነትን ይዞ መገኘት ማለት ጭምር ነው፡፡   

የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ይህን ሚና መወጣት ይችል ዘንድ ‹‹እጅግ ብዙ መረጃን የአጭር ጊዜ ውስጥ በዝቅተኛ ዋጋ ማስተላለፍ መቻል አለበት›› (የተጠቀሰው ገጽ 48) ችግራችን የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ የአገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሕግ ፈቃድ ከሚሰጥባቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ የሴሉላር ሞባይል አገልግሎት ፈቃድ ነው፡፡ ሌላው የኢንተርኔትና የዳታ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ነው፡፡ ስለ ሴሉላር ሞባይል ኔትወርክ በተለይ የሚደነግገው ይህ ሕግ፣ የባለ ፈቃድ ሴሉላር ሞባይል ኔትወርክ ሲስተም ዲጂታል ሆኖ የተለያዩ የዳታ አገልግሎቶች፣ አጫጭር መልዕክቶች፣ ተጓዳኝ አገልግሎቶችና የሮሚንግ አገልግሎት መስጠት አለበት ይላል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ብቸኛው አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ቢሆንም ባለፈቃድ ድርጅት በመሆኑ ከዚህ ሕግ በላይ አይደለም፡፡ ከዚህ ሕግ በላይም መሆን አይችልም፡፡

እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ብቻ ሥራውን የጀመረውና የማይንቀሳቀስ ንብረት የባለቤትነት ካርታ በመያዣነት እየተቀበለ፣ በኋላም አገር ቤት የተገዛ የሞባይል የስልክ ቀፎ ጭምር በተናጠልና በነፍስ ወከፍ ባለቤቱ ጉምሩክ ቀረጥና የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርብበት እያደረገ የሰጠው አገልግሎት ኤስኤምኤስን የሚጨምር አልነበረም፡፡ የሚገርመው የአጫጭር መልዕክቶች (SMS) አገልግሎት መስጠት የጀመረው ቆይቶና ከርሞ ብቻ ሳይሆን ለብቻው የምዝገባ እያስከፈለ ነበር፡፡ እንዲህ ባለ የገዛ ራሱን የተቋሙን የንግድ ሥራ አያይዞ በማያውቅ፣ በአላዋቂ አመራር ሥራውን የጀመረው የአጫጭር መልዕክት አገልግሎት ታሪክ የሕጋዊነት ጀርባ ታሪኩ ባልተገለጸ፣ ተጠያቂነት በሌለበት ሳይጠየቁ መቅረት ስለመዝገበ የሁለት ዓመት የኤስኤምኤስ ዕገዳ መጠልሸቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ዛሬ ዕድሜ ለቴክኖሎጂው እንጂ መደበኛ ስልክ እንኳን አንድ ሚሊዮን ደንበኛ ውስጥ መግባት አቅቶት በሚንቀራፈፍበት አገር (በሚኒስቴሩ የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት ሪፖርት መሠረት) 42.3 ሚሊዮን የሞባይል ስልክ ደንበኞች አሉ፡፡ እዚህ ሞባይል ደንበኝነት ላይ ይበልጥ የተንተራሰው ‹‹የኢንተርኔት ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር 12.4 ሚሊዮን›› ደርሷል፡፡ ቴክኖሎጂው የሰጠውን ግን ፖለቲካውና ማኔጅመንቱ እየተጋገዙ ነፍገውታል፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ‹‹እጅግ ብዙ  መረጃን በአጭር ጊዜ ውስጥ በዝቅተኛ ዋጋ ማስተላለፍ›› አልቻለም፡፡

እዚሀ ውስብስብ ችግር ውስጥ የተደበቀውን ገመና ደግሞ ፕሮፓጋንዳው እያወናበደ፣ እየፈጠረና፣ እየቀላመደ ተፈጥሯዊና ተመራጭ ነው ይለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የገቢና የኑሮ ደረጃ መራራቁን ያላገናዘበ፣ ዋጋን በዶላር ተመኑ ብቻ እያነፃፀረ ብቻ የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ዋጋ ከአሜሪካ የረከሰ ነው እየተባለ ዜና ይሠራል፡፡ የምንኖረው ይህን የመሰለ እውነት ያዘለ ውሸት ለሕዝብ መናገር በሚቻልበት አገር ነው፡፡

ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎታችንን ሲጀምር ይህን የመሰለ ሾተላይ የተጠናወተው መሆኑ ሳያንስ (ፍጥነቱ፣ ዋጋው፣ አቅሙ) ከኤሌክትሪክ ኃይሉ በበለጠና በከፋ ሁኔታ የፓርቲ ፖለቲካ አንዳች ነገር ባገኘው፣ በነካው፣ በተሰማው ቁጥር የሚታመም ጤና ያጣ የአገር ጉዳይ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ተቃውሞን የመከላከል መልክ የማስያዣና ልክ የማሳያ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ደግሞ የመነጨው የመንግሥት ሥራ አካሄድ ግልጽ ካለመሆኑ፣ በሕዝብ ዓይንና ተጠያቂነት ሥር አለመውደቁ የፓርቲና የመንግሥት ተግባራትና እንቅስቃሴዎች ከመቀላቀላቸው የተነሳ ነው፡፡

በዚህ አጠቃላይ ችግር ውስጥ የሰፊው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ግንኙነታችን የአገር ሕመም የሆኑ መላ ያልተበጀላቸው በቢሻኝ ውሳኔ የሚመሩ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው በቴሌኮሙዩኒኬሽን ግንኙነታችን ውስጥ የመንግሥት የጥበቃና የቁጥጥር ተግባር ነው፡፡ ሁለተኛው ግንኙነቱን ያለቅድሚያ ማስታወቂያና አስቀድሞ በማይታወቅ አሠራር ደርሶ እንቅ፣ ቁርጥና ዝግት የማድረግ ተግባር ነው፡፡ እያንዳንዱን በአጭር በአጭሩ እንቃኝ፡፡

ሁለቱም ጉዳዮች ሕገ መንግሥታዊ ምሽግ ባገባ የመብት ጥበቃ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 የተደነገገው የግል ሕይወትና የግላዊነት መብት መኖሪያ ቤትን፣ ሰውነትንና ንብረትን ከመመርመር ጣልቃ ገብነት ይጠብቃል፡፡ በግል የሚጽፏቸውን፣ የሚጻጻፉአቸውን፣ በፖስታ የሚልኳቸውን እንዲሁም በቴሌኮሙዩኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚያደርጓቸውን ግንኙነቶች አይደፍሩም ይላል፡፡ መንግሥትና ባለሥልጣናቱ እነዚህን መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ እነዚህ መብቶች ሊገደቡ የሚችሉበትን ውስን ሁኔታዎችም ያቋቁማል፡፡

ሌላው ሕገ መንግሥታዊ መሠረት በአንቀጽ 29 የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት የሚጠብቀው ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነትን የሚያካትተው መብት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ሊበጅ የሚችለውንም ገደብ በገደብ ይወስናል፡፡ ሁለቱም መብቶች ፍጹምና ልቅ ባለመሆናቸው ገደብ አለባቸው፡፡ ገደባቸው ግን ይበልጥ ገደብ አለበት፡፡

እነዚህን መብቶችና ነፃነቶች ከተጻፉበት ወረቀት በላይ በገሀዱ ዓለም ውስጥ በተግባር ኑሮ ውስጥ የሚታዩ ከመንግሥቶቻችንና ከባለሥልጣኖቻቸው የቁርጠኝነት መሀላ ውጪ የሚኖሩ ማድረግ ያልተቻለው፣ አንደኛ በአጠቃላይ የመንግሥት ሥልጣን ገደብ የለሽ መሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ከሕግ በላይ ስለሆነ ነው፡፡ መንግሥት ያሻውንና የፈቀደውን ባፈቀደው ጊዜ ማድረግ ስለሚችል ነው፡፡ ሁለተኛ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት፣ ሕግና ሥርዓት፣ ወዘተ የሚባሉ ምክንያቶችንና ሰበቦች በከፈቱት ‹‹ቀዳዳ›› መንግሥትን የመሰለ በመላ ታሪካችን በሰብዓዊ መብት ደመኛ ጠላትነቱ የሚታወቅ ፈላጭ ቆራጭ ሥልጣን እንዳሻው ስለሚገባበት ነው፡፡ ሕግ ማስከበርንና ማስፈጸምን፣ ሕዝብን ማፈርንና ማክበርን፣ ሕግና ተግባርን ማቀራረብን ወጉና ባህሉ ወዳደረገ ምዕራፍ አለመግባታችን ነው፡፡

መንግሥት ሕግ በማስከበር ስም በእነዚህ መብቶች ላይ ጣልቃ የሚገባው፣ የሚሰልለው፣ የሚሰማው፣ ጆሮ የሚጠባው፣ የሚመርጀው፣ የከፉ ቀን መረጃ የሚሰበስበው፣ የሚተነፈሰውን ሁሉ እከተታተላለሁ የሚለው ማለትም የአንቀጽ 26 የግለኝነት መብት ላይ ወረራ የሚያደርገው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የግዛት ወሰንና ክልል ሳይወሰን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ በመረጠው የማሠራጫ መሣሪያና ዘዴ ሐሳብን የመግለጽና ኢንፎርሜሽን የማግኘት መብት ላይ ገደብ፣ ልጓም፣ ቁጥጥር፣ ክልከላ፣ ውስጥ የሚገባው በዋነኛነት በተለይም ዛሬ በመገናኘው ኢንዱስትሪ ላይ በመመካት ነው፡፡

ፖስታ ቤቶችን፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን መሠረተ ልማት በመጠቀም የመከታተል ሥራ ይሠራል፡፡ የሬዲዮ ሞገድ ከመልቀቅ ጀምሮ የማተሚያ ቤቶችን አሠራር በመቃኘት፣ በርካታ የገደብና የክልከላ ሥራ ያከናወናል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ የተሰማሩ የልዩ ልዩ አገልግሎት ድርጅቶች ባለቤትነት በሕግ የመንግሥትና የመንግሥታት ብቻ ሲሆን ደግሞ፣ የመንግሥት ሁለቱም ዓይነት ተግባሮች በሥውርና በቀላሉ የሚፈጸሙ፣ የማይታወቁ፣ የማይጠየቁ አንዳንዴ ድንገት ወሬያቸው ሲሰማ የሚያስደነግጡ ይሆናሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ቤቶች፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅታችን የሥር የመሠረት ችግር በመንግሥት የሞኖፖል ባለቤትነት ሥር መሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ብቸኛ ባለቤት ራሱ የሚያስከፍለን ዋጋና ያሳየን ፍዳ ራሱን የቻለ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በወጡት የሪፖርተር የእንግሊዝኛና የአማርኛ ዕትሞች የተገለጹት የሚዲያ ኤክስፐርት በጥናት ፕሮጀክት መሪነታቸውና በውስጥ አዋቂነታቸው የሚያወቁትንና ያረጋገጡትን የአገራችንን የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ችግር ነግረውናል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቴክኒክ ተቀጣሪዎችን፣ እንዲሁም ፈንድ ያደረገውንና ሥራው ላይ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ተወካዮችንና ሌሎች ሰዎችን ቃለ ምልልስ በማድረግ እንደተረዳሁት የትኛውም ወገን ደስተኛ አይደለም፡፡ ውድድር ባለመኖሩና ጫና ስለሌለ የቴሌኮም አገልግሎትን የማሻሻል ፍላጎት የለም፡፡ የአገልግሎት ጥራቱ እጅግ የወረደ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሕዝብ ግን ቅሬታውን እያቀረበ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት እንዲሻሻል በተለይ ከቴክኒክ አንፃር ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡  ውድቀትንም ሆነ ስኬትን በታማኝነት መግለጽና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ ዕቅድ ከሌለ ቢያንስ ባለው ሥርዓት ውስጥ አማራጮችንና ማትጊያዎችን በማምጣት፣ ሁሉም ወገኖች እንዲወዳደሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እስካሁን ይኼ እየሠራ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በላይ የጎዳን ግን መንግሥት በንግድ ሥራ በባለቤትነቱና መንግሥት በፖለቲካ ሥልጣን ባለመብትነቱ መካከል ሊኖር የሚገባውን አጥር አለማበጀቱ ነው፡፡ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤትም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ባለቤት ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች የንግድ ሥራዎች ናቸው፡፡ የመንግሥት የአስተዳደር ሥራዎች አይደሉም፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ብቻ የሚከናወን መሆኑም አንድን የንግድ ሥራ የመንግሥት የአስተዳደር ሥራ አያደርገውም፡፡ መንግሥትንም በዚህ ውስጥ በተለያየ ልክና መልክ እንዳሻው እንዲሆን አይፈቀድለትም፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ትራንስፖርት፣ የንግድ ሥራና በኢትዮጵያ ሲቪል አቭዬሽን የመንግሥት የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥራ መካከል እፈተፍታለሁ፣ ሁለቱን አጣቅሳለሁ፣ የቢሻኝ አደርጋለሁ ቢል በዚህ ዘርፍ የሰፈነውና ኢንዱስትሪው ያቋቋመው ከበላዩ ጌታ የሌለው ሕግ አየሁህ፣ ነብር አየኝ በል ይለዋል፡፡

የአገር ውስጡ ሕግ አየሁህ ባይነት ‹‹ሳስበው ሳስበው ደከመኝና ተውኩት›› ቢል ቢፈዝና ቢጓደል ደግሞ፣ ሥር የያዘው የኢንዱስትሪው ዓለም አቀፋዊ አሠራር እየተከታተለና እያሳደደ ለሕጉ ጥበቃ የደርግለታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ሰማይ ላይ በነፃነትና በባለመብትነት መብረር የሚችለው ይህንን ሲያሟላና ሲፈጽም ነው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የንግድ ሥራና የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን የመንግሥት የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥራ ግን እንዲህ አልተፈላቀቁም፣ ለየቅል አልወጡም፡፡ በተለይ ደግሞ የዚህ ዘርፍ የመንግሥት የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥራው (በተለይም የምንነጋገርበትን ግንኙነት መጥለፍን፣ መከታተልን፣ ማገድን፣ መዝጋትን) የሚመለከተው በርካታ ባለቤቶች አሉት፡፡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፊት ለፊት የምናየው ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ነው፡፡ ብሔራዊ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎት የሚባል ተቋምም አለን፡፡ ዘርፉን በተለይ የሚመለከተው ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ (ቢያንስ ቢያንስ በሕግ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰብሳቢነት የሚመራው የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስቴሮች፣ ብሔራዊ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎት በአባልነት የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት አለ፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አንዱዓለም አድማሴ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ‹‹ቆይታ›› ይህን ጉዳይ የሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

‹‹ኢትዮ ቴሌኮም እንደ መንግሥት ተቋምነቱ የመንግሥትን ፍላጎት በማክበር የደኅንነት ሥራ ወይም አገራዊ ሥጋቶች ሲያጋጥሙ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን የመዝጋት ሥራ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቢዝነስ ተቋም መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ይህን ሚዛን እንዴት ነው መጠበቅ የሚችለው? የደንበኞቹንስ እምነት በቀላሉ ማግኘት ይቻላል?›› ተብለው ሲጠየቁ፣ አቶ አንዱዓለም፣ ‹‹የኢትዮ ቴሌኮም ሥልጣን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም አገልገልግሎት ሰጪ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ አይገባም፡፡ ኅብረተሰቡም ይህንን ሊያውቅ ይገባል፡፡ አንድ የግል ቴሌኮም አፕሬተር ሥራው አገልግሎት ሰጥቶ ደንበኞቹን ማርካት ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም ከዚያ የዘለለ ሥራ የለውም፡፡ ሥልጣንም የለውም፡፡ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ሥልጣን የተሰጠው አካል አለ፤›› ብለው መለሱ፡፡

ያነጋገራቸው የሪፖርተር ጋዜጠኛ ግን በነገሩ ገፍቶ ተከታይ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ደንበኞች እኮ የሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት ስለተጠቀሙ ነው፤›› አላቸው፡፡ አቶ አንዱ ዓለም፣ ‹‹ይህ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ መሠረተ ልማት የመንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ሊጋሩት ይችላሉ፡፡ አዲስ አበባ ፖሊስ ለምሳሌ የእኛን ታወሮች ተጋርተዋል፡፡ ሌላ ታወር መትከል ስለሌለባቸው፡፡ ሌላ መሬትም መውሰድ የለባቸውም ለዚህ ሲባል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ኢትዮ ቴሌኮም ኦፕሬተር ብቻ መሆኑን በእርግጠኝነት ልነግርህ እችላለሁ፤›› አሉ፡፡   

የእኛ መሠረተ ልማት የመንግሥት ነው፣ የመንግሥት ተቋማት ሊጋሩት ይችላሉ ማለት ምንድነው? ሌላው ቢቀር ለልማቱና ለኢንቨስትመንቱ ሲባል እንኳን ይህ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የመስጠት ሥራና የመንግሥት የቁጥጥርና የአስተዳደር ሥራ አስቀድሞ በሚታወቅ ለሕዝብ ይፋና ግልጽ በሆነ በሕግ መደንገግ የለበትም?  

ብቸኛና የመንግሥት የሞኖፖል አገልግሎት ሰጪ ድርጅት መሆኑ በዚህ ረገድ የተጣለበትን የአሠራር ግልጽነትና ኃላፊነት አያስቀርለትም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮምን ኮርፖሬት ድጋፍና ዕገዛ እንዲሁም እጅ ያለበትን መንግሥትን ክንዋኔ ሪፖርት ይፋና ግልጽ የማድረግ ግዴታና ይህንንም የሚገዛ ሕግ ይጎድለናል፡፡ እንዲህ ያለ ግዴታ ሳናሟላ እንዲህ ያለ የሕግ መሣሪያ ሳንይዝ ለውጭ ኢንቨስትመንት የመመረጥ ጉዳይ ያመልጠናል፡፡

የኢትዮጵያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ ወይም ኢትዮ ቴሌኮም እዚህ ውስጥ እጅ ያለው መሆኑን ድንገት የምንሰማው የደርጉ አንደኛ ምክትል ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የአማን አንዶምን የስልክ ንግግር የቴፕ ቅጂ አሰምተው፣ የደርግ ባለሥልጣናትን ድምፅ የመጠየቃቸውን ዜና በታሪክ አጋጣሚ ለዚያውም ከመንግሥት ግልበጣ በኋላ ሲነገረን መሆን የለበትም፡፡ አሁንም ድረስ የዚያን አሠራር ጉዳይ በዝርዝር አናውቅም፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ሚና፣ ኃላፊነቱንና ግዴታውን የእሱን አውታሮች ‹‹የሚጋሩትን›› አካላት ሚናና ድርሻ ሊነግረን ይገባል፡፡ አትሞ የማውጣት ግዴታም አለበት፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አንድም ሆኑ ብዙ ባለቤትነታቸው የመንግሥትም ሆነ የግል፣ ሐሳብን የመግለጽና የግለኝነት መብታችንን የሚመለከቱና የሚነኩ ፖሊሲዎቻቸውንና ተግባሮቻቸውን ይፋ ማድረግ አለባቸው፡፡

ዝም ብለው መንግሥት ወይም የቴሌን ታወር ‹‹የሚጋሩት›› አካላት ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ ጭራሹንም ታወራቸውን፣ አውታሮቻቸውን የሚያጋሩ መሆን አይችሉም፡፡

አገራችን ለቴሌሌኮሙዩኒኬሽንና ኤሌክትሪክ ኃይል አውታሮች ደኅንነት ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ ሕግ አላት (አዋጅ ቁጥር 464)፡፡ የዚህ ምክንያቱ በራሱ በሕጉ እንደተገለጸው ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማምጣት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ተሠራጭተው የሚገኙት እነዚህ አውታሮች በባህርያቸው ለጥቃት ድርጊት የተጋለጡ መሆናቸውና አገልግሎቶቹ ለአፍታ እንኳ ቢቋረጡ፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚና ደኅንነት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ይህ የሕጉ ቃል በቃል ግልባጭ ነው፡፡ ለአፍታ እንኳ ቢቋረጥ በብሔራዊ አኮኖሚና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታር በልዩ ሕግ የሚጠብቅ መንግሥት፣ የዚህን አውታር (ኔትወርክ) ሥራ በሙሉ ድርግም ሲያደርግም ሆነ በዕውቅና በተመረጡ ቦታዎች ሲያሰናክል፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ለምን እንደማይታየው ግራ ያጋባል፡፡

‹‹የኢንተርኔት መዘጋት ኢትዮጵያን ባይገልጽም ለደኅንነት ሲባል ከዚህ የባሰ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል›› ያሉት ወይም አሉ የተባሉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ናቸው (ሪፖርተር ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡፡ እውነት ከሆነ ይህን መልስ የሰጡት ‹‹በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግና በመረጃ የበለፀገና በአገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ኅብረተሰብ የመገንባቱን ሒደት ማጎልበት››፣ ‹‹በሁሉም የመንግሥት አካላትና ዘርፎች መካከል ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃና ኮሙዩኒኬሽን ሥርዓት እንዲኖር ማድረግና መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለውን ብቃት ማጠናከር››፣ ‹‹የመንግሥት ቃል አቀባይነት ሥራዎችን ጨምሮ የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ዋነኛ ምንጭ በመሆን ማገልገል፣ የመንግሥት መልዕክቶች መቅረፅና በልዩ ልዩ መንገዶች ማሠራጨት፣ በአገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የመንግሥትን አቋም መግለጽ›› ዓላማውና ሥራው አድርጎና ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካል ሆኖ በሕግ የተቋቋመው መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ናቸው፡፡

እስቲ እግዚብሔር ያሳያችሁ! ዛሬ የየትኛውም አገር መንግሥት ቃል አቀባይ መሆን (በአሜሪካም) በጭራሽ የማያስቀና፣ ይልቁንም ‹‹አይጣል››፣ ‹‹አያድርስ›› የሚባል ቢሆንም፣ አሁን የኢንተርኔት መዘጋት ኢትዮጵያን አይገልጽም፡፡ ለደኅንነት ሲባል ግን ከዚህ የባሰ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል ማለት መልስ ነው? የኢንተርኔት መዝጋት ኢትዮጵያን አይገልጽም ማለትስ እውነት ነው? ለደኅንነት ሲባል ከዚያ የባሰ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል ማለት የመሰለ ድፍንና ቦርቃቃ መደምደሚያስ የመንግሥት መልዕክትና አቋም ቅርፅ ወግ አለው? ዕውን አሁን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት ውስጥ የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ዋና የበላይ በሆነውና የ47 አባል አገሮች አካል ሆና እ.ኤ.አ. እስከ 2018 መጨረሻ በምትሠራበት በሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ውስጥ እጇን አውጥታ የምትደግፈው ሐሳብ ነው?

ኢንተርኔት ተዘግቷል? አልተዘጋም? ይህን እንኳን ደፍሮ አደባባይ ወጥቶ የሚነግረን የለም፡፡ ‹‹የኢንተርኔት መዘጋት ኢትዮጵያን አይገልጽም›› ብሎ ነገር በዚህ በዚህ እንኳን ኢትዮጵያ አትጠረጠርም፣ እንዲህ ያለ ነገርስ ኢትዮጵያ አይነካካትም ማለት ሆኖ ይገባ ዘንድ ዋናው ዋስትና የአገልግሎት ሰጪው ድርጅት የሥራ አካሄድ ወይም አሠራር ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ያለበት፣ በሕዝብ ዓይንና ጠያቂነት ሥር የወደቀ ለማናለብኝነት የማይመች ሆኖ ሲደራጅ ነው፡፡ የመብቶችን ረገጣ የመንግሥትን በሥልጣን የመባለግ አዝማሚያም ሆነ አባዜ የሚከላከል ፈጥኖ የሚሰማና የሚያሰማ ፍጥርጥርና ማዕቀፍ ሲኖረው ነው፡፡ ከመንግሥት አወቃቀርና አሠራር እስከ ሕዝብ ወሳኝነት ድረስ የራሱ መጠበቂያ ያለው ሳይጠየቁ መቅረትን እንቢ የሚል አደረጃጀት ሲኖር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ሥርዓቱና ኢንዱስትሪው ግን ሲጀመር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከላይ ወደታች በኮማንድ ፖስት፣ በፕሮሰስ ካውንስል፣ በሥራ ሒደት፣ በቡድንና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የተዋቀረ ነው፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ብቻ 1,250 ቡድኖች፣ 3,005 የአንድ ለአምስት አደረጃጀቶች አሉ (የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መጋቢት 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ)፡፡

ኢሕአዴግ፣ ‹‹እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ›› ከጀመረ ወዲህ የወጣው የመስከረም ጥቅምት 2009 የድርጅቱ የትንታኔ መጽሔት (አዲስ ራዕይ) ላይ ‹‹በሶሻል ሚዲያ ምኅዳሩ ተሳትፏችንን በማሳደግ ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣ›› ይላል፡፡ በዚህ የአቋም ጽሑፍ ላይ የሶሻል ሚዲያውን ጠቀሜታዎች ይገልጻል፡፡ ችግሮቹንም፣ ጉዳቶችንም ይዘረዝራል፡፡ የሚያሳስበውም ያስቸገረውም ይኼኛው የሶሻል ሚዲያው ‹ገጽታ› ነው፡፡ ኢንተርኔቱን ቴሌኮሙዩኒኬሽን ግንኙነቱን እንደ ቤት አምፑል በማብራያ ማጥፊያ ብልጭ ድርግም የሚያደርገው ዝግት ቁልፍ አድርጎ ድምፁን የሚያጠፋው፣ ይህንን ኢሕአዴግ አሰፈንኩት በሚለው የአገር ሰላም ጉሮሮ ውስጥ የተሰካ አጥንት፣ እንደ ጥፋት ሰይፍ በአገር ህልውና ላይ የተንጠለጠለ ችግር አድርጎ የሚቆጥረውን ሶሻል ሚዲያ ለመገላገል ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ግን ሶሻል ሚዲያው እነዚህ ችግሮች ቢኖሩትም ‹‹ኢሕአዴግ የሚኖረው አማራጭ ሚዲያው የሚሰጠውን ዕድል አሟጦ መጠቀምና የሚፈጥራቸውን ሥጋቶች ደግሞ መቀነስ ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡ ምክንያቱንም ይገልጻል፡፡ ‹‹ይህ የሚሆንበት ምክንያት ከቴክኖሎጂ አንፃር የሶሻል ሚዲያውን አገልግሎት መወሰን ወይም መግታት የማይቻል ስለሆነ አይደለም፡፡ ይልቁንም የምንከተለው ዴሞክራሲያዊ መስመርና የምንገነባው ሥርዓት ይህንን ግድ ስለሚል ነው፤›› ይላል፡፡ ይህ ‹‹ግድ›› የሚል ነገር ከኢሕአዴግ ፈቃድና ምርጫ ከሱም ቁርጠኝነት ውጪ የሚኖር ስለመሆኑ የኢሕአዴግ አቋም በማያሻማ ቋንቋ አይናገርም፡፡ ይህንን የሚከለክለው የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 9/4፣ የአንቀጽ 13/2 እና የአንቀጽ 29 ድንጋጌዎች ኢሕአዴግ ከሚከተለው መስመር በላይ እንደሚያስገድደው ለአንደበት ወግ ያህል እንኳን አይናገርም፡፡ ‹‹ለደኅንነት ሲባል ከዚህ የባሰ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል›› ማለት ያህል ምላሽ መስጠት የተቻለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

መንግሥትና የመንግሥት የሥልጣን አካላት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው እውነቱን፣ እርግጡንና ቁርጡን የመናገር ግዴታ አለባቸው፡፡ ኢንተርኔት ተዘግቷል? አልተዛጋም? የተዘጋው ወይም አገልግሎቱ የተቋረጠው በመንግሥት ውሳኔ ነው? ወይስ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታሩ ላይ በደረሰ አደጋ የጂቡቲ ፋይበር ኦፕቲክ በመበላሸቱ? ኢንተርኔት የተዘጋው በመንግሥት ትዕዛዝና ፈቃድ ከሆነ የዚህ የሕግ መሠረት ምንድነው? ኢንተርኔቱን ያዘጋው የአገር የደኅንነት ሥጋት የትኛው ነው? ባለሥልጣኖቻችን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊትና በዓለም የሕግ አደባባይ ላይ ከእነሱ በላይና የበላይ ሆኖ በሚገዛቸው ሕገ መንግሥት መመዘኛ ተናግረው የማያፍሩበት፣ እንደ ንግግራቸው በማስረጃ የሚያረጋግጡት ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ ‹‹የጥልቅ ተሃድሶው›› የጥበብ መጀመርያ እውነቱን በሙሉና እውነቱን ሁሉ መናገር፣ የወሰዱትን ዕርምጃ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ከእነ ምክንያቱ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ስሜት የማስረዳት ግዴታ አለብኝ ብሎ መነሳት ነው፡፡ መሪዎቻችን መሥራት የሚችሉት በሕግ በተወሰነ ሥልጣናቸው ውስጥ የተፈቀደውን ብቻ ነው፡፡ የእግር መንገዳቸው፣ የዓይን ብርሃናቸው የበላይ የሌለው ሕግ እንጂ ቴክኖሎጂው አይደለም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...