Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዋሊያዎቹ ውጤትና የቀጠለው የቁጭት ጩኸት

የዋሊያዎቹ ውጤትና የቀጠለው የቁጭት ጩኸት

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና አቻው የ5 ለ 0 ሽንፈት ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ፣ ከየአቅጣጫው የተለያዩ የምሬት አስተያየቶች እየተደመጡ ይገኛል፡፡  ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጋና የተመለሱት ዋሊያዎቹም የሚቀርብባቸው ትችትና ወቀሳ እየበረታም ቢሆን ዝምታን መርጠዋል፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝም ሆኑ ሌሎች ልዑካን ስለጨዋታው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ ምንም ዓይነት መግለጫም ሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያ የዋሊያዎቹን ውሎ የሚያብጠለጥሉ፣ ተጨዋቾችንና አሠልጣኞችን የሚኮንኑ፣ ፌዴሬሽኑንና የስፖርት ዘርፉን አመራሮች የሚተቹ በርካታ ስሜታዊ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፣ በመሰንዘር ላይም ናቸው፡፡

በቡድኑ ውጤት በእጅጉ ከተሰላቹ አስተያየት ሰጪዎችም እግር ኳስ ለኢትዮጵያ አይሆናትም እስከማለት የደረሱም አልታጡም፡፡ በርካቶች እንዲህ በተናገሩበት፣ አሠልጣኞች፣ ተጨዋቾችና ፌዴሬሽኑ በከፋ ደረጃ በተወቀሱበት በዚህ ጨዋታና ውጤት ላይ አስተያየታቸውን ካሰፈሩት መካከል የአፍሪካ እግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው በፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት ሐሳብ ይጠቀሳል፡፡

እንደ አቶ ታደለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተሸነፈ ቁጥር ከየአቅጣጫው የምሬት አስተያቶች ይሰማሉ፡፡ ዘጠና በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑት ከፊሉ ፌዴሬሽኑን፣ ከፊሉ ደግሞ አሠልጣኙን ተጠያቂ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይሁንና ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ግን የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ሙሉ አለመሆናቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መሪዎች በየጊዜው፣ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ደግሞ በበለጠ ፍጥነት ሲቀያየሩ መመልከት መለመዱን የሚገልጹት አቶ ታደለ፣ ውጤቱ ግን እየባሰበት ካልሆነ አልተየቀረም ይላሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ችግሩ ከመነሻው የፌዴሬሽን መሪዎች ወይም አሠልጣኞች ብቻ እንዳልሆነና ችግሩን ለይቶ ማወቅ የመፍትሔው ግማሽ አካል ተደርጎ መወሰድ፣ በጉዳዩ ዙሪያም በጥልቀት መነጋገር እንደሚገባም ያምናሉ፡፡

እሑድ ሰኔ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ አምስት ጎሎችን ያስቆጠረው የጋና ብሔራዊ ቡድን፣ እግር ኳሱ ያሟላቸውና አጠቃላይ መዋቅራዊ ቅርፁ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ልዩነት በንፅፅር መመልከት ቢያንስ ለቀጣዩ ጉዞ አጋዥ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለውም ይገልጻሉ፡፡ ይኼውም የጋና የከተማ ፕላን ባለሙያዎች በየሠፈሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ስለሚከልሉ የጋና ሕፃናት እየተጫወቱ ያድጋሉ፡፡ ክለቦቻቸው በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች ያሉ ተጨዋቾችን ስለሚይዙና ዓመታዊ ውድድሮችን ስለሚያዘጋጁላቸው፣ በአፍሪካ ሁሉንም የዕድሜ ክልል ውድድሮችን ማሸነፍ ለጋናውያን እንግዳ ነገር አለመሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ታደለ ሁሉ ሌሎችም በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማግሥት፣ በተለይም ቡድኑ ጠንከር ያለ ሽንፈት ሲገጥመው ብቻ ከየአቅጣጫው የሚደመጠው የምሬት ዋይታ እዚህ ላይ ሊቆም እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱም የተዘራውን እንጂ ያልተዘራነውን መመኘት እንደማይገባ ያስረዳሉ፡፡

ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል የዋሊያዎቹ ልዑክ በመሆን ወደ ሥፍራው ያመሩና ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ ውጤቱ በኢትዮጵያና በጋና ተጨዋቾች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ የተመለከቱበት አጋጣሚ መሆኑንና ከአካል ብቃት፣ ከሥነ ልቦናና የወቅቱ እግር ኳስ ከሚጠይቀው የአጨዋወት ዘይቤ (ታክቲክ) ጭምር ሰፊ ልዩነት መመልከታቸውን እንደተረዱ ነው የሚናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ቡድን በጋና አቻው ይህን ያህል በሰፊ የጎል ልዩነት ባይሆንም፣ በሜዳውና በደጋፊው ፊት እንደመጫወቱ በጠባብ ውጤት እንደሚሸነፍ እምነቱ እንደነበራቸው ያስረዱት አስተያየት ሰጪው፣ የተዋጠን ነገር መልሶ መላልሶ ከማላመጥ ነገ የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ አቅዶ መሥራትና መንቀሳቀስ እንደሚበጅ ያሳስባሉ፡፡

በውጤቱ ማግሥት ከየአቅጣጫው እየተደመጠ ያለው ጩኸት መደምደሚያው የአገሪቱን እግር ኳስ ለመታደግ እስከሆነ ድረስ ቁጭቱና ምሬቱ የአንድ ሳምንት ታሪክ ሆኖ እንዳይቀር የሚሠጉት አስተያየት ሰጪ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን በመሳሰሉ የክልል ከተሞች ጭምር ለእግር ኳስ ማዘውተሪያ ቀርቶ ለፀሐይ መከላከያ የሚሆኑ ዛፎች የሚበቅሉበት ቦታ እንኳን የጠፋ መሆኑም ይናገራሉ፡፡ ይህ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ሁኔታ ደግሞ ስለብሔራዊ ቡድን ውጤት መጥፋት መቆጨትና ማውራት ደግሞ ስህተት መሆኑን ጭምር ያብራራሉ፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ገና በጠዋቱ በጫትና መሰል ሱሶች ተጠምደው በሚውሉበትና በሚያድሩበት በዚህ ወቅት፣ ምን ዓይነት እግር ኳስ የሚጫወት ትውልድ እንደሚጠበቅ ለእሳቸው ከእንቆቅልሽም በላይ መሆኑንም ይናራሉ፡፡

በኢትዮጵያና በጋና እግር ኳስ መካከል ያለውን የደረጃ ልዩነት አስመልክቶ አቶ ታደለ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከሚያዘጋጃቸው የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ከ23 ዓመት፣  ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች በአውሮፓና መሰል አገሮች በሚገኙ ሀብታም ክለቦች ሳይቀር የጋና ታዳጊዎችና ወጣቶች ሰፊ የመታየት ዕድል ያላቸው ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በላይ ለጋና ዋናው ቡድን የሚጫወቱ ተጨዋቾች በአብዛኛው በአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች የላቀ ሥልጠናና ልምድ አግኝተው የመጡ እንደ መሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ላይ ያስመዘገቡት ውጤት እንደማይገርማቸው ነው የገለጹት፡፡ ‹‹ስለሆነም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከጋናም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆን ከሆነ ፍላጎታችን፣ በየደረጃው የሚገኙ ክለቦች ቀደም ሲል በተዘረዘረው የዕድሜ ክልል በትክክለኛው አካሄድ ማደራጀትና የውድድር ዕድሎችን መፍጠር የግድ ነው፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

ወደ ጋና ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ለቅንጅት ይረዳው ዘንድ ቢያንስ ከሦስት ያላነሱ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚዘጋጁለት ሲነገር ነበር፡፡ ይሁንና ቡድኑ ያደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሰርቢያዊው ሚቾ ጠያቂነት አንድነት ጨዋታ ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ቡድን እንደ ሌሎች አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ፊፋ በይፋ በሚያውቃቸው የወዳጅነት ጨዋታ መርሐ ግብር ተሳታፊ ሆኖ እንደማያውቅ የሚታወቅ ነው፡፡ እንዲያውም የብዙዎቹ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች በዚሁ የፊፋ የወዳጅነት መርሐ ግብ ተካፋይ በሆኑባቸው ወቅቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ማንነት እንኳ አይታወቅም ነበር፡፡ ከቡድኑ ተጨዋቾች ብዙዎቹ ከኢትዮጵያ ውጪ በፕሮፌሽናልነት ተጫውተው ሳይሳካላቸው የተመለሱ፣ ነገር ግን በአገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ተተኪ ከሚባሉት ተሽለው ኮከብ ጎል አስቆጣሪ መሆን የቻሉ መሆናቸውን ጭምር በመጥቀስ፣ ብዙዎች የአገሪቱ የሊግ ሁኔታም መታየት እንዳለበት ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ በሌላ ጽንፍ ያሉ ወገኖች ደግሞ አገሪቱ መቼም የማይለወጠውን እግር ኳስ ትታ አትሌቲክስ ላይ ብታተኩር ይሻላታል ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...