Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አሠራሩን በማስተካከል 2.6 ቢሊዮን ብር አዳንኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2008 ዓ.ም. ግብርና ምርት ዘመን በተከተላቸው አዳዲስ ማሻሻያዎች፣ 2.6 ቢሊዮን ብር (120 ሚሊዮን ዶላር) ማዳኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን አወቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በማዳበሪያ ግዢ አሠራር ላይ ማስተካከያ በመደረጉ ዓለም አቀፍ የማዳበሪያ አምራቾች በቀጥታ በመሳተፋቸው ሁለት የንግድ ሰንሰለቶች ተሰብረዋል፡፡ ‹‹በዚህም ለማዳበሪያ ግዢ ይውል የነበረ 2.6 ቢሊዮን ብር ወይም 120 ሚሊዮን ዶላር ሊተርፍ ችሏል፤›› ሲሉ አቶ ብርሃን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ ባንክ በሌተር ኦፍ ክሬዲት አከፋፈት ላይ ማስተካከያ በማድረግ 36 ሚሊዮን ብር መትረፉን አቶ ብርሃን ገልጸው፣ ማዳበሪያ ወደ አገር በሚገባበት ወቅት በወደብ አካባቢ ስንዴን የመሳሰሉ ክምችቶች ባለመኖራቸው ጥሩ የሚባል የትራንስፖርት ዋጋ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ የዘንድሮ የማዳበሪያ ግዢ በዋጋ ደረጃ መሻሻል የታየበት በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ በተለያዩ የማዳበሪያ ዓይነቶች በኩንታል ከ250 ብር እስከ 350 ብር ድረስ ቅናሽ ሊያገኝ ችሏል፤›› ሲሉ አቶ ብርሃን የምርት ዘመኑን መልካም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለ2008 እና 2009 ዓ.ም. የምርት ዘመን ሰባት ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ፈጽሟል፡፡

አቶ ብርሃን እንዳብራሩት በ19 ምድቦ ተከፋፍሎ የተገዛው ማዳበሪያ በአብዛኛው አገር ውስጥ የገባ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ መርከቦች ወደብ ደርሰው እያራገፉ ስለሆነ በዚህ ወር ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አገር ውስጥ ይገባል፡፡

በዚህ ዓመት በሁለት መርከቦች የተጫነው አንድ መቶ ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ፣ በሱዳን ወደብ (ፖርት ሱዳን) በኩል አገር ውስጥ ገብቷል፡፡ በጂቡቲ ወደብ በኩል የገባ በመሆኑ፣ በአጠቃላይ 836,430 ኩንታል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ገብቷል፡፡ የተቀረውን ማዳበሪያ የጫኑ ሦስት መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ደርሰው ማራገፍ የጀመሩ ሲሆን፣ አንድ መርከብ ማራገፊያ በመጠበቅ ላይ ነች፡፡ አንድ መርከብ ደግሞ ባህር ላይ ትገኛለች፡፡

‹‹በሰኔ ወር ሙሉ ለሙሉ የምርት ዘመኑ ማዳበሪያ አገር ውስጥ ይደርሳል፤›› ያሉት አቶ ብርሃን፣ ‹‹ባለፈው ዓመት ግን ሐምሌና ነሐሴ ወራት ውስጥ ተጠቃሎ አልገባም ነበር፤›› በማለት የዚህ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም መሠረታዊ ለውጥ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

አገር ውስጥ የገባውን ማዳበሪያ አሥር የከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረት ማኅበራት በማጓጓዝ ላይ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በወቅቱ ማዳበሪያ እየቀረበላቸው አለመሆኑን ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የአማራ ክልል የቡሬ ወንበርማ ወረዳ አርሶ አደሮችና የደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ እንዳስረዱት ማዳበሪያ በወቅቱ እየቀረበ ባለመሆኑ፣ በእርሻ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ አልቻሉም፡፡ ማዳበሪያውም በነጋዴዎች እጅ እየወደቀ የዋጋ ለውጥ እየታየበት ነው፡፡

የቡሬ ወንበርማ ወረዳ በግብርና ምርት ይታወቃል፡፡ የወረዳው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋው ለአማራ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ እንደገለጹት፣ ወረዳው በክልሉ ካሉና ትርፋማ አምራቾች ከሚባሉ ወረዳዎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በሰብል ልማት በተለይም ስንዴ፣ በቆሎና በርበሬ ይለማል፡፡ አሁን የግብርና ሥራዎችን ለማቀላጠፍ የግብዓት ችግር መግጠሙንና አርሶ አደሩም በወቅቱ ሥራውን ማከናወን አልቻለም ብለዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮችም በ1,134 ብር በኩንታል የተጀመረው የማዳበሪያ ሽያጭ ከአሥር ቀናት በኋላ ስድስት ብር መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ አቶ ብርሃን ቀደም ሲል አርሶ አደሮቹ የጠቀሱት ችግር እንደነበር አምነው፣ ነገር ግን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ይህ ችግር መፈታቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹በቡሬ አካባቢ የነበረውን ችግር ተረባርበን ፈተነዋል፡፡ ለአካባቢው ቅድሚያ በመስጠት 48 ከባድ ተሽከርካሪዎች ማዳበርያ ጭነው ተጉዘዋል፡፡ ከራሳችንም (ከኮርፖሬሽኑም) መጋዘንም አከፋፍለናል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ብርሃን፣ ‹‹በአርባ ምንጭ አካባቢ ችግሩ ተፈትቶ አሁን ያለው ችግር የመጋዘን ነው፡፡ ማዳበሪያ አርባ ምንጭ ማከማቸት ተችሎ ከባድ ተሽከርካሪዎች የሥምሪት ለውጥ ተደርጎላቸው ሻሸመኔ እንዲያራግፉ እየተደረገ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከዘንድሮ በስተቀር ባለፉት 25 ዓመታት በአብዛኛው የማዳበሪያ ዋጋ ንረት እንዳለ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በመጀመሪያ በማዳበሪያ አቅርቦት የሚታወቀው የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በአብዛኛው የኢንዶውመንት ኩባንያዎች የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ በኋላም ዘርፉ ለገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተትቷል፡፡ ከዚያ በኋላ መንግሥት በቀጥታ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ግዢ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በዚህ ሒደት ዋነኛ ተሳታፊዎች የንግድ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡

በአሁኑ ወቅት  በተለይ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግዢ አሠራሮች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ባወጣው ጨረታ፣ ዓለም አቀፍ ማዳበሪያ አምራቾች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህም አገሪቱ ታጣ የነበረው 2.6 ቢሊዮን ብር ሊያድን በመቻሉ፣ ቀድሞ በነበረው አሠራር ላይ ጥያቄ መነሳት መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች