Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የሰጠንን መብት ምርት ገበያው በአዋጅ ነጠቀን››

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ፣ የደቡብ ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች ማኅበራት ምክር ቤት ሊቀመንበር

የኢትዮጵያ የቡና ግብይት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በዘርፉ ተዋናዮች ስምምነት ተደርሶበት አዲስ የቡና የለውጥ አሠራር ውስጥ መተግበር ጀምሯል፡፡ እስካሁን የነበሩት አሠራሮችን ይቀይራሉ የተባሉ አዳዲስ የቡና ግብይት ዘዴዎችም እንደሚተገበሩ ይጠበቃሉ፡፡ በግብይቱ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያሉ ተቋማትም የእስከዛሬው አሠራራቸውን እንደሚቀይሩና በአዲሱ ሪፎርም የተቃኙ ሒደቶችን እንደሚከተሉ ይጠበቃል፡፡ የቡና ግብይት ሥርዓቱን የሚለውጥ አሠራር ለመቅረጽ ከአንድ ወር በላይ በፈጀ ውይይት ባለድርሻ አካላት አሉ ባሏቸው ችግሮች ላይ ተነጋግረው መፍትሔ እንዳስቀመጡም ተገልጿል፡፡ ከፖሊሲ አውጪዎች ጀምሮ፣ ቡና አልሚዎች፣ ላኪዎች፣ አቅራቢዎች፣ የቡና አምራች ማኅበራት፣ የውጭ ቡና ገዢዎች፣ ተወካዮችና ተመራማሪዎችም ተሳትፈውበታል፡፡ ይህ ሪፎርም የዓመታት ጩኸታችን የተሰማበት ነው፣ ስናቀርብ የነበው ጥያቄያችን ምላሽ ያገኘበት ነው የሚሉ ድምጾች እየተደመጡ ነው፡፡ ሊታይ የሚችለው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንኑ ተከትሎ የሚተገበሩ አሠራሮች የኢትዮጵያ የቡና ግብይት አዎንታዊ በሆነ መልኩ ይቀይራሉ በማለት ከሚሞግቱ አካላት መካከል  የቡና አቅራቢዎች ዘርፍ ይገኝታል፡፡ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምሥረታ ጀምሮ የተፈጠረው አሠራር የኢትዮጵያን ቡና እየጎዳ ነው በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ ከቆዩት ውስጥ የደቡብ ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አንዱ ነው፡፡ ለቡናው ሪፎርም የዚህ ማኅበር ተደጋጋሚ ጥያቄና በተደራጀ አኳኋን ሲቀርቡ የነበሩ ጥናታዊ ጽሑፎችም እንዳገዙ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ ይናገራሉ፡፡ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚጠበቀው አዲሱ አሠራር፣ የቡና አቅራቢዎችን መብት በምርት ገበያው ውስጥ የቆየውን ገዳቢ አሠራር እንደሚለውጥ ይነገራሉ፡፡ አቶ ዘሪሁን በአዲሱ ሪፎርም የምርት ገበያው ቦርድ አባል ሆነው ተሰይመዋል፡፡ ዳዊት ታዬ በቡና ሪፎርም ዙሪያና በተያያዥ ነጥቦች ዙሪያ አቶ ዘሪሁን ቃሚሶን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቡና ግብይትን ለመለወጥና አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት ሪፎርም ተጀምሯል፡፡ የግብይቱ ማነቆዎች ምንድን ነበሩ? ወደ ሪፎርም የተገባውስ እንዴት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ችግሩ ብዙ ነው፡፡ በጥልቅ ስታየው ግን አጠቃላይ የቡና ግብይት ሥርዓቱ በችግሮች የተተበተበ ነበር፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ መመሥረት ጋር ተያይዞ ከታች ጀምሮ ግብይት እንድትፈጽም የሚያስገድዱ አሠራሮች፣ ለአገሪቱ የቡና ገበያ እንቅፋት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ታች ያለው ግብይት ለቡና ጥራት እንቅፋት ነበር፡፡ የሪፎርሙ ጠያቂዎችና ባለቤቶች እኛ ነበርን ማለት እችላለሁ፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ተደራጅተን ቡና ትኩረት ስለማጣቱ ስንናገር ነበር፡፡ የዘርፉን ችግር ስንናገር ቆይተን በአዲስ የማኅበራት አደረጃጀት 2000 ዓ.ም. እንደገና ተቋቁመን ይህንኑ ጥያቄ ስናቀርብ ነበር፡፡ በዚህ መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲመጣ ዘመናዊ ግብይቱንም ተቀብለናል፡፡ ለምርት ገበያው ሐሳብ አፍላቂና መሥራች ዶ/ር ኢሌኒ ገብረ መድኅን ከፍተኛ አቀባበል አድርገንላቸዋል፡፡ ምክንያቱም አዲስ የመጣው አሠራር የእኛንም ጥያቄ ይመለሳል የሚል እምነት ስለነበረንም ነው፡፡ ምርት ገበያው ለአንድ ዓመት ከሠራ በኋላ የቡና ግብይት ችግር የበለጠ እየተባባሰ መጣ፡፡ አቅራቢዎች የባለቤትነት መብታችን ተነጠቀ፡፡ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የሰጠንን መብት ምርት ገበያው በአዋጅ ነጠቀን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሲሉ እንዴት እንደሆነ ግልጽ ቢያደርጉልኝ?

አቶ ዘሪሁን፡- ከባንክ ብድር ወስደን ቡና እንገዛለን፡፡ በምርት ገበያው የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከል አለ፡፡ ለአርሶ አደሩ አቅራቢያ በሆነ አካባቢ የሚቋቋም ነው፡፡ አርሶ አደሩ ቡናውን ለማዕከሉ ያቀርባል ተብሎ ቢጀመርም በአብዛኛው ግን ቡናውን ለደላላ ማቅረብ ጀመረ፡፡ እኛ እንደ አቅራቢ ከአርሶ አደሩ ጋር የነበረን ግንኙነት ተቋረጠና ግንኙነታችን ከደላሎች ጋር ሆነ፡፡ ደላሎቹ ቡናውን ሲሰበስቡ ውለው የፈለጉትን ዋጋ አውጥተው ይሸጡልሃል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሦስት ዓይነት ቡና ነው የምንገዛው፡፡ አረንጓዴ የተሸመጠጠ ቡና፣ ቀይዳማ ቡና እንዲሁም ቀይ እሸት ቡና እንገገዛለን፡፡ እነሱ ግን ሦስቱን ደባልቀው ይዘረጋሉ፡፡ ኪሎ እንዲያነሳላቸውም ውኃ ውስጥ በማሳደር በሁለተኛው ቀን ይሰጡሃል፡፡ አልወስድም ማለት አትችልም፡፡ ምክንያቱም ገንዘብህን መጀመሪያ ስለሰጠሃቸው የግድህን ትወስዳለህ፡፡ ስለዚህ ከጥራት አንፃር የተሻለ ለውጥ ያመጣል የተባለው አሠራር አልሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ታች ያለው የቡና ግብይት ችግር ነበረው ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን! በአስተሳሰብ ደረጃ ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በራሳችን ገንዘብ ማዘዝ አልቻልንም ነበር፡፡ ቡናው የእነሱ ስለሆነ፣ አንተ በገንዘብህ  የምትገዛውን አውቀህ ዋጋ ለመስጠት እንኳ አትችልም፡፡ አንተ ገንዘብ ተበድረህ ታመጣለህ፣ በገንዘብህ ግን አታዝበትም፡፡ ማዘዝ ማለት በዚህ ገንዘብ ይህንን ያህል እገዛለሁ ስትል ነው፡፡ ቀድመህ በሰጠኸው ገንዘብ ምክንያት በዚህ ዋጋ ካልሆነ አልሸጥልህም ውሰድ ከተባልክ በገንዘብህ እያዘዝክ አይደለም ማለት ነው፡፡ እስካሁን በነበረው አሠራር የሆነው ይህ ነው፡፡ እንደ አቀራቢ አንተ ቡናውን ለመሰብሰብ ገንዘቡን ከባንክ ስለተበደርክ ያንን ቡና አምጠተህ ፈልፍለህ፣ አስጥተህና አድርቀህ ለገበያ ታቀርባለህ፡፡ ይህ ቡና ግን በመጀመሪያ ግዥ ጣቢያ እንደ ነጋዴ ተደራድረህ የገዛኸው ቡና አይደለም፡፡ ቡናውን ጭነህ አምጥተህ በምርት ገበያው የመመርመሪያ ማዕከል ስትደርስ ጭነቱን አስረክበህ ትመለሳለህ፡፡ ቡናህን የሚያስመረምሩልህ በኮሚሽን የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ቡናው የሚቀመሰው በኮሚሽን ነው፡፡ የሚራገፈው በኮሚሽን ነው፡፡ በዚህ መንገድ መጋዘን የሚገባውን ቡናህን አታየውም፡፡ ይህንን ሒደት ቦሌ ኤርፖርት ሔደህ ሰው እንደመሸኘት ቁጠረው፡፡ ምርት ገበያው በራፍ ላይ ያስረከብከውን ቡና ዕጣ ፈንታ የምታውቀው በስልክ ደውለህ ነው፡፡ ስንተኛ ወጣ? ደረጃውን አለፈ ወይ? ተራገፈ ወይ እያልክ ስትከታተል ቆይተህ በመጨረሻው የሚሸጥልህ አገናኝ የሚባለው አዲስ አበባ ያለው ባለወንበር ነው፡፡ ይህ የሚያሳይህ የገዛ ቡናህን ተደራድረህ መሸጥ የማትችል መሆኑን ነው፡፡ ተደራድረህ ያልገዛህበትንና ተደራድረህ ያልሸጥከበት አሠራር ንግድ አይደለም የምለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በመቀማማት ውስጥ ነው ያሳለፍነው ማለት ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- እስካሁን በነበረው አሠራር እንዲህ ያለው ችግር መኖሩን ለማሳወቅ ምን ያህል ሞክራችኋል? የቡና ገበያ ሥርዓት ምቹ ካልነበረ የአሁኑ ዓይነት ዕርምጃ ለምን ከዚህ ቀደም አልተወሰደም?

አቶ ዘሪሁን፡- አሁን የነገርኩህን ብቻም ሳይሆን ሌሎችን ነጥቦች ዘርዝረን ችግር ላይ መሆናችንን አቅርበናል፡፡ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድም ሳላስቀር አቅርቤያለሁ፡፡  ይህንን ችግር አስተካክሉ፤ አደጋ ውስጥ ነን፤ የቡና ጥራት እየተበላሸ ነው ብለናል፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን፣ የውጭ ገዥዎችም ልክ እንደኛው ሥጋታቸውን አቅርበዋል፡፡ አሠራሩን ተመልክተው ይኼ አሠራር አያስኬዳችሁም፣ ቡናችሁን ያጠፋባችኋል ብለው ምክረ ሐሳብ ጽፈዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ አያስኬዳችሁም ያሉት የምርት ገበያውን አሠራር ማለት ነው?  ቡና ገዥዎቹ ለማነው ደብዳቤ የጻፉት?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን! የምርት ገበያውን አካሄድ ነው፡፡ የጻፉትም ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፡፡ እኛ ይህ አሠራር ችግር እንዳለው ስንናገር የመጀመሪያው ዓመት ላይ ተፈትሾ ነው፡፡ በሁለተኛው ዓመት የምርት ገበያው አሠራር አያስኬድም ተባለ፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ማለት ምርት ገበያው ወደ ሥራ በገባ በሁለተኛው ዓመት ማለትም በ2003 ዓ.ም. ማለት ነው? በዚያን ወቅት የምርት ገበያው አሠራር አያስኬድም ያላችሁበት የተጨበጠ ምክንያት ነበራችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን በ2003 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ የቡና ጥራት ላይ ችግር እንደሚፈጥር በመገንዘባችን ነበር፡፡ የቡና የባለቤትነት መብት ተወስዶብናል፡፡ በአገሪቱ ቡና ላይ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉ በመረዳታችን ነው፡፡ ይህንን የሚያሳዩ ጽሑፎችን በዓመት ለሦስት ጊዜ ያህል እያዘጋጀን ስናቀርብ ነበር፡፡ በአሠራሩ ደላላው ተደራድሮ በፈረሱላ 50 እና 100 ብር ለራሱ እላፊ ይዞ እንኳ ሽጥልኝ ስትለው አይሸጥህም፡፡ የታዩት የቡና ዘርፉ ውድቀቶች  የመጡት እኮ በግብይት ሥርዓቱ ችግር ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከመጀመሩ በፊት የነበረው የቡና ጥራት ትኩረት ተነፍጎታል ይባል ነበር፡፡ የቡና ኤክስቴንሽን ላይ ክፍተት መኖሩን፣ በቡና ላይ የሚደረግ ምርምር አነስተኛ መሆኑን፣ በጠቅላላው ለቡና የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ ጠቅሰናል፡፡ ስለ ሰብል ምርቶችና ስለ ግብርና ሲነሳ፣ ቡና ከመጀመሪያም ያደገ ነው እየተባለ ከቡና ይል ስለበቆሎ ነበር የሚወራው፡፡ ስለዚህ ለስምሪት የሚወጣው ካድሬም ከላይ የመጣ አቅጣጫ ነው ይልና ብዛት ያለውን የቡና ማሳ ትቶ ስለበቆሎ እያወራ ነው ብለን ችግሩን በመተንተን አመልክተናል፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዲህ ላሉት ችግሮች ተጠያቂው የምርት ገበያው አሠራር ብቻ ነው ሊባል ይችላል?

አቶ ዘሪሁን፡- ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ቡና ላይ የመጡ ሰዎች ቡናን አለማወቃቸው ነው፡፡ እነሱ የሠሩ በሚመስላቸውም ዘርፉ ግን እየተጎዳ ሄዷል፡፡ ሰዎቹ በትምህርት ብቃት ችግር የለባቸውም፡፡ በዕውቀት ደረጃ ችግር የለባቸውም፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃ አገርን ሊጎዳ የሚችል ነገር እንደማይሠሩ የሚታወቅ ነው፡፡ አሠራራቸው ግን ማነቆ ነበረው፡፡ ለእነሱ ሥራ የሆነው ነገር ለእኛ ግን አደጋ ፈጠረ፡፡ ይህንን ስንነግራቸው ስላልገባችሁ ነው ይሉናል፡፡ ይኼ ማለት ታመህ ሐኪም ቤት ሔደህ ሕመምህን ለሐኪሙ እያስረዳኸው አልታመምክም፣ በሽታ የለብህም እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ትግል ስናደርግ ቆይተን ቀውሱ እየመጣ ሲሄድ መንግሥትም ጉዳዩን መረዳት ጀመረ፡፡ በቅርቡ የመጨረሻው ውሳኔ ከተወሰነ ወዲህ ሌሎች ጥናቶችን ለማድረግ ሲሞከር ያየናቸው ነገሮችም ነበሩ፡፡

 ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጥናቶችና ናቸው? ምን ለማመላከት የሚረዱ ናቸው?

አቶ ዘሪሁን የአገሪቱን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ የሚፈጅብህን ወጪ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ለመላክ የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ታይቷል፡፡ የብራዚል፣ የኮሎምቢና የቬትናም የቡና ገበያ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ተፈትሾ፣ ከጥናቱ መረዳት እንደሚቻለው የብራዚል የቡና የኤክስፖርት ወጪ አሥር በመቶ፣ የኮሎምቢያና የቬትናም የቡና የኤክስፖርት ወጪ ደግሞ አራትና አሥራ አራት በመቶ ነው፡፡ የእኛ ግን 40 በመቶ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረው የቡና ግብይቱ ውስጥ ተደራራቢ ወጪ የሚጠይቁ አሠራሮች ስለሰፈኑበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኤክስፖርት ወጪ የሚባለው እንደምን ያሉትን የሚያጠቃልል ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- የኤክስፖርት ወጪ የሚሰላው ከታች ቡናውን ስትገዛ ጀምሮ ያለብህን ወጪ አካቶ ነው፡፡ የአርሶ አደሩን ቡና ለመግዛት ለደላላ ትከፍላለህ፡፡ ቡና ሲበተን የሥራ ማስኬጃ ወጪ አለው፡፡ የአጣቢና የለቃሚ ደመወዝ አለ፡፡ ይህንን ከተወጣን በኋላ ደግሞ ወደ ምርት ገበያው ስንመጣ ሌላ ወጪ ይጠብቀናል፡፡ የመጋዘን፣ በድጋሚ ሌላ የደላላ ወጪ አለ፡፡ የገበያ ወጪም ይደመራል፡፡  በሌሎች አገሮች ግን የገበያው ሰንሰለት አጭር ነው፡፡ ወጪውም ትንሽ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች አርሶ አደሩ፣ የቡና ገዥውና ኤክስፖርተሩ ነው የሚገናኘው፡፡ የእኛ ሰንሰለት ግን ረዥም ነው፡፡ በየቦታው የምትከፍለው ይበዛል፡፡ በዚህ ረዥም ሰንሰለት ውስጥ ያሉት ደግሞ ምንም እሴት የማይጨምሩ ዋጋ ግን የሚጨምሩ ናቸው፡፡ አሁን በተወሰነው መሠረት ግን ቡና ለመላክ ይወጣ የነበረውን ወጪ በግማሽ ለመቀነስ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡   

ሪፖርተር፡- ረዥም የተባለውን የቡና ገበያ ሰንሰለት ማሳጠር ብቻ ሳይሆን፣ ቡናን ለመላክ ይወጣል የተባለውን ወጪ ለመቀነስ ሲወሰን ምን ታሳቢ ተደርጎ ነው?  የሚጠበቁትን አንዳንድ ለውጦችም ቢጥቀሱልን?

አቶ ዘሪሁን፡- ቡናውን ራሳችን እንድንገዛና እንድንሸጥ ይፈቅዳል፡፡ በመኪና ላይ እንድንሸጥ፣ በስማችን እንድንሸጥ፣ ሸቀጥነቱ ቀርቶ ወደ ኋላ በመሔድ የቡናውን መነሻ እንድናውቅና እንድንመጣ የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን በተወሰነው መሠረት ነው ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጀንበት መንገድም በጥያቄያችን መሠረት መቶ በመቶ ምላሽ ስላገኘን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ቡና አቅራቢ እንደመሆንዎ ይተገበራል የተባለው አዲስ የቡና ግብይት አሠራር ያስገኛል የሚሉት ተጨባጭ ለውጥ ምንድን ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ለምሳሌ ከቡና አቅራቢዎች አንፃር የባለቤትነት መብታችን ተመልሷል፡፡ ከአርሶ አደር ጋር ተደራድረን ቡና ልንገዛ የምንችልበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እኛም የአርሶ አደር ልጆች እንደመሆናችን እየተጋገዝን ለውጥ ለማምጣት በር ይከፈትልናል፡፡ በደላላ ሳይሆን በቀጥታ እንገዛለን፡፡ ያዘጋጀነውን ቡና አምጥተን በማስመርመር በቡናችን ስም ተደራድረን እንድትሸጥ ተወስኖልናል፡፡ ገዥ ካገኘንም ቡና ገዝተው ኤክስፖርት ከሚያደርጉ ላኪዎች ጋር በመተሳሰር የሁለትና የሦስት ዓመት ውል ተዋውለን ቡና ልንሸጥ የምንችልበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጥሩ ዋጋ አግኝተህ ቡናህን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችልህ ብቃት ላይ ስትደርስ፣ ቡና ከማሳ ላይ ልትጭን የምትችልበት ዕድል እንዲኖር ተወስኗል፡፡ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮች መወሰናቸው ለዓመታት ስናቀርብ የነበረው ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስልን አስችሏል፡፡ ይህንን ውሳኔ መሬት ለማውረድ እየተሠራ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አዲሱ አሠራር የምርት ገበያውን የአሠራር ድርሻ እንደሚነካካ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አዲስ አሠራር የሚተገበር ከሆነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚና ምን ሊሆን ይችላል? በቅርቡ እንደተገለጸው አዲሱ አሠራር ሲተገበር ምርት ገበያው የልዩ ጣዕም ቡና ከሚባለው ውጭ ሌላውን ቡና ማገበያየቱ ይቀራል፡፡ ስለዚህ አዳዲስ ለውጦች ቢኖሩም በምርት ገበያው ነው የምትገበያዩት ወይስ ሌላ የግብይት መንገድ አላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን! ግብይቱ በምርት ገበያው በኩል ይቀጥላል፡፡ ምርት ገበያን ከቡና አንፃር ካየኸው ስሙ ነው እንጂ ያለው አሠራሩን ግን አፍርሰነዋል፡፡ ምርት ገበያው ቡናን ተረክቦ እንደ ሸቀጥ አንድ መጋዘን ላይ ከምሮ ለላኪ ነበር የሚሸጠው፡፡ በአዲሱ ለውጥ ግን ላኪ ቡናው የማን እንደሆነ አውቆ ነው የሚገዛው፡፡ እኔም ለማን እንደምሸጥ አውቄ ነው የምሸጠው፡፡ ስለዚህ ምርት ገበያው በአንድ መጋዘን ተመሳሳይ ደረጃ ያለውን ቡና እንደ ስኳር በአንድ መጋዘን አከማችቶ መሸጡ ቀረበት ማለት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ምርት ገበያው እስካሁን ግብይቱን የሚያስፈጽመው በአገናኞች ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ ግን አገናኝ የምንለውን አካል በአማራጭ እንጠቀምበታለን፡፡ የምርት ገበያው አሠራር እኔ ባዘጋጀሁልህ አንድ በር ውጣ የሚል ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ አሁን ግን አማራጮች እንዲከፈቱ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ቡናህን ቀርበህ መሸጥ ትችላለህ፡፡ የሚልከውም ገብቶ መግዛት ይችላል፡፡ ጊዜ ከሌለውና ታማኝነቱ ካለ ታማኝ ሆነው ሲገዙ የነበሩ ባለወንበሮች ቡና ሊገዙልህ ይችላሉ፡፡ ሊሸጡልህም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ብቻ  የነበረችውን መግቢያና መውጪያ በር አማራጮች እንዲኖሯት አሰፋልን ማለት ነው፡፡ ምርት ገበያው እስከ ዛሬ የተጓዘው በዚህች አገር ወጪ፣ በቡና ባለቤቶችና በቡና ተገበያይ አካላት ወጪና ኪሳራ ነው፡፡ ምርት ገበያው የዘመናዊ ግብይት ሞዴል ነው፡፡ እሱን ወደኋላ አንመልሰውም፡፡ ሶፍትዌር የመቀያየር ጉዳይ ግን ይኖራል፡፡ ቡና በአንድ ማዕከል ማገበያየት ስላለበት ይኼንን ሥራ ይሠራል፡፡ ሥራው ይቀጥላል፡፡ የገንዘብ ቅብብሎሹ ቀድሞ በተዘረጋው መንገድ መሄድ አለበት፡፡ መሠረታዊውን የአሠራር ችግር ግን አፍርሰነዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- መሠረታዊ አሠራሩ እንዲፈርስ ተደርጓል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- አንዱ የምርት ገበያው መሠረታዊ ችግር የባለቤትነት መብትን መግፋቱ ነበር፡፡ ቡናህን በስምህ ለመሸጥ መብት ያሳጣ የነበረው አሠራሩ ተቀይሯል፡፡ በዚህ በር ብቻ ግባ በዚህ በር ብቻ ውጣ የሚለው ነገር ቀርቶ የመውጪያና የመግቢያ አማራጭ በሮች ተከፍተዋል፡፡ እኔ ያደረኩልህ፣ እኔ የፈጠርኩልህ ነገር ብቻ ነው ትክክል ተብሎ ሲሠራበት የነበረውን በጋራ በነበረን ውይይት መድረክ ይኼ አካሄዱ ጥፋት መሆኑ ታውቆ ወደ አዲስ አሠራር እንድንገባ ተስማምተናል፡፡ ሠራን የሚሉትን ነገር በሪፖርት ሲያቀርቡ ይታይ የነበረው የገንዘብ ልውውጡ ነበር፡፡ ነገር ግን በሌላ ጎን ጥፋት እየተፈጠረ ነበር፡፡ ኤክስፖርቱ መውደቁን የምታውቁት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለቡና የወጪ ንግድ መውደቅ አንዱ የምርት ገበያው አሠራር ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን! ነገርኩህ እኮ፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የውጭ ቡና ገዥዎችም የምርት ገበያው ለቡና አዋጭ አይደለም በማለት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የእናንተ ቡና 16 ዓይነት ልዩ ልዩ ዝርያ ያለው ነው፡፡ ምርት ገበያው ግን ይህንን ሁሉ በአንድ ደባልቆ ነው የሚያቀርበው፡፡ ወደኋላ በመሔድ ለማገኘት የሚቻሉትንና የልዩ ጣዕም ቡናችንን አይሸጥም፡፡ ምርት ገበያው እኮ ይህንን ነው ያፈረሰው፡፡ ምርት ገበያው እንደሚታወቀው የዘመናዊ ግብይት ሞዴል ነው ነገር ግን የተለያየ ጣዕምና ባህርይ ያላቸው ቡናዎችን በራሳችን ስም እንዲሸጡ አያደርግም ነበር፡፡ ለምሳሌ የሲዳማ አካባቢ ያለ የፌሎ ቡና በስሙ ቢሸጥ የተሻለ ዋጋ ያስገኛል፡፡ ታች ድረስ ያሉ ተጠቃሚዎች ቡናውን ያውቁታል፡፡ ስለዚህ የተሻለ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ አሁን ቡናው ተቀላቅሎ በዚያ ላይ መደባለቅ ተፈቅዶ ስለሚሸጥ ኢትዮጵያዊ ቡና አልፈጠርም ነበር፡፡ ዓለም የሚያውቀው የኢትዮጵያን ቡና ሳይሆን ሌላ ቡና ነው፡፡ ምክንያቱም አንዱ ከሌላው ሲደበላለቅ ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እንዴት ነው የአገሪቱን ቡና የሌላ ቡና የሚያሰኘው?

አቶ ዘሪሁን፡- የጅማና የሲዳማ ቡናዎችን ቀላቅለህ ካቀረብክ ሌላ ስም ነው መሰየም ያለብህ፡፡ የተደበላለቀ ጣዕም ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲሱ አሠራር የአንድ አካባቢ ቡና ከሌላው ሳይቀየጥ በየአካባቢው ስም ለገበያ ይቀርባል ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ቡናችን በየአካባቢው ስም የሚሄድበት አሠራር እየተፈጠረ ነው፡፡ በቅርቡ በርካታ ገዥዎች በነበሩበት በአሜሪካ በተደረገ የቡና ንግድ ትርዒት ወቅት፣ ስለ አዲሱ አሠራር ገለጻ የተደረገላቸው ገዥዎች ይህን ካደረጋችሁ እኛም እንመለሳለን ብለዋል፡፡ እውነት ለመናገር መንግሥት ምላሽ ለመስጠት ፈጣን ነው፡፡ ሕዝብን ያዳምጣል፡፡ በቡና ዘርፍ ግን ከጉዳት በኋላ ነው የሰማው፡፡ ባይነገረው ኑሮ ችግር አልነበረውም፡፡ እየነገርነውም ችግሩ እየተፈጠረ ነው፡፡ ሳያውቁት እየሠራን ነው የሚሉ ሰዎች ለእነሱ ሥራ የመሰላቸው ነገር ለእኛ ሞት ሆነ፡፡   

ሪፖርተር፡- አዲሱን አሠራር ወደ መሬት ለማውረድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን አሠራሩን ለመተግበር ፍጥነት አልታየም፡፡ አሠራሩን ወደ መሬት ለማውረድ ከባድ ይሆናል እየተባለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ለውጥ ያመጣል ያላችሁት ይህ አሠራር በትክክል ለመተግበሩ ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- አገር ከዚህ በላይ ሊጎዳ አይገባም፡፡ ለውጡ ይመጣል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ቡናን የሚበልጥ ነገር እስካሁን አልተገኘም፡፡ ስለዚህ መንግሥት እስካሁን ያጣውን ነገር ሊመልስ የሚችልበት ዕድል በእጁ አለው፡፡ ይኼ ለእኛ ብቻ ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቡና የመንግሥት ነው፡፡ እኛ ኮሚሽን ነው የምንወስደው፡፡ እንደ አገር በኢኮኖሚው ወደፊት እንሄዳለን ከተባለ የውጭ ምንዛሪውን በማብዛት ተጠቃሚ መሆን መቻል አለብን፡፡ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ ባለበት ወቅት ይህንን አሠራር ወደታች ለማውረድ ይዘገያል ብዬ አላስብም፡፡ ይህንን አሠራር ወደታች ለማውረድ በአዲስ አስተሳሰብ እየተሠራ ነው፡፡ የምርት ገበያውና ለመተግበር አዲስ ቦርድ ለምርት ገበያው አደራጅቶ ይህንንም ወደ ታች አውርዱ ተብሎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ እስካሁንም የተወሰኑ ነገሮች መውረድ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሥራዎቹ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው፡፡ ከችግሩ አንፃር ቸኩለህ በመግባት የበለጠ እንዳታበላሽው መጠንቀቅ አለብህ፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን እየተሠራ ነው፡፡ ጊዜ መውሰዱ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በአገራችን ይህ ለውጥ እንዲመጣ የማይፈልጉ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በምን ምክንያት?

አቶ ዘሪሁን፡- በጦርነት ውስጥም እኮ የሚነግዱ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የምርት ገበያው አሠራር ይለወጣል ከተባለ ከሚታሰቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ በምርት ገበያው ትልቅ ቦታ ወይም ወንበር ያላቸው አገበያዮች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

አቶ ዘሪሁን፡- እነዚህ ወንበሮች ለአዲሱ አሠራር የገበያ አማራጮች ይሆናሉ፡፡ በመጀመሪያ እኮ ችግር ውስጥ የተገባው በእነዚህ ወንበሮች ብቻ ተገበያዩ በመባሉ ነው፡፡ ወንበር አማራጭ ነው መሆን ያለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ተማምነናል፡፡ ሁሉም በላድርሻ አካላት ተስማምተውበታል፡፡ ወንበሩ ምንም ሊሆን ይችላል፡፡ ለገበያ ነው የተፈጠረው፡፡ አማራጭ ነው መሆን ያለበት፡፡ በታማኝነት የቆዩት ወንበሮች አሁንም ይቀጥላሉ፡፡ ሌቦቹ ደግሞ ይወጣሉ፡፡ ባለወንበሮቹ ይወዳደራሉ ማለት ነው፡፡ ውድድሩ ታማኝነትና ቅልጥፍና ያመጣል ማለት ነው፡፡ እንደቀድሞ ግዴታ ሳይኖር እነርሱም በምርጫ ይሰሠራሉ፡፡ ወንበሮች ይጥፉ የሚል ነገር ግን የለም፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች ሲቀሩ ቡናን ለመላክ ይጠይቅ የነበረው ወጪ ይቀንሳል፡፡ ወጪውን ወደ 20 በመቶ ማውረድ የሚቻለው እንዲህ ዓይነቱን ድርብርብ ወጪ በመቀነስ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ወደ አሥር በመቶ ይወርዳል፡፡ ስለዚህ በግዴታ ሲገበያዩ የነበሩት ወንበሮች መንግሥት ሱቅ ከፍቶ እንደጣቸው ነው የሚቆጠረው፡፡ እነዚህ ሱቆች ደግሞ ከዚህ ብቻ ግዛ ይሉሃል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአዲሱ አሠራር የሚሆኑ መመርያዎች ፀድቀው ሥራ ላይ ይውላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይኼ ከሆነ በእርግጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና መጠንና የሚሰጠው ዋጋ ይጨምራል?

አቶ ዘሪሁን፡- መጠኑ በሒደት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት ግን ያድጋል፡፡ ምክንያቱም ይህንን የአሠራር ለውጥ ሲጠባበቁ የነበሩ ቡናችንን የሚፈልጉ የቀድሞ ደንበኞቻችን አሉ፡፡ ስለዚህ ያለምንም ጥርጥር የዓለምን ገበያ ያገናዘቡ ሽያጮች ይኖራሉ፡፡ ገበያው በእጃችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቀው በቡና ነው፡፡ ይህንን ለመመለስ ከባድ አይደለም፡፡ አሁን ራሳችንን አስተካክለን ነው የምንሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበት የሚደረግ ለውጥ ከሆነ ከአንድ ወር በላይ ፈጀ በተባለው ውይይት ምን ያህል ተማምናችኋል?

አቶ ዘሪሁን፡- የሚገርምህ ባለድርሻ አካላት የሚባሉት በዚህ ሒደት ውስጥ ሦስት ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ፣ አቅራቢ፣ ኤክስፖርተሩ፣ የውጭ ገዥ ኩባንያዎች ተወካዮች አሉ፡፡ ዋነኛ ተዋናዮች እነዚህ ናቸው፡፡ ሁሉም ተጎድተው የቆዩ ናቸው፡፡ ገዥዎች የሚፈልጉትን ዓይነት ቡና ማግኘት አልቻሉም፡፡ ላኪዎችም ጥራት የጎደለው ቡና ነበር የሚልኩት፡፡ የሚሠሩት ከገበያ ላለመውጣት ነበር፡፡ ብሶቱም ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ እኛ አቅራቢዎችም በሕገ መንግሥት የተሰጠንን መብት የተነጠቅንበት ነበር፡፡ ስለዚህ በመድረኩ ሁሉም ወደ ስምምነት ለመድረስ ያስቻለው ችግሬ ብሎ ያቀርብ የነበረው ጥያቄ ስለተፈታ ነው፡፡ ችግር የነበረበት አካልም ያስተካክል ተብሎ በመወሰኑ ነው፡፡ ለሁላችንም አገራችንን ማዕከል ያደረገ መግባባት ላይ ነው የተደረሰው፡፡ በተለይ የገበያው ሒደት ችግር ነበረበት የሚለው ጉዳይ የበለጠ ስላግባባን ነው መፍትሔ ይሆናል ወደ ሚለው ነጥብ የተገባው፡፡ ስለዚህ ትልቅ ተስፋ አለን፡፡ አዲሱ አሠራር ወደታች ይወርዳል፡፡ መንግሥት ያመነበትም ስለሆነ በትክክል ይተገበራል፡፡ ሥራው የአስፈጻሚ አካላቱን ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ጠንካራ ቦርድ ተመሥርቷል፡፡ ገበያው የሚመራው በቦርድ ነው፡፡ የአዲሱን የቡና ሪፎርም የሚከታተል ብሔራዊ ምክር ቤት ይቋቋማል፡፡ አጠቃላይ አፈጻጸሙን ይከታተላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ አሠራር ይተገበራል ከተባለው አንዱ የቡና የመኪና ላይ ሽያጭ መፈቀድ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ረዥም ሰንሰለቶችን አልፎ የመጣው ቡና መጋዘን ከገባ በኋላ ነበር የሚሸጠው፡፡ ከየትም ይምጣ ቡናው አንድ ላይ ይከማቻል፡፡ ይህ አሁን ቀርቷል፡፡ ቡናው የመጣበት አካባቢ በሰርተፍኬት መገለጽ ነበረበት፡፡ ቡናው መኪናው ላይ እያለ አጠቃላይ የጥራት ደረጃው ተለይቶ እዚያው መኪና ላይ ሆኖ ለጨረታ ይቀርባል፡፡ ይህ መሆኑ በተለይ ከጥራት አኳያ ይቀርቡ የነበሩ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ የተለያዩ የቡና ዓይነቶችን ቀላቅሎ ሲሸጥ የነበረውን አሠራር ያስቀራል፡፡ ከመኪናው ሳይወርድ ገዥው ቡናውን የሚያዘጋጅበት ቦታ ማድረስ ሁሉ ያስችላል፡፡ በአካባቢህ ስያሜ ቡናህን ለመሸጥ ትልቅ ዕድል ይፈጥርልሃል፡፡ ስለአተገባበሩ መመሪያ ይዘጋጃል፡፡ በነፃ ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡ በጥቅሉ አዲሱ አሠራር ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ላኪ አገር እንድትሆን የተያዘውን ዕቅድ ለመተግበር ትልቅ መሣሪያ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች