ገና በይሆናል በገና ደርድረህ
ሐሳብክን – ባሳቤ
ምኞትክን – በቅርፄ
መንፈስክን – በነፍሴ
ተክተህ – አኑረህ
የራስክን – ሰው – ፈጥረህ
ተዋወቅን – ማለትህ
ቂል ነው የሚያሰኝህ
እየኝ – ልይህ
ስሰጥህ ልቀበልህ
ግምትህን – ጥለህ፡፡
በአገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ‹‹ጨለማን ሰበራ›› (1985)
*******
ከቆሻሻ ሥፍራ በተሰበሰቡ መጻህፍት የተከፈተ ቤተ ንባብ
በኮሎምቢያ ቦጎታ ቆሻሻ በማንሳት ሥራ የተሰማራው የ54 ዓመቱ ጆሲ አልቤርቶ፣ ከየቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ያጠራቀማቸውን መጻህፍት በመጠቀም ቤተ መጻህፍት መክፈቱን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በትምህርቱ ከመጀመሪያ ደረጃ መዝለል ያልቻለው አልቤርቶ፣ ከ20 ዓመት በፊት ነበር ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ልብወለድ መጻሐፍ ተጥሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው፡፡ ከዛን ጊዜ ወዲህ በየቀኑ በሚያከናውነው የፅዳት ሥራ መጻህፍ ባገኝ እያለ ያማትር ነበር፡፡ አልቤርቶ እንዳለው፣ ከቆሻሻ መሰብሰብ ሥራው የተማረው ነገር፣ አገሬው መጽሀፍ እያወጣ መጣሉን ነው፡፡ ይህም ለሱ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮለት ከቦጎታ ከየቆሻሻ ሥፍራ ያሰባሰባቸውን 25 ሺሕ መጻህፍት በማካተት ቤተመጻህፍት ከፍቷል፡፡ ነዋሪዎችም በነፃ እንዲጠቀሙ አድርጓል፡፡ ለጋሾችም እጃቸውን ለአልቤርቶ እየዘረጉ ነው፡፡
*********
ውሾችን እንደ አዕምሮ ማነቃቂያ
በሥራ ቦታ ሆነው ሲደክምዎ ወይም ሲሰለችዎ ከቦታዎ ተነስተው ሰውነቶን ያፍታታሉ አሊያም ቡና ወይ ሻይ ይጠጡ ይሆናል፡፡ በካሊፎርኒያ የሚገኙ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግን በሥራ የደከመን አዕምሮ ፈታ ለማድረግ የተጠቀሙት ውሾችን ነው፡፡ ለዚህም ሲሉ ሠራተኞቻቸው ውሾቻቸውን ቢሮ ይዘው እንዲመጡ ፈቅደዋል፡፡
ኤም ኤስ ኤን እንዳሰፈረው፣ በተለይ በካሊፎርኒያ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቢሯቸውን ለሠራተኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ለውሾችም ምቹ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ሠራተኞች ውሾቻቸውን ይዘው ወደ ቢሮ እንዲመጡ እያበረታቱም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ውሾች በቢሮ ውስጥ መኖራቸው፣ የእያንዳንዱን ሠራተኛ ምርታማነት ስለሚጨምር፣ ጭንቀትን ስለሚቀንስና መልካም የሥራ ድባብን ስለሚፈጥር የሚል ነው፡፡
********
የአምስት ዓመት ልጁን ከንፈር የሳመው ዴቪድ ቤካም
የአምስት ዓመት ልጁን ከንፈሯ ላይ ሲስም የተነሳውን ፎቶ በኢንስታግራም የለቀቀው የቀድሞ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም፣ ፎቶው የ1.8 ሚሊዮን ሰዎችን ይሁንታ ‹‹ላይክ›› ቢያገኝም፣ ከየአቅጣጫው ነቀፋ እየተሰነዘረበት ነው፡፡
አባት የሴት ልጁን ከንፈር መሳም ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቤካምን የታመመ፣ ግራ የገባው፣ የአምስት ዓመት ልጁ ወደ ፊት ወንድ እንዳትወድ የሚያደርግ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዴቪድ ቤካም ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በታንዛኒያ ቪክቶሪያ ሐይቅ አካባቢ የአምስት ዓመት ልጁን አቅፎ ከንፈሯን ሲስማት የሚያሳየውን ፎቶ በኢንስታግራም ከለቀቀ በኋላ የጎረፈበትን ወቀሳ፣ ባለቤቱ ያጣጣለች መሆኑንና የአሁኑ ፎቶ በኢንስታግራም የተለቀቀው ባለቤቱ ቪክቶሪያ ከዓመት በፊት ከለቀቀችውና ወቀሳ ካሰነዘረባት ፎቶ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ሃፍንግተንፖስት ዘግቧል፡፡