Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ኢትዮጵያ እንደ ቤቴ ይሰማኛል››

‹‹ኢትዮጵያ እንደ ቤቴ ይሰማኛል››

ቀን:

ድምፃዊ ዴሚያን ማርሌ

‹‹. . . ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠያቂው ወገን ለመንግሥት ማኅበር የተበደረውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ. . .›› ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በመቃወም በጄኔቭ የመንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ካደረጉት ንግግር የተቀነጨበ ነው፡፡

ዓድዋ ላይ የተሸነፈው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ከ40 ዓመታት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በዓለም የተከለከለውን የመርዝ ጋር ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ሠራዊት ያደረሰውን እልቂት ለዓለም አቤት ያሉበት ንግግር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የመላው ጭቁን ሕዝቦችን ፍትሕ ማጣት የተቃወሙበት ንግግርን ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በዓለም ቅርስነት ያሰፈረው ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በተዘዋዋሪ ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርሶች አንዱም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ንግግሩ ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ተምሳሌት የሚወስዱ ጥቁር ሕዝቦችን እሮሮ ያስተጋባ ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉና ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንዲታገሉ ያነሳሳ ነበር፡፡ የነፃነት ትግሉ ከተጧጧፈባቸው መንገዶች አንዱ በምድረ ጃማይካ የተወለደው ሬጌ ሙዚቃ ነበር፡፡ በመላው ዓለም ከነጮች የጭቆና ቀንበር ለመውጣት የታገሉ ጥቁሮች ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ማማ ያያሉና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር በሬጌ ሙዚቃ ያስተጋባ ጀመር፡፡

የምንጊዜውም የሬጌ ኮከብ ቦብ ማርሌ ስለ ንግግሩ ካቀነቀኑ አንጋፋ ድምፃውያን አንዱ ሲሆን፣ የመጨረሻ ልጁ ዴሚያን ማርሌ (ጁኒየር ጎንግ) ንግግሩን ‹‹ኮንፍሮንቴሽን›› የተሰኘው ዘፈኑ መግቢያ አድርጎታል፡፡ ግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል የተካሄደው ‹‹ዋን ላቭ›› የተሰኘው ኮንሰርት፣ ኢትዮጵያውያኑ የሬጌ ድምፃውያን ዘለቀ ገሠሠና ጆኒ ራጋ እንዲሁም ሌሎችም ድምፃውያን ያቀነቀኑበት ነበር፡፡ ዴሚያን ከኢትዮጵያውያኑ ቀጥሎ እኩለ ሌሊት አካባቢ ወደ መድረክ የወጣው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር ታጅቦ ነበር፡፡

ግዮን ሆቴልን ከጥግ ጥግ የሞላው ታዳሚ የ‹‹ኮንፍሮንቴሽን›› ዘፈን መግቢያ የሆነውን ንግግር ሲያዳምጥ አካባቢውን በድጋፍ ጩኸት፣ ፉጨትና ጭብጨባ አናጋው፡፡ ዴሚያንም የከበረ ሰላምታ ሰጥቶ፣ ለኢትዮጵያ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እየገለጸ ማቀንቀኑን ቀጠለ፡፡ ኢፍትሐዊነትን በመቃወም እኩልነት፣ ፍቅርና ሰላምን የሚሰብኩ ሙዚቃዎቹን አድማጮች አብረውት ያዜሙ ነበር፡፡ ላይተር ለኩሰው፣ ስልካቸውን አብርተው ከፍ በማድረግ ግቢውን ያደመቁትም ይጠቀሳሉ፡፡ ብዙዎች ኮንሰርቱን በቪዲዮና ፎቶ ለማስቀረት ሲጣጣሩም ታይተዋል፡፡

ዴሚያን እንደ አገሩ የሚቆጥራትን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እንደሚወድ እየደጋገመ ሲናገር ሕዝቡም በምላሹ ፍቅሩን ገልጾለታል፡፡ ዴሚያን ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ‹‹ኢትዮጵያ ስመጣ እንደ ቤቴ ይሰማኛል፤›› በማለት ነበር ለአገሪቱ ያለውን ፍቅር የገለጸው፡፡ ወደ ሁለት ሰዓት ገደማ ከመጀመሪያ የስቱዲዮ አልበሙ ‹‹ሚስተር ማርሌ›› ጀምሮ ካሉት አልበሞቹ ተወዳጅ የሆኑትን ዘፈኖች በተከታታይ አቀንቅኗል፡፡ ሬጌ፣ ዳንሶልና ሂፕ ሃፕ የተዋሃዱባቸው ዘፈኖቹ በመላው ዓለም ተወዳጅነትን ያተረፉ ሲሆን፣ የግራሚ ተሸላሚም አድርገውታል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያጣቅሱ እንደ ‹‹ሴት አፕ ሾፕ›› እና ‹‹ሮድ ቱ ዛየን›› የተሰኙ ዘፈኖቹን በኢትዮጵያ ምድር ማንቀንቀን ተምሳሌታዊ ነውና ታዳሚዎቹ ሙዚቃዎቹን በሐሴት ሲያጣጥሙ ተስተውሏል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለኔ ትልቅ ቦታ አላት፡፡ እዚህ መጥቼ በመዝፈኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ይደገማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ሲልም ይናገራል፡፡

‹‹ላቭ ኤንድ ኢኒቲ››፣ ‹‹ስትሮንግ ዊል ኮንቲንዩ›› እና ሌሎችም አንድነትን እየሰበኩ የነፃነት ትግልን የሚያበረታቱ ዘፈኖችም ከታዳሚዎች ቀና ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ከናስ ጋር በጥምረት የሠራውና በአፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ‹‹ዲስታንት ሪሌቲቨስ›› አልበም ውስጥ የተካተቱት ‹‹ላንድ ኦፍ ፕሮሚስ›› እና ‹‹ፔሸንስ››ን የመሰሉ ሙዚቃዎቹ፣ የመላው የዓለም ሕዝቦች መነሻ የሆነችውን አፍሪካ ያወድሳሉ፡፡ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ያጠይቃሉ፡፡

‹‹ስለ አፍሪካ የሚያወሱ በርካታ ሙዚቃዎች ሠርቻለሁ፡፡ አፍሪካ ውስጥ መጥቼ ሙዚቃዎቹን አለማቅረቤ ያስቆጫል፡፡ አሁን ግን እዚህ ተገኝቼ መዝፈኔ አርክቶኛል፤›› በማለት ስሜቱን ይገልጻል፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሳቢያ ታሪካቸው እንዳልነበር ቢሆንም፣ ገናና ማንነታቸውን እንዲያንፀባርቁም ይጠይቃል፡፡ መልዕክቱን የተጋሩት ታዳሚዎች ሰንደቅ ዓላማ በማወዛወዝ ያጅቡት ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የጃማይካ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁም የይሁዳ አንበሳ ምልክትም ጎልተው ታይተዋል፡፡

ማኅበረሰባዊ መልዕክት ካዘሉ ሙዚቃዎች ባሻገር እንደ ‹‹አፌርስ ኦፍ ዘ ኸርት›› እና ‹‹ሄይ ገርል›› ያሉት የፍቅር ዘፈኖቹም የታዳሚውን ቀልብ ገዝተዋል፡፡ ዴሚያን እንደሚናገረው፣ በእንግሊዝ ለንደን፣ በጃማይካ ኪንግስተንና ሌሎችም አገሮች እንደሚያደርገው በኢትዮጵያም ሙዚቃዎቹን በተደጋጋሚ ማቅረብ ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኮንሰርቱ አዘውትሬ እየመጣሁ አገሪቱን የምጎበኝበትና ሙዚቃም በተደጋጋሚ የማቀርብበት ጅማሮ እንደሚሆን አምናለሁ፤›› ይላል፡፡

ዴሚያን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በደቡብ አፍሪካ (ጆሐንስበርግና ደርባን)፣ በኬንያ (ናይሮቢ)፣ በሪዩንየን አይስላንድ (ፒየሪ)፣ በሞሪሽየስ (ፖርት ሉዊስ) የነበረውን ሙዚቃዊ ጉዞ ሲያጠናቅቅ ነበር፡፡ የአህጉረ አፍሪካ ጉዞው መደምደሚያ የነበረችው አዲስ አበባ፣ ድምፃዊውን ለመቀበል ዝግጅት የጀመረችው ከሳምንታት በፊት ነበር፡፡

በየጎዳናው ፖስተሩ ተለጥፎ፣ በየመገናኛ ብዙኃኑም የተዋወቀ ሲሆን፣ መግቢያ ትኬቱ መደበኛ በ400 ብርና ቪአይፒ በ600 ብር ተሸጧል፡፡ የኮንሰርቱ ዕለት ታዳሚዎች ግዮን ሆቴል መድረስ የጀመሩት ከምሽቱ 12 ሰዓት አንስቶ ነበር፡፡ ወደ ሆቴሉ መግባት ስላልተጀመረ ታዳሚዎች ለሰዓታት ተሠልፈው ነበር፡፡ ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ በሁለት አቅጣጫ በሁለት ዙር የተዘጋው ሠልፍ በአንድ ወገን ሀዲያ ሱፐር ማርኬትን በሌላ ወገን ባርኮት ሬስቶራንትን አልፎ ነበር፡፡ መግቢያ በሩ በጊዜ ስላልተከፈተ የሠልፈኞች ቁጥር ጨምሮ ግርግር እስከ መፈጠር ደርሷል፡፡

አስቀድመው ትኬት የገዙና በዕለቱ ለመግዛት ወረፋ ይጠብቁ የነበሩ ሰዎች በአንድ መስመር ከመሠለፋቸው ባሻገር የሕዝቡን ግፊያ መቆጣጠር ያልቻሉ የፀጥታ አስከባሪዎች ለግብግብ ተጋብዘዋል፡፡ በግርግሩ መካከል የወደቁ፣ የተመቱና ለሰዓታት ቢሠለፉም ለመግባት ተቸግረው የተመለሱም ነበሩ፡፡ ግዮን ሆቴል ውስጥ የነበረው ድባብ ከውጪው አንፃር የተረጋጋ ቢሆንም፣  ታዳሚዎች ሌላ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ ‹‹ጓደኛዬን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ስልክ ተሰርቀዋል፤›› የምትለው ሜላት መሳይ፣ ፀጥታ አስከባሪዎች ስርቆቱን ለመከላከል አንዳች ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሰዎችን ያንገላቱ እንደነበር ትገልጻለች፡፡

በማኅበረሰብ ሚዲያዎች በዋነኛነት በፌስቡክ ያለፉት ቀናት መነጋገሪያ የሆነው ይኸው የስርቆት ጉዳይ ነበር፡፡ ወደ ኮንሰርቱ መግባት ያልቻሉና በፀጥታ ኃይሎች እንግልት ደርሶብናል ያሉም ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ሜላት እንደምትለው፣ ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አዘጋጆቹ አስቀድመው መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ‹‹ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው ኮንሰርቱ በጣም አስደስቶኛል፤›› ትላለች፡፡

የዴሚያን አድናቂዋ ሜላት፣ ‹‹ትርዒቱ አስገራሚ ነበር፡፡ ያለማቋረጥ በአስገራሚ ብቃትና ጉልበት ዘፈኖቹን ከማሰማቱ በላይ ከታዳሚው ጋር የፈጠረው ትስስር ያስደስታል፤›› ትላለች፡፡ ከአንድ ዘፈን ወደ ሌላው የሚሸጋገርበት መንገድ፣ ከመድረክ መብራቱና የሙዚቃው ጥራት ጋር ተደማምሮ የማይረሳ ጊዜ ማሳለፏን ትገልጻለች፡፡ በእርግጥ የዴሚያን ብቃት ከኮንሰርቱ ታዳሚዎች በተጨማሪ በሙዚቀኞች፣ በዲጄዎችና ሌሎችም የዘርፉ ተዋንያኖችም እየተደነቀ ነው፡፡ ሙያዊ ሥርዓቱን ጠብቆ፣ ታዳሚውን በማክበር ሥራውን ማቅረቡም አስመስግኖታል፡፡

ወደ ኮንሰርቱ መደምደሚያ አካባቢ ታዳሚዎች ትርዒቱ እንዳያልቅ አለመፈለጋቸው ታይቷል፡፡ ዴሚያን ከራሱ ዘፈኖች በተጨማሪ የአባቱን ሥራዎችም አቅርቧል፡፡ ‹‹ቦብ ማርሌን ትወዱታላችሁ?›› ብሎ ሲጠይቅ ታዳሚው ባለ በሌለ ኃይሉ በመጮህ ፍቅሩን ገልጿል፡፡ ‹‹ኖ ሞር ትራብል››፣ ‹‹ጌት አፕ ስታንድ አፕ››፣ ‹‹ኩድ ዩ ቢ ላቭ››፣ ‹‹አፍሪካ ዩናይት›› እና ሌሎችም ዘፈኖችን ሲያስደምጥ ብዙኃኑ የዘፈኖቹን ግጥም አብረውት ይዘፍኑ ነበር፡፡ የትርዒቱ መዝጊያ ያደረገው በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮችም ተወዳጅ የሆነውን ‹‹ዌልካም ቱ ጃምሮክ›› ነበር፡፡

የጃማይካን ማኅበራዊ ውጣ ውረዶች በማንሳት የፖለቲካ ሥርዓቱን የተቸበት ዘፈን እ.ኤ.አ. በ2005 ያወጣው አልበም መጠሪያም ሲሆን፣ በቤስት ሬጌ አልበምና ቤስት ኧርባን (ኦልተርኔቲቭ) ፐርፎርማንስ ዘርፍ በአንድ ምሽት ሁለት ግራሚ ተሸልሟል፡፡ ሽልማቱ በአንዴ ሁለት ግራሚ የወሰደ ብቸኛው ጃማይካዊ ድምፃዊ ያደርገዋል፡፡ ‹‹ዌልካም ቱ ጃምሮክ››ን ተጫውቶ ታዳሚውን የተሰናበተው እንዳጀማመሩ ኢትዮጵያን በማሞገሥ ነበር፡፡ ‹‹ዳግም እስክንገናኝ እርስ በራሳችሁ ተደጋገፉ፡፡ የሰላምን መልዕክት አሰራጩ፤›› ብሎ አገባዷል፡፡

ዴሚያን እንደሚለው፣ ከአሥር ዓመት በፊት ከወንድሞቹ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ያቀረበው ኮንሰርት በርካቶች የታደሙት ትልቅ ኮንሰርት ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ብቻውን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሲወስን ምን እንደሚጠብቀው መገመት እንዳልቻለ ይናገራል፡፡ ‹‹ስመጣ ምን እንደሚጠብቀኝ አላወቅኩም ነበር፡፡ የተሰጠኝን ፍቅርም ተቀብያለሁ፤›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያን በሙዚቃዎቹ ከማወደስ ባሻገር መንፈሳዊ ትስስርም እንዳለው የሚገልጸው ድምፃዊው፣ ‹‹ሙዚቃ መግባቢያ ነው፤›› ይላል፡፡ በበርካታ አገሮች ሲዘዋወር የሚዘፍንበትን ቋንቋ ሳያውቁ ግጥሙን አብረው የሚሉ ተመልካቾች ገጥመውታል፡፡ ሙዚቃ የስሜት ግንኙነት መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ‹‹በሙዚቃ ስሜት፣ ሐሳብ፣ ፍቅርና መንፈሳዊነትን እናስተላልፋለን፤›› ሲልም ይገልጻል፡፡

ሌላው የኮንሰርቱ ታዳሚ ልዑል ሥዩም፣ ‹‹መድረክ ላይ ለሰውና ለአገሪቱ ያሳየው እውነተኛ ፍቅር ማርኮኛል፤›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡ እምብዛም ኮንሰርቶች በማይዘወተሩበት አገር ብዙ ሺዎችን በአንድ ምሽት መመልከትም አስደስቶታል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትርዒት አቅርቧል፤›› በማለት ዴሚያንን ይገልጸዋል፡፡

ከዴሚያን በተጨማሪ የሚያደንቀው ዘለቀ ‹‹ሀገሬ››ን ሲጫወት የደስታ ሲቃ ተናንቆት እንደነበር ይናገራል፡፡ ለዓመታት የሚወዳቸውን ‹‹ዶንት ሌት ሚ ዳውን›› እና ‹‹አልማዜ›› ዘለቀ ሲዘፍንም ተመሳሳይ ስሜት ነበረው፡፡ ሔኖክ መሐሪ እና መሐሪ ብራዘርስ እንዲሁም ጆኒ ራጋም ‹‹ምሽቴን አድምቀውታል፤›› ይላል፡፡

ሆኖም ኮንሰርቱ ላይ የተፈጠሩ ያልተገቡ ግርግሮች በቀጣይ ኮንሰርት የሚሄዱ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የሚሠጋው ልዑል፣ አዘጋጆቹ መርሐ ግብሩን ሲያሰናዱ በርካታ ነገሮችን ከግምት ማስገባት እንዳለባቸው ያምናል፡፡

ሙዚቃ መልዕክት አዘል ሆኖ ለለውጥ ሲያነሳሳ ትርጉም የሚሰጠው ልዑል፣ ዴሚያን በድፍረት የማይወሩ እውነታዎችን በማስደመጡ ያደንቀዋል፡፡ በእርግጥም ዴሚያን ሙዚቃ በድህነት ሳቢያ የሚመገቡት ያጡ ልጆቻቸውን ማስተማር የተነሳናቸውና በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ሰዎች ድምፅ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ ‹‹ሙዚቃ የጋራ ስሜታችን መገለጫ ነው፤›› ይላል፡፡ ሙዚቃ የሚሰጠው ኃይል በዓይን ባይታይም ልብን የሚሞላ በመሆኑ ለቀና ነገር መዋል እንዳለበት ያክላል፡፡

‹‹በሙዚቃዬ የማስተላልፈው መልዕክት የአስተዳደጌ ውጤት ነው፤›› የሚለው ድምፃዊው፣ በሥራዎቹ እምነቱ፣ ከቤተሰቦቹ የወረሰው ማንነት እንደሚያንፀባርቅ ይገልጻል፡፡ የማንንቱ መነሻ የሆኑ እውነታዎችና የሕይወት ተሞክሮው የሙዚቃው መሠረትም ናቸው፡፡ በፖለቲካው ረገድ መሪዎች ሕዝባቸውን እንዳይጨቁኑ፣ ዓለም በጦርነት እንዳትሸበርና የሰዎች ሰብአዊ መብት እንዲከበር የሚያሳስቡ ሙዚቃዎች ላይ ያተኩራል፡፡ አፍሪካ ውስጥና ከአፍሪካ ውጪ ያሉ ጥቁሮችን ከሚያስተሳስሩ ሙዚቃዎች ባሻገር በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ፕሮጀክቶች በቀጥታ ይሳተፋል፡፡

ዴሚያን ከትርዒቱ በኋላ ከመድረክ ጀርባ ባለ ድንኳን ከአድናቂዎቹ ጋር ፎቶ ተነስቷል፡፡ ወደ ድንኳኑ ለመግባት የነበረውን ግፊያ ለማስቆም የፀጥታ ኃይሎች ሰዎችን ሲገፉ የተመለከተው ዴሚያን፣ የሰዎች ክብር በመነካቱ ተበሳጭቶ በሥነ ሥርዓት እንዲስተናገዱ ሲያሳስብ ነበር፡፡ ድምፃዊው በኢትዮጵያ ቆይታው የሙዚቃ ቪዲዮ የቀረፀ ሲሆን፣ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ያለውን የአባቱን ሐውልትም ጎብኝቷል፡፡ ወደ ላሊበላ ሊያደርግ የነበረው ጉዞ ቆይታው አጭር ስለነበር አልተሳካም፡፡

የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱን በሞት የተነጠቀው ዴሚያን፣ ከ13 ዓመቱ ጀምሮ በሙዚቃው ሕይወት ይገኛል፡፡ ከዕውቅ ሬጌ ድምፃውያን ልጆች ጋር በጥምረት የመሠረተው ‹‹ዘ ሼፐርድስ›› ባንድ ሲፈርስ በግሉ መሥራት ጀመረ፡፡ ‹‹ሀፍ ዌይ ትሪ›› የተሰኘው አልበሙ የግሉን የማንነት ጥያቄ በመመርኮዝ በኢኮኖሚ ከተለያዩ ቤተሰብ  መገኘትን ይዳስሳል፡፡ ‹‹ለሙዚቃ የሚያነሳሳኝ ሕይወት ነው፤›› የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡

ሙዚቀኛው በበጎ ፈቃድ ሥራዎች የሚሳተፍ ሲሆን፣ አፍሪካ ውስጥ ትምህርት ቤቶች የማቋቋም እንቅስቃሴው ይጠቀሳል፡፡ ፍቅርና እኩልነት እንዲሰፍን በሙዚቃ የሚታገለው ድምፃዊው፣ ከሕይወት ተሞክሮው በተጨማሪ ከሰዎች ጋር ሲያወራ የሚገኘውን፣ በመጻሕፍት የሚያነበውንና በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጨውንም መረጃ በሙዚቃዎቹ እንደሚዳሰስ ይናገራል፡፡

የአባቱን ፈለግ የተከተለው ድምፃዊው፣ በዋነኛነት ከስቴፈን ማርሌ ጋርና ከሌሎቹ ወንድሞቹ ዚጊ ማርሌ፣ ጁልያን ማርሌና ኪማኒ ማርሌ ጋር በጥምረት ይሠራል፡፡ ቦብ ከልጆቹ ባለፈ እንደ ጆመርሳ ማርሌ ባሉ የልጅ ልጆቹም ጭምር ትውልድ መሻገሩን ለዓለም አስመስክሯል፡፡

ዴሚያን ባለፉት ዓመታት ከዕውቆቹ ስቲል ፐልስ፣ ሚክ ጃገር (ዘ ሮሊንግ ስቶንስ)፣ ኬናን፣ ኢቭ፣ ቦቢ ብራውን፣ ብሩኖ ማርስና በርካታ ሙዚቀኞች ጋር ተጣምሯል፡፡ ‹‹አስ ዊ ኢንተር›› በተሰኘው ዘፈኑ የኢትዮ ጃዝ አባቱ ሙላቱ አስታጥቄ ቅንብር ተካቷል፡፡ ቀጣዩ አልበሙ ‹‹ስቶኒ ሂል›› በቀጣዩ ወር እንደሚለቀቅም ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...