Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዳይሬክተሮች ሹመት ውድቅ ተደረገ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዳይሬክተሮች ሹመት ውድቅ ተደረገ

ቀን:

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማኔጅመንት አማካይነት አዳዲስ ዳይሬክተሮችን ለማሾም ቀርቦ የነበረው ጥያቄ፣ በባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ውድቅ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ 26 የሚጠጉ በዳይሬክተሮች የሚመሩ ኃላፊነቶች እንዳሉት የሚታወቀው ባንኩ፣ እነዚህ ቦታዎችን በአዳዲስ ሰዎች ለመሙላት ለቦርዱ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ቦርዱ ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ለእነዚህ ተመሳሳይ የሥልጣን እርከኖች ላይ ለውጥ ካደረገ አንድ ዓመት ቢሞላውም፣ ለውጡ እንዲደረግ መፈለጉ ግን ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ሪፖርተር ያናገራቸው የተወሰኑ የባንኩ ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሚመራው ቦርድ በተለይ ባንኩ ወሳኝ ቦታዎች የሚላቸው የብድር፣ የፕሮጀክት ማፅደቅና መከታተል ኃላፊነቶች ላይ የሚሠሩ ዳይሬክተሮችን ለመቀየር የቀረበውን ጥያቄ ተቃውሟል፡፡

ቦርዱ ጥያቄውን የተቃወመው ጥያቄውን ያቀረበው የባንኩ ማኔጅመንት ለመቀየር የፈለገበትን ምክንያት በቂ ሆኖ ስላልተገኘና ያንንም ተከራክሮ ማሳመን ስላልቻለ እንደሆነ የተለያዩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሮችን ለመለወጥ የቀረበው ጥያቄ በባንኩ አመራር ላይ ለውጥ ከተደረገ ሦስት ሳምንት በኋላ የመጣ ነው፡፡

አቶ ጌታሁን ናና የቀድሞውን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረን ከተኩ በኋላ የመጣ ሲሆን፣ አቶ ጌታሁንም ፕሬዚዳንትነቱን ከያዙ በኋላ በባንኩ ውስጥ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ለብዙ ዓመታት የሠሩ አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ማለትም የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ታደሰ ሃትያ፣ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አብርሃ፣ የፋይናንስና ባንክ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አልማዝ ጥላሁን፣ እንዲሁም የፕሮጀክት ፋይናንስ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ደረጀ አውግቸውን ከቦታው አንስተው በአዲስ ሰዎች ተክተዋል፡፡

ከድሮዎቹ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ውስጥ የሊዝ ፋይናንስና ቅርንጫፍ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ ብቻ በቦታው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ አሁን የቀረበው የዳይሬክተሮች ለውጥም የዚሁ ለውጥ ቀጣይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌሎች ለውጡ ላይ አስተያየት የሰጡ ሠራተኞች፣ የላይኛው አመራር ሊሾም ያቀረባቸው ዳይሬክተሮች በሥራ ብቃታቸው ተመዝነው የቀረቡ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹እንደኔ አሁን ያለው ሠራተኛ ብቃት ያለውና ሥራውን በብቃት ማከናወን የሚችል ነው፤›› ሲሉ ለባንኩ ሥራ ቅርበት ያላቸው አንድ ባለሀብት ተናግረዋል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተመሠረተው ልማት ባንክ በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ብድር በማቅረብ ይታወቃል፡፡ የአገሪቱን ፖሊሲ መሠረት አድርጎ ብድሮችን ያከፋፍላል፡፡

በዚሁ ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ 36 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል፡፡ ከአሥር ዓመት በላይ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ኢሳያስ ባህረ ያሰናበተው ልማት ባንክ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ እያለፈ ነው፡፡

በተለይም በጋምቤላ ክልል ከሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ቀርቦ በነበረው ሪፖርት ሳቢያ፣ ባንኩ ከባለሀብቶች ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡

በባንኩ በኩል ቀርቦ ስለነበረው ዳይሬክተሮችን የመቀየርና የመሾም ጥያቄ ሪፖርተር አቶ ጌታሁንን ለማግኘት የሞከረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

አቶ ጌታሁን በስልክ አጭር መልዕክት ለተጠየቁት ጥያቄዎች መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ አቶ ሽፈራውን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ስልካቸው ላይ ቢደውልላቸው፣ ከአገር ውጭ እንደሆኑ በመግለጽ የስልክ ንግግራቸው ተቋርጧል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...