Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊገዳይ ጉድጓዶች

ገዳይ ጉድጓዶች

ቀን:

 ዘነበች ወልዴ 28 ዓመቷ ነው፡፡ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ባለቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከአራት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ ባለቤቷ የዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እሷ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ነበረች፡፡ በወቅቱ ከተወለደች ሁለት ወር የሆናት ሁለተኛ ልጃቸውን እየተንከባከበች ድንገተኛው የባለቤቷ ሕልፈት በሐዘን ቅስሟን ቢሰብረውም ፈተናዋን መውሰድ ነበረባት፡፡

ትማር የነበረው በሰበታ ዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ሲሆን፣ መጀመሪያ  የወሰደችው ፈተና እንግሊዝኛ ነበር፡፡ ፈተናውን ጨርሳ ወደ ቤቷ በመመለስ ላይ ሳለች ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሕይወቷን ክፉኛ ያናወጠ አደጋ ደረሰባት፡፡ ወደ ቤቷ የሚወስደውን አስፋልት መንገድ ተሻግራ እግረኛ መንገድ ላይ ለመውጣት እግሯን ስታነሳ የተቀበላት መሬት ሳይሆን ጥልቅ ጉድጓድ ነበር፡፡

‹‹እግረኛ መንገድ መሀል የነበረው ጉድጓድ ውስጥ ስገባ ድንጋይ ጭንቅላቴን መታኝ፡፡ ባለቤቴን ማጣቴ፣ አራስ ልጄን ትቼ አደጋ ላይ መውደቄና ከብሔራዊ ፈተና መደናቀፌ ሕይወቴን ገለባበጠው፡፡ ካገገምኩ በኋላ ሥራ ማግኘት ስላልቻልኩ ልጆቼን ለማሳደግ ተቸገርኩ፡፡ ጎዳና ከመውጣት ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ አበባ መጥቼ ቱጌዘር የዕርዳታ ድርጅት ውስጥ ገባሁ፤›› ትላለች ዘነበች፡፡ ልጆቿን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷ ጭላንጭል ተስፋ ቢሰጣም፣ አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መዘዋወር በተለይ ለዓይነ ሥውራን ከባድ መሆኑን ትገልጻለች፡፡

‹‹ጠዋት የማውቀው መንገድ ማታ ስመለስበት ተቆፍሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ውኃ ለመቅዳት ወጥታ ተቆፍሮ ክፍት በተተወ ጉድጓድ ገብታ የተጎዳች ሴትም አውቃለሁ፤›› ትላለች፡፡ በመንግሥትና በግል ተቋሞች ለተለያዩ ሥራዎች ጉድጓዶች ከተቆፈሩ በኋላ ሳይከደኑ ይቀራሉ፡፡ ለግንባታ፣ ለግንባታ ግብዓት ለማውጣት፣ መንገድ ላይ ቱቦና ኬብል ለመዘርጋት እንዲሁም ቆሻሻ ለመጥረግ የሚቆፈሩና የሚከፈቱ ጉድጓዶች ፈጥነው ሲደፈኑ ወይም የአደጋ ልዩ ምልክት ሲደረግላቸው እምብዛም አይስተዋልም፡፡ ይህም ለዓይነ ሥውራንም ሆነ ለዓይናማዎች አካል ጉዳተኛ ለሆኑም ሆነ ላልሆኑት መሰናክል ከሆነ ሰንብቷል፡፡

ግንባታ ሲካሄድ መንገድ ለመቆፈር የሚወስደው ፍጥነት፣ ሥራው ካለቀ በኋላ በቁፋሮው የተፈጠሩ ጉድጓዶችን ለመድፈን የሚደረገው ጥረትም የጎላ አይደለም፡፡ በተለያየ ምክንያት የተቆፈሩ ጉድጓዶች ሳይደፈኑ ሳምንታትና ወራትም ብሎም ዓመታት ይነጉዳሉ፡፡ እነዚህ ጉድጓዶች ለብዙዎች አካል ጉዳት መንስዔም ሆነዋል፡፡ ‹‹ብዙ ነገር መሥራት የምንችል ሰዎች ችላ ተብለው ክፍት በተተው ጉድጓዶች ሳቢያ ሕይወታችን ይሰናከላል፤›› ስትል ዘነበችም ሁኔታውን ትገልጻለች፡፡

አደጋ በደረሰባት ወቅት ጉድጓዱን ክፍት የተወውን አካል ለመፋረድ ብትሞክርም አልተሳካም፡፡ ከአቅሟ በላይ የነበረውን የሕክምና ወጪ የሸፈነችው ከሁለት ልጆቿ ጉሮሮ ነጥቃ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ወድቀው ከተጎዱ በኋላ ገንዘብ ማግኘቱ ትርጉም ባይኖረውም፣ ቢያንስ የሕክምና ወጪ ይሸፍናል፡፡ አቤት ብልም የሰማኝ አልነበረም፤›› ትላለች፡፡ ዓይነ ሥውራን ብቻ ሳይሆኑ በዊልቸር ወይም በክራንች የሚሄዱ አካል ጉዳተኞችም የችግሩ ሰለባ ናቸው፡፡

ዘነበች በጉዳቷ ሳቢያ ሙሉ በሙሉ ቤት ባትውልም ጉዳቷ ከፍቶ ልጆቿን ለማሳደግ የምትቸገርበት አጋጣሚ ግን ሰፊ ነበር፡፡ ባለመደፈናቸው የአደጋ መንስዔ የሆኑ ጉድጓዶች ጉዳይ በተደጋጋሚ ቢነሳም ችግሩ እምብዛም መፍትሔ አላገኘም፡፡  

የቀድሞው የከተሞችና ቤቶች ልማት ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት የግንባታ ዘርፉን ዋና ዋና ተዋንዮች ሰብስበው ክፍት የተተው ጉድጓዶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደፈኑና ካልተደፈኑም ከፍተኛ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረው ነበር፡፡ የጉድጓዶች መደፈን የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነና ከተሰጠው ጊዜ ገደብ ማለፍ ይቅር እንደማያስብል አስረግጠው ተናግረውም ነበር፡፡ ሆኖም ዛሬም በተለያዩ መኖሪያ ሠፈሮችና ኮንዶሚኒየሞች አካባቢ ክፍት በተተው ጉድጓዶች ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ የአዕምሮ ሕሙማንና አቅመ ደካሞችም እየተጎዱ ነው፡፡

ከውኃና ፍሳሽ፣ ከስልክና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ጋር ከተያያዙ ቁፋሮዎች በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ ግንባታ ሲካሄድም የሚከፈቱ ጉድጓዶች ቢያንስ በ48 ሰዓት ውስጥ መከደን አለባቸው፡፡ ጉድጓዶች ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆዩ ከሆነም ለእግረኞች ጉድጓድ ስለመኖሩ የሚገልጹ ምልክቶች መቀመጥ አለባቸው፡፡ ስንቶቹ ተቋሞች ይህን ሕግ ይከተላሉ? የሚለው ግን አጠያያቂ ነው፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለአገሪቷ ዕድገት ያለው ጠቀሜታ ባያጠያይቅም፣ ኅብረተሰቡን ዋጋ ማስከፈል የለበትም፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የመንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት በአንድ አካባቢ ቁፋሮ ያካሂዳሉ፡፡ በተቋማቱ መካከል መናበብ ስለሌለም አንድ መንገድ ሁለት ሦስቴና ከዛም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲፈርስና ሲሠራ ይስተዋላል፡፡ በእነዚህ መንገዶች በየጊዜው ቁፋሮ የመካሄዱን ያህል አስተካክሎ እንደነበረ መመለሱ ላይ ክፍተት አለ፡፡ በመሆኑም በእግረኛ መንገዶች ጉድጓዶች፣ ተቆፍረው ያልተስተካከሉ መረማመጃዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ሲሆን ግን በየጎዳናው የሚመላለሰው ሕዝብ ጉድጓዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት ዓይኑን ከመሬት ሳይነቅል በዝግታ ሊጓዝ ይችላልን? የሚለውም ጥያቄ ይሆናል፡፡

መጪው ክረምት እንደመሆኑ ያልተደፈኑ ጉድጓዶች በዝናብ እየሞሉ የአደጋ ተጋላጭነቱን ማስፋታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ጥፋት ይደርስ የነበረው በእሳት አደጋ ሳቢያ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ያልተደፈኑ ጉድጓዶችን ጨምሮ ከግንባታ ጋር የተያያዙ አደጋዎች ቁጥር እያናረ መጥቷል፡፡ ስሜ አይጠቀስ ብለው አስተያየታቸውን የሰጡን የ67 ዓመት አዛውንት አራት ኪሎ አካባቢ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የእግረኛ መንገድ ላይ የነበረ ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡

‹‹ጉድጓዱ መጠነኛ በመሆኑ እግሬን ወለም ብሎኝ ተርፌያለሁ፡፡ ነገር ግን ሌላ መንገድ ላይ ያየኋቸው ረዣዥምና ሹል ብረት ያላቸው ጉድጓዶች ውስጥ ወድቄ ቢሆን አልተርፍም ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ከአንድም ሁለት ሦስቴ ስለ ችግሩ አሳሳቢነት የመንግሥትና የግል ተቋሞች ሲናገሩ ቢሰማም መገናኛ ብዙኃንም ቢዘግቡም የመፍትሔ ሐሳቦች ሲተገበሩ እንዳላዩ ይገልጻሉ፡፡ ሰዎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው ለመመለሳቸው የሚያሠጉ ከሰው ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች በበዙበት ዓለም፣ ቀላል የሆነው ጉድጓዶችን መድፈን ለሰው ሕይወት መጥፊያ መሆኑን ‹‹ችግሩ እየታወቀና መፍትሔው ቀላል ሆኖ ሳለ ችላ መባሉ ግራ ያጋባል፤›› ሲሉ አዛውንቱ ይናገራሉ፡፡

የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን በያዝነው ዓመት በዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ 58 ሰዎች ሲሞቱ 91 ሰዎች መቁሰላቸውን (በቆሼ ናዳ የተጎዱትን ሳይጨምር) ያመለክታል፡፡ ከነዚህ መካከል 28 ሰዎች ተቆፍረው ክፍት በተተው ጉድጓዶች ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደሚናገሩት፣ ከ18 እስከ 41 ዓመት ድረስ ያሉ ግለሰቦች በተለያየ ምክንያት ጉድጓዶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል የመዋኘት ችሎታ ሳይኖራቸው ጉድጓድ ውስጥ ለመዋኘት የገቡ ሕፃናት ይገኙበታል፡፡ ያልተከደኑ ጉድጓዶችን ጨምሮ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ሌሎችም አደጋዎች ተጎጂዎች ቁጥር ክረምት ላይ ሊጨምሩ ይችላሉ የሚል ሥጋትም አለ፡፡

‹‹ክረምት ላይ የአደጋው መጠን ይጨምራል፡፡ አምና የተጎዱት 35 ሰዎች ሲሆኑ፣ ዘንድሮ ቁጥሩ ጨምሯል፤›› የሚሉት አቶ ንጋቱ፣ በግንባታ አካባቢዎች ጥንቃቄ ስለማይደረግ ሠራተኞችና መንገደኞችም አደጋ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ በክረምት ወራት ቁፋሮ ማካሄድና የተቆፈሩ ጉድጓዶች በፍጥነት አለመደፈናቸው ችግሩን ያባብሰዋል ይላሉ፡፡

የተቆፈሩ ጉድጓዶች በፍጥነት ስለማይደፈኑ በተለይም ከሥራ ሰዓት ውጪ ብዙዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ አብዛኞቹ የግንባታ አካባቢዎች በጉድጓድ ዙሪያ ምልክት አያኖሩም፡፡ አጥርም አያጥሩም፡፡ በ2007 ዓ.ም. በመንግሥት የመሠረተ ልማት አቅራቢዎች ማለትም ውኃና ፍሳሽ፣ ቴሌና መብራት ኃይል ባልደፈኑዋቸው ጉድጓዶች ምክንያት ሰባት ሰዎች ሞተዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ ሞቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ከመዘገባቸው ውጪ ሪፖርት ያልተደረጉ ሊኖሩም ይችላሉ፡፡ አብዛኞቹ ጉድጓዶች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በሚበረክትባቸው ዋና ዋና ጎዳናዎች መገኘታቸውም የጉዳቱን መጠን ያሰፋዋል፡፡

የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋሞች ስለ ችግሩ መረጃ ቢኖራቸውም፣ ሕግጋቱን የማይተገበሩባቸው ጊዜያት እንዳሉ አቶ ንጋቱ ያስረዳሉ፡፡ መሥሪያ ቤቱ ለባለድርሻ አካላት የአደጋ ተጋላጭነት ጥናት ቢልክም ከዓመት ዓመት አደጋ መጨመሩ ጥናቶቹ በሥራ ስለመዋላቸው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ያልተደፈኑ ጉድጓዶች መኖቸው ሲጠቆም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ ቢኖርም፣ ቸል ተብሎ የሚደርሰው አደጋ ይከፋል ይላሉ፡፡ ‹‹በአዋጅ ጉድጓድ የማስደፈን ሥልጣን ባይኖረንም ሙያዊ አስተያየት እንሰጣለን፡፡ ኃላፊነታችን ችግሩን ማሳየትና ኅብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ መረጃ መስጠት ነው፤›› ይላሉ ባለሙያው፡፡

ለመጪው ክረምት ከጉድጓዶች ጋር የተያያዙ የግንባታ አደጋዎችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መረጃ የመስጠት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የአደጋው መጠን ከመቀነስ ይልቅ መጨመሩ፣ ኅብረተሰቡ አሁንም በቂ ግንዛቤ እንደሌለው ያሳያል ይላሉ፡፡ አዲስ አበባ ግንባታ የተስፋፋባት ከተማ እንደመሆኗ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ አለማደጉ ቅድመ አደጋ ጥንቃቄ ትኩረት እንዲነፈገው ማድረጉንም ያክላሉ፡፡

ከተማዋ በርካታ ግንባታዎች እየተከናወኑባት የሚገኙ፣ ለወደፊትም የሚከናወኑባት እንደመሆኗ ገንቢዎቹ ተቋማት መውሰድ ካለባቸው ጥንቃቄ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ዘንድም ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ሰፊ ግንባታ ካላቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ይጠቀሳል፡፡ ባለሥልጣኑ የቀረፀው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና የፍሳሽ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ከተያዙት ዕቅዶች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ 100 ሺሕ ሜትር ኩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የፍሳሽ ማጣሪያ በመገንባት ኅብረተሰቡ ዘመናዊ ፍሳሽ መስመር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ያለመ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት ሰፊ ግንባታ እንደመጠየቁ በከተማዋ በርካታ ቁፋሮዎች አሉ፡፡

የፕሮጀክቱ ሳይት ማናጀር ኢንጂነር በረከተአብ ዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ ለፕሮጀክቱ ቁፋሮ ከተጀመረ ወደ ዓመት ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በቁፋሮው ወቅት ጉድጓዶች ቢያንስ በአንድ ቀን እንዲደፈኑ ይደረጋል፡፡

ከቁፋሮ በፊት አስፈላጊ ግብዓቶች መሟላታቸውን የሚያጣሩ ሲሆን፣ ጉድጓዱ በአንድ ቀን ሳይደፈን የሚቀረው ከግብዓት ጋር የተያያዘ ክፍተት ሲኖር ብቻ ነውም ይላሉ፡፡

በፕሮጅክቱ የደኅንነት ኮሚቴ አማካይነት የቁፋሮውን ጥልቀት የሚገልጹ የአደጋ ምልክቶች ይተከላሉ፡፡ በግንባታው አካባቢ በሠራተኞችና በኅብረተሰቡም ላይ አደጋ እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግም ኢንጂነሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቁፋሮውን እየተከታተለ ጥቅም ላይ የማይውለውን አፈር የሚጭንና ጉድጓዶቹን የሚደፍን መኪና አለ፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን አደጋ ባይገጥማቸውም፣ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች ጥንቃቄ እንደሚጎላቸው ይስማሙበታል፡፡ ‹‹በተለይም ሕፃናትና የአዕምሮ ሕሙማን ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ ቁፋሮ በሚካሄድበት አካባቢ ማስጠንቀቂያ ምልክት ማድረግ ሙያዊ ግዴታ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ይህን ማድረግ ወጪው ትንሽ ሲሆን፣ ቸል ማለት የሚያደርሰው አደጋ ከፍተኛ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ጉድጓዶችን በኮንክሪት መሙላትና ዙሪያቸውን ማጠር የግድ መሆኑንም ያክላሉ፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥዑመይ ወልደገብርኤል እንደሚናገሩት፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን መንገድ ለመሥራት ወይም ለማሻሻል ከሚያካሂዳቸው ቁፋሮዎች በተጨማሪ፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የግል ተቋራጮች የሚካሄዱ ግንባታዎች በከተማዋ ተስፋፍተዋል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የግንባታ ፈቃድ የሚሰጣቸው አካላት የማኅበረሰቡን ደኅንነት በጠበቀ መንገድ የመሥራት ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ በጥንቃቄ ጉድለት ለሚደርስ አደጋም ተጠያቂ ናቸው፡፡

‹‹በግንባታ ቦታ አንፀባራቂ ምልክት ማድረግና ጉድጓድ በ48 ሰዓታት መክደን በሕጉ ተቀምጧል፡፡ ከ48 ሰዓታት ከበለጠ የጥንቃቄ ምልክት መኖር አለበት፤›› ይላሉ፡፡ አደጋ በሚደርስበት ወቅት ግንባታውን እያካሄደ ያለው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር ቢኖርም፣ ምን ያህል ተጎጂዎች ተገቢውን ካሳ ያገኛሉ? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ ግንባታዎች ችግሩን የበለጠ እንዳወሳሰቡት አቶ ጥዑመይ ያስረዳሉ፡፡ ተቋሙ ከሰጠው ፈቃድ በላይ የእግረኛ መንገድ ወስደው ግንባታ የሚያካሂዱ፣ የሚሠሩ፣ የእግረኞችና ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በሚያስተጓጉል መልኩ አሸዋና ጠጠር የሚከምሩ እንዲሁም ጉድጓድ ቆፍረው ሳይደፍኑ የሚተው አካላት የሕግ ተጠያቂ ሆነው የተቀጡበት ጊዜ እንዳለም ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለሰው እንቅፋት መሆን የለበትም፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በግንባታ አካባቢ ሠራተኞች ግንባታውን የሚያካሂደውን ተቋም የሚገልጽ ልብስ መልበስ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ በግንባታ ምክንያት የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዳይገታ አማራጭ መንገድ መዘጋጀት እንዳለበትም ያክላሉ፡፡

የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የእሳት አደጋን ጨምሮ 410 አደጋዎች መድረሳቸውን ገልጿል፡፡ ከነዚህ 119ኙ ከግንባታ ጋር የተያያዙ አደጋዎች ናቸው፡፡ ግንባታዎቹን የሚያካሂዱ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ ቢወስዱ አደጋዎቹ እንደማይከሰቱ የምትናገረው አዳነች የኋላእሸት፣ ‹‹አዲስ አበባ የጉድጓዶች ከተማ ከሆነች ሰነባብታለች፤›› ትላለች፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች የሚያስቀምጧቸው የቅድመ ጥንቃቄ ዕርምጃዎች በጣት በሚቆጠሩ የግንባታ ቦታዎች ብቻ እንደሚተገበሩ ትናገራለች፡፡ በቅርቡ አምባሳደር አካባቢ የቦሌ ታክሲ ለመያዝ ከሰዎች ጋር ስትገፋፋ ተቆፍሮ የተተወ ጉድጓድ ውስጥ ከመግባት ለጥቂት ተርፋለች፡፡ ጉድጓዱ እግረኛ ሊያስተውለው በሚችለው ቦታ ካለመሆኑም በላይ ምንም ዓይነት አጥር በዙሪያው አልነበረም፡፡ ከዓመት በፊት 22 አካባቢ የተቆፈረ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ድንጋይና ፌሮ ነበረው፡፡ በቆሻሻ ተሞልቶም አካባቢው ይሸት ነበር፡፡ ሰዎች ጉድጓዱ ውስጥ ሲገቡ ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጉድጓዱን ጅባ አልብሰው በድንጋይ ለመክደን ተገደው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

አዳነች ተቆፍረው የተተው ጉድጓዶች ብቻ ሳይሆኑ በማያስተማምን መንገድ የተደፈኑ ጉድጓዶችም አስጊ ናቸው ትላለች፡፡ ‹‹የሚመለከታቸው ተቋማት ተገቢውን ጥንቃቄ እየወሰዱ ከሆነ የእግረኛ መንገዶችና አቋራጮች ለዓመታት ባልተደፈኑ ጉድጓዶች እንዴት ተሞሉ?›› ስትል ትጠይቃለች፡፡ ምን ያህል ሰው እስኪሞት ወይም ምን ያህል ሰው አካል ጉዳተኛ እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? ስትልም የሚነገረውና በሚተገበረው እንደማይጣጣም ትናገራለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...