Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹በእግር ኳሱ በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ እየተመለከትን ነው››

‹‹በእግር ኳሱ በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ እየተመለከትን ነው››

ቀን:

አቶ ተፈራ ደምበል፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያየ ደረጃ ከሚያወዳድራቸው ዓመታዊ መርሐ ግብሮች መካከል ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ (ሱፐር ሊግ) እና ብሔራዊ ሊግ ይጠቀሳሉ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እግር ኳሱን እስከታች ወረዳ ድረስ እንዲደርስና በኅብረተሰቡ ዘንድም ቅቡልነት እንዲኖረው እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን ስፖርቱ ከሚያስፈልገው መሠረተ ልማት እስከ ተሟላ የሰው ኃይልና አደረጃጀት ጭምር ዝቅተኛ መሆኑ ይወሳል፡፡ እግር ኳሱ ከሚሰጠው ልዩ ልዩ ፋይዳው ይልቅ የብጥብጥና ሁከት መንስዔ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ከኅልፈተ ሕይወት እስከ አካል ጉዳት ከማስከተሉም ባሻገር በንብረት ላይ ውድመትና ኪሳራ እያስከተለ መሆኑ ይታያል፡፡ በየአካባቢው በየደረጃው የሚገኙ ውድድሮች በሰላም ተጀምረው በሰላም ለመጠናቀቃቸው ዋስትና እየጠፋም ነው፡፡ እግር ኳስ ከመዝናኛነቱ ይልቅ ዜጎች በማንነታቸው እንዲያፍሩ ምክንያት እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለው ደንብና መመርያ መሠረት የዲሲፕሊን ዕርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ ይሁን እንጂ ከስፖርታዊ ባሕሪው ይልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም እየተሰጠው የእንኪያ ሰላንቲያ መድረክ እየሆነም ይገኛል፡፡ የተወሰኑ ቡድኖች፣ የቡድን አመራሮችና ደጋፊዎች፣ ተጨዋቾችም ጭምር ሽንፈትን በፀጋ ተቀብለው ለሚቀጥለው ሠርተው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ፍላጎትና ተነሳሽነት እንደማያሳዩ ጠቋሚ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ተገቢነት የሌላቸው በኅብረተሰቡ ይልቁንም ለሽንፈታቸው በሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል አላስፈላጊ ቁርሾ እንዲፈጠር መንስኤ እየሆኑ ነው፡፡ ስፖርቱ ቀስ በቀስ ከእግር ኳስ ባሕሪው መውጣት ጀምሯል፡፡ ውድድሮች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁና ለተጨማሪም ወጪ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደየጥፋት መጠኑ የዲሲፕሊን ዕርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ እየወሰደም ይገኛል፡፡ ይሁንና ውሳኔዎች እንዴትና በማን አማካይነት እንደሆነ በውል ባይታወቅም ውሳኔው እንዲሻር መድረጉ ይነገራል፡፡ በዚህም የስፖርቱ ኅብረተሰብ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች ተወሰዱ የሚለውን የፌዴሬሽኑን አባባል መጠራጠር ጀምሯል፡፡ እንዲያውም ተቋሙ ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› መባል ጀምሯል፡፡ ረብሻዎች፣ ብጥብጦችና ሁከቶች ደግሞ በዚያው መጠን እየቀጠሉ ይገኛል፡፡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ኮሚቴ ከእግር ኳሱ ጋር በተያያዙ ሁከቶች ምክንያት ከሰሞኑ የተለያዩ የዲሲፕሊን ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ተጨዋቾችና አሠልጣኝ እንዲሁም  የተለያዩ ክለቦችንም ቀጥቷል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደምበልን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደመሆንዎ ለዚያ የሚያበቃና ከስፖርቱ ጋር ሊያገናኝዎት የሚችል ነገር ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- በ1970ዎቹ መጀመሪያ በራሪ ኮከብ ተብሎ ለሚታወቀው ቡድን ተጫውቻለሁ፡፡ በራሪ ኮከብ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ህልውናው እንዳበቃ በተለይም በጊዜው 50ዎቹ ተብለው ቡድኖች ሲቋቋሙ ከተጨዋችነት ወደ እግር ኳስ ዳኝነት መጥቼ ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1995 ዓ.ም. ድረስ በፌዴራል ዳኝነት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያም ዳኝነቱን በትምህርት ምክንያት አቋርጨ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ፡፡ ከዚያም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባልነት በተለያየ ደረጃ በሥራ ቆይቻለሁ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላና አሁን እስካለሁበት ደግሞ በሰብሳቢነት እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሕግ አማካሪና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የግሌን ቢሮ አቋቁሜ በጥብቅና ሙያ ላይ እገኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፖርቱ አካባቢ የሚንፀባረቁ አላስፈላጊ ውዝግቦች  ከምን ጊዜውም በላይ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ ደግሞ በቀጥታ በእርስዎ የሚመራውን ኮሚቴ የሚመለከት እንደመሆኑ እንዴት እያስተናገዱት ይገኛል?

አቶ ተፈራ፡- እውነት ነው፡፡ በእግር ኳሱ አሁን አሁን የምናያቸው ነገሮች ትክክል አይመስሉኝም፡፡ በጣም አሳሳቢም እየሆነ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ባሉት ዓመታትም በስፖርቱ አለመግባባቶች እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ይኼ በየትም ዓለም የተለመደና ያለም ነው፡፡ አሁን አሁን የምንመለከተው ግን ከስፖርት ባሕሪያት ያፈነገጡ ነገሮችን ነው፡፡ በግሌ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አንድ ነገር ላይ መገታት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በእግር ኳሱ በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ እየተመለከትን ነው፡፡ እግር ኳስ ወንድማማችነትንና አንድነትን የምናፈራበት መድረክ ከመሆኑም በላይ አሁን አሁን ትልቅ የገቢ ምንጭም እየሆነ ነው፡፡ የአገራችን ስፖርት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ረገድ ጥግ ድረስ ሄዷል፡፡ ሥራም ፈጥሯል፡፡ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚም እያደረገ ይገኛል፡፡ አሁን እነዚህን ነገሮች በሚፃረር መልኩ እየታየ ያለው ጠላትነት ፍፁም ተገቢ ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዲያመሩ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያት የሚሉት ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- የስፖርቱ ባለድርሻዎች ማለትም የክለብ አመራሮች አሠልጣኞች፣ ተጨዋቾች፣ ደጋፊዎችና የመሳሰሉት ሽንፈቶችና ውጤትን በፀጋ መቀበል የሚለውን የእግር ኳሱ መርህ ደብዛውን እያጠፉት ነው፡፡ እግር ኳስ በባሕሪው ስሜታዊነትን የሚያስከትል ነው፡፡ ይህንኑ ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ በደልና ተፅዕኖ እንኳ ቢደርስ መቀበልና ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ ከሰሞኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔ ከጠቀስኳቸው አካላት አንዳንዶቹ ከአንድ አመራር፣ አሠልጣኝና ተጨዋቾች የማይጠበቁ አድራጎቶች መነሻነት የተወሰዱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የዲሲፕሊን ጉድለቶች የዲሲፕሊን መመሪያውን አጣቅሶ ውሳኔ ለመስጠት እንኳ የሚያዳግቱ ናቸው፡፡ የመሀል ዳኛን ማዋከብ፣ የግለሰቦች ስም እየተጠቀሰ ተልካችሁ ነው የሚሉና ሌሎችም በተለያዩ ደጋፊዎችን ወዳላስፈላጊ ብጥብጥና ሁከት የሚወስዱ ሆነው ብዙዎቹ ማስረጃ የቀረበባቸው ናቸው፡፡ ይኼ ለአገሪቱ ስፖርትም አደገኛ በመሆኑ ከወዲሁ ማረምና መገሰፅ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን አዝማሚያው አደገኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅጣት መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል?

አቶ ተፈራ፡- ቅጣት መፍትሔ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለሌሎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ጥፋተኛ የሆነን አካል ትክክል አይደለህም ብሎ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ትክክል ያልሆነን አካል ትክክል እንዳልሆነ ማሳያው ደግሞ ሁሉም በተስማማበት የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ሲቻል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ሲኖራቸው አይስተዋልም፡፡ በቅርቡ ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ ተወሰደባቸው የተባሉ የክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞችና ተጨዋቾች እንዲሁም ሌሎችም የዘርፉ አካላት ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ሲሻሩ ታይቷል?

አቶ ተፈራ፡- ውሳኔዎች በመደበኛ ፍርድ ቤትም እንደየሁኔታው የሚቃለሉበትና የሚሻሩበት አግባብ ይኖራል፡፡ እንደ ሕግ ሰው ይህንን ማድረግ ስህተት ነው የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ ነገር ግን ወደ አጠቃላዩ ነገር ስንመጣ አዝማሚያው አንድ አቅጣጫ ሊቀመጥለት እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም አካል በብቃቴ ተሸነፍኩ ማለትን እንደ ነውር እየቆጠረ ነው፡፡ የስፖርቱ ዓለም አቀፍ ባህልና ሥርዓት እየጠፋ ነው፡፡ በየትኛውም አገር እግር ኳስ በሥራ እንጂ በሁከትና ብጥብጥ ሲያድግ አልታየም፡፡ ልንታረምና ወደ ትክክለኛ አሠራር ልንመለስ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን አገሪቱን እንዳናፈራርስ እሠጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለሚጠቅሷቸው ችግሮች በሙሉ ምክንያት የላቸውም ብለው ይወስዳሉ?

አቶ ተፈራ፡- ሜዳና ሌሎችም ለእነዚህ ችግሮች ምክንያት ሊሆኑ አይገባም እያልኩ አይደለም፡፡ እያንዳንዱን ነገር ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን መመልከት ይኖርብናል፡፡ የጨዋታ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች ከአቅም ብቃት ጋር በተገናኘ የችግሮች መስንኤ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ በጨዋታ ሪፖርት አቀራረብ ላይ በርካታ ክፍተቶች እንደሚኖሩ እወስዳለሁ፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ደግሞ በማብቃት ልናስተካክላቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ግን አሁን አሁን የክለብ ደጋፊዎች ስለት ይዘው የተያዙበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ምን እየሆንን ነው? ዳኞችን ሳይቀር እነዚህኑ መሣሪያዎች በማሳየት ማስፈራራትና ውጤት የማስቀየር አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ተጨዋቾች ከተፈጥሮ ባገኙት ጉዳይ እየተሰደቡ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኛስ ማን ሆነን ነው? ሌሎችን ከተፈጥሯዊ ባሕሪው ጋር አገናኝተን የምንሳደበው? ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ማን ነው በሚፈልገው መልክ የሚፈጠረው? እነዚህ ነገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትሉ እንደሆኑ እናምናለን፡፡ እዚህ ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን የሚመለከታቸው ሁሉ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዲሲፕሊን ኮሚቴው በዚህ ረገድ ሥራ እንደበዛበትና ተፅዕኖም እንደሚደረግበት ይሰማል?

አቶ ተፈራ፡- ሥራ በዝቶባችኋል በሚለው እስማማለሁ፡፡ ተፅዕኖ ስለሚባለው ግን በግሌ የደረሰብኝ ነገር የለም፡፡ በሌሎችም ተመሳሳይ የሥራ ነፃነት እንዳለ ነው የማውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ያለው የውድድር ሥርዓት (ፎርማት) እንደገና ሊጠና እንደሚገባው የሚናገሩ አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- ይኼ የሚያነጋግር አይደለም፡፡ እኔም የውድድር ሥርዓቱ (ፎርማቱ) እንደገና መጠናት ይኖርበታል ከሚሉት ነኝ፡፡ አሁን እየሄድንበት ያለው ለእግር ኳሱ ዕድገትም እየጠቀመ አይደለም፡፡ ያተረፈው ቢኖር ጥላቻን ብቻ ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ነገር ደግሞ በሰዎች ጭንቅላት ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተሳሳተ አመለካከት ውስጥ እንዳለን ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ እንደ ፌዴሬሽን በተለይ ከውሳኔ ጋር ተያይዞ አቅሙ ውስን ነው የሚሉ አሉ?

አቶ ተፈራ፡- በግሌ አቅም እንዳለው ነው የምወስደው፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው በአገር ደረጃ ከፍተኛ ችግር እንዳለው ግምት ወስዶ፣ ነገሩን መመልከት እንደሚያስፈልግ ግን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ደጋግሜ መግለጽ የምወደው እግር ኳሱን ምክንያት በማድረግ እየተኬደበት ያለው መንገድ ተገቢና ትክክል አይደለም፡፡ ለስፖርቱ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በሌላው አገር ጥፋት ቀርቶ ዳኞችን ለማታለል መሞከር በራሱ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከዚህ አኳያ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...