የኢኮኖሚ ሕግጋት የማይገዙት የሚመስለው የአገራችን ምስቅልቅል ገበያ አሁንም የሸማቾች ራስ ምታት እንደሆነ ቀጥሏል ማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የማይመለከተው የታችኛው ማኅበረሰብ አኗኗርን በትኩረት ለሚከታተል ዜጋ ገበያው ከማስገረም አልፎም ያሳዝናል፡፡ በስመ ነፃ ገበያ መረን የተለቀቀው የንግድ ሥርዓቱ አስከፊ ገጽታ ትዝብቴን ከገጠመኞቼ ጋር እንዳካፍላችሁ አስገድዶኛል፡፡ እንደኔ አስተውላችሁ እንደሆነ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ከተራ ሻይ ቤት እስከ እህል በረንዳ ድረስ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ትናንት በ30 ብር የሚቀርብ ቀይ ወጥ ወይም ቅቅል 50 ብር ይገባል፡፡ በስድስት ብር ይሸጥ የነበረ ማኪያቶ አሥራ አምስት ብር ይሆናል፡፡ በኩንታል 1,200 ብር የነበረ ቀይ ጤፍ 1,800 ብር ይገባል፡፡ ኪሎው 35 ብር ይሸጥ የነበረ ምስር ክክ 55 ብር መግባቱ ይነገራችኋል፡፡ ልብ በሉ ነዳጅ በሊትር የጨመረው 0.50 ሣንቲም ገደማ ቢሆን ነው፡፡ ሸማቹ ግን በእንዲህ ዓይነት ጭማሪ ይመታል፡፡ በሌላ ጊዜ የጨመረው የነዳጅ ዋጋ ሲወርድ ቅናሽ ብሎ ነገር የለም፡፡
የኢኮኖሚ ሕጉን በግርድፍ ስንረዳው የገበያ ዋጋን ከሚገዙት መካከል በሸቀጦችና በአገልግሎቶች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው መስተጋብር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር ውስጥ በምርቶች ውስጥ የሚታየው የዋጋ ለውጥም አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዋጋ ሲጨምርም ሆነ ሲቀንስ እነዚህ ክስተቶች እንደ መለኪያ ይታያሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ የእኛ የገበያ ሁኔታ ሲታይ ግን ጤናው የታወከ ነው፡፡ ጥቂት ገበያውን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ዋጋ እየወሰኑ ሸማቹን ለችግር ይዳርጋሉ፡፡ ነፃ ገበያ የሚባለው የግብይት ሥርዓት በዋጋና በጥራት ጤናማ ውድድር የሚደረግበት ሆኖ እያለ፣ እዚህ አገር ያለውን ምን ዓይነት ስያሜ መስጠት ያስፈልጋል? በጣም አናዳጅ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአገሪቱን የቢራ ገበያ የተቆጣጠሩት ኩባንያዎች በአድማ ዋጋ ከመወሰን ወጥተው በምርት ጥራትና በዋጋ መወዳደር ሲጀምሩ ማየት ደስ የሚያሰኝ ጅማሬ ነበር፡፡ የውጭ ኩባንያዎች የአገራችን ቢራ ገበያ ውስጥ በገቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነፃ ገበያ ማለት ውድድር መሆኑን ማሳየት በመጀመራቸው እኔ በበኩሌ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ይህ ዓይነቱ ውድድር ወደ ሌሎች መስኮችም ተዛምቶ አጋዥና መከታ ያጣውን ሸማች ከብዝበዛ ማውጣት ቢቻል በጣም ጥሩ ነው፡፡ አለበለዚያ አየር በአየር ንግድ ጥርሳቸውን የነቀሉት የአገራችን ነጋዴዎችማ ተስፋ አስቆርጠውናል፡፡
በአንድ ወቅት በሥራዬ ምክንያት ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቦትስዋናና ደቡብ አፍሪካ እመላለስ ነበር፡፡ በእነዚህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ምሳሌ ሊሆኑ በሚችሉ አገሮች ውስጥ ሥጋ፣ ዓሳና ዶሮ እንደ ድንች በየቦታው በርካሽ ዋጋ ሲበሉ ስመለከት ያሳፍረኝ ነበር፡፡ እኛ እዚህ የበግ፣ የበሬና የዶሮ ሥጋ ለበዓል ብቻ የክት የሆኑብን ብርቅ ምግቦች ናቸው፡፡ እዚያ በብዛትና በጥራት በአነስተኛ ዋጋ ይቀርባሉ፡፡ እዚህ ዓሳ ብርቅ በሆነበት አገር እንኖራለን፡፡ እዚያ ከተለያዩ ምግቦች ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለች፣ የተለያዩ ዓይነት የምግብ ፍጆታዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ሰፊ የመሬት ሀብት እያላት፣ ምግብ አሁንም ለሕዝቡ በበቂ ሁኔታ አለመቅረቡ ያናድዳል፡፡ እንቁላል፣ ወተት፣ አይብ፣ ቅቤና መሰል የእንስሳት ተዋጽኦዎች ብርቅ የሆኑብን መሥራት ባለመቻላችን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ እንራባለን፡፡ ወይም ሆዳችንን መሙላት አቅቶናል፡፡ ይህም አሳዛኝ ነው፡፡
ትዝ ይለኛል አንድ ወቅት ነዳጅ እንደቀነሰ ምሳዬን የምመገብበት ሬስቶራንት እሄዳለሁ፡፡ የተለመደውን ምግቤን ካጣጣምኩ በኋላ ማኪያቶ ጠጥቼ ቢል እንዲመጣልኝ አዛለሁ፡፡ አስተናጋጁ በቢል ማቅረቢያ ውስጥ ያመጣውን ከፍቼ ሳየው ደነገጥኩ፡፡ ዝርዝሩን ልተወውና የ28 ብር የዋጋ ጭማሪ ነው የቀረበልኝ፡፡ ምግቡ ላይ የመጠንም ሆነ የጥራት ለውጥ የለም፡፡ ማኪያቶውም በፊት የማውቀው ነው፡፡ ምክንያቱን ስጠይቅ፣ ‹‹የዋጋ ማስተካከያ በማድረጋችን ነው›› የሚል መልስ ተሰጠኝ፡፡ በጣም ተናድጄ ስለነበር ባለቤቱን ጥሩት ስል የለም ተባለ፡፡ ሥራ አስኪያጅ ተብዬው እየተቅለሰለሰ፣ ‹‹በተለያዩ አቅርቦቶች ላይ ጭማሪዎች ስለገጠሙን ነው፤›› ብሎ የእኔን ምላሽ ሳይሰማ ጥሎኝ ሄደ፡፡ መልዕክቱ ገባኝ፡፡ ‹‹ብትፈልግ ተቀበል ካልፈለክ አትምጣ፤›› ነው፡፡ ለነገሩ ምንጩ የማይታወቅ ገንዘብ የሚሰበስቡ ሰዎች ለዋጋ ግሽበት ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን ለማወቅ ዓይንን ገለጥ አድርጎ ዙሪያችንን ማየት ይበቃል፡፡
መንግሥት ገበያው ውስጥ ይህን አድርጉ ወይም አታድርጉ እያለ ገብቶ ዋጋ ይወስን የሚል አስተያየት የለኝም፡፡ ነገር ግን የተመሰቃቀለው የግብይት ሥርዓት ፈር እንዲይዝ የተቆጣጣሪነት ሚና አለው፡፡ አንደኛው ዋጋ የሚወስኑ አድመኞችን መበተን፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ጤናማ እንዲሆን ማድረግ፣ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ንግድ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግና ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ጭምር መቆጣጠር፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ያቋቋሙዋቸው የንግድ ተቋማት የመንግሥት ወይም የሕዝብ እንዲሆኑ ማድረግ ወይም ወደ ግል ይዞታ ማስተላለፍ፣ ሙሰኛ ባለሥልጣናትንና ጀሌዎቻቸውን በሕግ መጠየቅ፣ ወዘተ ጠቃሚ ሐሳቦች ይመስሉኛል፡፡ ሕዝቡ ከመጠን በላይ የሆነ ችግር ውስጥ በመሆኑ ይታሰብበት፡፡
በቅርቡ አንድ ዕቃ ለመግዛት ፒያሳ እሄዳለሁ፡፡ የተለያዩ መደብሮች ውስጥ ገብቼ ስጠይቅ 900 ብር ለሚሸጥ ዕቃ በመሀላቸው የ300 ብር ልዩነት አለ፡፡ ዕቃው የሚሸጥበት አካባቢ መደብሮቹ የሚገኙት 50 ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ነው፡፡ ዕቃው የሚመጣው ከአንድ ከታወቀ አገር ነው፡፡ ነጋዴዎቹ ምክንያቱን ሲጠየቁ ቀረጥና ታክስን ሰበብ ያደርጋሉ፡፡ ምንም በማያሳምን ምክንያት ገበያውን እንዲህ ያምሱታል፡፡ ለነገሩ እስኪ መድኃኒት መደብሮች ሒዱና በሐኪም የታዘዘ መድኃኒት ጠይቁ፡፡ የምትሰሟቸው ዋጋዎች ሌላ በሽታ ይፈጥራሉ፡፡ ይህንን የነገርኳችሁን ወግ የነገርኩት አንድ የውጭ ዜጋ የሥራ ባልደረባዬ፣ ‹‹ሥነ ምግባር በሚጠፋበት ቦታ ሁሉ ዘረፋ ወንጀል መሆኑ ቀርቶ ፅድቅ ይሆናል፤›› ሲለኝ መልስ አልነበረኝም፡፡
(ዮሐንስ ቤተ ማርያም፣ ከላፍቶ)