የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ያቀረቡት 320.8 ቢሊዮን ብር ቀጣይ በጀት፣ 53.9 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት አለበት፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የበጀት ረቂቅ አዋጅ፣ የበጀት ጉድለቱ በተለይ ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች እንደሚሸፈን ገልጿል፡፡ ይህም ጉድለቱን ለመሸፈን የሚገኘው የአገር ውስጥ ብድር ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አንፃር የሚኖረው ድርሻ 2.5 በመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በ2008 ዓ.ም. የፀደቀውና በግማሽ ዓመቱ የፀደቀው ተጨማሪ በጀት በድምሩ 292.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ለ2010 ዓ.ም. የተያዘው በጀት ከ2009 በጀት ጋር ሲነፃፀር የ28.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡
ለበጀት ዓመቱ ከተያዘው ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ለክልሎች በድጎማ የሚከፈፋፈለው 117.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በመቀጠል ለካፒታል ፕሮጀክቶች 114.8 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 81.8 ቢሊዮን ብር፣ ለድህነት ቅነሳ ወይም ለዘላቂ ልማት የተያዘው ደግሞ ሰባት ቢሊዮን ብር መሆኑ በረቂቅ ሰነዱ ተብራርቷል፡፡
የ2010 ዓ.ም. በጀት በሚዘጋጅበት ወቅት ታሳቢ ከተደረጉ ቁም ነገሮች ውስጥ የበለፀጉ አገሮች ለታዳጊ አገሮች የሚሰጡት ብድርና ዕርዳታ ሊቀንስ እንደሚችል ታሳቢ መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ይህንን ግዙፍ የፌዴራል መንግሥት ወጪ ለመሸፈን የታቀደው ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ፣ ከዕርዳታና ብድር፣ እንዲሁም ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ነው ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የበጀት ጉድለቱ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ተግባራዊ ከተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተመጣጠነ በመሆኑ በዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም፡፡ ቀጣዩ በጀት ሲዘጋጅ በወቅቱ የሚኖረው አማካይ የዋጋ ዕድገት ከስምንት በመቶ እንደማይበልጥ፣ አጠቃላይ የአገሪቱ የምርት ዕድገትም 19.1 በመቶ እንደማያድግ፣ የዚያኑ ያህልም የገቢ ዕቃዎች (ኢምፖርት) 12.5 በመቶ ዕድገት እንደሚኖራቸው ታሳቢ ተደርጓል፡፡
የአገሪቱ ዕድገት 11.1 በመቶ እንደሚሆን ታሳቢ ስለተደረገ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ አጠቃላይ የፋይናንስ ውስንነት በመኖሩ፣ የወጪ ንግድ መዳከም እየታየ በመሆኑ፣ የግዙፉን ዕቅድ ተፈጻሚነት ዕውን ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሰይድ ኑር (ዶ/ር) ሰነዱን በዝርዝር ባይመለከቱትም፣ አጠቃላይ ሊወሰድ የሚገባውን በወፍ በረር ዕይታ ለሪፖርተር ለማብራራት ሞክረዋል፡፡
‹‹ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ተፈጥሮ ካፒታል በጀት እስካልቀነሰ ድረስ በጀት ማደጉ አይቀርም፤›› ሲሉ ዶ/ር ሰይድ ገልጸው፣ በጀት በአሥር በመቶ አደገ ቢባል የዋጋ ግሽበት በዚያኑ ያህል ካደገ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው በጀት ሊታይ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የበጀት ጉድለት ኖረም አልኖረም አሁን ባለው ሁኔታ በአገር ውስጥ ገቢ ሲሸፈንም ችግር የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡ በጀት በውጭ ምንዛሪና በአገር ውስጥ ገንዘብ ሲሸፈን ልዩነት አለው፤›› በማለት የገለጹት ዶ/ር ሰይድ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ ቢቻል እንኳ፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ወደ አገር የምናስገባቸው ዕቃዎች ብዛት አላቸው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እንደሚታየው የወጪ ንግድ የዚያኑ ያህል እያደገ አይደለም፤›› ሲሉ ነባራዊ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡
የበጀት ጉድለት በተለይ በግብርና ምርታማነት ሊካካስ ስለሚችል፣ በበጀት ጉድለት ሊፈጠር የሚችልን የዋጋ ግሽበት መከላከል እንደሚቻል ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
መንግሥት ላለፉት በርካታ ዓመታት ከወጪ ንግድ ለማግኘት ያቀደውን ማሳካት አልቻለም፡፡ በ2008 በጀት ዓመት የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት (2007 ዓ.ም.) ጋር ሲነፃፀር በ8.5 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ሰባት ወራት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም በ2008 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ37.5 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በዚህም በአጠቃላይ የተያዘው በጀት በውጭ ምንዛሪ ግኝት ካልታገዘ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡
ለሚቀጥለው ዓመት የተዘጋጀው የበጀት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ፣ ምክር ቤቱም ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡