Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ ለአዳዲስ በረራዎች ፈቃድ ተጠየቀ

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ ለአዳዲስ በረራዎች ፈቃድ ተጠየቀ

ቀን:

  • መንግሥት ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርቧል

በሳዑዲ ዓረቢያ ያለሥራና ያለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የትራንስፖርት ችግር መኖሩ ተጠቆመ፡፡ ኢትዮጵያዊያኑን በፍጥነት ለመመለስም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ለአዳዲስ በረራዎች ፈቃድ ተጠይቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንዲሁም ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ በሚደረገው የአውሮፕላን በረራ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያንን የዕፎይታ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት፣ የትራንስፖርት ችግር ማጋጠሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ እንዳስታወቁት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ እንዲመለሱ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ዜጎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ካጋጠሙት እንቅፋቶች መካከልም የትራንስፖርት ችግር አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንዲሁም ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረውን በረራ ለመጨመር፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፈቃድ እንደተጠየቀ አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡ የዕፎይታ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ዜጎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፈቃደኛ በሚሆንበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ጅዳ፣ ከአዲስ አበባ ጂዛንና ከአዲስ አበባ ሪያድ አዳዲስ በረራዎች እንደሚጀመሩ አስረድተዋል፡፡ ከማጓጓዙ ጋር በተያያዘም የሚካሄደው የትኬት ሽያጭ በትኬት ጽሕፈት ቤቶች ብቻ ውስን ስለነበረ፣ በአሁኑ ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ ሲባል በሪያድ፣ በጂዳና በጂዛን የሚገኙ የኮሙዩኒቲ ጽሕፈት ቤቶች የትኬት አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ያስቀመጠችው ጊዜ ገደብ ከሃያ ቀናት ያልበለጡት በመሆኑ፣ ዜጎችን በመመለስ ጥረት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የብሔራዊ ዜጎች አስመላሽ ግብረ ኃይል ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ጥረት የበለጠ ለማፋጠን በአንድ አምባሳደር የተመራ በአጠቃላይ 12 ዲፕሎማቶችን የያዘ ልዑካን ቡድን ወደ ሪያድና ጂዳ እንደተላከ አቶ መለስ ጠቁመው፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ዜጎችን በመመለስ አገራዊ ተልዕኮ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም ዜጎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ክልሎች እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ የኦሮሚያ፣ የአማራና የደቡብ ክልሎች ሃያ የሚሆኑ ኃላፊዎችን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለቅስቀሳ ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራው ዜጎችን አስመላሽ ግብረ ኃይል፣ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመሄድ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራቱ ተጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያው ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሳይንገላቱ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡበት ጉዳይ ላይ የመከረ መሆኑን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ዓመት በላይ እልህ አስጨራሽ ምክክርና ድርድር በኋላ በኢትዮጵያና በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታት መካከል የተፈረመው የሥራ ሥምሪት ስምምነት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዋና ጭብጦች ናቸው ከተባሉ ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሲሄዱ፣ በሁለቱ መንግሥታት በኩል ሊሟሉ የሚገባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሄዱ የሚያደርገውን ይህንን ስምምነት ጨምሮ እስካሁን የተፈረሙ ስምምነቶች አራት እንደሚያደርሰው አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ከኩዌት፣ ከኳታርና ከዮርዳኖስ ጋር ስምምነቶች መፈረማቸውን አስታውሰዋል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብታቸው በሕግ ተከብሮ እንዲኖሩ ማድረግና አሠሪውም ሆነ ሠራተኛው ኮንትራቱን እንዲያከብር በስምምነቱ ላይ ተገልጿል ብለዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ በገቡ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ላይ በደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳትና እንግልት ምክንያት መንግሥት የጉዞ ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ‹‹የአፍሪካ አገሮች፣ የኅብረቱ ሊቀመናብርትና ሠራተኞች ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ዕጩአቸው አድርገው እስከ መጨረሻ በመደገፋቸውና የእስያ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የካሪቢያንና የአውሮፓ አገሮች ድምፃቸውን ለእሳቸው በመስጠት ላደረጉት ትብብር መንግሥት ታላቅ ምሥጋና ያቀርባል፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን ጥቅም ለማስከበር ከተለያዩ አካላት ጋር ተባብራ እንደምትሠራ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ በዓለም አቀፍና በበይነ መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ ያላትን ውክልና ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አክለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች አገራቸውን ወክለው በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲወዳደሩ በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የውክልና ቦታዎችን አዘጋጅቶ በማቅረብ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ተደማጭ በማድረግና የአፍሪካን አጀንዳም በማራመድ መድረክ የተጠናከረ ሥራ ወደፊት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...