Monday, March 4, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በእስራኤል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለአምስት ቀናት በእስራኤል የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የቀድሞው የእስራኤል ፕሬዚዳንት ሽሞን ፔሬዝ ባረፉ ጊዜ ለቀብር ወደ እስራኤል አቅንተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ካለፈው እሑድ ጀምሮ በእስራኤል ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ ናቸው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩንና የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩን ያካተተው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራው ልዑክ እስራኤል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዳደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእስራኤል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ውይይት በአገሪቱ ተከስቶ ስለነበረው ድርቅ ተወያይተዋል፡፡ ከወራት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ስለነበረው አለመረጋጋትም አንስተው ሐሳብ መለዋወጣቸውን፣ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ደግሞ ዕድገቱ ያመጣው የሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ አይሁዶች ጋር ግንኙነቱን እንደ አዲስ ለመጀመር መንግሥት ዕቅድ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውም ታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ሬዩቨን ሪቭሊን ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መምከራቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም  ለፕሬዝዳንት ሪቪሊን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ሲወዳደሩ አገራቸው በመደገፏና ድምፅ በመስጠቷ አመስግነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ‹‹እዚህ የመጣሁት የኢትዮጵያና የእስራኤልን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ተቀደሰችው አገር በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታም ለፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የእስራኤል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የአሥር ዓመታት ጉዳይ ሳይሆን ከንግሥት ሳባ ጉብኝት ጋር የተያያዘና ሺሕ ዓመታት ወደኋላ የተጓዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሺሞን ፔሬዝ ባረፉ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ በመገኘታቸውም ከልብ አመስግነዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ የመጣ በእስራኤል የሚኖር ታላቅ ሕዝብ አለን፡፡ ከእነዚህ መካከል ዶክተሮች፣ ፓይለቶና አምባሳደሮች ይገኙበታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በጋራና በተናጠል ብዙ ችግሮች እንዳሉብን ቢታወቅም ወደፊት በጋራ ሆነን እንደምንፈታው ተስፋ አለኝ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

‹‹ለጋራ ግንኙነታችንና አንድነታችን አብረን መሥራትና አብረን መቆም አለብን፤›› ያሉት ሪቭሊን፣ ኢትዮጵያንና እስራኤልን የሚያመሳስላቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹የአፍሪካና የእስራኤል ግንኙነት ዋነኛውና ትክክለኛው የግንኙነት መግቢያ በር ኢትዮጵያ ነች፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ እየተጠናከረ የመጣውን የእስራኤልና የአፍሪካ ግንኙነት ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምታሻግረው እምነታቸው እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

የእስራኤልንና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ረገድ አገራቸው ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሽብርተኝነት፣ አክራሪነትና የአየር ንብረት ለውጥ የጋራ ጠላቶቻችን በመሆናቸው አብረን ልንታገላቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሪቭሊን፣ ‹‹ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጥሩ ሰብዕና ያላቸው ሰው በመሆናቸው፣ በምርጫው ወቅት የእርሳቸው ደጋፊ በመሆናችንና ድምፃችንን ለእሳቸው በመስጠታችን ኩራት ተሰምቶናል፡፡ የዓለም ሕዝብም ሊኮራባቸው ይገባል፤›› በማለት ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት መመረጣቸውን አሞካሽተዋል፡፡

በናዚ ለተጨፈጨፉት አይሁዶች መታሰቢያነት በተገነባው ሙዚየም በመገኘት የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በእየሩሳሌም በሚገኘው እስራኤል እንድትመሠረት ትልቅ ዋጋ የከፈሉ መሪዎች አስከሬን ባረፈበት ብሔራዊ መካነ መቃብር በመገኘትም የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ጋር በመሆን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር እንደጎበኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአይሁዶች ምኩራብ ታላቁ ግንብ የአይሁዶች መለያ የሆነውን ቆብ አድርገው በተመስጦ ውስጥ ሆነውም ታይተዋል፡፡

የኢትዮጵያና የእስራኤል የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1956 ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረው ግንኙነት በቆንስላ ደረጃ የተወሰነ እንደነበርና ከ1961 ዓ.ም. ወዲህ ወደ አምባሳደርነት ደረጃ ማደጉን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ዓላማ አድርጎ በመካሄድ ላይ ያለው  የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የእስራኤል ጉብኝት፣ ከዚህ በፊት ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች በተጨማሪ በውኃ አጠቃቀም፣ በዓሳና በእንስሳት እርባታ ላይ አዳዲስ ስምምነቶችን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ ላይቤሪያ በሚካሄደው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከላይቤሪያ ተመልሰው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ እየተጠበቀ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -