Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የስህተት መንገድ መድረሻው ገደል ነው!

የሚሠራ መሳሳቱ አይቀርም፡፡ ላለመሳሳት ተብሎም ሥራ አይቆምም፡፡ በዓለማችን አስደናቂ የሆኑ ፈጠራዎች የተገኙት እየወደቁ እየተነሱ ትጋት ባሳዩ ታታሪዎች ነው፡፡ በአጠቃላይ የሚሠራ ቢሳሳትም፣ ከስህተቱ እየተማረ እርምት ስለሚያደርግ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ግስጋሴው ዕፁብ ድንቅ የሚባሉ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ ስህተት አስከፊ የሚሆነው ግን ሲደጋገምና አሰልቺ ሲሆን ነው፡፡ ስህተትን በስህተት ለማረም በሚደረግ እንቅስቃሴ ደግሞ ለማመን የሚከብዱ ጥፋቶች ይፈጸማሉ፡፡ ‹‹ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም›› እየተባለም ሰነፎችና ግዴለሾች ሲፅናኑበት ይታያል፡፡ መሳሳትን የመታረሚያ አጋጣሚ ማድረግ ሲገባ በስህተት መንገድ ላይ እየነጎዱ ራዕይ አልባ ጉዞ ማድረግ፣ አሁን ላለውም ሆነ ለመጪው ትውልድ አደጋ መደቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስህተትን ለማረም ወይም ጥፋትን አውቆ ላለመታረም በተለያዩ ጊዜያት በታዩ ግትርነቶች፣ ትውልዶች ያላግባብ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› በሚባል ድርቅና ምክንያት አገር አሳሯን በልታለች፡፡ ሕዝባችንም የመከራ ቀንበር ተሸካሚ ሆኗል፡፡ ‹‹የዝንጆሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል›› እንዲሉ አሁንም ከዚያ አረንቋ ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡

ኢትዮጵያዊያን በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ የሚደርስባቸውን በደል ተቋቁመውና ተሳስበው ይኖሩ የነበሩትና አሁንም የቀጠሉት፣ ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ባላቸው ወደር የሌለው ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ጥልቅ ፍቅር ምክንያት ደግሞ ወራሪዎችን ለመመከትና ለማንበርከክ በተደረጉ ጦርነቶች ሕይወታቸውን በፈቃዳቸው መስዋዕት አድርገዋል፡፡ በሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረው የገዥዎችን ጭቆና አንቀበልም በማለት ሕይወታቸውን የገበሩም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መተዛዘንና አንተ ትብስ አንቺ ትብስ የሚባባሉበት ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ይህ ለዘመናት የዘለቀ የጋራ እሴት በጠንካራ የአንድነት መንፈስም የተገመደ ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ መንፈስ የሚፈታተኑ ችግሮች በዚህ ዘመን በጣም አግጥጠው እየታዩ ነው፡፡ መነሻቸውም መድረሻቸውም ስህተት በመሆኑ በጊዜ ካልታረሙ፣ በሥውር እንደተቀበረ ፈንጂ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች በጊዜ መላ ካልተፈለገላቸው አገሪቱንና ሕዝቧን በታትነው ለታሪካዊ ጠላቶች ያጋልጣሉ፡፡

የአገር ጉዳይ በጥልቅ ሐሳብና አመራማሪ በሆኑ ምልከታዎች በጥሞና መታየት ያለበት፣ ወደ ጥልቁ ገደል የሚያመሩ የስህተት ጎዳናዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡ ወቅቱ የአገርን ዕጣ ፈንታ፣ የሕዝብን ህልውና፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አኳኋን እያሰናሰሉ ካልተነጋገሩበት በጥራዝ ነጠቅነትና በግዴለሽነት የሚበላሹ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስለአገር ጉዳይ ሲነሳ መፈክር ከማንጋጋትና ጉሮ ወሸባዬ ከማለት በላይ፣ ስህተቶችን አርሞ ቀናውን መንገድ ለመያዝ መነሳት ጠቃሚ ነው፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ የላቀ የአገር ጉዳይ እያለ በማንነት ስም ብሔር ውስጥ በመወሸቅ አገራዊ መለያን ማጣት ፋሽን እየሆነ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊያን የጋራ ስምምነት ፀንታ የኖረች አገርን በክፋት መንፈስ ተሸብቦ ማጥላላትና ማናናቅ የማንነት መገለጫ እየተደረገ ነው፡፡ ይልቁንም ባለፉት ዘመናት የተከሰቱ የተዛቡ ግንኙነቶችን አስተካክሎና ከዘመኑ ጋር አጣጥሞ የተሻለ ሆኖ መገኘት ሲገባ፣ ነገሥታቱንና ለአገር ሉዓላዊነት የተዋደቁትን ማክፋፋት በርትቷል፡፡ የባሰባቸው ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አናውቅም ይላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወደ ዘንዶ ጉድጓድ የሚወስድ ስህተት፣ ሌላው ቀርቶ የታሪካዊ ጠላቶች መሣሪያ እንደሚያደርግ አለማሰብ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡ የተፈጠረባትን ምድር የሚያንቋሽሽ የዘቀጠ ሰብዕና የተላበሰ ለመሆኑ ይህ ጥቂቱ ማሳያ ነው፡፡ ጠባብነት የሚብላላበት አደገኛ አረንቋ ነው፡፡ እዚህ አረንቋ ውስጥ ደግሞ ሕዝብ በበቀል ደም እንዲፋሰስ እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፡፡

በሌላ በኩል ለአገር አንድነት ከእኛ ወዲያ ማን አለ እየተባለ ከበሮ በሚደለቅበት ሥፍራ ደግሞ፣ ለዘመናት ሲያደነቁሩ የነበሩ የስህተት ዲስኩሮችን መስማት የተለመደ ነው፡፡ አግላይነትና እኔ ብቻ የሚል ጽንፈኝነት ውስጥ በመግባት፣ ሌላውን ማንቋሸሽና ማዋረድ መለያው ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነት የእስትንፋስ ያህል በሚፈለግበት በዚህ ዘመን ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚወረወር አስተያየትን አለማዳመጥ፣ ቢቻል ደግሞ ማፈን፣ ካልሆነ ደግሞ በጠላትነት ፈርጆ ለነገ ቂም በቀል ማመቻቸት የዘወትር ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የግማሽ ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የያዘውን ጭፍን ጥላቻና ማጥላላት የተለመደ አጀንዳ ማድረግ አልላቀቅ ያሉት በሽታ ነው፡፡ ለቅራኔዎች መፍቻ የሚረዱ ተግባራት ውስጥ ከመጠመድ ይልቅ፣ ለነገ መተላለቅ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ጥላቻዎችን ማባዛት ሊፋቱት ያልቻሉት መከራ ነው፡፡ እልህ፣ ግትርነትና ቂመኝነት እየተወራረሱ ለሥልጡን ፖለቲካዊ ግንኙነት ራስን ማዘጋጀት ጭራሽ ተዘንግቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ እጅግ የተሳሳተ ጎዳና ከዚህ ቀደም አለማዋጣቱ እየታወቀ፣ እልኸኞች እየጨፈሩበት ነው፡፡ መድረሻው ግን አገር ለማፍረስ እንጂ ለመገንባት አይጠቅምም፡፡ ከሥልጣኔ ጋር የሚጋጭ አዘቅት ነው፡፡ እዚህ አዘቅት ውስጥ የተዘፈቀ ኃይል ዓይኑን ጨፍኖ ለሌላ ዙር ፍጅት ሕዝብ ይቀሰቅሳል፡፡ ከዚህ አደገኛ አዘቅት ውስጥ በፍጥነት መውጣት የግድ ይላል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ጦርነቶች ተካሂደውባታል፡፡ የውጭ ወራሪዎችን ለመመከትና በመሣፍንቱ መካከል ይነሱ የነበሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ሕዝቧን ለድህነት፣ ለኋላቀርነት፣ ለማይምነት፣ ለበሽታና ለድርቅ ብሎም ለረሃብ ዳርገዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከሥልጣኔ ተራርቃ ፍዳዋን አይታለች፡፡ በቅርብ ዘመን ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነት በርካታ መከራዎች አጋጥመዋል፡፡ በዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ውስጥ ግን ኩሩውና ጀግናው ሕዝባችን አገሩን ከማፍቀር የገታው ምንም ምድራዊ ኃይል አልነበረም፡፡ እርስ በርሱም ተከባብሮና ተፈቃቅሮ ነው እየኖረ ያለው፡፡ ዋናው ችግር የሚመነጨው ግን ዕውቀት ቀስመናል በሚሉ ልሂቃን ልጆቹ ነው፡፡ ራሳቸውን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በተለያዩ ጉዳዮች እየከፋፈሉ አገርን ለአደጋ የሚዳርጉ ድርጊቶች ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ከሥልጣኑ ወዲያ ማዶ ላለው የአገር ህልውና፣ ሥልጣን የሚፈልገው ሌላው ጎራ ደግሞ ለአገር ዘለቄታዊነት ከማሰብ ይልቅ በተለመደው የስህተት መንገድ ላይ የጎሪጥ እየተያዩ ቀጥለዋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የብሔር ካርታ እየመዘዙ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራክሱ አሉ፡፡ እነዚህ ድርጊታቸው ለጠላት ቀዳዳ በመክፈት ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባበታል›› እንዲሉ፣ የአገሪቱንና የሕዝቡን ህልውና ይፈታተናሉ፡፡ በጠባብ የጥቅም መነጽር የአገርን ጉዳይ እየተመለከቱ ከጠላት ጋር መተባበርም ሆነ፣ በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይገነባ መንገዱን መዘጋጋት የመጨረሻ ግቡ አገርን በጠላት ማስበላት ነው፡፡ የስህተት መጨረሻው ደግሞ ይኼ ነው፡፡ ከጠላት ጋር ዋንጫውን እያነሳ ያለ ኃይል ለማንም ደንታ የለውምና፡፡ አገር ከማፈራረስ በስተቀር፡፡

በአገር ጉዳይ እንደ ኩሩዎቹ ኢትዮጵያውያን እያሰቡ፣ የአሁኑ ዘመን ዓለም ወዴት እያመራ እንደሆነ እየመረመሩ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አፍሪካ ቀንድ ድረስ የሚስተዋለውን ትርምስና ሥጋት እያስተዋሉ፣ ወዘተ. መነጋገርና የጋራ መፍትሔ መፈለግ አለመቻል በገዛ እጅ አገርን ችግር ውስጥ መክተት ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው መስክ የሚስተዋለው የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ወደ ጎን ተብሎ፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ያተኮረ ሥልጡን ግንኙነት ካልተመሠረተ የዓመታት ስህተት እያናጠረ ይቀጥላል፡፡ አንድ ቀን ደግሞ ሁሉንም እንደ ጎርፍ ጠራርጎ ይወስዳል፡፡ ይህ ዘመን ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚባልበትን የደካሞች ፍልስፍና አይፈልግም፡፡ ለትውልዱም ሆነ ለመጪው አይጠቅምም፡፡ ዓለም የሚያምነው በሰጥቶ መበቀል መርህ ነው፡፡ ይህ መርህ ደግሞ ተግባራዊ የሚደረገው በድርድር ነው፡፡ ድርድር በሁለት  ተደራዳሪ ወገኖች መካከል የሚካሄድ ሲሆን፣ የጨዋታ ሕጉ ደግሞ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ድርድር እንዲኖር ደግሞ ለዴሞክራሲ የሚመጥን አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ እንደ አሮጌ ቁና መጣል ይመጣል፡፡

የተመጣበት መንገድ በተደጋጋሚ በስህተት ላይ ሌላ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ አያዋጣም፡፡ በታሪክ ገድላቸው በደማቅ ቀለም የተጻፈላቸው አባቶችና እናቶች ለውዲቷ አገራቸው ባፈሰሱት ደም እውነተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እነሱ ያሳለፉትን ብርቱ ድካምና ውጣ ውረድ ማንኳሰስ የማይቻለው፣ በሚወዷት እናት አገራቸው ላይ ሴራ በመሸረብ ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር ካሰፈሰፉ ኃይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው ድል በመጎናፀፋቸው ነው፡፡ ይህ አኩሪ ታሪካችን ነው፡፡ እነዚህን ጀግኖችና አርበኞች ለመንቀፍ ብዕር ከማሾልና አጉል ከመፈላሰፍ በፊት፣ የኋላውን በአንክሮ ተመልክቶ የወደፊቱን መተለም ይበጃል፡፡ ይህ ደግሞ የማንኛውም አገሩን የሚወድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ‹‹ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት ግን እጅግ ከባድ ነው›› እንደሚባለው የአገርን ህልውና ከሚፈታተኑ ድርጊቶች በመታቀብ፣ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስተናገድ፣ በጎሪጥ ከመተያየት ይልቅ በመነጋገርና በመደራደር የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት መረባረብ ይቅደም፡፡ ከሥልጣን በላይ አገር ትበልጣለች፡፡ ስለአገር ክብር የመጨረሻውን እውነተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን እያሰቡ በዚያ መንፈስ አገርን ታላቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ውለታ ቢስ ሆኖ በግልና በቡድን ጥቅም ስሜት ብቻ አገርን ችግር ውስጥ መክተት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡  ለዚህም ነው የስህተት መንገድ መድረሻው ገደል ነው የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...