Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተፈጥሯል

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተፈጥሯል

ቀን:

  • ለስምንት ሚሊዮን ተጎጂዎች 555 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

   ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ቡድን፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች አስቸኳይ የዕርዳታ ምግብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መፈጠሩን በይፋ አስታወቁ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ፣ በድርቁ አካባቢዎች ከመደበኛ ምግብ በተጨማሪ በተለይ ፅኑ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መፈጠሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ ደግሞ አሁን ያለው የአስቸኳይ ዕርዳታ ምግብ እንደሚሟጠጥ አስታውቋል፡፡

      በመግለጫው መሠረት ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በማሽቆልቆሉ ሳቢያ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ በድርቅ የተጎዱ ወገኖች የዕለት ዕርዳታ ጠባቂዎች ለፅኑ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ለአስቸኳይ ዕርዳታ የሚውል ምግብ መጠንም በአሳሳቢ ደረጃ መቀነሱ ተገልጿል፡፡

ከሐምሌ ወር ጀምሮ 500 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ግዥና ለትራንስፖርት እንደሚያስፈልግ፣ 55 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ድርቁ በከፋባቸው ቦታዎች ፅኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለደረሰባቸው ወገኖች በአስቸኳይ እንደሚፈለግ በመግለጫው ተካቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርቁ በስፋት በሚታይባቸው ደቡባዊና ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍሎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ መጠን በጣም ከፍ ማለቱን መግለጫው ጠቁሞ፣ ለዚህ መንስዔው ደግሞ የበልግ ዝናብ አነስተኛ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ 7.9 ሚሊዮን ዜጎች የዓመቱን የመጨረሻ ኮታቸውን የሚወስዱት በሰኔ ወር መጨረሻ በመሆኑ፣ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የችግሩ መጠን ሊሰፋ እንደሚችል ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ዝናቡ በማነሱ ምክንያት የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 7.78 ሚሊዮን ማሻቀቡ ይታወሳል፡፡ ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት ወራት ሊጨምር እንደሚችል የተመድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ቀደም ለድርቁ ተጎጂዎች ያስፈልጋል የተባለው ዕርዳታ 948 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ አሁን ግን 550 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚፈለገው፡፡ ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በሚፈለገው መጠን እየተገኘ ባለመሆኑ፣ አሁንም የተጠናከረ ዕርዳታ መቅረብ እንዳለበት እየተጠየቀ ነው፡፡ በተለይ የዕለት ደራሽ ምግቦች፣ የተመጣጠኑ ምግቦችና ንፁህ የመጠጥ ውኃ አንገብጋቢ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ድርቁ የከፋባቸው ሥፍራዎች በጣም የራቁ በመሆናቸውና የውኃ ጉድጓዶችም በመድረቃቸው የውኃ እጥረት ፈተና መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ድርቁ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ የተለያዩ ሥፍራዎች 7.8 ሚሊዮን ዜጎችን ያጠቃ ሲሆን መንግሥት የውኃ፣ የምግብ፣ የጤናና የትምህርት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም የተለያዩ ሚኒስቴሮችን አቀናጅቶ በመሥራት ላይ መሆኑንና 98 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምግብ ለተረጂዎች ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ አሥር አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ጉብኝት አመቻችቷል፡፡ ‹‹ሆርን ኦፍ አፍሪካ ፓርትነርሺፕ ሚሽን›› የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው የልዑካን ቡድን ከሰኔ 1 ቀን እስከ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በሁለቱ አገሮች ለደረሰው አስከፊ ድርቅ ዕርዳታ ለማሰባሰብ የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ጉብኝት ያደርጋል ተብሏል፡፡

በልዑካን ቡድኑ ውስጥ አሥር የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች መካተታቸው ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ ከሐሙስ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዋርዴር ዞን ከከፍተኛ የአገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ጉብኝት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ ዋርዴር ዞን ኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ዞን በድርቁ ምክንያት በርካቶች ለአስቸኳይ ዕርዳታ ተጋልጠው፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል በቅርቡ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ የተፈናቀሉ 2,395 ሰዎች (475 ቤተሰቦች) አስቸኳይ የዕርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጓቸው ተገልጿል፡፡ በአምስት ቀበሌዎች ውስጥ ኗሪ የነበሩ ወገኖች ቤቶቻቸው በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው የቤት ዕቃዎቻቸው፣ ማብሰያዎቻቸው፣ ልብሶቻቸው፣ ምግባቸውና ምግብ ነክ ያልሆኑ ንብረቶቻቸው ወድመውባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 950 ተማሪዎች ደብተሮቻቸውና የመማሪያ መጻሕፍቶቻቸው ከጥቅም ውጪ ሆነውባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ለሦስት ወራት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና መቋቋም እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...