Wednesday, February 21, 2024

መልስ ያላገኘው የቢሊዮን ብሮች ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የዘንድሮ የሥራ ዘመኑን 33ኛ መደበኛ ስብሰባ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዟል፡፡ የስብሰባውን ሒደት በመከታተል በአገሪቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት የደረሰበትን ደረጃ ለመመዘን እንዲቻላቸው የተፈቀደላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በመሰብሰቢያ አዳራሹ የታዛቢ እንግዶች መስተናገጃ ሥፍራ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ምክር ቤቱ ለዕለቱ የያዛቸውን መወያያ አጀንዳዎች እንዲከታተሉ የጠራቸው በመላ አገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ እንዲሁም ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም በዚሁ የእንግዶች ሥፍራ ቦታቸውን ይዘው የውይይቱን መጀመር በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በዚሁ ሥፍራ ቦታቸውን ከያዙት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ ይታያሉ፡፡

በዕለቱ ለውይይት በተያዘው አጀንዳ ላይ ለመሳተፍ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ነገር ግን በሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት የተነሳ አልፎ አልፎ የሚገኙ ባለሥልጣናትም ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የማዕድን ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ወርቁ፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ፣ ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የዕለቱን ስብሰባ ለመጀመር የተሰየሙት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ምልዓተ ጉባዔው መሟላቱን ካረጋገጡ በኋላ የተያዙትን አጀንዳዎች አስተዋውቀዋል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2008 በጀት ዓመት ኦዲት ግኝት ሪፖርት ከአጀንዳዎቹ አንዱ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ዓመታዊ የበጀት አጠቃቀም ሕጋዊነት ላይ፣ እንዲሁም የሥራ አፈጻጸሙ ላይ የሚደረግ ኦዲትና የኦዲት ግኝት ሪፖርት ትልቅ ትኩረትን የሚስብ አጀንዳ በመሆኑ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያም በተለምዶ ሰፋ ያለ ሽፋን የሚሰጠው ርዕስ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ከአዘቦት ቀን በተለየ አለባበስ ሞገስ አግኝተው በወንበራቸው ተገኝተዋል፡፡ አንዳንዶቹ የወከሉትን ማኅበረሰብ በሚያንፀባርቁ ባህላዊ አልባሳት ደምቀዋል፡፡

የቀደመው መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ከፀደቀ በኋላ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን የሚከታተለው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ወደ መድረክ እንዲወጡ አፈ ጉባዔው ጥሪ ካደረጉ በኋላ፣ የዕለቱ ዋነኛ አጀንዳ የሆነው የኦዲት ግኝት ሪፖርት እንዲቀርብም ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ቦታቸውን እንዲይዙ በአፈ ጉባዔው ተጋብዘዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩን እንኳን ደህና መጡ በሚል ደማቅ ፈገግታ የተቀበሉት አፈ ጉባዔ አባዱላ አፀፋውን ከዋና ኦዲተሩ አግኝተዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ የአፈ ጉባዔውን እጅ ነስተው በዕለቱ ዋነኛ ርዕስ ሥር ያዘጋጁዋቸውን ሚስጥር ያዘሉ 57 ገጾች መግለጥ ሲጀመሩ የምክር ቤቱ ድባብ ተቀይሯል፡፡ የታፈኑ ተቃውሞዎች የሚመስሉ ጉርምርምታዎች ይደመጣሉ፣ የቁጭት ፈገግታዎች ይስተዋላሉ፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት (በዋና ኦዲተርነት ከተሾሙ አንስቶ) በግንቦት ወር ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡትን የኦዲት ግኝት ሪፖርት ዘንድሮም ሳይሰለቹ በንባብ ማሰማታቸውን ጀምረዋል፡፡ በ2008 የበጀት ዓመት ሒሳብ አቅራቢ ከነበሩ 165 የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች መካከል 158ን ኦዲት ለማድረግ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በታቀደው መሠረት፣ የሁሉንም 158 መሥሪያ ቤቶች ኦዲት መከናወኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ኦዲቱም በአብዛኛው የተለመደውን የናሙና ኦዲት ሥልት በመከተል እንዲሁም እንደ ኦዲቱ አስፈላጊነትና አግባብነት ሙሉ በሙሉ ኦዲት በማድረግ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

እያንዳንዱ የኦዲት ሥራ እንደተጠናቀቀም ከሚመለከታቸው የኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር በኦዲት ግኝቶቹ ላይ የመውጫ ስብሰባ (Exit Conference) ከመደረጉ በተጨማሪ፣ ረቂቁ ተልኮላቸው የሰጡትን ምላሽ ያገናዘበ የመጨረሻ ሪፖርት በመሆኑ የመረጃዎቹ ተዓማኒነትና አግባብነት በሁሉም ወገን ተቀባይነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹ ዝርዝር ሪፖርት ራሳቸውን ችለው በተጠናከሩ ሁለት ጥራዞች፣ የኦዲት አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው አምስት መሥሪያ ቤቶችን፣ እንዲሁም የጎላ ችግር ያለባቸው ሆነው በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው 53 መሥሪያ ቤቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶች፣ በተጨማሪም 18 የክዋኔ (የሥራ አፈጻጸም) ኦዲት ግኝቶችን የያዙ ሪፖርቶቹን ለአፈ ጉባዔው፣ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለሌሎች የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች በዝርዝር መመርመርና ዕርምጃ መውሰድ እንዲቻላቸው በጥልቀት ተዘጋጅቶ እንዲደርሳቸው መደረጉን፣ የሪፖርቶቹ ቅጂ ሁለት ጥራዞችም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲደርሱ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም በዕለቱ ለተሰየመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርቡት ሪፖርት የምክር ቤቱን ትኩረት ሊያገኙ ይገባል ተብሎ የታመነባቸው አንኳር ግኝቶችን ብቻ የተመለከተ ስለመሆኑ አስቀድመው ገልጸዋል፡፡

የዋና ኦዲተሩ የቢሊዮን ብሮች ጥያቄ

የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሒሳቦች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ ለገንዘብ ጉድለትና ምዝበራ ያጋልጣል የሚሉት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ፣ የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ በየወቅቱ ተቆጥሮ ከመዝገብ ጋር እንዲመሳከር፣ እንዲሁም የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ መዝገብ መግለጫ ላይ የተመለከተው የጥሬ ገንዘብ መጠን ተቆጥሮ ትክክለኝነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የጥሬ ገንዘብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 144,716 ብር ጉድለት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በሒሳብ መግለጫ መዝገብ ሪፖርት የተደረገውንና በቆጠራ የተገኘ የገንዘብ መጠንን ለማመሳከር በአምስት መሥሪያ ቤቶች በተደረገ ኦዲት 379,390 ብር ጎድሎ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ መሥሪያ ቤቶችም በአዲስ አበባ ኤርፖርት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲና ዲላ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በድምሩ ሁለት ሚሊዮን 445 ሺሕ ብር በሒሳብ መግለጫ መዝገብ ከሰፈረው በልጦ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የመጨረሻው የፋይናንስ አስተዳደር ችግር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ምዝበራ መኖሩንም አመላካች ስለመሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት የኦዲት ሪፖርቶች የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ቢኖርም፣ መጠኑ አነስተኛ መሆኑን ሪፖርተር ያደረገው ዳሰሳ ያረጋግጣል፡፡ ለአብነት ያህል በ2007 በጀት ዓመት ዋና ኦዲተር ያቀረበው ሪፖርት ላይ የተገኘው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት 298 ሺሕ ብር ነበር፡፡

ውዝፍና ተሰብሳቢ ሒሳቦች የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ሌላው ትኩረት ነበር፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 መሠረት ወጪ የተደረገ ሒሳብ በወቅቱ መወራረድ አለበት፡፡ በድንጋጌው መሠረት የማንኛውም ወጪ ሒሳብ በሰባት ቀናት ውስጥ በማስረጃ መወራረድ አለበት፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በ113 መሥሪያ ቤቶችና 28 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አምስት ቢሊዮን 262 ሚሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 375 ሚሊዮን 557 ሺሕ ብር ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደመዘገበና ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ሊቀርብበት ባለመቻሉ፣ ትክክለኝነቱን (ተሰብሳቢነቱን) ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ተሰብሳቢ (ያልተወራረደ) ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን 2.38 ቢሊዮን ብር ተሰብሳቢ የተገኘበት ግንባር ቀደም ተቋም ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ 720.1 ሚሊዮን ብር፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ላይ 461 ሚሊዮን ብር፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ላይ 352.3 ሚሊዮን ብር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ላይ ብር 172.1 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ላይ 122.4 ሚሊዮን ብር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት ላይ 119.1 ሚሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ በዋነኛነት ተገኝቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኦዲተሩ ሪፖርት ስማቸው ያልተገለጹ ሁለት ተቋማት፣ በድምሩ 11 ሚሊዮን 155 ሺሕ ብር ያላግባብ ከተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ ሰርዘው ተገኝተዋል፡፡

መሰብሰብ የሚገባቸውን ገንዘቦች ተቋማቱ እንዲሰበስቡ፣ ያልተወራረደውንም እንዲያወራርዱ ያሳሰቡት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ በዚህ የኦዲት ዓይነት ችግር የሚገኝባቸው ተቋማት አመራሮች የተገኘው ተሰብሳቢ ወይም ያልተወራረደ ሒሳብ እነርሱ ወደ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት የተከማቹ አድርገው ከኦዲት መሥሪያ ቤቱ ጋር እንደሚከራከሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹አንዳንዶቹ እኔ ከመወለዴ በፊት የተከሰቱ አድርገው ይከራከራሉ፤›› ያሉት አቶ ገመቹ፣ ይህንን ጉንጭ አልፋ ክርክር ለማስቀረት በማሰብ ተሰብሳቢ ወይም ያልተወራረዱ የተባሉትን ሒሳቦች በዕድሜ በመዘርዘር በዚህ ሪፖርታቸው እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተገለጸው 5.2 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ በቆይታ ጊዜው ሲተነተን፣ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 134.1 ሚሊዮን ብር፣ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዕድሜ ያለው 3.2 ቢሊዮን ብር፣ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ድረስ የቆየ 373 ሚሊዮን ብር፣ ከአሥር ዓመት በላይ የሆነው 196.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ቀሪውን 1.5 ቢሊዮን ብር የቆይታ ጊዜ በግልጽ ለመለየት አለመቻሉን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

‹‹በእኔ የኃላፊነት ዘመን የተፈጠረ አይደለም›› ለሚሉ ወይም ዘመናትን ያስቆጠረና ሲንከባለል የመጣ እንደሆነ አድርገው ለሚከራከሯቸው ባለሥልጣናት፣ ‹‹አሁን በዕድሜ ውስጥ መደበቅ አይቻልም፤›› ሲሉ ትችት አዘል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የዋና ኦዲተሩ የኦዲት ግኝት ሪፖርት እንደቀጠለ ነው፡፡ የመንግሥት ገቢ በወጡት ሕጎች መሠረት መሰብሰቡን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤትና በሥሩ ባሉ አሥራ አምስት ቅርንጫፎች 1.1 ቢሊዮን ብር በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ ሕጎች መሠረት አለመሰብሰቡ ተረጋግጧል፡፡ በፌዴራል መንገሥት የግዥ አፈጻጸም መመርያ መሠረት ውል የገባ አቅራቢ ሳይፈጽም በቀረው የውል መጠን ላይ ውል ሰጪ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በየቀኑ 0.1 በመቶ ከውሉ ዋጋ አሥር በመቶ ሳይበልጥ የጉዳት ካሳ ሊሰበስቡ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ የሕግ አግባብ የመንግሥት ተቋማት በውሉ መሠረት ባልፈጸሙ አቅራቢዎች ላይ ዕርምጃ ስለመውሰዳቸው በተደረገ ኦዲት፣ 19 መሥሪያ ቤቶች ከሕንፃ ተቋራጮችና ዕቃ አቅራቢዎች ያልሰበሰቡት 226.3 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መገኘቱን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር 44.8 ሚሊዮን ብር፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ 23.7 ሚሊዮን ብር፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 23 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 19.7 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳዎችን ባለመሰብሰብ ከተጠቀሱት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በሚመሩበት ሕግ መሠረት የመንግሥት ገቢን በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰብ በሕግ የተጣለባቸው ኃላፊነት መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን ኃላፊነታቸውን ተቋማት እየተወጡ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዘጠኝ ቅርንጫፎችና በሌሎች አምስት ተቋማት ከውዝፍ ግብር፣ ወለድና ቅጣት መሰብሰብ የሚገባው አራት ቢሊዮን ብር እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡

ማንኛውም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መንገደኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ከተፈቀደው መጠን በላይ የውጭ ገንዘብ የያዘ እንደሆነ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚያዘጋጀው ዴክለራሲዮን ላይ መመዝገብ እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ከሕጋዊው መጠን በላይ ተመዝግቦ የገባው የውጭ ምንዛሪ ግለሰቡ ተመልሶ ለመውጣት ሲፈልግ ገንዘቡን ያስመዘገበበት ዴክለራሲዮን ካላቀረበ በስተቀር ገንዘቡን መልሶ ይዞ መውጣት እንደማይችል በሕግ የተከለከለ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አብራርተዋል፡፡ በተገለጸው ሕጋዊ አግባብ እየተሠራ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በአዲስ አበባ ኤርፖርት የጉምሩክ ቅርንጫፍ በውጭ ዜጎች ባለቤትነት በ2008 ዓ.ም. የተመዘገበ 211,220 ዩሮና 1,700 ዶላር፣ እንዲሁም 4,336 ኪሎ ግራም ወርቅ የግለሰቡ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ሳይኖርና የገንዘቡ ሕጋዊነት በአግባቡ ሳይረጋገጥ ለግለሰቡ እንዲመለስ መደረጉን ሪፖርት አድርገዋል፡፡

ተቋማት የተፈቀደላቸውን በጀት በአግባቡ ወጪ አድርገው መጠቀማቸው የሚረጋገጠው በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመርያዎች መሠረት ለወጪው ተገቢውን ማስረጃ ሲያቀርቡና ወጪ ሒሳቡን በትክክል ሲመዘግቡ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ ያስረዳሉ፡፡ ተቋማት በዚህ አግባብ እየሠሩ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረጉ ኦዲቶች በ59 መሥሪያ ቤቶች 236.5 ሚሊዮን ብር የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ ወጪ ተደርጎ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከመዘገቡት ተቋማት መካከል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 21.1 ሚሊዮን ብር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት 20.9 ሚሊዮን ብር፣ ጂማ ዩኒቨርሲቲ 47.6 ሚሊዮን ብር፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 25.8 ሚሊዮን ብር የተገኘባቸው ዋነኞቹ ተቋማት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ካገኙት አገልግሎት በላይ ብልጫ በመክፈል በርካታ መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ሪፖርቱ ተለይተዋል፡፡ በ18 መሥሪያ ቤቶች ለግንባታና ለተለያዩ ሌሎች ግዢዎች 19.5 ሚሊዮን ብር፣ በ25 መሥሪያ ቤቶች ለደመወዝ፣ ለውሎ አበልና ለሌሎች ክፍያዎች 10.4 ሚሊዮን ብር በድምሩ 29.9 ሚሊዮን ብር፣ በአንድ መሥሪያ ቤት ደግሞ 2,500 ዶላር በብልጫ መከፈሉን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመውም ዝቅተኛ ዋጋ ካቀረቡት ድርጅቶች ግዥ በመፈጸምና ከተገባው ውል ውጪ በመክፈልና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ79 ተቋማት የመንግሥትን የግዥ አዋጅ ሳይከተሉ በድምሩ የ324.9 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸማቸውን የኦዲተሩ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ግዥው የተፈጸመው ያለ ጨረታ በቀጥታ መሆኑ፣ የዋጋ መወዳደሪያ ሳይሰበሰብና መሥፈርቱ ሳይሟላ በውስን ጨረታ የተፈጸሙ መሆናቸውን ያመለከታል፡፡

እነዚህን ሕግ ያልተከተሉ ግዥዎች ከፈጸሙ ተቋማት መካከል ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 69.4 ሚሊዮን ብር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር 24.6 ማሊዮን ብር፣ ጂማ ዩኒቨርሲቲ 11.7 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 11.03 ሚሊዮን ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ማንኛውም ግንባታ ሲከናወን ሥራው በትክክል ስለመሠራቱ ብቃቱ ተረጋግጦ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጡ፣ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የማማከር አገልግሎት ፈቃድ በተሰጠው ድርጅት ሲረጋገጥ ብቻ ክፍያዎች ለተቋራጮች ሊፈጸሙ እንደሚገባ በሕግ የተቀመጠ አሠራር መሆኑን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንዲከታተሉ በስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ውል ፈርመው የተገኙት አማካሪዎች በራሳቸው በዩኒቨርሲቲ ተቋማቱ የተቋቋሙ፣ ነገር ግን የማማከር ፈቃድ የሌላቸው የግንባታ ጽሕፈት ቤቶች በሰጡት የግንባታ ትክክለኝነት ማረጋገጫ 260.9 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በአማካሪነት የተቀጠሩት በዩኒቨርሲቲዎቹ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህራን የሆኑ ባለሙያዎች ቢሆኑም፣ የማማከር አገልግሎት ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ ሕግን ያልተከተለ አሠራር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በግንባታዎቹ ላይ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የማያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በተከፋይ ሒሳብ የተያዙ ሒሳቦች በተገቢው ጊዜ ውስጥ መከፈላቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በ73 ተቋማት 1.9 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የ833.8 ሚሊዮን ብር የቆይታ ጊዜ የማይታወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለማን እንደሚከፈልም ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከተጠቀሰው የተከፋይ ሒሳብ የገንዘብ መጠን ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የሚመለከተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን ሲሆን፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ላይ ደግሞ 159.5 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል፡፡

በሌላ በኩል በመንግሥት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሒሳብ ላይ በተደረገ ኦዲት፣ 3.6 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም ወደ ግል ይዞታ በሽያጭ ከተላለፉ ድርጅቶችና የመንግሥት የትርፍ ድርሻ ክፍያ በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ገቢ አለመደረጉን ይፋ አድርገዋል፡፡

የኦዲተር መሥሪያ ቤት የፋይናንስ ሕጋዊነትን ከተመለከቱ ከኦዲት ሥራው በተጨማሪ የክዋኔ ኦዲቶችንም በተለያዩ ተቋማት ላይ በማከናወን ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት እንዲያደርግበት ተብሎ በቀረበው ሪፖርት ላይ ስማቸው ከተነሳ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እና እየገነባው የሚገኘው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ይገኙበታል፡፡

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን የአዋጭነት ጥናት በ1999 ዓ.ም. መንግሥት ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ ያስጠና ሲሆን፣ በዚህ ጥናት መሠረት ፋብሪካውን ለመገንባት አራት ዓመት ጊዜ የሚፈጅ መሆኑን አጥኚ ድርጅቱ ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጥናቱን በመከለስ የፋብሪካውን ግንባታ በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ሐሳብ እንዳቀረበ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሁለቱ ኩባንያዎች የቀረቡት ጥናቶች እንዲጣጣሙ ሳይደረግና በእርግጥም ይህ የሚቻል መሆኑ ሳይረጋገጥ፣ ሜቴክ ግንባታውን በ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በ2006 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ በ2004 ዓ.ም. ውል ቢፈጽምም ፋብሪካው በውሉ መሠረት መጠናቀቅ አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 21 ቀን 2016 ድረስ ከአጠቃላይ የፕሮጀክት የውል ዋጋ 11.08 ቢሊዮን ብር ውስጥ አምስት ቢሊዮን 653 ሚሊዮን ብር ወይም የውሉ 60 በመቶ ለሥራ ተቋራጩ (ሜቴክ) የተከፈለ ቢሆንም፣ እስከ መጋቢት 2009 ዓ.ም. ድረስ የፋብሪካው ሦስቱም ዩኒቶች አፈጻጸም ማለትም የዩሪያ ማዳበሪያ ዩኒት አፈጻጸም 28.05 በመቶ፣ የተርማል ፓወር ፕላንትት ዩኒት አፈጻጸም 11 በመቶና የድንጋይ ከሰል ዩኒት አፈጻጸም 3.05 በመቶ መሆናቸውን፣ አጠቃላይ የፋብሪካው ግንባታ አፈጻጸምም 42.3 በመቶ ላይ እንደሚገኝ በክዋኔ ኦዲቱ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

ይህ የፕሮጀክት አፈጻጸም ዝቅተኛና በዕቅዱ መሠረት ያልተከናወነ ከመሆኑም በላይ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ፣ የፋብሪካው ባለቤት የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ለፕሮጀክቱ ከባንክ ለተበደረው ብድር እስከ የካቲት 2008 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 1,825,513,172 ብር ወለድ መክፈሉ በኦዲት ሥራው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር ምንም ገቢ ሳይመነጭ ለባንክ የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ መጠን ሊያድግና በፋብሪካው ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሥራ ተቋራጩ ለሚያከናውነው ለእያንዳንዱ የፕሮጀክት ሥራ የተተነተነ ዝርዝር ዕቅድ፣ የሥራ ዓይነቶች፣ እያንዳንዱ የሥራ ዓይነት ከጠቅላላ ፕሮጀክቱ ሥራ የሚይዘው ክብደት፣ የሥራዎቹ የገንዘብ መጠን፣ ሥራዎቹ የሚሠሩበት ጊዜና የሥራዎቹ ጊዜ አፈጻጸምን በመከፋፈል በጊዜ መርሐ ግብሩ መሠረት በሚፈለገው ደረጃ አጠቃሎ እንደማያቀርብም ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው የፋብሪካው ጥናት ውስጥ መካተት የነበረባቸው ሥራዎችን የፋብሪካው ግንባታ ከተጀመረ በኋላ በተጨማሪነት የሥራ ተቋራጩ አቅርቦ ተጨማሪ 3.4 ቢሊዮን ብር የተጠየቀ ቢሆንም፣ የኦዲት ሥራው እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በፕሮጀክቱ ባለቤት ውሳኔ እንዳልተሰጠው ዋና ኦዲተሩ አብራርተዋል፡፡

የማይታረሙ ተቋማት

ላለፉት አሥር ዓመታት ሲቀርቡ በነበሩ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች ውስጥ በተደጋጋሚና በየዓመቱ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ወይም የማይታረሙ ተቋማት አሁንም የመንግሥት በጀትን ሕጋዊ ባልሆነ ሥርዓት መጠቀማቸውን ገፍተውበታል፡፡ ተቋማቱ በተመሳሳይ የኦዲት ምርመራ መንገድ የሕዝብ ሀብትና ንብረቶችን ሕገወጥ በሆነ መንገድ እያስተዳደሩ መቀጠላቸው፣ ሃይ ባይ ማጣታቸውንና ይህም በድፍረት እንዲሞሉ እንዳደረጋቸው ማሳያ ነው፡፡

ከዚህ አለፍ ሲልም አለመቀጣታቸው ለሌሎች ተቋማት መማሪያ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዓመት ዓመት ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ገጾች ከማይጠፉት ተቋማት መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግንባር ቀደም ነው፡፡ ዋና ኦዲተሩ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረቡት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ እንኳን በበርካታ ገጾች በተለያዩ የኦዲት ዓይነቶች 9.2 ቢሊዮን ብሮችን የተመለከቱ የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ተደርጎበታል፡፡

በተመሳሳይም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በዚሁ የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በተለያዩ የኦዲት ዓይነቶች ከ400 ሚሊዮን ብሮች በላይ የተመለከቱ የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ተደርጎበታል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት 20.9 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 21.1 ሚሊዮን ብር የኦዲት ግኝቶች ተጠይቀዋል፡፡

የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት የሚጠብቁ ተቋማት የደኅንነት ሚስጥሮችን ለመጠበቅ ሲባል ኦዲት መደረግ የማይገባቸውን የፋይናንስ አጠቃቀምችን በሚስጥር በመያዝ ኦዲት ቢደረጉ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቻቸውን ብቻ ለኦዲት ክፍት እንዲያደርጉ ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ በሕግ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩም በዚህ የሕግ አግባብ መሠረት ክፍት የተደረጉላቸውን የሒሳብ መዝገቦች ብቻ ኦዲት በማድረግ፣ ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ላይ የፋይናንስ አጠቃቀም ሕገወጥነት መኖሩን ነው ያረጋገጡት፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከሞላ ጎደል ሁሉም በሕገወጥ የበጀት አጠቃቀም የተፈረጁ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት (2008 ዓ.ም.) የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ከተጠየቀባቸው የኦዲት ዓይነቶች መካከል ያልተሰበሰበ ውዝፍ የገቢ ሒሳብ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ መሠረት ከውዝፍ ግብር፣ ከወለድና ከቅጣት ሊሰበሰብ የሚገባው 391 ሚሊዮን ብር እንደነበር ተመልክቷል፡፡

በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ አዋጆች መሠረት 118.7 ሚሊዮን ብር እንደሰበሰበ ተመልክቷል፡፡ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በባለፈው ዓመት የኦዲት ሪፖርት በውዝፍ ተሰብሳብ ሒሳብ የኦዲት ዓይነት ብቻ 139.2 ሚሊዮን ብር ተገኝቶበታል፡፡

በእንቁላሉ ጊዜ…

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ የቢሊዮን ብሮች ጥያቄያቸውን ሪፖርት ካደረጉ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት በቁጭት ውስጥ ሆነው የማብራሪያ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ መቼ ነው የሚያበቃው ከሚል የቀጥታ ጥያቄ አንስቶ፣ በሕዝብ ፊት ተጠያቂዎቹ እኛው ነን እስከሚል የጥፋተኝነት ስሜት የተንፀባረቀባቸው የምክር ቤቱ አባላት መፍትሔውን አሁንም ከዋና ኦዲተሩ ይሻሉ፡፡

ለምንድነው የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን በቀጥታ ለዋና ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የማይልከው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዓመት የኦዲት ሪፖርት የጥፋት ግኝቶቹ የመጨመር አዝማሚያ ያሳዩት ለምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፡

አቶ ገመቹ፣ ‹‹ዕርምጃ ስላልተወሰደ ነው ችግሮቹ እየጨመሩ ያሉት፤›› ብለዋል፡፡ ከ2002 እስከ 2006 ዓ.ም. በተደረጉ ኦዲቶች ከደንብና መመርያ ውጪ ክፍያዎች ያላግባብ በመከፈላቸው ገንዘቡ ለመንግሥት ካዝና እንዲመለስ ማሳሰባቸውን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ያስታውሳሉ፡፡ በተጠቀሱት ዓመታት በአጠቃላይ ያላግባብ ክፍያ በመፈጸሙ እንዲመለስና ቅጣት እንዲሰበሰብ ከተባለው 656,155,107 ብር ውስጥ የተመለሰውና የተሰበሰበው 17,472,954 ብር ብቻ ወይም (2.6 በመቶ) መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አሁንም ይህ ገንዘብ መመለስ አለበት፡፡ አንተወውም፡፡ እንከታተለዋለን፤›› ብለዋል፡፡

ለዋና ዓቃቤ ሕግ የኦዲት ግኝቶችን ለምን እንደማያቀርቡ የተጠየቁት ዋና ኦዲተሩ፣ ‹‹የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ስናገኝ ወዲያውኑ ነው ለሕግ አስከባሪ ተቋማት የምንልከው፡፡ እስካሁን ወንጀል ነክ ማስረጃ አላጋጠመንም፡፡ የተገኙት ሒሳቦች ፍትሐ ብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ይህም ቢሆን ለዋና ዓቃቤ ሕግ ልከናል፡፡ እንደማስበው የላላውን መረጃ እያደራጀ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ እንደሚሉት በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴም ሆነ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥርዓት ለማስያዝ ጫና እየተፈጠረ ቢሆንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ‹‹እስከነጭራሹ እንደምንም እየቆጠሩት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ በማጠቃለያው ላይ በሰጡት አስተያየት፣ አገር አቀፍ ንቅናቄ መድረኩ በሰኔ ወር እንደሚካሄድ ጠቁመው በኦዲት የተገኙ መረጃዎች ደግሞ ለዋና ዓቃቤ ሕግ ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡

አፈ ጉባዔው እንዳሉት፣ በሚፈጠረው አገር አቀፍ ንቅናቄ የሚለወጥ ነገር ይኖር ይሆን የሚለው አሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -