የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለበርካታ ዓመታት የኦዲት ግኝት ሪፖርቶቹን ለፓርላማው ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በፌዴራል መንግሥት የበጀት አጠቃቀም ሕጋዊነትና በሥራ አፈጻጸም ላይ የሚደረጉ ኦዲቶችና ግኝቶች ሪፖርቶች በአብዛኛው የተመሠገኑና ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋና ኦዲተሩም ፓርላማ ቀርበው ሪፖርታቸውን ካሰሙ በኋላ ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች በሚሰጧቸው ማብራሪያዎች፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስመሥጋኝ ተግባራትን ለማከናወኑ በቂ ማረጋገጫ ናቸው፡፡ አንዳንድ መጠነኛ ክፍተቶች ቢኖሩም እንኳ፣ በአብዛኛው ለአገሪቱ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ ተቋም መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ ይህንን ማስተባበል አይቻልም፡፡ ዘንድሮም በቀረበው የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት እንደተለመደው አስደንጋጭ የሚባሉ ነገሮች ተሰምተዋል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ኦዲት ከሚደረጉ የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች 158 የሚሆኑት ኦዲት ተደርገዋል፡፡ ውይይት በማድረግና ረቂቁም ተልኮላቸው የእነሱንም አስተያየት ያገናዘበ የመጨረሻ ሪፖርት መቅረቡም ተነግሯል፡፡ የሪፖርቱም ተዓማኒነት በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት እንዳገኘ በይፋ ተገልጿል፡፡ ይህ እንግዲህ ለአገር በጣም ጠቃሚ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡
የዋና ኦዲተር ሪፖርት ራሳቸውን ችለው በተጠናቀሩ ሁለት ጥራዞች አሉ የሚባሉ ግድፈቶችን ጨምሮ ለፓርላማው አፈ ጉባዔ፣ ለፓርላማው በተለይ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴና ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከመድረሳቸው በተጨማሪ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ቀርቧል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ወጪ ሒሳብ በሰባት ቀናት ውስጥ መወራረድ ቢኖርበትም፣ በሪፖርቱ መሠረት ግን ከ5.2 ቢሊዮን ብር በላይ በ113 መሥሪያ ቤቶችና በ28 ቅርንጫፎች ለረጂም ጊዜ አልተወራረደም፡፡ ከዚህ ግዙፍ የአገር ሀብት ውስጥ ከ375 ሚሊዮን ብር በላይ ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተዘመገበና ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ሊቀርብበት አልቻለም፣ ትክክለኛ ተሰብሳቢነቱም አልተረጋገጠም ይላል ሪፖርቱ፡፡ በአገሪቱ ጠያቂና ተጠያቂ የሌለ ይመስል እንዲህ ዓይነት የሕግ ጥሰት ሲፈጸም ዝም ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊትም በአጥፊዎች ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ብዙ ቢነገርም ምንም ዓይነት ለውጥ አልታየም፡፡ ቃል ተግባር መሆን እያቃተው ችግሩ ከመጠን በላይ እየገዘፈ ነው፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በኦዲት ሪፖርቱ ይህንን ግዙፍ ሒሳብ ማወራረድ ያልቻሉ የሚታወቁ መንግሥታዊ ተቋማት በዝርዝር ከሚፈለግባቸው አኃዛዊ መግለጫ ጋር ቁልጭ ተደርገው ተሰይመዋል፡፡ እዚህ ሁሉ ጉድ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉበት፡፡ የትምህርት ተቋማቱ ነገርማ ይዘገንናል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ነጥብ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት አመራሮች የኦዲት ግኝቱ ሲቀርብላቸው የሚሰጡት ምክንያት ነው፡፡ እነሱ ወደ ተቋማቱ ከመምጣታቸው በፊት የተከማቹ መሆናቸውን እንደሚከራከሩ ተሰምቷል፡፡ ለዓመታት የተከማቹ ጉድፎችን ማፅዳትና ኃላፊነትን መወጣት ይሻላል? ወይስ በተከማቸው ችግር ላይ ሌላ ችግር እያከሉ ጉንጭ አልፋ ክርክር ማድረግ? ለዓመታት የተጠራቀሙ ያልተወራረዱ ሒሳቦችን ታቅፎ ከማላዘን፣ በተሰጠ ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ የሚረዱ መላዎችን መፈለግ ይገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የመንግሥት ገቢ በወጡ ሕጎች መሠረት መሰብሰቡን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡ ተገልጿል፡፡ ከውዝፍ ግብር፣ ወለድና ቅጣት መሰብሰብ የሚገባው አራት ቢሊዮን ብር እንደተገኘም ታውቋል፡፡ ሌሎች ከግዥ ጋር የተገናኙ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት በርካታ መሥሪያ ቤቶች ስማቸው እየተጠቀሰ ተነቅሰዋል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? ምንድነው የሚጠበቀው?
ሌላው ቀርቶ ባለፉት አሥር ዓመታት በቀረቡ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ መንግሥታዊ ተቋማት አሉ፡፡ አሠራራቸውን ማረም ባለመፈለጋቸው ወይም የሚያስገድዳቸው በመጥፋቱ ብቻ የመንግሥት በጀትን በሕገወጥ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የአገር ሀብት ከሕጉና ከሥርዓቱ ውጪ እየተዝረከረከ ነው፡፡ ዋና ኦዲተርም አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቢያ እየሰጠ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ብቻ በድፍረት የተሞሉ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሌሎች በመጥፎ አርዓያነት ማስተማሪያ እየሆነ ነው፡፡ በየዓመቱ በሪፖርቱ ጉልህ ሥፍራ የያዙ ሕገወጥ አሠራሮችን ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት ጉዳይ አገሪቱ ከምትታገሰው በላይ እየሆነ ነው፡፡ በፓርላማ ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን ቁጭት አዘል ጥያቄዎች ቢነሱም ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው በቁርጠኝነት ካልተንቀሳቀሱ በስተቀር ምንም ውጤት አይገኝም፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሚገባ ፈትፍቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት መነሻ አድርጎ ለዕርምጃ አለመነሳት የሕዝብ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አሁንም ብዙዎችን በቁጭት እያነጋገረ ነው፡፡
በዘንድሮ ሪፖርት የጥፋት ግኝቶቹ የጨመሩት ለምድነው ተብሎ በፓርላማ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ መልሱም ግልጽ ነው፡፡ ዋና ኦዲተሩ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹. . .ዕርምጃ ስላልተወሰደባቸው ነው ችግሮቹ የጨመሩት. . .›› ብለዋል፡፡ ከ2002 እስከ 2006 ዓ.ም. በተደረጉ የኦዲት ግኝቶች ከደንብና ከመመርያ ውጪ ክፍያዎች ያላግባብ በመፈጸማቸው ለመንግሥት ካዝና እዲመለሱ ቢያሳስቡም፣ ቅጣትን ጨምሮ ከ656.1 ሚሊዮን ብር ውስጥ የተመለሰው ከ17.4 ሚሊዮን ብር (2.6 በመቶ) አይበልጥም ማለታቸው የችግሩን ከመጠን በላይ መግዘፍ ያሳያል፡፡ የሚፈጸሙ የሕግ ጥሰቶችና የዕርምጃ አወሳሰዶች ምን ያህል እንደማይገናኙ በቂ ማሳያ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ ተጥሶ የአገር ሀብት ሲድፋፋ ማን ሊጠየቅ ነው ታዲያ? ጫናዎች ሲበዙ በሕግ ተጠያቂ ይደረጋሉ ተብሎ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ የሚውለው ፉከራ ለማን ይጠቅማል? የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕግ ምን እየሠራ ነው? በእርግጥ እንደተባለው በቀናት ውስጥ ምርመራውን አካሂዶ ክስ ይጀምራል? ወይስ ማስረጃ ፍለጋ ይባዝናል? ይህ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡
የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ተጠያቂነት እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት የማያውቅ እስኪመስል ድረስ ግን የአገር ሀብት ተዝረክርኳል፡፡ እያንዳንዱ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በተቋቋመበት ሕግ መሠረት ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ብዙዎቹ ግን በዚያ መሠረት እየሠሩ አይደሉም፡፡ በተለይ በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ማብራሪያ ላይ እንደተገለጸው፣ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴም ሆነ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥርዓት ለማስያዝና ጫና ለመፍጠር ቢሞከርም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ዋና ኦዲተሩ እንዳሉት ጭራሹን ከምንም የማይቆጥሩት በርክተዋል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የመሰለ ጠንካራ ሪፖርት ይዞ ሕግ ማስከበር አለመቻል ያሳፍራል፡፡ አሁንም በፓርላማው አፈ ጉባዔ አማካይነት አገር አቀፍ ንቅናቄ እንደሚደረግና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ የኦዲት መረጃዎች ይላካሉ ተብሏል፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በእርግጥ በፓርላማው፣ በአስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው ዘንድ ትኩረት አግኝቷል? በሪፖርቱ ግኝቶች መሠረት ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል? ወይስ እንደተለመደው ሁሉም ተጯጩሆ ይበታተናል? አሁን ግን የቸገረው ነገር ለዋና ኦዲተር ሪፖርት የሚሰጠው ምላሽ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ መሆኑ ነው!