Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የቱርክ ትምህርት ቤቶችን የሚመሩ ሰዎች ከአሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ያምናል››

ዶ/ር አደም ኮስ፣ በኢትዮጵያ የቱርክ ማሪፍ ፋውንዴሽን ኃላፊ

ዶ/ር አደም ኮስ ከአንድ ዓመት በፊት በቱርክ መንግሥት የተመሠረተውን የማሪፍ ፋውንዴሽን ለመምራት ወደ አዲስ አበባ ተመድበው ከመጡ ሁለት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ የመጡበት ዋናው ዓቢይ ጉዳይ ግን ከዚህ ቀደም ሲል በቱርካውያን የተመሠረቱ ኢትዮ-ተርኪሽ አል ነጃሺ እንዲሁም ሬንቦው በሚሉ ስያሜዎች የሚታወቁ ትምህርት ቤቶችን በመውረስ ለማስተዳደር ነው፡፡ የቱርክ መንግሥት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ለተቃጣው የመንግሥት ግልበጣ ተጠያቂ የሚያደርገው የፌቱላህ ጉለን ንቅናቄን ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙት ስድስት ትምህርት ቤቶች ባለቤቶችም ከፌቱላህ ጉለን ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ይወነጅላቸዋል፡፡ ውንጀላ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግሥት ጨምሮ ጥቂት የአፍሪካ አገሮችም ትምህርት ቤቶቹን ከግለሰቦቹ ነጥቀው እንዲያስረክቡት ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ከሳምንታት በፊት በቱርክ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹን ለቱርክ መንግሥት አሳልፎ እንደሚሰጥ ይፋ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጥ ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት እየተቆጠበ ቢገኝም፣ ትምህርት ቤቶቹን አሳልፎ ለመስጠት እንቅስቃሴ እንደጀመረ ከሚያመላክቱ ዕርምጃዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትምህርት ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ ያረጋግጣል፡፡ ይህንን ተከትሎም ማሪፍ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ሕጋዊ ሆኖ ለመመሥረት የሚያስቸለውን ሒደት እንዳጠናቀቀ፣ ትምህርት ቤቶቹን ለመረከብ እንደሚጠባበቅ፣ ትምህርት ቤቶቹን ከተረከበ በኋላም የክፍያ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በርካታ ለውጦችን እንደሚያደርግ ዶ/ር አደም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የቱርክ መንግሥት ከአሸባሪዎች ጋር አብረዋል የሚላቸው ግለሶቦች ‹‹የአገር ሚስጥራዊ መረጃ ሸጠዋል፣ አሳልፈው ሰጥተዋል፣ ተላልፈለው እንዲሰጡን ጠይቀን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን›› የሚሉትን ጨምሮ፣ ሌሎች ጉዳዮችን ያነሱበትን ቃለ ምልልስ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡  

ሪፖርተር፡- ዓምና የተካሄደው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ አሁንም ድረስ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የሚብላላ ትኩስ ክስተት ነው፡፡ ለከሸፈው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ የቱርክ መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርገው ፌቶ በማለት የፈረጀውን አካል ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከእነዚህ አንደኛው ማሪፍ ፋውንዴሽን የተባለውን መንግሥታዊ ተቋም መመሥረት ሲሆን፣ በአብዛኛው በትምህርት ዘርፍ በመንቀሳቀስ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ቱርካውያንን ማገልገልም ዓላማው ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ተቋም መመሥረቱ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር አደም፡- የፌቶ ንቅናቄ በቱርክ እንዴት እንደተጀመረ በመግለጽ ልጀምር፡፡ ያለፉትን 40 ዓመታት እንዳጣናቸው እናምናለን፡፡ ይኸውም ለምንድነው? እነዚህ ሰዎች ቱርክን በውጭው ዓለም እንወክላለን እያሉ ባንዲራዋን እየተጠቀሙ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ፌቱላህ ጉለን የተባሉ ሃይማኖታዊ መምህርና የአሸባሪ ቡድኑ መሪ በነበረባቸው ችግር ምክንያት ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተቋማቸው የሚከያናውናቸውን እኩይ ተግባራት መታዘብ ጀምረናል፡፡ ፌቶ በጣም ውስብስብ የአስተዳደር ሥርዓት ያለው በጠባዩም ሚስጥራዊ የሆነ ተቋም ነው፡፡ በቱርክና በወዳጅ አገሮች ላይ ሚስጥራዊ አጀንዳ አለው፡፡ በቱርክ ሕዝብ መዋጮ ትምህርት ቤቶችና የዕርዳታ ድርጅቶችን ከፍተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ መንግሥት የሚሰጣቸውን የታክስ ዕፎይታ ዕድሎች ሆነ ብለው ለሌላ ዓላማቸው አውለዋል፡፡ የቱርክ ሕዝብ በሰጣቸው ገንዘብ ልዩ ልዩ ንብረቶች አፍርተዋል፡፡ ትኩረት ልሰጥበት የምፈልገው ጉዳይ በኢትዮጵያ የተመሠረቱት ትምህርት ቤቶች የቱርክ ሕዝብ ንብረቶች መሆናቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ማሪፍ ፋውንዴሽን እነዚህን ትምህርት ቤቶች ተረክቦ እንዲያስተዳድርና ሌሎችም ሥራዎችን እንዲያከናውን በቱርክ መንግሥት ሲመሠረት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ድምፅም በማግኘት ጭምር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ማሪፍ የተመሠረተው ከግልበጣ ሙከራው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከከሸፈው የመንግሥት ግልበጣ አንድ ወር ቀደም ብሎ የተመሠረተ ነው፡፡ አጀንዳችን ያለንን በማካፈል እህት አገሮችን ማገዝ ነው፡፡ በጋራ ሆነን የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት ማሻሻል እንፈልጋለን፡፡ እዚህ የመጣነው ለድብቅ ተልዕኮ አይደለም፡፡ ማሪፍ በቱርክ መንግሥት የሚመራ፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም ተገቢውን ሒደት ጠብቆና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ነው፡፡

 ሪፖርተር፡- ጥያቄው ግን እናንተ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የምትሏቸው ግለሰቦች እንደ ማንኛውም ሰው የንግድ ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩ ናቸው፡፡ በተገቢው መንገድ ንግዳቸውን ሲያከናውኑ የነበሩና እናንተ በአሸባሪነት እስከ ወነጀላችኋቸው ጊዜ ድረስ መንግሥት መሬት፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድና ሌሎችንም አገልግሎቶች በመስጠት እንዲንቀሳቀሱ የፈቀደላቸው ናቸው፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- አዎን እንዲያ ሲሠሩ የነበሩት የቱርክ መንግሥት በገባላቸው ዋስትና ምክንያት ነበር፡፡ መርሳት የሌለብን የቱርክ መንግሥት ድጋፍ ሲሰጣቸው እንደነበር ነው፡፡ ከአደገኛ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከማወቃችን በፊት፣ በኢትዮጵያ የቀድሞው የቱርክ አምባሳደርም ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርጉላቸው ነበር፡፡ ፍላጎታቸውንና ሐሳባቸውን በቀላሉ መረዳት አትችልም፡፡ በጣም ቀናና ርህራሔ ያደረባቸው ሰዎች ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ድብቅ አጀንዳ አላቸው፡፡ ይህንን በከሸፈው ግልበጣ ወቅት አረጋግጠናል፡፡ አንድ የእንግሊዝኛ አባባል አለ፡፡ ‹አንዴ ብታሞኘኝ ኃፍረቱ ያንተ ነው፡፡ ሁለቴ፣ ሦስቴ ብታሞኘኝ ግን ሞኙ እኔው ራሴ ነኝ› ይባላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን፣ የተማሪዎቹን ወላጆችና ቤተሰቦች ለማስጠንቀቅ የምንፈልገው ልጆቻቸውን የሚልኩበት ተቋም አደገኛ እንደሆነ ነው፡፡ እኛ ከኢትዮጵያውያን መምህራንና ሠራተኞች ጋር ጠብ የለንም፡፡ ከእነሱ ምንም ጉዳይ የለንም፡፡ ጠባችን ትምህርት ቤቶቹን ከሚያስተዳድሩት ቱርካውያን ጋር ነው፡፡ ምናልባት የጀርመን፣ የኔዘርላንድስ ወይም የሌላ አውሮፓዊ አገር መታወቂያና ፓስፖርት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ጨዋታ ለመጫወት እየሞከሩ ነው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩት በዚያው መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ሰዎች ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ካላቸው በመንግሥት ክትትልና ምዘና የሚደረግበትን ትምህርት ቤት መመሥረት ለምን ፈለጉ?

ዶ/ር ኮስ፡- ምክንያቱም በቀላሉ አዕምሯቸውን በመቀየር የወደፊት ምልምሎቻቸውን ማዘጋጀት የሚችሉበትና እንደ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ ወይም ካዛኪስታን ያሉ አገሮች መንግሥታት ላይ እንዲነሱ ለማድረግ ስለሚያመቻቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ወታደራዊ ኃይል እየመሠረቱ ነበር እያሉን ነው ማለት ነው?

ዶ/ር ኮስ፡- ወታደሮችን ብቻ አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶችን የሚመርጡት ወታደራዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎችን ለመቅረፅም ነው፡፡ በሚስጥር ሥራቸውን የሚሠሩት የእነዚህ ሰዎች መሪ በጣም አደገኛ ሰው ነው፡፡ ቱርክን በሦስት ወገን ለመከፋፈል ፈልገው ነበር እኮ፡፡ በአናቶሊያ፣ በአውሮፓና በግሪክ በኩል ለሦስት የተከፋፈለች ቱርክን ለመፍጠር ይፈልጉ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የቱርክ ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ የፌቱላህ ጉለንን ርዕዮተ ዓለም ያስተምሩ ነበር እያሉ ነው?

ዶ/ር ኮስ፡- አዎን በትክክል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ማረጋገጫ አለዎት?

ዶ/ር ኮስ፡- የአካዴሚክ ቀን አቆጣጠራቸውን ማየት ትችላለህ፡፡ በየትምህር ቤቶቹ ያሉትን መጻሕፍት ማየት ትችላለህ፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ ስለፌቱላህ ጉለን ያውቃል፡፡ አንዱን ተማሪ ብትጠይቀው የትምህርት ቤቶቹ አስተዳዳሪዎች የፌቱላህ ጉለን ተከታዮች መሆናቸውን ሊነግርህ ይችላል፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የተማሪዎቹን ወላጆች አነጋግሬ ነበር፡፡ እነሱም የሔዝመት ንቅናቄ ስለሚባለውና ኋላ ላይ የጉለን ንቅናቄ ስለሆነው እንቅስቃሴ ነግረውኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሔዝመት ንቅናቄ መንግሥትን ለመጣል ወይም የመንግሥት ተቋማትን ለመቆጣጠር የተጀመረ ስለመሆኑ የሚገልጽ ነገር አላገኘሁም፡፡ የመንግሥት ተቋማትንና ፓርላማን በቦምብ እናጋያለን የሚሉም አይደሉም፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- እርግጠኛ ነህ እንዲህ ያለውን ነገር ማግኘት አልቻልክም?

ሪፖርተር፡- አዎን ካነበብኳቸው ነገሮች ውስጥ እንዲህ ያለውን የሚጠቅስ፣ በተለይም የገዛ አገራቸውን በሽብር እንደሚንጡ የሚገልጽ ነገር አላገኘሁም፡፡ የሔዝመት ንቅናቄ ሰላማዊና መቻቻልን የሚፈልግ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ እንዲያውም ፌቶ የሚባለውን ቃል የፈጠረው የቱርክ መንግሥት ነው እያሉ ነው፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- የሔዝመት አቀንቃኞች እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት በቱርክ የተማሪዎች ማደሪያዎች ውስጥ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የጉለን ንግግሮች በጣም ታዋቂ እየሆኑና እየተደመጡ መጡ፡፡ ሰውየው የበለጠ ታዋቂ እየሆኑ የመጡበት ምክንያት ምንም እንኳ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ቱርክ የሙስሊሞች አገር ብትሆንም፣ በወቅቱ ግን ሃይማኖታዊ ተግባራት መፈጸም ለእኛ የተከለከለ ስለነበረ ነው፡፡ የወቅቱ የቱርክ መንግሥት ኢስላማዊ ሃይማኖታዊ ተግባራት በግልጽ እንዳይካሄዱ ከልክሎ ነበር፡፡ ይህም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን መርህ ለመተግበር የተደረገ ነበር፡፡ ድንገት ግን እኚህ የሃይማኖት መሪ ተነስተው ሰዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንዲከተሉ መስበክ ጀመሩ፡፡ ከንግግሮቻቸውና አስተምህሮታቸው ጀርባ ግን ምዕራባውያን አገሮች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹም አዳሪ ትምህርት ቤቶችንና ኮሌጆችንም ለመክፈት በቁ፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት ችለዋል፡፡ ሲመረቁም በአስኳላና በሃይማኖት ትምህርቶች ታጥቀው ሊወጡ ችለዋል፡፡ ድብቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የመንግሥት ተቋማትን መቀላቀል ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ ጠበቃ፣ መሐንዲስ እየሆኑ በተለይ ደግሞ የፀጥታ መዋቅሩን ተቆጣጠሩት፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን፣ የፖሊስና ወታደር እንዲሁም የሚዲያ አካላትን አጥለቀለቁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ቱርክ በጣም ደሃ ስለነበረች ጉለንና ተከታዮቹ ስትራቴጂካዊ ተቋማትን ለመያዝ አመቻቸው፡፡

በወቅቱ ጉለን በአስተኛ ጠባብ ቤት ውስጥ ቢኖሩም በርካታ የሚዲያ ተቋማት ነበሯቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳዩም ነበር፡፡ አዕምሯቸው ቢጠመዘዝም ከተራው ቱርካዊ የተለየ ነገር አይታይባቸውም ነበር፡፡ አጠራጣሪ ነገር አይታይባቸውም ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ነበሩ፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ጀምሮ የጉለን ንቅናቄ በውጭ አገሮች በተለይም በባልካን አገሮች ውስጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡ ተከታዮቹም በአዘርባይጃን፣ በካዛኪስታን፣ በኪርጊስታንና በሌሎችም አገሮች ውስጥ መስፋፋት ጀመረ፡፡ ከሶቪዬት ኅብረት መውደቅ በኋላም እነዚህ ሰዎች ወደ ሩሲያ አቅንተዋል፡፡ በአብዛኛው በአሜሪካ የሚደገፉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ በመምህራንና በሌሎች የትምህርት ቤት ሠራተኞች አማካይነት በእነዚያ አገሮች ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ ትፈልግ ስለነበር ነው፡፡ ተማሪዎችንና ወላጆቻቸውን በቀላሉ ስለምታውቃቸው በትምህርት ቤት አማካይነት በጣም ጠቃሚ መረጃ ማሰባሰብ ትችላለህ፡፡ በቀላሉ መረጃ ታገኝባቸዋለህ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለስለላና ደኅንነት ሥራዎች እየተናገሩ ነው?

ዶ/ር ኮስ፡- አዎን ሚስጥራዊ መረጃዎች በዚያ መንገድ ይገኙ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም የቱርክ ትምህርት ቤቶችን የሚመሩ ቱርካውያን ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለሌሎች አገሮች ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ በጣም ከባድ ውንጀላ ነው፡፡ ነገሩን ከባድ የሚያደርገውም ይህንን አባባልዎን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ የመቻልዎ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ያለው ከፍተኛና ከባድ ውንጀላ ደግሞ አንዱ አገር ሌላውን ይሰልል ነበር የሚያስብል መነሻ ሲኖረው የአገሮችን ግንኙነት ሊያሻክር የሚችል ነው፡፡ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለ ተጨባጭ ማስረጃ የሚናገሩት ነገር ተዓማኒነት አለው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ኮስ፡- የምትፈልገውን ንገረኝ ላሳይህም፣ ልሰጥህም እችላለሁ፡፡ እባክህ በትክክል ማወቅ የምትፈልገውን ጠይቀኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከፌቶ ጋር ንክኪ ያላቸው አካላት አሉ ብለውኛልና ይህንን እንዴት ሊያረጋግጡ እንደቻሉ ጠይቄዎታለሁ፡፡ ይህንን ሲሉስ ተጨባጭና ማረጋገጫ ያለው ማስረጃዎ ምንድነው?

ዶ/ር ኮስ፡- በአገራችሁ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የውጭ አገር መምህራን ቡድን ስለአገራችሁ እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ማወቁን ልትገምተው ትችላለህ? ስለወርቅ ክምችታችሁ፣ ስለነዳጅ ሀብታችሁ ያውቃሉ፡፡ ይህንን በደንብ ያውቃሉ፡፡ ካላመንክ ኢንተርኔት ውስጥ ፈልግ፡፡ ስለኡጋንዳ የሚናገሩትን ማዳመጥም ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ግን እኮ እንዲህ ያለው መረጃ የግድ በሚስጥር የሚያዝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ስላለው የወርቅ ክምችት ማወቅ የሚፈልግ ሰው በይፋ የሚያገኘው፣ ሕዝብ የሚያውቀው መረጃ ነው፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- አዎን ግን ኡጋንዳ ውስጥ ይህ ቡድን በቱርክ ለሚኖሩ የንግድ ሰዎች መረጃዎችን ያቀብላል፡፡ ኡጋንዳ ሰፊ የወርቅና የነዳጅ ክምችት አላት፡፡ ከፌቶ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ግን መረጃዎችን በማቀበል የቱርክ ሰዎችም ወደ ኡጋንዳ ሄደው እንዲሠሩ ሲጠይቁ ይታያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ግን ሚስጥራዊ መረጃዎችን የማቀበል ተግባር አይመስለኝም፡፡ የአሜሪካም ሆነ የእንግሊዝ አማካሪ ኩባንያዎች እንዲህ ያሉ መረጃዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢንቨስተሮች ያቀብላሉ፡፡ ዲሎይት ወይም ማኬንዚ የተባሉትን ተቋማት ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ እነዚህ አማካሪ ድርጅቶች ሲሆኑ እንዲህ ያሉትን መረጃዎችም ያቀብላሉ፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- ተጠንቀቅ እያወራን ያለነው ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ኩባንያዎች በተፈጥሮ ሀብት ንግድ ሥራ ውስጥም ስለመግባታቸው ነው፡፡ ከመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ያፈነገጠ ሥራ ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ በገሃድ የትምህርት ሥራዎችን የሚሠራ ኩባንያ ትመራለህ፣ ከጀርባ በድብቅ ግን ለሚስጥራዊ አጀንዳህ ትንቀሳቀሳለህ፡፡ እንዲህ ነው የሚያደርጉት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት መሥራት ስለምፈልገው ሥራ ዓይነት ማስረጃዎቼን እንዳቀርብ ይጠይቀኛል፡፡ ለንግድ ሥራ መምጣቴን በሚገባ ሲያረጋግጥ ፈቃድ ይሰጠኛል፡፡ በትምህርት መስክ እንድሠራ ፈቃድ ተሰጠኝ እንበል፣ መሥራት የሚጠበቅብኝ በዚሁ መስክ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ፈቃድ በሌለኝ መስኮች ላይ የምሰማራ ከሆነ ግን ችግር ውስጥ ነኝ ማለት ነው፡፡ መሥራት የምትፈልገው ነገር እንቅስቃሴህን ይወስነዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን እንዴት ይሠሩ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በሚስጥር የአገራችሁን መረጃዎች ሲጋሩና ሲያጋሩ ነበር፡፡ ይህንን ከአገሬ ተሞክሮ አውቃለሁ፡፡ ከፍተኛ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለሌሎች አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ የደኅንነቱን፣ የሕግ ሥርዓቱንና የፖለቲካውን ብሎም የሌሎቹን ተቋማት መረጃዎች ሰጥተዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እናም ይኸው ተመሳሳይ ተግባር እዚህም ተፈጽሟል እያሉ ነው ማለት ነው?

ዶ/ር ኮስ፡- እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስለእነዚህ ሰዎች በደንብ ቢያጣሩ ሊደርሱበት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ማሪፍ ፋውንዴሽን ትምህርት ቤቶቹን ለመውሰድ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ግን እንደ ማንኛውም ከውጭ እንደ መጣ የንግድ ተቋም ነበር የሚታዩት፣ የሚንቀሳቀሱትም፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- እዚህ የመጣነው በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንድንመጣ ጋብዘውን ነው፡፡ በቅርቡ በፕሬዚዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው መግለጫ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ኢትዮ-ተርኪሽ አል ነጃሺ፣ እንዲሁም ሬንቦው የሚባሉት ትምህርት ቤቶች ወደ ማሪፍ ፋውንዴሽን ይተላለፉ ብለዋል፡፡ ማሪፍ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ በቂ የበጀትና የሰው ኃይል የተሟላለት ነው፡፡ አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት ያለው ተቋም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ የዜና አውታር እንዳነበብኩት ግን ማሪፍ ከሳዑዲና ከኳታርም የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል?

ዶ/ር ኮስ፡- ሊሆን አይችልም፡፡ ማሪፍ ፋውንዴሽን በሕግ አግባብ የተቋቋመ የቱርክ መንግሥት ተቋም ነው፡፡ ዕርዳታም ሆነ ድጋፍ ከማንም አንሻም፡፡ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እንዲሁም በትምህርት መስኮች መሻሻሎች እንዲመጡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መሥራት እንፈልጋለን፡፡ አንድ የምናከናውነው ጠቃሚ ጉዳይ ቢኖር የትምህርት ቤቶቹን ክፍያ እናሻሽላለን፡፡ በዓመት የሚከፈለው መጠን ሁለት ወይም ሦስት ሺሕ ዶላር ከሆነ እኛ ግን ወደ 1,000 ዶላር ዝቅ እንዲል እናደርጋለን፡፡ ይህም ሲባል ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት አሰጣጥ እንደሚኖር በማረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ የትምህርት ቤቶቹን ሕንፃዎች በማደስ በአዲስ መንገድ እናደራጃቸዋለን፡፡ በአዲሱ የትምህርት ዘመን አስፈላጊዎቹ ለውጦችና ማሻሻያዎች በሙሉ ይከናወናሉ፡፡ ነገሮች እልባት እስኪያገኙ ለአምስት ወራት ጠብቀናል፡፡ በኢትዮጵያና በቱርክ ግንኙነት ውስጥ አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ዋናው ጉዳይ የትምህርት ቤቶቹ ለማሪፍ ተላልፎ መሰጠትን ነው፡፡ በምዕራፍ ሁለት ሥራዎቻችን ሌሎች ትምህርት ቤቶችን ልንገነባና ልንከፍት እንችላለን፡፡ ዋናው ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ግን ያሉት ትምህርት ቤቶች ተላልፈው እንዲሰጡን ነው፡፡ ይህ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጥያቄ እንድጠይቅዎ ይፍቀዱልኝ፡፡ የዚህ ጋዜጣ አንባቢያን ‹ተመልከቱ የቱርክ መንግሥት የኢኮኖሚ አቅሙን ተጠቅሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር የግል ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉለትና ተላልፈው እንዲሰጡት አደረገ› ቢሉ ምላሽዎ ምን ይሆናል?

ዶ/ር ኮስ፡- ይህ መልካም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የቱርክ ትምህርት ቤቶችን የሚመሩ ሰዎች ከአሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ያምናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በፀረ ሽብር እንቅስቃሴዎች ላይ ለመተባበር የሚያስችሉን ስምምነቶች አሉን፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ ብቻም ሳይሆን በቦኮ ሐራም፣ በአልሸባብ፣ በፌቶና በሌሎችም ላይ ለመተባበር ስምምነት አለን፡፡ አብረን ለመሥራት የሚያስችሉን ስምምነቶች አሉን፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች መልካም አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ አገር ነች፡፡ ከኢኮኖሚ ዕድገቷ፣ ከሕዝብ ቁጥሯ አኳያ ስትታይም ትልቅ አገር ነች፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ትምህርት ቤቶችን ሲያስተዳድሩ የቆዩት ሰዎች አሸባሪዎች ናቸው ካላችሁ ትምህርት ቤቶቻቸው ይዘጉልን ይሰጡን ከማለት ይልቅ፣ ሰዎቹ ራሳቸው ተላልፈው ይሰጡን ብላችሁ ለምን አትጠይቁም?

ዶ/ር ኮስ፡- እነዚህ ከፌቶ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በቱርክ መንግሥት የሚፈለጉ  ናቸው፡፡ የራሳቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ፓስፖርቶች ተሰርዘውባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 249 ንፁኃን ዜጎቻችን እንዲገደሉ፣ ከ2,000 የሚበልጡትም እንዲቆስሉ ምክንያት በሆነው የግልበጣ ሙከራ ውስጥ እጃቸው ስላለበት ነው፡፡ በግልበጣ ሙከራው ምክንያት በአንድ ሌሊት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ በአገራችን ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በቱርክ ቦታ የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጠን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ተላልፈው ይሰጡን ብላችሁ በይፋ መንግሥትን ጠይቃችኋል?

ዶ/ር ኮስ፡- አዎ፡፡ ጥያቄውን አቅርበን የመንግሥትን ትዕዛዝ እየተጠባበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚገኙት ከፌቶ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላችኋቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው?

ዶ/ር ኮስ፡- ቁጥራቸው በትክክል ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም መታወቂያቸውንና ፓስፖርታቸውን በየጊዜው ይቀያይራሉ፡፡ አንዱን ቀን እዚህ ናቸው ስትል ሌላው ቀን ምናልባት ሐረር ወይም መቐለ ታገኛቸዋለህ፡፡ ወይም ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች ይሄዳሉ፡፡ ሁሌም እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ ለቱርክ መልካም አሳቢዎች ከሆኑ ለምን እንዲህ በየቦታው ይዞራሉ? ለምንስ በየጊዜው ቦታ ትቀያይራለህ? ስለምንስ ትፈራለህ?

ሪፖርተር፡- የንግድ ሰዎች እኮ በየቦታው መንቀሳቀስ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ በዚያም ላይ ከቦታ ቦታ መዘዋወር መብታቸው አይደለም እንዴ?

ዶ/ር ኮስ፡- አዎን መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ስለንግድ ሰዎች ማውራት አልችልም፡፡ የእኔ የተለየ መደብ የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ለማንኛውም ወላጆችን፣ ቤተሰቦችን፣ የመምህራንና የወላጆች ማኅበራትን ማስጠንቀቅ የምፈልገው ካሁን በኋላ ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳይፈጽሙ ነው፡፡ ለመጪው ዓመት በእነዚህ ሰዎች ለሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ክፍያም ሆነ ምዝገባ እንዳይፈጽሙ እንጠይቃለን፡፡ ቱርክ የእነዚህ ትምህርት ቤቶችን ማስረጃዎችና ሰርተፊኬቶች የማትቀበል መሆኗን በማወቅ፣ ወላጆች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የትምህርት ቤቶቹ ሰርተፊኬቶች ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ ሆኖም ለተማሪዎች ማረጋገጥ የምንፈልገው ነገር ቢኖር ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባለው የትምህርት እርከን ውስጥ የነፃ ትምህርት ዕድል እንደምንሰጣቸው እንዲያውቁ ነው፡፡ ተመሳሳይ የፈተና ሥርዓት እንዘረጋለን፡፡ ማሪፍ ፋውንዴሽን ከቱርክ ዩኒቨርሲቲዎች በተጓዳኝ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገሮች ካምፓሶች ስላሉት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በመላክ እንዲማሩ ማመቻቸት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ቤቶቹን መረከብ ጀምራችኋል ማለት ነው?

ዶ/ር ኮስ፡- ገና ነን፡፡ የመንግሥትን ውሳኔና አካሄዶች እየተጠባበቅን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶቹን ስለምንረከብባቸው ጉዳዮች የተለያዩ ስብሰባዎችን እያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ማሪፍ ፋውንዴሽን ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት በኢትዮጵያ መመሥረትና መንቀሳቀስ የሚችልባቸውን ሒደቶች አጠናቀናል፡፡ እኛ ዝግጁ ሆነን እየጠበቅን ነው፡፡ ከቱርክ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚጠባበቅ የሰው ኃይልም ዝግጁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሚዲያ ዘገባዎችም ሆኑ ሌሎች ተቺዎች ከግልበጣ ሙከራው ማግሥት ጀምሮ የቱርክ መንግሥት በጣም ጠንካራ እየሆነ፣ የዴሞክራሲ፣ የነፃ ፕሬስ፣ እንዲሁም በነፃነት የመናገር መብቶች እየጠበቡ መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- አይደለም፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሰዎች ስለእነዚህ ነገሮች የሚናሩት በትክክል በተጨባጭ ያሉትን ሀቆች ሳያዩ ነው፡፡ ቱርክ ምን ያህል ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር እንደሆነች ለማረጋገጥ ካሻችሁ ሄዳችሁ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ዴሞክራሲያችን የተጠበቀው ደማቸውን ባፈሰሱ ሰማዕታት ነው፡፡ የግልበጣ ሙከራው የከሸፈው በ249 ንፁኃን ሞት ነው፡፡ እንዲህ በማድረግ የአገሩን ዴሞክራሲ የታደገ የምዕራብ አገሮችም ሆነ የሌላው አገር ሕዝብ ካለ ልታሳየኝ ትችላለህ?

ሪፖርተር፡- አዎ የቱርክ ሕዝብ መንግሥት በኃይል እንዳይገረሰስ ተከላክሏል፡፡ ጥያቄው ግን መንግሥት በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ባገኘው የበላይነት የሚነሱበትን ትችቶች ዝም እያሰኘ ነው የሚል ነው፡፡

ዶ/ር ኮስ፡- ይህ እውነት አይደለም፡፡ ሚዲያ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም በእኛ ጉዳይ ግን አብዛኞቹ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሐሰተኛ ዘገባዎችን ሲያሠራጩ ነበር፡፡ አሸባሪዎችን በብዕራቸውና በድረ ገጾቻቸው ሲደግፉ ነበር፡፡ በመታወቂያቸው ጋዜጠኞች ቢሆኑም በተግባር ግን የአሸባሪ ቡድኖች ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ጠንካራ ዴሞክራሲና ጠንካራ የምርጫ ሥርዓት አለን፡፡ ይህም በቅርቡ በተደረገው ሪፈረንደም ታይቷል፡፡ መላው የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት የሪፈረንደም ሒደቱን ታዝበዋል፡፡ አንድም የተጭበረበረ ነገር ግን አላገኙም፡፡ ዓለም በሙሉ ሒደቱን ሲከታተለው ነበር፡፡ አሁንም በማሪፍ ፋውንዴሽን በኩል ዴሞክራሲያችንን ማሳየት እንቀጥላለን፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...