Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ባለ ጥላው ስታዲየም

በዓይነቱና በይዘቱ ልዩ ሆኖና የዘመናዊ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ሆኖ ብቅ ያለው በሼሕ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ሙሉ ወጪ ከግማሽ ቢሊዮን ብር  በላይ የተገነባው የወልድያ ስታዲየም ነው፡፡ ‹‹ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ›› ተብሎ የሚጠራው ስታዲየምና የስፖርት ማዕከሉ ከከተማው በስተ ምዕራብ የሚገኘው በመቻሬ ሜዳ ሲገኝ፣ የቆዳ ስፋቱ 117 ሺሕ ካሬ ሜትር ነው፡፡ ከ25 ሺሕ በላይ ተመልካቾችን የሚያስተናግደው ስታዲየሙ በስፖርቱ ማዕከሉ የሜዳ ቴኒስ፣  የቅርጫት፣ የመረብ፣ የእጅ ኳስና ውኃ ስፖርትን አጠቃሎ ይዟል፡፡ ስታዲየሙ ከአራት ዓመታት በፊት ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የመነሻ ንድፍ (ዲዛይን) የቀረበው የአማራ ክልላዊ መንግሥት በአልትሜት አርክቴክት አማካይ ያሠራው ሲሆን፣ ይህም ንድፍ ለገንዘብ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ ተብሎ  የተሠራ መሆኑ ይወሳል፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛው የዲዛይን ማሻሻል ሥራው በሁዳ ሪል ስቴት መሐንዲሶች አማካይነት ሲሠራ፣ የስፖርት ማዕከሉ ዓለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረውና አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት መስጫ ይዞታቸው እንዲያካትት መደረጉ ይጠቀሳል፡፡ የስታዲየሙ ፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የዲዛይን ፕሮጀክት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ዮናስ ብርሃኔ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምሕንድስና የተመረቁት አቶ ዮናስ፣ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ባለው ሁዳ ሪል  ስቴት በዋና ሥራ አስኪያጅ እየተሠሩ ነው፡፡ የስታዲየሙ ግንባታ ሒደትና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙ የግንባታ አነሳስ እንዴት እንደነበር ከማስታወስ ብንጀምር፤

አቶ ዮናስ፡-  የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲን ስታዲዮም ለመገንባት የታቀደው የዛሬ  አራት ዓመት አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱም በሸራተን አዲስ በተደረገው ገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ ሼሕ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲን ‹‹እኔ ሙሉ በሙሉ ወጪውን በመሸፈን እገንባዋለሁ›› በማለት በገቡት ቃል መሠረት ግንባታው ከወልዲያ አስተዳደር ወደ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እንዲዘዋወር ሲደረግ፣ ፕሮጀክቱን ዶ/ር አረጋ ይርዳው በበላይነት  እንዲመሩትና እንዲያስፈጽሙ ተደረገ፡፡ በተከታታይም  ዲዛይኑ ላይ ክለሳ በማድረግ ወደ ግንባታ ሥራው መግባት ቻልን፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙን ዲዛይን በድጋሚ ክለሳ ማድረግ ለምን ተፈለገ?

አቶ ዮናስ፡- መጀመሪያ ዲዛይኑ የተቀበልነው ከአልትሜትስ ፕላን ኢንተርናሽናል ከሚባል ተቋም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የተሠራው ዲዛይን ለገቢ ማሰባሰቢያ ተብሎ የወጣ ነበር፡፡ ከዛም ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከተረከበ በኋላ ዲዛይኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር ሁለት ጊዜ በድጋሚ በማጥናት ምን ዓይነት ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉት በመወያየት ወደ ሥራው ገባን፡፡

ሪፖርተር፡- የግንባታው ሒደት ምን ይመስል ነበር?

አቶ ዮናስ፡-  በግንባታው ወቅት ብዙ ችግሮች ገጥመውን ነበር፡፡ ዋንኛው ችግር የነበረው የአፈር መቁረጥ ሥራ ነው፡፡ ቢያንስ ከሁለት ሜትር ከ50 ርቀት በላይ የሚቆፈር አፈር ነበር፡፡ መሠረቱ ሲሰፋም እስከ 15 እና 20 ሜትር በመቆፈር ተስማሚ አፈር በመተካት ወደ ሥራው ገባን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድመው ከነበሩት ስታዲዮሞች ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡-  ስታዲዮሙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ያመጣና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ነው፡፡ በስታዲየሙ ውስጥ ሁለት ቡድኖች በተለያየ ሰዓት የሚያደርጉትን ጨዋታ ለማከናወን የዳኛዎችን ጨምሮ ወዲያው እንዲዘጋጁ ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው ቡድን ጨዋታውን አጠናቆ እስኪመለስ ሌላኛው መጠበቅ አይገባውም፡፡ ባለው ቀሪ የመልበሻ ክፍል ዝግጅቱን ማድረግ ያስችላል፡፡ ሌላኛው የፊዚዮቴራፒ፣ የጋዜጠኞች አዳራሽ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ የካሜራ ባለሙያዎች መቀመጫ ክፍል፣ እንዲሁም ዝናብ በመጣ ሰዓት ተመልካቹ ያለምንም ሥጋት እንዲመለከት የሚረዳ ሽፋን (ጥላ) አለው፡፡

በተጨማሪም በምሽት ጨዋታ ሲካሄድ ተጨዋቾች በመብራት አማካይነት የራሳቸውን ጥላ እንዳያሳስታቸው የሚረዳ በቴክኖሎጂ የረቀቁ አምፖሎች ተገጥመውለታል፡፡

ሪፖርተር፡- የወልድያ ስታዲየም ተገንብቶ የተጠናቀቀው በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ እንዲገነባ መደረጉ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ዮናስ፡-  በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ እንዲገነባ የተደረገበት ምስጢር፣ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ሲገነባ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ መሐንዲሶች እንዲማሩ በማድረግ ለቀጣይ ሥራዎች ትምህርት እንዲቀስሙ በማሰብ ነው፡፡ በተለይ የስታዲየሙን ሽፋን በምንሠራበት ወቅት አስቸጋሪ የግንባታ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ግን በሒደት ያለውን ችግር በመመካከርና በማጥናት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም መገንባት ችለናል፡፡

በተለይ ጣራውን በተመለከተ ተመልካቾች ዝናብ በሚመጣበት ወቅት ጨዋታው በቀላሉ መከታተል ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሜዳው ውኃ እንዳያሠርግ የማድረግ ሥራ፣ ፀሐያማ በሆነ ወቅት ተመልካቹ በሙቀት እንዳይጎዳ የሚረዳ ቴክኖሎጂን ስንሠራ ትልቅ ትምህርት አግኝተንበታል፡፡ ለምሳሌ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሜዳው ላይ ያረፈ ዝናብ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ያለውን አፈር ይዞ ሳይሄድ ውኃው ብቻ ወደ ታች እንዲወርድ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መጠቀም  ችለናል፡፡ ስለዚህ ጨዋታ ሳይቋረጥ ማከናወን እንዲያስችል የሚያደርገውን ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚገነባ ለማወቅ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገር ያስመጣችሁት ወይም የተጠቀማችሁት ግብዓት የለም?

አቶ ዮናስ፡-  ከውጭ አገር  የተጠቀምነው ነገር የስታዲዮሙ ሽፋን ነው፡፡ ሽፋኑ ፖሊ ካርቡኒት ይባላል፡፡ እንደሳንድዊች ዓይነት ሲሆን፣ ብርሃን የሚያስተላልፍና ከፍተኛ ሙቀትን ማስቀረት አቅም ያለው ነው፡፡ ያም ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ስለማይገኝ ከውጭ አስመጥተናል፡፡ ሌላው በስታዲየሙ 56 ፓውዛዎች ተገጥመውለታል፡፡ በእያንዳንዱ ፓውዛዎች  ውስጥ 146 አምፖሎች አሉ፡፡ ይኼም በሜዳው ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ጥላ እንዳይኖር ለማድረግ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገጠመ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የመብራት ብርሃኑ የሰው ዓይን እንዳይጎዳ ብቻ ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስያዝ ለሦስት ቀናት የውጭ አገር ባለሙያዎች መጥተው አስተካክለውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስታዲየሙን ለከተማው ካስረከበ በኋላ በውድድር ሒደት ለሚከሰቱ ችግሮች ምን ዓይነት ክትትል ለማድረግ  አቅዳችኋል?

አቶ ዮናስ፡-  ግንባታውን አጠናቀን ከወጣን በኋላ የወልዲያ ከተማ መስተዳድር ተረክቦ በኃላፊነት የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ሁዳ ሪል ስቴት በወልድያ አካባቢ የተለያዩ  ግንባታዎችን ስለሚሠራ ቢሮውን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ቢሮው የተከፈተው አንደኛ የወልድያ ስታዲየም ሲሠሩ የነበሩ ወጣት ባለሙያዎች እንዳይበተኑ በማሰብና በአካባቢው በመንግሥትም የሆነ በግል የሚወጡ የግንባታ ጨረታዎችን በመወዳደር ለመሥራት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስታዲየሙ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት ለመርዳት ነው፡፡ ለዚህም ግንባታውን ስናከናውን የወልድያ ወጣት ባለሙያዎች በብዛት አሳትፈን ስለነበር የመብራት፣ የኤሌክትሪክ ወይም ተዛማጅ ችግሮች ቢያጋጥሙ በቅርበት እንዲያስተካክሉ መሐንዲሶቹን አዘጋጅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የወልድያ ስታዲየም ሲገነባ ብዙ ባለሙያዎች ትምህርት እንደቀሰሙ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ግንባታዎች እየተከናወኑ ሲሆን ሌሎች ግንባታዎችን ተረክቦ ለመሥራት ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደርገችሁ ነው?

አቶ ዮናስ፡- የወልድያ ስታዲየምን 90 በመቶውን ወጣት ኢትዮጵያን ባለሙያዎች ናቸው የገነቡት፡፡ ስታዲየሙ ሲገነባ ብዙ ልምድ አግኝተናል፡፡ በቀጣይ የበለጠ ለመሥራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ላይ መሳተፍ የሚቻለው በጨረታ ስለሆነ፣ አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠሩ ሁለት ግንባታዎች ላይ ጨረታ ብንሳተፍም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ችግር ኖሮብን ከሆነ በሒደት የምናስተካክለው ይሆናል፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የግንባታ ጨረታውን ማሸነፍ ባንችልም ጥረታችንን ግን አናቆምም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...