Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሐረሪን በትውፊታዊ ተውኔት

ሐረሪን በትውፊታዊ ተውኔት

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በትውፊታዊ ትውን ጥበባት ክፍሉ ካዘጋጃቸው ተውኔቶች መካከል የቃቄ ወርድወት ይጠቀሳል፡፡ የቃቄ ወርድወት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጾታን መሠረት ያደረገ ጭቆና በመቃወም ለሴቶች እኩልነት የታገለች ሴት ስትሆን፣ ተውኔቱ የሷን ታሪክ ማዕከል በማድረግ የጉራጌ ማኅበረሰብን ባህላዊ እሴቶች ያንፀባርቃል፡፡ ከቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች አንስቶ ባህላዊ አልባሳት፣ ውዝዋዜ፣ የእርቅ ሥርዓትና ሌሎችም እሴቶች በቴአትሩ ይታያሉ፡፡ ትውፊታዊ ተውኔቶች መሰል ማኅበረሰባዊ እሴቶችን ከታሪክ ነገራ ጋር አዋህደው በማቅረብ የሚታወቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሐረሪ ብሔረሰብን ባህል የሚያሳይ ቴአትር ለማዘጋጀት የመጀመሪያ ዙር የጥናት ሥራውን አጠናቋል፡፡

የቴአትር ቤቱ የትውፊታዊ ትውን ጥበባት የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች የብሔረሰቡን ታሪክና ባህል በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ እንዲሁም በሌሎች የተውኔት ግብዓቶች ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ የቴአትሩ ፍሰት፣ መቼቱና ለቴአትር የሚጠቀሟቸው ግብዓቶች የማኅበረሰቡን እሴቶች እንዲያሳዩ ተጨማሪ ዳሰሳና ባለሙያዎች ጋር ውይይቱ ቢጠብቃቸውም የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡

በብሔራዊ ቴአትር የትውፊታዊ ትውን ጥበባት ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ ላዕከማርያም ልሳነወርቅ እንደተናገሩት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ አጠቃላይ ባህላዊ እሴቶችና መገለጫዎች ለመድረክ ከሚያስፈልጉ የተውኔት አላባውያን (ድራማቲክ ኤለመንትስ) አንፃር ተጠንተዋል፡፡ ከታኅሣሥ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. አንስቶ ለ20 ቀናት የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ለደራስያን ግብዓት ሆኖ ከቀረበ በኋላ ቴአትሩ ተሠርቶ ለተመልካች ይበቃል ተብሎም ይታሰባል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከአዲስ አበባ በ515 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሐረሪ ብሔረሰብ መገኛ ሐረር ከተማ ከተቆረቆች ከ1,000 ዓመት በላይ አስቆጥራለች፡፡ በሐረር የመንግሥት አወቃቀር ታሪክ የሚሰቀሱ 76 አሚሮች ያስተዳደሯት ሲሆን፣ በተለያየ ዘርፍ ለአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ 48 ሔክታር ስፋት ባለው መሬት ያረፈው የሐረር ግንብ (ሠንጋ በር፣ ሸዋ በር፣ ፈላና በር፣ ኤረር በርና ቡዳ በሮችን ጨምሮ) በብዙኃን ዘንድ ይታወቃል፡፡ በሮቹ የሚሰጡት አገልግሎትና አጠቃቀማቸው ለተውኔቱ ግብዓት ይሆናሉ ከተባሉ መካከል እንደሆኑም አጥኚው ይናገራሉ፡፡

አምስቱ በሮች የየራሳቸው ቁልፍ የነበራቸው ሲሆን፣ ማታ ተቆልፈው ጠዋት ይከፈታሉ፡፡ ቁልፉን ይዞ ማታ ለአሚሩ የሚያስረክብ ሰው ከመኖሩ ባሻገር አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚያመቹ ማማዎች በግንቡ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሮቹ ወደ ከተማዋ የሚገባና የሚወጣውን ለመቆጣጠርና የሸቀጦች ቀረጥ መሰብሰቢያም ነበሩ፡፡ በትውፊታዊ ቴአትሩ መቼት የሐረሪ ባህላዊ ቤት አሠራር ይታያል፡፡ በቤት አሠራሩ የእስልምና አድማደ ምሰሶዎችን መሠረት በማድረግ አምስት መደቦች አሉ፡፡ በመደቦቹ ከአሚሮች አንስቶ የተለያዩ ግለሰቦች እንደየደረጃቸው ይቀመጣሉ፡፡ በቤት ውስጥ የሚሰቀሉ መገልገያዎችና ጌጣ ጌጦች አቀማመጥም ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ለምሳሌ በቤት የሚገኝ የጦር መሣሪያ አቀማመጥ በአካባቢው ሰላም ወይም ግጭት ስለመኖሩ ማወቅ ይቻላል፡፡

በሐረሪ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ የተለየ ሲሆን፣ በሁሉም የሐረሪ ቤት ቆሻሻ የሚወገድበት ትልቅ ጎድጓዳ ስፌት አለ፡፡ ቆሻሻ እንዳይሸትና በፍጥነት እንዲብላላ ስፌቱ ላይ ቅጥልና አመድ ተደርጎ የተጠራቀመው ቆሻሻ ማለዳ ከመኖሪያ አካባቢ ርቆ ይጣላል፡፡ ቆሻሻው ሲደርቅ ለመሬት ማዳበሪያነት ይውላል፡፡ ከሁሉም ሰው ቤት የሚወጣው ፍሳሽ ቆሻሻ በጥንቃቄ የሚወገድበት ሥርዓትም አለ፡፡

የብሔረሰቡ ማኅበራዊ ተቋሞች በቴአትሩ ቦታ ያላቸው ሲሆን፣ በሐዘንና ደስታ ወቅትም ኅብረተሰቡ የሚደጋገፍበት አፎቻ ከማኅበራዊ ተቋሞቹ መካከል ይገኝበታል፡፡ በለቅሶ፣ በሠርግ፣ የተቸገረን በመርዳት ትልቅ ድርሻ የሚሰጠው አፎቻ፣ የወንዶችና የሴቶች ምድብ አለው፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ኑሮ ዋስትና የሚወሰድ ከመሆኑ በተጨማሪ አባላቱ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ይወጣሉ፡፡ በሐረሪ በሠርግ ወቅት ሽማግሌ ከመላክ ጀምሮ ጥሎሽ በመላክና በሠርግ ዕለትም የሙሽሮቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ጓደኞች የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

በቴአትሩ ተዋንያን የሚለበሱ የሐረሪ አልባሳት ሌላው የባህል መገለጫ ናቸው፡፡ በዕድሜና በትዳር ሁኔታ የተለያዩ ልብሶች የሚለብሱ ሲሆን፣ ጠይ ኢራዝ የተባለው የእናቶች ልብስ በሁለት በኩል የሚለበስ ነው፡፡ ሮዝ ቀለም ያለው የቀሚስ ክፍል ለደስታ በግልባጩ ያለው ጥቁር ደግሞ ለሐዘን ይለበሳል፡፡ ሐዘንና ደስታ እንደማይነጣጠሉ የሚያመላክቱበት መንገድ ሲሆን፣ ወንዶችም በሥራ ወቅት፣ ቤት ውስጥና ለበዓላት የተለያየ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ከአልባሳት ባሻገር በባህላዊ ምግቦች ረገድ የማሽላና በቆሎ እንጀራ ከተለያዩ ማባያዎች ጋር የተለመደ ነው፡፡ ከአልኮል ነፃ የሆኑ የሱፍ ውኃን የመሰሉ መጠጦችም ይዘወተራሉ፡፡

አቶ ላዕከማርያም ባህላዊ ስም አወጣጥና ባህላዊ ሕክምናንም ዳሰዋል፡፡ በባህላዊ ሕክምና በኩል በመኖሪያ ቤት አካባቢ የተለያዩ ዕፅዋት በመትከል ሕመም ሲኖር የመጠቀም ልማድ አለ፡፡ ሐረር በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት) የሰላምና የመቻቻል ከተማ ከመሆኗ በተጨማሪ በከተማዋ ምሽት ላይ ሰዎች ጅቦችን ሲመግቡ ያለው ትርዒት የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ እንደሚስብ ይናገራሉ፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ጅቦቹ ገንፎ የሚመገቡበት ሥርዓትም ተጠቃሽ ነው፡፡

በአጥኚው ገለጻ፣ ከተማዋ የምሥራቅ አፍሪካ የሥልጣኔ ማማ መሆኗ፣ በንግድ መስመሮች የነበራት እንቅስቃሴ፣ የኪነ ሕንፃ ጥበብ፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት፣ ለትምህርት የሚሰጠው ዋጋ እንዲሁም ሌሎችም እሴቶች በትውፊታዊ ተውኔቱ መንፀባረቅ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ ባለሙያ አቶ ደረጀ ተክሉ ባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ በትውፊታዊ ተውኔቱ መታየት እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ከሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ከፍየል ቆዳ የሚሠራው ከበሮ (ከረቡ) ይጠቀሳል፡፡ በቡድን የሚዜሙ መንፈሳዊና ባህላዊ ዜማዎች ይታጀቡበታል፡፡

በመዳፍ ተይዞ እርስ በርስ እየተጋጨ እንደ ጭብጨባ ድምፅ የሚያወጣው መሣሪያ (ከበል)፣ የሐረሪ ባህላዊ ዜማ ማድመቂያ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከክርና ከጭራ እየተወጠሩ የተሠሩ ክራርና መሰንቆ የሚመስሉ መሣሪያዎች ቢኖሩም በግብፅ  መወሰዳቸውን አጥኚው ያስረዳሉ፡፡ በሐረሪ በየዕድሜ ደረጃው ሰዎች የሚሳተፉባቸው የዜማ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ ግጥሞቹ እንዲተላለፍ በተፈለገው መልዕክት ይወሰናሉ፡፡ ሴቶችና ወንዶች በተናጠል የሚከውኗቸው ሙዚቃዎች ያሉ ሲሆን፣ በበዓል አከባበር ሥርዓት የሚደመጡት እስላማዊ መሠረት ያላቸው መንፈሳዊ ዜማዎች ናቸው፡፡

በሠርግ ወቅት ከሚዜሙ ሙሽራውና ሙሽሪትን የሚያወድሱ ባህላዊ ዘፈኖች ጎን ለጎን በሥራ ወቅት የሚደመጡ ዘፈኖችም ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ በእርሻ ወቅት የሚዜም የሐረሪ የባህል ዘፈን አለ፡፡ የተለያዩ ቡድኖች (ሙጋዶች) አንድነታቸውን የሚገልጹበትን የኅብረት ዜማ በቡድን ወይም በጥንድ ሆነው ያዜማሉ፡፡ የሥራ ተነሳሽነትና ሙያ የሚደነቅባቸው ዜማዎች ይንቆረቆራሉ፡፡ ሽለላና ፉከራም የባህላዊ ሙዚቃው ናቸው፡፡ አቶ ደረጀ እንደሚለው፣ የሐረሪ የሙዚቃ ቅኝቶች፣ ከትውፊታዊ ትውን ጥበባት ክፍል በተጓዳኝ ለኢትዮጵያ የባህላዊ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ግብዓት መሆንም ይችላሉ፡፡

በክውን ጥበባት ሊካተቱ የሚችሉ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ክብረ በዓላትን የገለጹት የቴአትር ቤቱ ባለሙያ አቶ ሳሙኤል አካሉ፣ ሐረሪዎችን የፍቅርና መቻቻል ምሳሌ ያደረጓቸው እሴቶች በቴአትሩ ጎልተው መታየት አለባቸው ይላሉ፡፡ ከእሴቶቹ መካከል አዎች ወይም ኢናያች የሚባለው በጎ ሥራ ለሠሩ ሰዎች የሚቆመው ሐውልት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ መልካምነትን የሚያበረታታና ጥሩ የሚያደርጉንም የሚያወድስ በመሆኑ ለሰላሙ መሠረት መሆኑን አጥኚው ያመለክታሉ፡፡ የሚወደሱት ሰዎች ለተምሳሌነት በተቀመጠ ሐውልታቸው ቀጣዩ ትውልድ ፈለጋቸውን ተከትሎ በበጎ ሥራ እንዲተካ ያነሳሳሉ፡፡

ከመኖሪያ ቤት አንስቶ በርካታ ነገሮች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ መታነፃቸው ሰዎች በምድር ሳሉ መልካም ነገር በማድረግ እንዲኖሩ ይሰብካሉ፡፡ ለምሳሌ ቤት ሲሠራ ውስጡ መቃብር የሚወክል ቦታ አለ፡፡ ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡና ሲገቡም ሞትን በማሰብ ክፉ ከመሥራት እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ ሥፍራ ነው፡፡ በቤት መግቢያ በር አናት ላይ ጎዶሎ ቁጥር ያላቸው እንጨቶች የሚደረደሩ ሲሆን፣ ዓለም መቼም ስለማትሞላ ሰዎች ፈጣሪን እንዳያማርሩ ለማሳሰብ ያለመ ነው፡፡ አጥኚው የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ያላቸው ማኅበራዊ ውክልና የትውፊታዊ ተውኔት አላባዎች ይሆናሉ ይላል፡፡

በመድረክ ግንባታና ተዋንያኑ ማኅበራዊ ውክልናዎቹን እንዲያሳዩ በማድረግ ባህሉን ማንፀባረቅ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ በማኅበረሰቡ በግልጽነት የመናገር፣ አንድ ሰው ሲያስቀይም የመታገስና ሌሎችም የመቻቻል ሥርዓቶች ይዘወተራሉ፡፡ ቂም ከመያዝ ይልቅ አንዳች ስሜት በተሰማበት ወቅት ግልጽ መናገርም በማኅበረሰቡ ይደገፋል፡፡ ይህ ሰላማዊነት በሌሎች ማኅበረሰቦችም እንዲሰራጭ ቴአትሩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አጥኚው አያይዞ ያነሳል፡፡

በቴአትሩ ከሚካተቱ ድራማዊ ክንዋኔ ያላቸው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች መካከል አሹራ (በሙስሊሞች አዲስ ዓመት የመጀመሪያው ወር በዘጠነኛው ቀን የሚከበር ዓመታዊ በዓል) ይጠቀሳል፡፡ በበዓሉ ጀግንነት የሚታይበት የቅል ሰበራ ሥርዓት (ውርሻቶ)፣ ጎረቤት ተጠርቶ ገንፎ የሚበላበትና ጅቦች ገንፎ የሚመገቡበት ሥርዓት የበዓሉ ድራማዊ ክንዋኔዎች ናቸው፡፡

በዓመት አንዴ ጅቦች ገንፎ ከሚመገቡበት ሥርዓት በተጨማሪ ዘወትር ጅቦች የሰው ስም ተሰጥቷቸው ሥጋ የሚመገቡበት ሥርዓት ተዋንያንና ተመልካቾች ያሉበት ድራማዊ ክዋኔ ሲሆን፣ የማኅበረሰቡ እንስቶች ለሰላም የሚፀልዩበት ‹‹ሠፈር›› የተባለ ሥርዓት ሌላው ዓመታዊ ባህላዊ ክብረ በዓል ነው፡፡ የረመዳን ጾም አልቆ ኢድ አልፈጥር ከተከበረ በኋላ በስምንተኛው ቀን የሚከበረው ሸዋል ኢድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ሲሆን፣ የመተጫጫ በዓልም እንደሆነ ይነገራል፡፡

አህመድ ዘካሪያ (ረዳት ፕሮፌሰር) ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባለሙያዎችና የሐረሪ ተወላጆችም ለትውፊታዊ ተውኔቱ ግብዓት የሚሆኑ ባህላዊ እሴቶች መጠናታቸው፣ የማኅበረሰቡን ባህል ለማስተዋወቅና ለቀጣዩ ማኅበረሰብ ለማሸጋገርም ይረዳል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከቁሳዊው ባህል በተጨማሪ ሥነ ቃልና አፈ ታሪክ የቴአትሩ ግብዓት እንዲሆን የጠየቁ ነበር፡፡

ገበያ ከጥንት ጀምሮ የማኅበረሰቡ እሴቶች የሚንፀባረቁበት ሥፍራ በመሆኑ የተውኔቱ አንድ አካል እንዲሆንም ተጠይቋል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ትውፊታዊ ተውኔቶችን የሚያዘጋጀው በረዥም ጊዜ ልዩነት ቢሆንም፣ ለቴአትር ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶች መሠራታቸው መልካም መሆኑም ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...