Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሳምንት በዳሬሰላም

ሳምንት በዳሬሰላም

ቀን:

ከአውሮፕላኑ እንደወረድን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ የተቀበለን የአገሪቱ ወበቃማ አየር ነበር፡፡ ወደ እንፋሎት ለሚያደላው ለዳሬሰላም አየር እንግዳ የሆነ በሙቀቱ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ በተለይም ዶፍ ዝናብ እየጣለ የአየሩ መፋጀት የሚያስደንቅ ነው፡፡

ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያስፈልገውን ፈቃድ ለማግኘት የቢጫ ወባ ካርድ ማሳየት፣ ፎርም መሙላት፣ ረጅም ወረፋ መጠበቅና ሌሎችም አሰልቺ ሂደቶችን መከተል ነበረብኝ፡፡ እነዚህን ሁሉ አሟልቼ ስወጣ ተቀብሎኝ ወደ ተያዘልኝ ሆቴል  የሚያደርሰኝን ሰው በዓይኔ ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን እኔን ብሎ የመጣ ማንም አልነበረም፡፡

ሁኔታዬን የተረዱት የታክሲ ሾፌሮች ከበቡኝና የፈለኩበት ቦታ ሊያደርሱኝ እንደሚችሉ ያግባቡኝ ጀመረ፡፡ እኔም ተቀባዮቼ እስኪመጡ ለሰዓታት ከመቆም ይሻላል ብዬ በኮንትራት ታክሲ ወደ ሆቴሉ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ ከጁሊየስ ኔሬሬ ኤርፖርት እስከማርፍበት ሆቴል ድረስ ያለው መንገድ ከ15 ደቂቃ ያልበለጠ የሚወስድ ቢሆንም፣ 35 ዶላር ወይም 875 ብር አካባቢ እንድከፍላቸው ሾፌሮቹ ጠይቀውኛል፡፡ የጠሩት ዋጋ አላግባብ መወደዱን በሚያሳይ መልኩ ፊቴን አጨፍግጌ ከአሥር ዶላር የበለጠ እንደማልከፍል ስነግራቸው ጥለውኝ ወደየአቅጣጫው ተበተኑ፡፡ በዚያ መካከል እንዲቀበለኝ የተመደበው ሰው ደረሰና መንገድ በመዘጋጋቱ መቆየቱን ነግሮኝ ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሆቴሉ ለመሄድ መንገዳችንን ጀመርን፡፡

በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የቆየችው ታንዛኒያ በተለይም ዳሬሰላም ወደ ጎን የሚሰፉና አጠር ያለ ቁመት ያላቸው ሕንፃዎች ይበዙባታል፡፡ የአብዛኛዎቹ ሕንፃዎች የግድግዳ ቀለም ነጭና ጣሪያቸው ደግሞ ቀይ ሸክላ ነው፡፡ አዳዲስ የተገነቡ ዘመናዊ ሕንፃዎችም አሉ፡፡ ሁሉም ዓይነ ግቡና ረቂቅ የሥነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይባቸው ናቸው፡፡

የዳሬሰላም አስፋልት ጠባብ በመሆኑ እንደልብ ለመንቀሳቀስ አያስችልም፡፡ በመሆኑም ወደ ሆቴሉ እስክንደርስ በየመንገዱ ለደቂቃዎች መቆም ነበረብን፡፡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉትን ሕንፃዎች እያደነቅኩ ሆቴሉ ደረስኩ፡፡ ንፁህ አየር ማግኘት የቻልኩት ሆቴሉ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡ በየቦታው አየር የሚያመጣጥኑ ማሽኖች (ኤሲ) በመገጠሙ የተሻለ አየር እንዲኖር አስችለዋል፡፡

ወደ ታንዛኒያ ያቀናሁት ባለፈው ሳምንት እሑድ አፍሪካን ሚዲያ ኢኒሼቲቭ የተባለ ድርጅት የከተሞችን መስፋፋት አስመልክቶ ያዘጋጀውን ሥልጠና ለመካፈል ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ከ40 በላይ ከሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከ70 በላይ ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡

በመክፈቻው የአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሼቲቭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤሪክ ቺንጅ በአኅጉሪቱ ስለሚታየው  የከተማ መስፋፋት፣ ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዙሪያ አጠር ያለ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ በከተሞች መስፋፋት ረገድ የመሪዎችን ሚና በተመለከተም ንግግር አድርገዋል፡፡ ለጥቀውም ‹‹ሁ ወዝ ዘ ሥማርተሥት ሊደር ኢን አፍሪካ?›› በአፍሪካ ጎበዙ መሪ ማን ነበር? ሲሉም ጠይቀው ነበር፡፡ በአዳራሹ ያሉት ጋዜጠኞች እጃቸውን እያወጡ ጎበዝ መሪ ናቸው የሚሏቸውን የመሪዎች ስም ይዘረዝሩ ጀመረ፡፡ ከመካከል አንደኛው መለስ ዜናዊ ሲል ተናገረ፡፡

ኤሪክም ሲጠብቁት የነበረው ስም ነበረና አዎ መለስ ዜናዊ ብለው ከተሳታፊው አፍ ነጥቀው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለሠሯቸው ትልልቅ ሥራዎች ያብራሩ ጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ እንደሚገኝም ደጋግመው ተናገሩ፡፡ ከንግግራቸው ስለ አገሪቱ ፖለቲካ በቅርበት እንደሚያውቁ ያስታውቃል፡፡ እኔም የአገሬ ስም ከረሀብ፣ ከድርቅና ከችግር በተቃራኒ በዚህ መልኩ በመነሳቱ ተኩራራሁ፡፡ ደስም አለኝ፡፡ ሁኔታዬን የተመለከቱ ከጎኔ የነበሩ የናይጄሪያ ጋዜጠኞችም ሳቁ፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ስም በመልካም ጎኑ በምሳሌነት ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ አዲስ አበባ መጥተው የሚያውቁ ብዙዎች ከተማዋ እንደምትናፍቃቸው በተለይም ባህላዊ ምግቡ እንደማይረሳቸው ነግረውኛል፡፡ ከአዲስ አበባ የቆዳ ቦርሳዎችና ሌሎችም አልባሳት መግዛት የሚፈልጉም በሆነ አጋጣሚ አዲስ አበባ ብመጣ እያሉ ምኞታቸውን ነግረውኛል፡፡

ከዚህ በተቃራኒም ገጥሞኛል፡፡ ከኬፕቨርዴ ከመጣች አንዲት ጋዜጠኛ ጋር እያወራን ሳለ ከየት እንደመጣሁ ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ከኢትዮጵያ እንደሆነ ነገርኳት፡፡ የነገርኳትን እንዳልሰማች ሁሉ ደግሜ እንድነግራት ጠየቀችኝ፡፡ ኢትዮጵያ ስልም ጠንከር አድርጌ ነገርኳት፡፡ እንዲህ ዓይነት አገር አፍሪካ ውስጥ አለ እንዴ ብላ ጠየቀችኝ፡፡ የምሯን መሆኑን ሳውቅ ተበሳጨሁ፡፡ በመድረኩ ተደጋግሞ ስሟ ሲነሳ የነበረውን ኢትዮጵያን አላውቃትም ያለችኝ ሆነ ብላ እኔን ለማበሳጨትም መሰለኝ፡፡

ለአንድ ሳምንት በዘለቀው በዚህ ፕሮግራም ላይ በአፍሪካ ስላለው የሚዲያ ነፃነት ጉዳይም ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ አወያዩ የነበሩት ኤሪክ ሚዲያ ከየአቅጣጫው የሚኖሩበትን ጫና ተቋቁሞ በመሥራት ለውጥ መፍጠር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚሠሩትን አያውቁም የሚል ደካማ ሰበብ እየሰጡ አብሮ ለመሥራት የማይፈልጉ አካላት እንዳሉ፣ ይህ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየትም የሚዲያ ባለሙያዎች በቆራጥነት መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛ የነበሩ በአሁኑ ወቅት ግን የአንድ አገር ባለሥልጣን የሆኑን ሰው ስም በመጥቀስ ‹‹በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው ጠይቄው ጋዜጠኞች የሚሠሩትንና የሚያደርጉትን አያውቁም፡፡ ስለዚህ በእነሱ ጉዳይ መግባት አልፈልግም አለኝ›› በማለት፣ የሚዲያ ተቋማት ላይ የሚነሱ አሉታዊ አስተያየቶችን ጋዜጠኞች በቁጭት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ኤሪክ ገልጸዋል፡፡

 አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሚዲያው ችግር የአቅም ማነስ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ፕሮግራሞችን ስፖንሰር የሚያደርጉ ባለሀብቶችና ተቋማት በዚህኛው ፕሮግራም ወይም በዚህኛው ጽሑፍ ላይ ድርጅቴን አላስተዋውቅም በማለት የሚዲያ ተቋማቱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከቱ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የስፖንሰር አድራጊዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚገደዱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውም ተነግሯል፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የጋዜጠኛውን ነፃነት ሳይጋፉ እንዴት መሥራት እንደሚቻል ከራሳቸው በመነሳት ልምዳቸውን ያካፈሉም ነበሩ፡፡

ሳምንት በፈጀው በዚህ ሥልጠና ላይ ሁላችንም በበቂ ለመተዋወቅ ባንችልም ከናይጄሪያ፣ ከሱዳን በተለይም ደግሞ ከሶማሌ ከመጡ ጋዜጠኞች ጋር ልምድ መለዋወጥ ችዬ ነበር፡፡ ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ፣ የአገሪቱ ሴቶች ፊታቸውን ቀይ ለማድረግ የተለያዩ የሚያነጡ ቅባቶችን እንደሚጠቀሙና አብዛኛዎቹ የሱዳን ሴቶች ተፈጥሯዊ ቀለማቸውን እንዳጡ በማማረር ነግራኛለች፡፡ ለአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በተፈጥሮ የሱዳናዊ ቀለም ያላትን ዜና አንባቢ ለማግኘት ብዙ እንደተቸገሩና በስንት ልፋት አንዲት አንባቢ እንዳገኙ፣ በጉዳዩ ላይም አንድ ጽሑፍ መጻፏን ነግራኛለች፡፡

ሌሎቹ ከሶማሌ ላንድና ከሶማሌያ የመጡ ናቸው፡፡ ሁለቱ አገሮች ለዘመናት ሲጋጩ የቆዩ ቢሆንም፣ ከሁለቱ አገሮች የተገኙት እኚህ ጋዜጠኞች አይነጣጠሉም ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አንድ የሚያከራክራቸው ነገር ቢኖር  የሶማሌ አንድነት ጉዳይ ነው፡፡

 አንደኛው ከሶማሊያ የመጣው ሶማሊያ አንድ እንጂ ሁለት አይደለም፣ ሶማሊ ላንድ የሚባል አገርም የለም ሲል እየተመፃደቀ ይናገራል፡፡ ከሶሜሊ ላንድ የመጣው ደግሞ ሶማሊላንድ የተባለ አገር ስላለ ነው ጊዜ ሰተህና ስራዬ ብለህ ስላለመኖሩ የምትከራከረው  ሲል  እጆቹን በእልህ እያወናጨፈ ይመልስለታል፡፡ በዚህ ክርክራቸው እንደ ታዛቢ አንዳንዴ ደግሞ አስማሚ ሆኜ አሳተፋለሁ፡፡

ከእነዚህ ጓደኞቼ ጋር የተለያዩ ባህላዊና ሌሎች ዕቃዎችን ለመግዛት ወደ ገበያ ማዕከሎች ሄደናል፡፡ አንድ ዶላር 2,200 የታንዛኒያ ሽልንግ የሚመነዘር ሲሆን፣ በ1,500 ሽልንግ የሚመነዝሩም አጋጥመውኛል፡፡ 100 ዶላር ሰጥቼ 110,000 የታንዛኒያ ሽልንግ ሲሰጡኝም ሀብታም የሆንኩኝ መስሎኝ ነበር፡፡

ነገር ግን አንድ ፍሬ አፕል በ1000 ሽልንግ፣ የጥርስ ብሩሽ በ7000፣ የጥርስ ሳሙና በ16000 ሽልንግ ስገዛ ገንዘቡ ዋጋ እንደሌለው ተረዳሁ፡፡ አንድ የቻይና ሸሚዝ 160,000 ሽልንግም ይሸጣል፡፡ እንዲህ ያሉ የዋጋ ተመኖችን ስመለከት በዕቃዎቹ ላይ የተለጠፉ ኮዶች ይመስሉኝ ነበር፡፡ መሸጫ ዋጋው መሆኑን ሳረጋግጥ ስልኬን አውጥቼ ሒሳቡን መሥራት እጀምራለሁ፡፡ ሽልንጉን ወደ ዶላር፣ ዶላሩን ደግሞ ወደ ብር እቀይራለሁ፡፡

በሚገባ የሚያውቀው አሌክስ ኔልሰን የተባለ የታንዛኒያ ነዋሪና ጋዜጠኛ የተሻለ የገበያ ስፍራ መኖሩን ነግሮኝ የሚያስፈልጉኝን ለመግዛት ‹‹ካሪያኮ›› ወደ ተባለች የገበያ ስፍራ አቀናን፡፡ ካሪያኮ በዳሬሰላም ከሚገኙ ክፍት የገበያ ቦታ አንዷ ነች፡፡ በግራና በቀኝ በትልልቅ ሕንፃዎች የተከበበችና በሰዎች እንዲሁም በሱቆች የተጨናነቀች ነች፡፡ በካሪያኮ መኪና የሚተላለፉበት መንገድ አይገኝም፡፡

መሀል አስፓልት ላይ ሳይቀር የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት መገልገያ ዕቃዎች፣ ፍራፍሬዎችና ሌሎችም በርካታ ሸቀጦች ይሸጣሉ፡፡ የማሣይ ጎሳዎች የተለያዩ ባህላዊ የአንገት ጌጦችን እንዲሁም ሸበጦችን በየህፃው ጥግ እንዲያውም በየመንገዱ አንጥፈው ይሸጣሉ፡፡ የተጠበሰ በቆሎ፣ ተልጦ የተከተፈ ድንች፣ ካሮትና ሌሎች በካሪያኮ ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ ዋጋውም ቢሆን ከሌሎቹ አካባቢዎች አንፃር የተሻለ የሚባል ነው፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች ዳሬሰላም የገቡ የውጭ አገር ዜጎች ካሪያኮን ሳይጎበኙ እንደማይሄዱ አሌክስ ይናገራል፡፡ ይሁንና በኑሮ ውድነት የማይማረር የለም፡፡ ታዲያ የከተማዋ ነዋሪዎች በወር ምን ያህል ገቢ ቢኖራቸው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ይችላሉ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ እንደ አሌክስ ያሉ ወጣት ጋዜጠኞች በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ሽልንግ እንደሚከፈላቸው ይናገራል፡፡

ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ከዳሬሰላም ሙቀትና ከኑሮ ውድነት ጋር ተላምጄ ነበር፡፡ የት ሄደው ምን መግዛት እንደሚችሉ በቀን ውስጥ በየትኞቹ ሰዓት መንቀሳቀስ እንዳለብዎ ካወቁ ገንዘብዎን ለመቆጠብ፣ ቆዳዎን ከጠራራ ፀሐይ ለመከላከል ይችላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...