Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአሰግድ ተስፋዬ (1962 - 2009)

አሰግድ ተስፋዬ (1962 – 2009)

ቀን:

በብዙዎች ዘንድ ‹‹ፔሌ›› በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል፡፡ የድሬው አሰግድ ተስፋዬ በኳስ ጠቢብነቱ፣ በጎል አግቢነቱ፣ አብዶ በመሥራት ሰነጣጥቆ ሲያልፍ፣ በከረሩ የኳስ ምቱና በመሳሰሉት ትዝታዎቹ ሲከዘር የሚኖር ድንቅ የእግር ኳስ ሰው ነበር፡፡ እግር ኳስ መጫወት ካቆመም በኋላ ተተኪ ታዳጊዎችን ‹‹አሴጋ›› በሚል መጠሪያ አካዴሚ አቋቁሞ የወደፊቶቹ ተስፋዎች ለማፍራት ሲጥር ቆይቷል፡፡

አመለ ሸጋው የፊት መስመር ፊት አውራሪውና አሥር ቁጥር ለባሹ አሰግድ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የመጀመሪያውን መደበኛ ጨዋታ የጀመረው በተወለደበት ድሬዳዋ ከተማ ለሚገኘው ለድሬዳዋ ኮካ ኮላ ቡድን በመሠለፍ ነበር፡፡ በዚሁ የጀመረው የተጨዋችነት ታሪኩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ጋር ከ16 ዓመታት በላይ የዘለቀ የእግር ኳስ ሕይወትና ዝና ያተረፈባቸው ዓመታት ለማሳለፍ አብቅተውታል፡፡

በድሬደዋ ዳቻቱ ከአባቱ ተስፋዬ ደበላና ከእናቱ ወ/ሮ ጌጤ ደበሌ በ1962 ዓ.ም. የተወለደው አሰግድ፣ በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ከፍ ሲልም በአህጉር ደረጃ የአገሪቱን ስም በማስጠራት ታላቅ ግልጋሎትን አበርክቷል፡፡ በ1985/86 በኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ በነበረበት የጨዋታ ዘመኑ በወቅቱ የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ (ካፍ ካፕ) የአፍሪካ ምርጥ አራት ውስጥ መግባት የቻለም ነበር፡፡ ከዚያም በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው 23ኛው የምሥራቅና መካለኛው አፍሪካ ዋንጫና በዚያው ዓመት በዛንዚባር አስተናጋጅነት በተካሄደው የሲካፋ የክለቦች ሻምፒዮና ኳስና መረብን በማገናኘት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ብቃቱን ያስመሰከረ የወቅቱ ድንቅ የፊት መስመር ተጨዋችም ነበር፡፡

አሰግድ ኢትዮጵያ ቡና በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በተለይም በ1989/90ዎቹ እና ከዚያም በፊት በአንድ ጨዋታ አምስት ጎሎችን ከመረብ በማሳረፍ እስካሁን ብቸኛው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፍ) ውድድር ላይ ከክለቡ ጋር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ በዚሁ የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ በአንድ ጨዋታ ሦስት ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር (ሀትሪክ በመሥራት) ብቸኛው ተጨዋች መሆኑም ስለ ሕይወት ታሪኩ ከተነበበው መረዳት ተችሏል፡፡ በ1989 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ክለቦች ጥሎ ማለፍ አሸናፊም ነበር፡፡

አሰግድ ተስፋዬ ከእግር ኳስ ዘመኑ ማብቃት በኋላም በተለያዩ ዘርፎች ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ከግልጋሎቶቹ በክለብና በብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሁም በተጨዋቾች ተወካይነትና በመሳሰሉት ተሞክሮውን አካፍሏል፡፡

በግለሰብ ደረጃ የታዳጊዎች እግር ኳስ አካዴሚ ‹‹አሴጋ›› በሚል ስያሜ በማቋቋም ከ250 በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎችን በማሠልጠን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተጉዟል፡፡ ድንገተኛው የሕይወት ኅልፈቱ ከመሰማቱ በፊት፣ የአሴጋ ታዳጊዎችን በመያዝ ወደ አራት አገሮች ለመጓዝና ታዳጊዎቹን በውድድር ላይ ለማሳተፍ በዝግጅት ላይ እንደነበርም ከሕይወት ታሪኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በተለያዩ ዓለማት በተለይም የዘመኑን እግር ኳስ ነባራዊ እውነታ በአካል ተገኝተው እንዲረዱት አድርጓል፡፡ በእግር ኳሱ ትልቅ ህልም የነበረው መሆኑ እነዚሁ ሥራዎቹ ምስክር ናቸው፡፡

አሰግድ ተስፋዬ ከእግር ኳሳዊ የሕይወት ተሞክሮው በተጓዳኝ የማቲዮስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲ የቦርድ አባል፣ እንዲሁም የችግረኞችን ሕይወት በማትረፍ የሚታወቀው የድሬዳዋው ትረስት ፈንድ መሥራችና ምክትል ሰብሳቢ በመሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አገልግሏል፡፡ በሚያውቁት ወዳጆቹ፣ አድናቂዎቹ እንዲሁም በቅርብ ቤተሰቦቹ ሁሉ ተወዳጅ፣ ትሁትና ሰው አክባሪ የነበረው አሰግድ ተስፋዬ፣ ባለ ትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር፡፡

ሥርዓተ ቀብሩ በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የተፈጸመው አዲሱ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ በተገኙበት ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...