- የልማት ድርጅቶች የትርፍ ድርሻ ውሳኔ አላገኘም
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሰኔ 2008 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 916 ሲቋቋም ተጠሪነታቸው ለሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሆኖ፣ የኮርፖሬት አስተዳደርና የፋይናንስ አፈጻጸማቸውን ብቻ እንዲከታተል ኃላፊነት ከወሰደባቸው ግዙፉ መንግሥታዊ ኮርፖሬሽኖች ጋር የሥልጣን መደራረብ በመፈጠሩ፣ ይኼንን የሥልጣን መደራረብ የሚያስቀር ጥናት እንዲያካሂድ ታዋቂው የአሜሪካ አማካሪ ኩባንያ መኬንዚ ተቀጠረ፡፡
ለሌሎች ሚኒስቴሮች ቀጥታ ተጠሪ ሆነው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የኮርፖሬት አስተዳዳርና የፋይናንስ አፈጻጸም ክትትልና ድጋፍ የሚደረግላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ናቸው፡፡
እነዚህ ግዙፉ ኮርፖሬሽኖች ተጠሪነታቸው ለሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በመሆኑ፣ በሥራ አመራር ቦርድ የሚመሩ ናቸው፡፡ የኮርፖሬት አስተዳዳርና የፋይናንስ አፈጻጸማቸው ደግሞ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ይካሄዳል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሥራውን በሚያካሂድበት ወቅት የኃላፊነት ወሰን እየተደራረበ በመሆኑ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ ይኼ አሠራር ሊስተካከል እንደሚገባ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገር ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያልሞላውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ በድጋሚ አሠራሩን ለማስተካከል ተወስኗል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ረዳት ኃላፊ አቶ አሰበ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአሜሪካው ኩባንያ መኬንዚ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት፣ አጠቃላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አደረጃጀት ምን መሆን እንዳለበት አጥንቶ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡
‹‹ምክንያቱም ኮርፖሬሽኖቹ ተጠሪነታቸው ለሁለት መሥሪያ ቤቶች መሆኑ ችግር ፈጥሯል፤›› ሲሉ አቶ አሰበ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካው ኩባንያ ከአደረጃጀት ጥናት በተጨማሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርን የሚመለከቱ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ባወጣው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡
ይኼንን ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የቻይና፣ የህንድ፣ የሲንጋፖርና የቬትናም ልምዶች በማየት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋቸውን ለመንግሥት ፈሰስ ከማድረግ ይልቅ፣ ራሳቸውን ለማሳደግ እንደሚያውሉት ዕቅድ ተይዟል፡፡
‹‹የልማት ድርጅቶች ለመንግሥት ታክስና የትርፍ ድርሻ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ የትርፍ ድርሻ ክፍያው ግን አብዛኛው በገንዘብ ሚኒስቴር የሚወሰን ሲሆን፣ መጠኑ የተለያየ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች እንደ ተጨባጭ ሁኔታቸው በማስላትና ዕቅዳቸው ላይ በመመሥረት እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን የትርፍ ድርሻ ክፍያ ራሳቸው ሥራ ላይ እንዲያውሉት ይደረጋል፤›› የሚለው ሚኒስቴሩ ያወጣው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የሌሎች አገሮችን ልምድ ጠቅሶ፣ ‹‹በኢትዮጵያ በኩልም አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በጋራ ይሠራል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡
በተለይ በመንግሥት ሥር እንዲቆዩ የተደረጉ ስትራቴጂካዊ ኮርፖሬሽኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ ሆነው እንዲሠሩ፣ ትርፋቸውን ለብሔራዊ ግምጃ ቤት ፈሰስ ከማድረግ ይልቅ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ እንደሚገባ ዕቅዱ ያስረዳል፡፡
የቀድሞ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቢያንስ 20 በመቶ ትርፋቸውን ራሳቸው እንዲጠቀሙ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ እስካሁን በመቆየቱ፣ ኤጀንሲው በሚኒስቴር ደረጃ ከተዋቀረም በኋላ በትልቅ ዕቅድ ይህንኑ ሐሳብ አሻሽሎ አቅርቧል፡፡
ነገር ግን በትርፍ ድርሻ ፈሰስ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ውሳኔ ያልተሰጠበት በመሆኑ፣ አማካሪ ድርጅቱ መኬንዚ ይኼንኑ ጉዳይ ጨምሮ እንደሚያጠና እና የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡